Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዘላቂነት ያለው ዝግጅት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዘላቂነት ያለው ዝግጅት እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

ቀን:

በአልጀሪያ በተካሄደው ሦስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣት ቡድን፣ በመድረኩ 11 የወርቅ፣ ስምንት የብርና ስድስት የነሐስ በድምሩ 25 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ውድድሩን አጠናቀቀ፡፡ ቡድኑ ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲገባ አቀባበል ይደረግለታል፡፡

የወጣቶቹ ድል እሰየው እንደሚያሰኝ ቢታመንም፣ በተለይም በዘንድሮው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች የተመዘገው የሜዳሊያ ብዛት ካለፉት ዓመታት አንፃር ቁጥሩ ያነሰ ማነሱ ታይቷል፡፡ የተመዘገቡት ውጤቶች ብዙ ጊዜ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሚነገርላቸው ውጪ ባሉ አዳዲስ ስፖርቶችና የውድድር መስኮች የተገኙ ድሎች የታዩበት መሆኑ ግን ተስፋ የታየባቸው የውድድር መስኮችን ማሳየቱ አልቀረም፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቡድኑን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ትኩረት የማያገኙ ስፖርቶችን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ስፖርቶች ዘላቂነት ያለውና ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 6 እስከ 18 ቀን 2018 ለሚደረገው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመሩን የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በአልጀርሱ የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ምንም እንኳ በአትሌቲክሱ ዘጠኝ፣ በብስክሌት ሰባት፣ በቦክስ አምስት፣ በወርልድ ቴኳንዶ አራት፣ በድምሩ 25 ሜዳሊያዎች ቢመዘገቡም፣ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ውጤቱ በቂ ነው እንደማይቻል በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ለውድድሮች የሚሰጠው ትኩረትና ዝግጅት በቂ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለመደው ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› ዓይነቱ አሠራር ተላቆ ስፖርቱ የሚጠይቀው አቋምና አቅም ላይ መገኘት እንደሚያስፈልግ፣ ‹‹ለዚህም ሲባል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለቦነስ አይረሱ የወጣቶች ኦሊምፒክ ዝግጅቱን ከወዲሁ ለመጀመር መወሰኑን ይፋ ያደርጋል፤›› ሲሉ ዶ/ር አሸብር አክለዋል፡፡

በመሆኑም በአትሌቲክስ፣ በቦክስና በወርልድ ቴኳንዶ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ አትሌቶች በመጪው የኦሊምፒክ ውድድር ቀጥታ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ሲታወቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡት ግን የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ወደፊት በሚያወጣው መሥፈርት መሠረት የተሳትፏቸው ሁኔታ እንደሚወሰን ተነግሯል፡፡

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ያነሱት ሌላው ጉዳይ፣ መገናኛ ብዙኃን ለሁሉም ስፖርቶች እኩል ትኩረት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ነው፡፡ በአልጀርሱ የአፍሪካ ወጣቶች ውድድር ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 25 ሜዳሊያዎች 16ቱ የተመዘገቡት በብስክሌት፣ በቦክስና ወርልድ ቴኳንዶ ነው፡፡ እነዚህ ስፖርቶች ከአትሌቲክሱና እግር ኳሱ አኳያ ሲታዩ የሚሰጣቸው የሚዲያ ትኩረት እጅጉን ያነሰ እንደሆነ አመራሮቹ በማስታወስ ሚዲያው ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ከዝግጅት አኳያ አንዳንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የማዘውሪያ እጥረት እንዳለባቸው፣ ችግሩን ለማቃለል ሲባል በብሔራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሜ ልምምድ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም፣ ከአካዳሜው አንዳንድ ኃላፊዎች ቀና ትብብር እንደማይደረግላቸው በመግለጫው ወቅት ተነስቷል፡፡

ብሔራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሜ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በበኩላቸው፣ በዚህ ጉዳይ እስከ አሁን ባለው አካሄድ ከአካዳሜው ትብብር አላገኘሁም ብለው ቅሬታ ያቀረቡላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አካዴሚው ከተሰጠው ተልዕኮ በመነሳት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር እየሠራ የሚገኘው በትብብር ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ በሁሉም ስፖርቶች ማለት በሚያስችል መልኩ አካዴሚው ያፈራቸው ወጣቶች የብሔራዊ ቡድን ውክልና ማግኘት እየቻሉ ስለሆነ ትብብሩ በከፊል ሳይሆን የተሟላ ነው፤›› በማለት ተቋሙ የሚቀርብበት ወቀሳ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...