Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቦምብ ፍንዳታው ምክንያት የታሰሩ ተጠርጣሪዎች ለአምስተኛ ጊዜ ተጨማሪ ምርመራ ተጠየቀባቸው

በቦምብ ፍንዳታው ምክንያት የታሰሩ ተጠርጣሪዎች ለአምስተኛ ጊዜ ተጨማሪ ምርመራ ተጠየቀባቸው

ቀን:

ለአራተኛ ጊዜ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርበው ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› በማለት ፍርድ ቤቱ አራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተሰጥቶባቸው በነበሩት፣ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጣሪዎች ላይ ለአምስተኛ ጊዜ ተጨማሪ ሦስት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተው በኋላ መርማሪ ቡድኑ የተሰጠው ጊዜ ቅዳሜና እሑድን የጨመረ ቢሆንም፣ ምስክሮችን መስማቱንና ሰነዶችን መሰብሰቡን መዝገቡ እንደሚያሳይ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ የተለየና የሚያሳምን ነገር ከሌለ በስተቀር የምርመራ መዝገቡን በሦስት ቀናት ውስጥ አጠናቆ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከተሰጠው አራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ውስጥ የሠራውን ተጠይቆ ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው፣ አጠቃላይ የምርመራ መዝገቡን ገምግሟል፡፡ በግምገማው ውጤትም ተጨማሪ ምስክሮችን መስማት፣ ሰነዶችን መሰብሰብና ወደ ክልል ከተላከ የምርመራ ቡድን ጋር ተገናኝቶ የተሠሩ የምርመራ ውጤቶች ላይ መወያየት እንደሚቀረው በማረጋገጡ፣ ይኼንን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንደሚያስፈልገው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መሥራት የሚገባቸውን ባላቸው ኃላፊነት መፈጸማቸውን ገልጸው፣ ‹‹ለምን እንደታሰርኩ አልገባኝም፤›› በማለት የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተቃወሙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ግርማ ካሳ ናቸው፡፡ የምርመራ ቡድኑ ለአምስተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀበት ምክንያት ተመሳሳይና አንድ ዓይነት መሆኑን አስረድተው፣ ‹‹እኔ በምርመራ ሥራ ብዙ ሠርቻለሁ፡፡ ይኼ ምርመራ ከሁለትና ከሦስት ቀናት በላይ አይወስድም፡፡ ሥራው የተመራበት ሰነድ በእጃቸው ነው፡፡ ሠልፉን ለማካሄድ የተነደፈው ዕቅድ በእጃቸው ነው፡፡ የሥራ ኃላፊነትን ከማስፈጸም ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ ፍላጎታቸው ተጨማሪ ጊዜ እየጠየቁ እኔን ማቆየት ነው፤›› ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ጨምረው እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን እንደሚይዝ ለፍርድ ቤቱ የተናገረ ቢሆንም፣ አንድም ሰው አልያዘም፡፡ ምስክሮችም ቢሆኑ፣ ‹‹ያለፍኩት ተፈትሼ ነው ወይም ሳልፈተሸ ነው፤›› ይላሉ እንጂ ሌላ የሚሉት የለም ብለዋል፡፡ የቀለበት አንድና የቀለበት ሁለት ኃላፊነት የፌዴራል ፖሊስ ሆኖ፣ ለምን እሳቸው እንደተያዙ እንዳልገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የምርመራ ቡድኑ ምርመራውን በአግባቡ ቢመረምር ኖሮ  በአጭር ጊዜ ምላሽ ያገኙ እንደነበር ጠቁመው፣ ‹‹እኔ ለአገሬ በሀቅ፣ በእውነትና በታማኝነት የሠራሁ ሰው ነኝ፡፡ ጥፋት ቢኖርብኝ በራሴ ላይ የምመሰክር ነኝ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብቴን ፍርድ ቤቱ ያስከብርልኝ፡፡ ክስ የሚመሠረተብኝ ከሆነ ወደፊት እከራከራለሁ፤›› በማለት የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚቃወሙ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

የምክትል ኮሚሽነር ግርማ ጠበቃ በተጨማሪ ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ ለፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ክርክር የሚያቀርቡት የላቸውም፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ ‹‹በተደጋጋሚ የሚነሳው ተመሳሳይ ነገር በመሆኑ ተከራክረን ጨርሰናል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ ብሎ የሰጠውን ተጨማሪ የአራት ቀናት የምርመራ ጊዜ አክብሮና አጠናቆ ማቅረብ የነበረበት መርማሪ ቡድኑ ነው፡፡ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ስለተፈለገና ዝም ተብሎ የሚቀርብ ሳይሆን፣ በሕግ የሚፈቀድ ነው፡፡ መርማሪዎቹ ደመወዝ የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናቸው፣ ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት አለባቸው እንጂ፣ ለአምስት ጊዜያት ተመሳሳይ ነገር ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ የለባቸውም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ለምን ትዕዛዝ እንደማያከብር መጠየቅ እንዳለበትና ያላግባብ ሰዎችን አስሮ ማስቀመጥ እንደማይችል እንዲነግርላቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምርመራ የሚያስፈልገው እውነትን ለማፈላለግ ነው፡፡ እያየን ያለነው ነገር ግን ይኼንን አያሳይም፡፡ ሥራው የጠበቃ ወይም የመርማሪ ቡድን ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ነው፤›› በማለት ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑን መጠየቅና የምርመራ መዝገቡንም ማየት እንዳለበት ጠበቃው ተናግረው፣ ደንበኛቸው ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ጋር በቦምብ ፍንዳታው ተጠርጥረውና ታስረው የሚገኙ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ ታስረው የሚቆዩበት ምክንያት እንዳልገባቸውና ፍርድ ቤት ካላስቆመው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጥያቄ እንደማይቆም ጠቁመው፣ ኃላፊነታቸውን በሚገባ በመፈጸማቸው መርማሪ ቡድኑ በታሰሩባቸው 38 ቀናት ውስጥ ለምርመራ የጠራቸው ከሁለትና ከሦስት ጊዜ እንደማበልጥ አስረድተዋል፡፡ መጠርጠራቸውን የማይቃወሙ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተጣሰ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹መርማሪዎቹ የአለቆቻችንን ውሳኔ እየጠበቁ ነው፤›› የሚሉት ተጠርጣሪዎቹ፣ ፍርድ ቤቱ መብታቸውን ጠብቆ በዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡ ትኩረት ያደረገው ኃላፊነታቸውን አለመወጣት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የቦምብ ፍንዳታው ሆነ ተብሎ የተደረገ ነው የሚል ነው ብሏል፡፡ ምስክሮቹ በርካቶች በመሆናቸውና አንዳንዶቹ፣ ‹‹የሆነ ነገር ዓይቼ ስነግረው ዝም አለኝ፣ ተጠርጣሪ ይኼ ይፈተሽ ስለው አልፈትሽም አለኝ፤›› የሚሉና የተወሰኑት ደግሞ የተጋነኑ በመሆናቸው እያጣራ መሆኑን፣ ሰነዶቹንም በድጋሚ እየፈተሸ እንደሆነ መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ችግር እንደሌለና መርማሪው ሥራውን መሥራት ይችላል እያሉ ነው ችግራችሁ ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶለት፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ የሠራዊቱ አካል በመሆናቸው ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ በመሆኑም የዋስትና ጥያቄያቸውን እንቃወማለን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ‹‹በተሰጣቸው ተጨማሪ አራት ቀናት ውስጥ ለምን አልጨረሳችሁም?›› በማለት በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ አጠቃላይ የምርመራ መዝገቡን ሥራ ገምግሞ ቀሪ ሥራዎችን መለየቱንና በመሀልም ቅዳሜና እሑድ ስለነበር ከሌላ መርማሪ ቡድን ጋር መነጋገሩን አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካሰማ በኋላ፣ ከላይ እንደተገለጸው ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሦስት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...