Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፈተናዎች የታጠረ ሕይወት

በፈተናዎች የታጠረ ሕይወት

ቀን:

ራሷ ላይ ሻሽ ሸብ አድርጋለች፡፡ ስትንቀሳቀስ ከወገቧ ጎንበስ ብላ ሲሆን፣ ስታወራም በዝግታና እየደከማት ነው፡፡ ጎዳናን ቤቷ ካደረገች ከስድስት ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ በጎዳና ላይ ተደፍራ ያረገዘችውን ፅንስ ለማቋረጥ አሥር ዓይነት ባህላዊ መድኃኒቶችና ከ18 በላይ ዘመናዊ መድኃኒቶችን አፈራርቃ በመጠቀሟ፣ ለዕድሜ ልክ የጉበት በሽታ ተዳርጋለች፡፡ ወጣቷ ኮከብ በቀለ ትባባለች፡፡ የተወለደችው ጅማ ከተማ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡

‹‹በሦስት ዓመቴ አዲስ አበባ ያለችው የእንጀራ እናቴ እኔን ለማሳደግና ለማስተማር አየር ጤና አካባቢ ወዳለው መኖሪያ ቤቷ ወሰደችኝ፡፡ ለዘጠኝ ዓመታት ግን በእኔ ላይ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰችብኝ፣ የቤት ሠራተኛ ሆኜ እየሠራሁ ቆየሁ፡፡ ከዚያም አንድ ቀን ባገኘሁት አውቶብስ በመሳፈር ተክለ ሃይማኖት አካባቢ ላስቲክ በመዘርጋት የጎዳናውን ኑሮ ተቀላቀልኩ፤›› የምትለው ኮከብ፣ ቀስ በቀስ የሁሉም ሱሶች ተገዥ የሆነችበትን ሕይወት እንዲህ ትተርካለች፡፡

የጎዳና ሕይወት በተለይ ብቻዋን ላለች ሴት ‹‹የምድር ገኃነም ነው›› በማለት አደገኛውን የጎዳና ሕይወት ትገልጻለች፡፡ እህትና ወንድሟን ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸው ጎዳና ላይ አግኝታቸው ነበር፡፡ አብረው ለመኖር ቢሞክሩም ስላልተሳካ በድጋሚ ተበታትነናል፡፡

የወሰደቻቸው መድኃኒቶችም ያሰበችውን ሳያሳኩ በመቅረታቸው ለመውለድ የተገደደችው ኮከብ፣ በምጥ ለመውለድ አቅሙም ጉልበቱን ስላልነበራት በቀዶ ጥገና ተገላገለች፡፡ ቁስሉም ቶሎ ባለመድረቁ ብዙ ጊዜ በኢንፌክሽን ተሰቃይታም ነበር፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነባትን የጎዳና ሕይወት ትታ ወደ ዘመድ ለመጠጋት ያደረገችው ሙከራ፣ ሞራል በሚነካ ስድብ ወደ ጎዳና እንድትመለስ አደረጋት፡፡

በፌዴራል የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል መንግሥትና በኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ኤቨሎፕመንት ማኅበር አማካይነት በትብብር ሕፃናትን ከጎዳና በማንሳት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ፣ የማቋቋሚያ ገንዘብ በመስጠት፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ በሐዋሳ እየተሠራ ይገኛል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወ/ሮ የዓለም ፀጋዬ፣ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፓርላማ አባላትና የክልሉ ባለሥልጣናት ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በቦታው ተገኝተው የማኅበሩን ተግባር ጎብኝተው ነበር፡፡ ከጎዳና ተነስተው ወደ ተቋሙ በመግባት፣ ከአምስት ጊዜ በላይ ሥልጠና ወስደው ተመልሰው ዳግመኛ ጎዳና ከወጡ ልጆች ጋር ሚኒስትሯ ተነጋግረዋል፡፡

ልጆቹ ከመንግሥት ምን እንደሚፈልጉ? በተደጋጋሚ ጊዜ ጎዳና ለመውጣት የሚገደዱበትን ምክንያት በተለመለከተ የተደረገው ውይይት ትልቅ ትኩረትን የሳበ ነበር፡፡ ሕፃናቱ ወደ ጎዳና የወጡበትንም ምክንያት ሲናገሩ ያለምንም ፍርኃትና ውሸት አለመሆኑን ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ አብዛኛው ንግግሮቻቸውም በአዳራሹ የተገኘውን ታዳሚ በዕንባ ያራጨ ነበር፡፡

የአሥር ዓመቱ ኤርምያስ ታየው፣ ወላይታ አካባቢ እንደተወለደ ይናገራል፡፡ ወደ ጎዳና ከወጣም አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ወላጅ አባቱ ሰክሮ እየመጣ ሌሊት እሱንና እናቱን እየደበደበ ስላሰለቸው ነበር የጎዳናን ሕይወት የተቀላቀለው፡፡ ወደ ቤት ቢመለስም ከወላጆቹ ቤት የተሻለ ሕይወት ጎዳና ላይ እንዳለ ገብቶት ወጣ ገባ ሲል ቆይቷል፡፡ አንድ ቀን ግን አባቱ እንደተለመደው እናቱን በሆዷ አስተኝቶ ጀርባዋን በብረት ክፉኛ ሲደበድባት በአፏ ደም ሲወጣ ዓይቶ በዛው ሌሊት ወጥቶ ቀረ፡፡ ይህንን እንደ ጎርፍ በሚወርደው ዕንባው ታጅቦ ሲገልጽ፣ ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ ለቅሶውን ተጋርቷል፡፡ በመከራ የታጀበውን የጎዳና ሕይወት በአንደበታቸው መግለጽ አቅጧቸው ምንም ሳይተነፍሱ ዕንባ እየተናነቃቸው ከመድረኩ የወረዱም ነበሩ፡፡

‹‹እኛ ዛሬ የተገኘነው ለመናገር ወይም ጎብኝተን ለመሄድ አይደለም፡፡ ተናጋሪዎች እናንተ ድጋሚ የማንወጣው ይህ ሲሆን ነው የምትሉትን በመስማት ለመፈጸምና የጉዳዩ ባለቤትም እንድትሆኑ ነው፤›› በማለት ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡  ዕድል አግኝተው መናገር ከቻሉት ከስድስት እስከ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎች መካከል በልጅነታቸው ልጅ የታቀፉና ልጆቻቸው የጠፋባቸው እናቶች ይገኙበታል፡፡

በቤተሰቦቻቸው ተገፍተው ወላጅ አልባ ሆነው፣ ጥቂቶቹ ደግሞ በጓደኞቻቸው መካሪነት ወደ ጎዳና እንደወጡ ተናግረዋል፡፡ ከጎዳና ሕይወት ለማላቀቅ የተለያዩ ድጋፎች በባለድርሻ አካላት ቢደረጉላቸው መልሰው መላልሰው ጎዳና የሚወጡት በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ተከታታይነት የሌለው የመንግሥት ድጋፍ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ ተብሎ የሚሰጣቸው ገንዘብ አናሳ መሆን፣ መጠለያ ማጣትና ማኅበረሰቡ ለእነሱ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

በግቢው ከሚገኙት አገልግሎት መስጫ ውስጥ አንዱ በሆነው ሕክምና መስጫ የሚሠሩት አቶ ተስፋሁን ዮናስ፣ ‹‹በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕፃናት በአብዛኛው በቆዳ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን፣ ሴቶቹ ደግሞ በሚተላለፍ በሽታ ይጠቃሉ፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ወደ ማዕከሉ የሚገባ ማንኛውም ሠልጣኝ መጀመርያ በክሊኒክ የጤና ምርመራ ተደርጎለት ክትትል የሚያስፈልገውን በመለየት አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አደንዣዥና አነቃቂ ዕፆችን የሚጠቀሙም ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡ የሱስ ተገዥ የሆኑትን አክሞ ከሱስ እንዲፀዱ የማድረጉ ሒደት ከሌላው ከበድ ይላል፡፡ የሚፈልጉትን ሲያጡ ራሳቸውን ስተው የሚሆኑት ግራ የሚገባቸው አሉ፡፡ አንዳንዴም በአጥር ዘለው ለመውጣት ሙከራም ያደርጋሉ፡፡

በኤልሻዳይና በክልሉ መንግሥት ትብብር የሚሠራው ይህ የጎዳና ልጆችን አንስቶ፣ አሠልጥኖ፣ መቋቋሚያ ሰጥቶ፣ ወደ ወላጆቻቸውና ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀለው ማሠልጠኛ በ2009 ዓ.ም. 120 ድንኳኖችን ተክሎ ነበር ወደ ሥራ የገባው፡፡ ዘጠኝ ሔክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 4,800 ወጣት ሥራ ፈላጊዎችን በመጀመርያው ዙር ተቀብሎ 2,300 ዜጎችን ሥራ አስይዟል፡፡ ማኅበሩ 2,500 የሚሆኑትን ደግሞ ከሱስ ነፃ በማድረግ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና በመስጠት ወደ ቤተሰቦቻቸው አቀላቅሏል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ 16 ሺሕ ወጣቶችን ከሱስ በማላቀቅ አምራች ዜጋ በማድረግ ወደ ኅብረተሰቡ አቀላቅሏል፡፡ ከአንድ ወር በፊትም ማኅበሩ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ መኖሪያ ክፍሎችን፣ መመገቢያ አዳራሾችና መዝናኛ ክፍሎችን አስገንብቷል፡፡

ማኅበሩ ከሐዋሳ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተራራ ሥር ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ይገኛል፡፡ ንፅህና በግቢው የመጀመርያ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ፣ ሁሉም ክፍሎች ንፁህ ናቸው፡፡ አንዱ ክፍል እስከ 40 ሰው ሊያስተኛ ይችላል፡፡ በመኝታ መግቢያ በራቸው ላይ የተለያዩ አደባባዮችን በአበባ ሠርተው ግቢውን አረንጓዴ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡

በዚህ ግቢ ከአንድ ቀን የጎዳና ሕይወት ጀምሮ እስከ አሥር ዓመት ድረስ ጎዳና ላይ የኖሩ ሰዎች፣ በሱስ ተጠምደው የነበሩና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እዚህ ላይ ትልቅ ሥራ ካልተሠራ ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ግጭት ይፈጠርና መመለሳቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ በእናቶቹ ልጅ ይዘው ከወጣቶች ጋር አንድ ክፍል መጋራታቸው አስቸጋሪ ነው፡፡

የኤልሻዳይ ሪሊፍ ዴቨሎፕመንት ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ወልደ አብርሃ ሃድጎ ልጆችን ለማሠልጠን ከፍተኛ ወጪ ከወጣ በኋላ ተመልሰው ወደዚያው ሕይወት ለምን ይገባሉ? የእናንተስ ድርሻ ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ኤልሻዳይ መጀመርያ ፕሮጀክት ያቀርባል፡፡ ከዚያም ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት ጋር በመመካከርና በመተጋገዝ ይተገበራል፡፡ ከዚያም ልጆቹን ተቀብሎ በአገሪቱ ያሉ በተመረጡ መምህራንና በሳይኮሎጂ ሐኪሞች በመታገዝ ተቀብሎ ያስተምራል፣ ያሠለጥናል፣ ከሱስ ነፃ በማድረግና ለሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ልጆቹን የመሰብሰብ፣ ሥልጠና ሲጨርሱ ሥራ የማስያዝና ከቤተሰቦቸው የማገናኘት የሌሎች አካላት ሥራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኤልሻዳይ ልጆች ለምን እንደሚመለሱ በራሱ ባጠናው ጥናት መሠረት አንዳንድ ኃላፊዎች የሥራ ድርሻቸውን ስለማይወጡ፣ ለዚህ ተግባር የተመደበ በጀት ለሌላ ጉዳይ ስለሚውልና በቂ ክትትል አለመደረጉ ለልጆቹ መመለስ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...