Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበተያዘው ዓመት ለሦስተኛ ጊዜ የመሬት ሊዝ ጨረታ ወጣ

በተያዘው ዓመት ለሦስተኛ ጊዜ የመሬት ሊዝ ጨረታ ወጣ

ቀን:

የዘገየው የሊዝ አዋጅ ማሻሻያ በርካታ ጥያቄዎችን አንቆ ይዟል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን ጨምሮ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 127 ቦታዎችን ለጨረታ አቀረበ፡፡

ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በይፋ በሚከፈተው ጨረታ ይፋ የተደረገው 30ኛው የሊዝ ጨረታ በቦሌ 91፣ በየካ 17፣ በቂርቆስ ስድስት፣ በጉለሌ አንድ፣ በልደታ አንድና በቂርቆስ አንድ ቦታዎችን ይዟል፡፡

ይህ 30ኛው የሊዝ ጨረታ በ2010 ዓ.ም. ሦስተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በየወሩ የመሬት ሊዝ ጨረታ የማውጣት ዕቅድ ቢኖረውም፣ በተያዘው  ዓመት ማቅረብ የቻለው ሦስት ጊዜ ብቻ ሲሆን የቦታ መጠኑም ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የ2010 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሀርጋሞ ሀማሞ በመሩት በዚህ ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፣ መሬት ባንክ የገቡ ቦታዎችን ለተጠቃሚው አለማስተላለፍ፣ በምትክነት የተሰጡ ቦታዎችን ከሕገወጥ መሬት ወራሪዎች ጠብቆ ማቆየት አለመቻል፣ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ወደ ግንባታ እንዲገቡ ጫና አለማሳደር፣ እንዲሁም በመሬትና መሬት ነክ ይዞታዎች የተንሰራፋውን ሙስና በተገቢው መንገድ አለመዋጋት የሚሉት ጉዳዮች በድክመት ተነስተዋል፡፡

ነገር ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ከዚህ የዘለለ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡

በባለሙያዎቹ ችግር ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 እንደሚሻሻል ከተገለጸ የቆየ ቢሆንም፣ አዋጅ ተሻሽሎ ባለመውጣቱና አስተዳደሩ የራሱን ደንብና መመርያ አውጥቶ ወደ ሥራ ባለመግባቱ የመሬትና መሬት ነክ ይዞታዎች ታንቀው ተቀምጠዋል፡፡

ይህ አዋጅ ተሻሽሎ ተግባር ላይ ቢውል ለየአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የማሥፈሪያ ፕሮጀክቶች፣ የተነፃፃሪ (ፕሮፖርሽናል) ካርታ ጉዳይና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርጋሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሊዝ አዋጁ መዘግየቱን ያምናሉ፡፡

‹‹የሊዝ አዋጁ የዘገየ በመሆኑ እንዲፈጥን እየጠየቅን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሚዘገይ ከሆነም የተወሰኑ ጉዳዮችን በመለየት ለካቢኔ አቅርበን ለማፅደቅ እያሰብን ነው፤›› ተብለዋል፡፡

በሊዝ አዋጅ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች ፀድቀው ወደ ተግባር ከተገባ፣ በርካታ የመሬት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ