Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር በአንድ ወር ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አቅዷል

የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር በአንድ ወር ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አቅዷል

ቀን:

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሰውም የለውጡ አካል ለመሆን እንደሆነ ገልጿል፡፡ ወደ አገር ቤት የሚመለሰውም በተቋማት ሪፎርምና በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ በዚህም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን እንደሚጀምር ገልጿል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከመበታተንና ከመለያየት የምትድነው እውነተኛ ዴሞክራሲ ሲመጣ በመሆኑ፣ እኛም የምንፈልገው ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እንዲመሠረት ነው፤›› ሲሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) አስታውቀዋል፡፡

ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ማክሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ከአሜሪካ ለኢሳት፣ ለቪኦኤና፣ ለሌሎች የውጭ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዴሞክራሲ እንዲኖራት፣ አሁን እየታየ ያለው መልካም ጅምርና እንቅስቃሴ ማለፍ እንደሌለባት ተናግረዋል፡፡ አገርን በተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ለማስቀመጥ በየጊዜው የሚመጣውን ለውጥ እያካተተ የሚሄድ የፖለቲካ ሥርዓት መፈጠር እንዳበትም አክለዋል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ወቅት አገራዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቁመው፣ ሁሉን አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ከተፈጠረ ሕዝቡ ራሱ የሥርዓቱ ጠባቂ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡ አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ መታገል ያለባቸው፣ አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ሳይሆን፣ ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት መሆን እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖሊሲና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊለያዩ ቢችሉም፣ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ ማስኬድ እንዳለባቸውና አንድ በሚያደርጓቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ የተለያዩ ጥቅሞች ባሉበት አገር ‹‹የእኔ ብቻ አመለካከት ትክክል ነው›› ማለት አደገኛ መሆኑን የተናገሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ በየደቂቃው የሚለዋወጥና የሚነሳ የፖለቲካ ጥያቄን በአንድ ጊዜ መመለስ አደጋ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥያቄ ማኅበረሰቡን የሚመለከት ሆኖ በቤተሰብ፣ በቡድን፣ በግልና በአገር ደረጃ ምላሽ የሚሰጥበት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚሰጥ ውሳኔ ለኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን፣ በክልሉ ለሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰብ ክፍሎችም መሆን እንዳለበት በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

ወደ አገር ቤት ሲመጡ ሊገጥማቸው የሚችሉ አደጋዎችን እንዴት ለመቋቋም እንዳሰቡ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በለውጥ ሒደት ውስጥ አደጋዎች አሉ፡፡ አደጋው ግን የሚመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከሆነ አገር ትፈራርሳለች እንጂ ሕዝቡ አይቀበለውም፣ ትግሉም አይቀለበስም፡፡ በዚህ ሒደት ሰው ሊጎዳ ይችላል፡፡ ይኼንን ኃላፊነት ለመውሰድም ቆርጠን ነው ወደ ትግሉ የገባነው፤›› ብለዋል፡፡ አልጋ በአልጋ ከሆነ በኋላ እንሄዳለን ብለው እንደማያስቡም አክለዋል፡፡ በፖለቲካ ድንጉጦች እንዳልሆኑና ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያዩ የኖሩት ሒደት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በአሜሪካ ዋሽንግተን ባደረጉት ውይይት በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ውስጥ መለወጥ ያለባቸው ተቋማትን ብቻ ሳይሆኑ፣ የተበላሸውንና የዘቀጠውን የማኅበረሰቡን የሞራልና ግብረ ገብነት ጭምር መሆኑንም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ያለ ሞራል ስለማይሆን፣ ሥር የሰደደ የሞራል ዝቅጠት እንደገና መገንባት እንዳለበትም በውይይታቸው መስማማታቸውን አክለዋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያም ባደረጉት ውይይትም 300 እና ከዚያ በላይ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ከአራት ያልበለጡ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ስለማይኖሩ ወደዚያ በማጥበብ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ለመሄድም እንደሚሠሩ መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶላቸው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ በምርጫ ተወዳድረው ሥልጣን መያዝ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ ሁሉንም የሚያስማማ ዝርዝር ፕሮግራምና ፖሊሲ ይዘው እንደሚቀርቡም ገልጸዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱላቸው ሌላ ጥያቄ መከላከያ፣ ፖሊስና ደኅንነት ከማንኛውም ወገንተኝነትና ፖለቲካ ነፃ ሆነው ሁሉንም ፓርቲዎች ሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች በእኩልነት እንዲያገለግሉ በአዲስ ማዕቀፍና አደረጃጀት እንዲዋቀር የሚል ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳቡ ጥሩ መሆኑን ደግፈው ይኼ የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንደሆነና ግን ተግባራዊ እንደሚደረግ እንደተስማሙ ገልጸዋል፡፡

ነፃ ሆኖ የሚሠራ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግን እንደሚለወጡ ስምነት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ይኼንን የተገኘ ዕድል የማትጠቀም ከሆነ ጉድ ትሆናለች፤›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርር ባለ ሁኔታ ሳይሆን ‹‹ያሠራል ወይም አያሠራም›› የሚለውን ማየት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ፌዴራሊዝም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ የቋንቋ ፌዴራሊዝም ጉዳት የታየ በመሆኑ፣ ለሕዝቡ የሚጠቅም ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡    

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ሲል የተፈረጀበት አሸባሪነት በቅርቡ ከተነሳለት በኋላ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመጀመር ተኩስ ማቆሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...