በሕግና በሥርዓት የማይተዳደር አገር የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ ይሆናል፡፡ በተለይ አገር የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ስትሆን ሕግና ሥርዓት ካልኖረ ለትርምስ በር ይከፈታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚሰሙት የግጭት፣ የሞትና የውድመት ዜናዎች እረፍት ይነሳሉ፡፡ ለዓመታት የተዘጉ እስር ቤቶች ተከፍተው እስረኞች ሲለቀቁ፣ በከባድ የጭቆና ቀንበር ውስጥ የቆዩ ሰዎች ዘና ሲሉ፣ በዝምታ ተሸብበው የነበሩ አንደበቶች መናገር ሲጀምሩ፣ ስለፍትሕና ነፃነት ሲጮኹ የነበሩ ተስፋ ሲሰንቁና አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ አጓጉል ድርጊቶች አደብ ሲገዙ ለውጥን ማስተናገድ አለመቻል ያስተዛዝባል፡፡ የመከራ ቀንበር ተጭኖብን ቆይቷል የሚሉ ወገኖችም ሆኑ፣ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያለፉ ሰዎች ለውጥን ማስተናገድ አቅቷቸው በየቦታው ሞትና ውድመት ሲሰማ ለምን ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ችግር ውስጥ የሚከቱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ሲፈጸሙ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ አይቻልም፡፡ ሕግና ሥርዓት እየተናዱ በየቦታው ጉልበተኞችና እንዳሻቸው አዳሪዎች ሲፈነጩ ዝም ማለት፣ ራስን ለሌላ ዙር ቀውስ ማዘጋጀት እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በአንድ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ ‹‹የጭቆና ቀንበርን መሸከም የቻለ ጫንቃችን ነፃነትን ማስተናገድ እንዴት ያቅተዋል?›› እንዳሉት፣ ምራቃቸውን የዋጡ አንጋፋዎች በእየካባቢያቸው ይኼንን መልዕክት የማስተላለፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ በረባ ባልረባው ምክንያት የሚፈጠር የግለሰብ ፀብ ሳይቀር የብሔር ገጽታ እየተላበሰ በየቀኑ የግድያ ዜና መስማት ያሳምማል፡፡ ለውጡን በይቅር ባይነትና በፍቅር መቀበላቸውን በአደባባይ የሚገልጹ ሰዎች ሳይቀሩ፣ ጥላቻና ቂማቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ እነሱን እንደ አርዓያ የሚከተሉ ወጣቶች ደግሞ አንድ ነገር ሲፈጠር ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ይሰማራሉ፡፡ ፀጥታ ማስከበር የሚገባቸው ተቋማትም ሆኑ አመራሮች ከሕገወጦች ጋር መፋጠጥ ስለማይፈልጉ አሳዛኝ ጉዳቶች እየደረሱ ነው፡፡ ሕግ ማስከበር የሚገባቸው አካላት ሳይቀሩ ሲፍረከረኩ ሕግና ሥርዓት እንዴት ይኖራል? ይኼ ችግር በጊዜ እልባት ካልተደረገለት የአገር ጉዳይ ያሳስባል፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ አፅንኦት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል እጅግ በጣም ከመበላሸቱ የተነሳ፣ የቂምና የቁርሾ ሕመም አገር እንደሚያጠፋ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ለማጥፋትና የበላይነት ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ የፖለቲካው ደዌ ማሳያ ነው፡፡ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት እርም በሆነበት ልማዳዊ አኗኗር ላይ፣ ብልሹው ፖለቲካ ተጨምሮበት አገርና ሕዝብ ብዙ መከራ አይተዋል፡፡ ለአገሩ ላቡን ጠብ አድርጎ የሠራ ትሁት ሰው በአደባባይ በጥይት በሚገደልበት በዚህ ዘመን፣ መረጃና ማስረጃ ተጠናቅሮ በይፋ የገዳዩ ማንነት ሳይረጋገጥ የደም ፍላት ዕርምጃ በተገኘው ላይ ለመውሰድ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል በበዛበት በዚህ ጊዜ፣ ኧረ ይኼ ነገር ለአገር መዘዝ አለው የሚል የሽማግሌ ድምፅ በማይሰማበት በዚህ ወቅት፣ የሕግ የበላይነት ልዕልና ካላገኘ ጦሱ የሚተርፈው ለሕዝብ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው ማንኛውም ክስተት ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ አንደኛው የበላይነት ያገኘው ከማንም የበለጠ የሚደመጥበት፣ ሁለተኛው ተሸናፊው ወይም ቀን ዘንበል ያለበት ድምፀ ሰላላ መሆኑን ነው፡፡ ይኼን ጊዜ ታዲያ ፍትሕ ያስፈልጋል፡፡ ፍትሕ የሚሰፍነው ደግሞ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት መኖሩ የሚበጀውም ሕገወጥነትን ለመከላከል ይሆናል ማለት ነው፡፡
የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕግና ሥርዓት ሲያስከብሩ የዜጎች ነፃነትና መብት ዋስትና ያገኛሉ፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብ በነፃነት መግለጽ አለበት፡፡ የፈለገውን የመደገፍ ያልፈለገውን የመቃወም መብቱም እንዲሁ፡፡ በመላ አገሪቱ በፈለገው ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት በሕግ የተረጋገጠለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በማንነቱም ሆነ በእምነቱ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስበት የሚከላከልለት ሕግ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ዋስትና የሰጠውን ሕግ ተማምኖ በመላ አገሪቱ ተሠራጭቶ የሚኖር ኢትዮጵያዊ በሕገወጦች ምክንያት ከቀዬው ሲፈናቀል፣ ሲዘረፍ፣ ሲገደልና ሲሳደድ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበትን የቅርብ ጊዜ ክስተት ብቻ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ መብራት ለምን ጠፋብን ተብሎ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው በማይመለከታቸው ጉዳይ ሲገደሉ ወዴት እያመራን ነው መባል አለበት፡፡ አንድ ችግር ባጋጠመ ቁጥር የገዛ ወገንን የጥቃት ሰለባ ማድረግ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ ከፊታችን ከፍ ያለ አደጋ ይጠብቀናል፡፡
አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ነገሮችን እየታዘበ ነው፡፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሚመለከታቸው አካላት የሚናገረው ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ልማትና ዕድገት አይታሰቡም፡፡ ሰላም ከሌለ እንኳን ልማት አገርም አትኖርም፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበል የዘለቀው አብሮ በሰላም በመኖር ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ማንነትና እምነት ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ ትስስር ፈጥሯል፡፡ ይህ የሚያኮራ የጋራ እሴቱ በዚህ ዘመን በሕገወጦች ሲደፈር በሕግ መባል አለበት፡፡ የገዛ ወገኑን በአደባባይ ገድሎ የሚደበቀውም ሆነ ነውሩን መሸፈን ያልቻለው በሕግ ሊዳኝ ይገባዋል፡፡ ከዚህ በፊት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እያጋጩ ደም እንዲፈስ ያደረጉና በአገር ላይ ሰቆቃ የፈጠሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ለሕግ ባለመቅረባቸው፣ አሁንም የንፁኃን ደም በየቦታው ያለጠያቂ ይፈሳል፡፡ ሕግ በሌለበት ሥፍራ እንዴት ስለመብትና ነፃነት መነጋገር ይቻላል? በግልጽ የተፈጸመ ወንጀል እየተድበሰበሰ እንዴት ሆኖ ነው ስለሕግ የበላይነት ማውራት የሚቻለው? ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
መንግሥት ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነቱ የሚጀምረው ደኅንነቱን በመጠበቅ ነው፡፡ የፀጥታና የፍትሕ አካላትም ወንጀል ሲፈጸም ተከታትሎ በመያዝ ተገቢው ፍትሕ እንዲሰፍን የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነት እያገኘ ሲሄድ ውጤቱ ውድመት ነው፡፡ አገር የለውጥ ማዕበል ውስጥ ሆና ከአገር ቤት እስከ ሰሜን አሜሪካ ድረስ የአንድነት መዝሙር እየተሰማ፣ በተቃራኒው አገርን የሚያፈራርሱ ሕገወጥ ድርጊቶችን በቸልታ ማለፍ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት የፈጸሙ፣ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ላይ ግድያ የፈጸሙ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች በወገኖቻችን ላይ ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት ከላይ እስከ ታች ያሉ የሚመለከታቸውን መዋቅሮቹን በፍጥነት አንቀሳቅሶ ለሰላምና ለመረጋጋት ሥጋት የሆኑ ድርጊቶችንና ፈጻሚዎችን በሕግ መፋረድ አለበት፡፡ የአገርን አንድነትና የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩ ድርጊቶች መቀጠል የለባቸውም፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ሰብዓዊነት ጠፍቶ ጭካኔ ይነግሳል፡፡ ወደ እንስሳነት ይወረዳል፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ አገር በረት ይሆናል!