Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልክረምት በሥነ ቃል

ክረምት በሥነ ቃል

ቀን:

ሐምሌ በብዙ ነገሩ የክረምትን ውበትና ጣዕም ያሳያል፡፡ ክረምትን ተከትለው የሚመጡት ለመብል የሚውሉት እነ በቆሎ፣ በለስና ስኳር ድንች ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ክረምት ለማሰላሰያ ዕድል ይሰጣል የሚሉም አሉ፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ሌሎችም ባመዛኙ የሚያርፉበት በመሆኑ የጽሞና ጊዜን እንዲያሳልፉ ዕድል ይሰጣል።

ለዚህም ነው በያሬዳዊ ብሂል የዝናብ ኮቴ ሲሰማ፣ ዝናብ ሲዘንብ የተቸገሩ ይደሰታሉ፣ የተጠሙ የተራቡ ይጠግባሉ የሚባለው፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው የክረምት ወቅት የዝናብ ወራት ነው፡፡ በፀደይና በመፀው መካከል ያለ ክፍለ ዓመት ሲሆን እስከ መስከረም 25 ድረስ ይቆያል፡፡

መዝሙረኛው እንደሚለው ሰማዩ በደመናት የሚሸፈንበት ለምድርም ዝናብ የሚዘጋጅበት ሣር በተራሮች ላይ የሚበቅልበት ለምለሙ ሁሉ ለሰው ልጆች ጥቅም የሚውልበት ነው ክረምት፡፡ በረዶውና ውሽንፍሩ ብርቱውም ዝናብ በምድር ላይ የሚወድቁበት ነው ክረምት፡፡

የደመናትን ንብርብር፣ ከድንኳኑም የሚሰማውን ነጎድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል? በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፣ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል?  ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትም እንደተዘጋጁ ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ለሰው ልጅ ሁሉ ተዘጋጁ፡፡

በየዓመቱ ከሐምሌው ክረምት ጋር ተያይዞ የመጀመርያ ሳምንት «የዛፍ ሳምንት» እየተባለ ሲከበር የነበረውላቅሴት ያለውን የኢትዮጵያን የደን ሀብት ከማልማትና ከመንከባከብ አንፃርብረተሰቡንዲያተኩርበት ለማድረግ ነው፡፡

ዛፍ ከባህልና ከኪነ ጥበባት ጋር የተቆራኘ በተረትና ምሳሌ የመገለጽ ዕድሉም የጎላ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዛፍ ተምሳሌ ነው፡፡ የቤተሰብን መሠረት፣ የመኖሪያ አካባቢን በማጠናከር ረገድ ይጠቀሳል፡፡

ዛፍ የተለያየ ዓይነት ዝርያንዳለው ሁሉ አንዱ ከአንዱ ልዩነት ያለው በመሆኑም ለተለየ አገልግሎት የሚመረጥ ይሆናል፡፡ ከሰዎችም የሚለዩ በሥልጣን፣ በዕውቀት ወይም በሹመት የሚመረጡ ልሂቃንም ይኖራሉና፡፡ «ከሰው መርጦ ለሹመት ከዛፍ መርጦ ቦት» የተሰኘውን አነጋገር አትርፏል፡፡

በዕውቀት የጎለመሱ፣ ለአገር መልካም ትሩፋት ያተረፉ ሊቃውንት የመበርከቸው ያህል «የአቡጊዳ ሽፍቶች» ለዕውቀት የማይተጉም ያጋጥማሉ፡፡ ሊቃውንቱ በዝም ይሁን በቦ ባለመኖራቸው ብልጣ ብልጦች የሚከሰቱበት አጋጣሚም አይጠፋም፡፡ በዚህም አጋጣሚ ነው የዛፍ ተምሳሌዊነት ብቅ ያለው፡፡ «ዛፎች ቢጠፉ፣ ቁጥቋጦዎች ተሠለፉ፣ ዋርካ በሌለበት ዋጮ አድባር ይሆናል፡፡» ተብሎ የተተረተው፡፡

ከውጭ ከሚመጡት የዛፍ ችግኞች ይልቅ አገር በቀሉ ዛፍ ለመልከዓ ምድሩ አስፈላጊ መሆኑብረተሰቡንምንደሚደግፍ መንበታል፡፡

«እኔን ይክፋኝንጂ አገሬን መች ከፋው

አበቀለ ግራር ዝሆን የማይገፋው» የግራር ጠቃሚነትን ያነፀረበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከምዕት ዓመት በፊት የነበራት የዛፎች ብርካቴየመነመነ ሄዶ መልከዓ ምድሩ መራቆቱ ግልጽ ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋውን ያስተዋለው አገሬውንዲህ ተቀኝቷል፡

«ቆረጡት ቆረጡት

ዋርካውን ቆረጡት

ዝግባውን ቆረጡት

ነዛፍ አያውቁ

ምን ያፈራ ይሆን

ብለው ሳይጠይቁ፡፡»

ይህን ክስተት ለመታደግ ነው፡፡ በሚሊኒየሙ አከባበር አጋጣሚ፣ በዋዜማው «ሁለት ዛፍ ለሁለት ሺሕ» እ «ሦስት ዛፍ ለሦስት ሺሕ» በሚል መሪ ቃላት የችግኝ ተከላው በይሁንእየዘለቀው፣ ልጄ ብቻ አይደለም ትምህርት የሚያስፈልገው ደጄም ዛፍ ማግኘት አለበት በሚል መነሻም «ትምህርት ለልጄ፣ ዛፍ ለደጄ» የሚለው ብሂልንም ስንቁ አድርጎት ነበር፡፡ ስለመዝለቁ አልተሰማምንጃ፡

ዛፍ ለገጣሚዎችም መነሻ ሆኗል፡፡ ተስፋን፣ ጉጉትንና ምኞትን ከዛፍ ጋር አስተሳስሮ የተቀኘው ደበበ ሰይፉ «የተስፋዬ ዛፉ» ባለው ግጥሙንዲህ ያመሰጥረዋል፡፡

«የተስፋዬ ዛፉ

ሲከረከም ቅርንጫፉ

ሥሩ ሲነቃቀል

ሲበጠስ ሲፈነገል፣

ጭላንጭል ስትዳፈን

ብርሃን ዓይኑ ሲከደን፣

አንጥፌ ደርቤ ማቄን

ዘንግቻት ዕንቁጣጣሽን

ፀደይ አበባ ዓደዬን፣

በድቅድቁ ተቀመጥሁኝ

ላለማሰብ እያሰብሁኝ፣

የልቤን ልበ ባሻነት ገሰፅኩኝ

ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አረኩኝ፡፡»

ለ95 ቀናት በሚዘልቀው ወርኃ ክረምት መካከል የሚገኘው «የዛፍ ሳምንት» የሚከበርበት ሐምሌ ገናና ወር በመሆኑ በአርሶ አደሩ የክረምት ንጉሥ ይባላል፡፡ ዛፍ ከችግኝነት አልፎንዲያብብም በማድረግም ትወሳለች፡፡

በአማን ነጸረ ‹‹የክረምት ጓዝና ቅኔያት›› በሚለው መጣጥፉ ዕፀዋትና ዝናም ያላቸውን ተዘምዶ የሚያጠቃቅስ የአንድ መምህር ቅኔን ምስጢር በአንድ ዓረፍተ ነገር ያጠቃለለው ‹‹ወዳጄ! የሰማይ ጉድለት፣ ምድርን በዕፅዋት ስትከድናት ይሞላል›› በሚል ነው አከለበትም፡፡ ‹‹ዕፀዋት ካሉ፣ ዝናማት አሉ! የዝናም መውረድ መቆም በዕፅዋት ነው!››

ሰኔ ላይ ግም ብሎ (‹ም› ይጠብቃል)፣ የሐምሌን ጨለማ፣ የነሐሴን ሙላት ተሻግሮ በመስከረም መሰስ ብሎ የሚወጣውን ክረምትን ባለቅኔዎች የዝናብ የዘመን (የወቅት) ለውጥ ጌታ ይሉታል፡፡ ገጣሚው ይህንኑ ንጥረ ሐሳብ እንዲህ አሳይቶታል፡፡

‹‹ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ

ገበሬው ተነሳ ማረሻውን ስሎ፡፡

ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ

ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡

ነሐሴ ተተካ ኃይለኛው ክረምት

ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት››

በተለያዩ የዓለም ክፍል ኅብረተሰቦች ዘንድ ለዛፎች ልዩ ክብርንደሚሰጡ በየአገሮቻቸው ስለዛፍ ከተነገሩ ቁም ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ የሥነ ሕይወት ባለሙያው ኘሮፌሰር ለገሠ ነጋሽ ካጠናቀሩት የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ «የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ፣ ሕይወትን ማደሱ ነው፤» «ዕውነትን መሻት ጥሩ ነው፡፡ የበለጠ ጥሩው ግን ስለዛፍ እውነቱን መናገር ነው» (የዓረቦች አባባል) «ሠርግ ደግስ፣ ደስታ! ያንድ ቀን ነው፡፡ ተሾም ተሸለም፣ ደስታ! ያንድ ወር ነው፡፡ ዛፍ ትከል፣ ደስታ! የዕድሜ ልክ ነው፡፡

ኤመርሰን «በዛፎች ስታጀብ በጥበብና እምነት እታጀባለሁ» እንዳለው ሁሉ እኛም በጥበብናእምነት ለመታጀብ ዛፍን በተለይም አገር በቀሉን እንትከል ይላሉ የሥነ ሕይወት ባለሙያው፡፡

ክረምትና ክፍሎቹ

እስከ መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም. የሚሆነው የክረምት ቆይታ በ95 ቀኖች ውስጥ ዘጠኝ ንዑሳን ክፍሎችን ያስተናግዳል፡፡ እነዚህም ቀጥለው ተመልክተዋል፡፡

(1) ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 18 ዘር፣ ደመና፣ (2) ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 9 መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ ወንዞች፣ ጠል፣ (3) ከነሐሴ 10 እስከ 27 የቁራ ጫጩት፣ ደሴቶች፣ የሁሉም ዓይን፣ (4) ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 5 – (6) ወጋገን፣ ንጋት፣ ጠዋት፣ ብርሃን፣ ቀን፣ ልደት፣ (5) ከመስከረም 1 እስከ 7 ዘመነ ዮሐንስ (6) መስከረም 8 ዘካርያስ፣ (7) ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ፣ (8) መስከረም 16 ሕንፀት፣ (9) ከመስከረም 17 እስከ 25 ዘመነ መስቀል ናቸው፡፡

አገርኛው ብሂል ፀደዩን ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳስፈጸመን ክረምቱንም መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰላም አስፈጽሞ ለመፀው (መስከረም 26) ያብቃን፣ ደኅና ያክርመን ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...