Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ወደ ከተማው ቢመለስም የግብር ከፋዮች ቅሬታ ቀጥሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ባለሥልጣን ከፌዴራል መንግሥት ተለይቶ እንዲመለስ ካስገደዱ ምክንያቶች መካከል የግብር ከፋዮች ቅሬታ ዋነኛው ቢሆንም፣ የግብር ከፋዮች ቅሬታ ግን አሁንም ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡

በተለይ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች በ2009 ዓ.ም. ከተጣለባቸው ግብር የበለጠ መጠየቃቸውን በመግለጽ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደረጀ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች እንደሚገልጹት፣ የግብር አወሳሰኑ ፍትሐዊ አይደለም፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት ተጥሎብኝ ከነበረው የበለጠ ግብር መጥቶብኛል፡፡ ምክንያቱን ስጠይቅም ተርን ኦቨር ታክስ ከተጠቃሚው መሰብሰብ ነበረብዎ የሚል ነው፤›› ሲሉ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ግለሰብ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የችግሩ ማጠንጠኛ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተርን ኦቨር ታክስ ምጣኔ  ከአሥር በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንደሚደረግ መረጃ ወጥቶ ነበር፡፡ አነስተኛ የቁርጥ ግብር ከፋዮች ይህንን ሥሌት ታሳቢ በማድረግ ግብር ይጨምራል ሳይሆን ይቀንሳል የሚል እሳቤ የነበረባቸው ከመሆኑ አንፃር፣ በ2009 ዓ.ም. ከከፈሉት የ2010 ዓ.ም. ግብር እንደሚቀንስ አስበው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የታክስ ምጣኔ የመቀየር ሥልጣን የለውም፡፡

‹‹በዚህ ዓመት የተለየው ነገር ከተጠቃሚው የሚሰበስበውን ተርን ኦቨር ታክስ መሰብሰብ የነበረባቸው አነስተኛ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ባለመሰብሰባቸው የተፈጠረ ችግር ነው፤›› በማለት አቶ ሺሰማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው ይገኛሉ ተብለው ከሚጠበቁ 221 ሺሕ ቁርጥ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ግብራቸውን ማስታወቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ማስታወቅ የቻሉት አንድ መቶ ሺሕ ብቻ ናቸው፡፡  በ2009 ዓ.ም. ግብር መክፈያ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የግብር ከፋዮች ቅሬታ ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ በ2003 ዓ.ም. በውክልና ወደ ፌዴራል መንግሥት ተዛውሮ ለሰባት ዓመታት የቆየው የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተላቆ ወደ ከተማው የተመለሰው በ2010 ዓ.ም. መጀመሪያ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ወደ ከተማው እንዲመለስ የተደረገው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ታሳቢ ያደረገው ገቢ መሰብሰብ ላይ ብቻ በመሆኑ ሲሆን፣ ይህም የከተማውን አነስተኛ ግብር ከፋዮች ችግር ውስጥ ከቷል በሚል ምክንያት ነው፡፡

ነገር ግን የከተማውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ የታክስ አሰባሰብ አሠራር እየተዘረጋ ነው ቢባልም፣ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ቁርጥ ግብር ከፋዮች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2008 ዓ.ም. 35.4 ቢሊዮን ብር፣ በ2010 ዓ.ም. 40.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. ደግሞ 45.7 ቢሊዮን ብር በጀት የያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የአንበሳው ድርሻ የሚመነጨው ከከተማው ነዋሪዎችና ከነጋዴዎች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች