Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አካል ጉዳተኞችን በመተው ስለልማት እኩልነትና ፍትሐዊነት ማውራት ከባድ ነው››

አቶ ወርቅነህ አበበ፣ የጄንደር ኤንድ አዶለሰንስ ግሎባል ኢቪደንስ የኢትዮጵያ የሪሰርች አፕቴክ ኤንድ ኢምፓክት አስተባባሪ

ጄንደር ኤንድ አዶለሰንስ ግሎባል ኢቪደንስ (ጂኤዲኢ) ሪሰርች ፕሮግራም መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ስድስት አገሮች ያሉትን ወጣት ወንዶችና በተለይም ልጃገረዶችን በጥናት ለመደገፍ ሲባል የተቋቋመ ነው፡፡ ይህ የጥናትና ምርምር ፕሮግራም የተቋቋመው በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም እዚሁ ከተማ የሚገኘው ኦቮርሲስ ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት (አዲኢ) ነው፡፡ ፕግራሙም በይፋ ሥራ የጀመረው በ2007 ዓ.ም. ሲሆን፣ መጀመሩን ያበሰሩትም የዩናይትድ ኪንግደም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሚሆኑባቸው አገሮች መካከል ከደቡብ እስያ ባንግላዲሽና ኔፖል፣ ከመካለኛው ምሥራቅ ሌባንና ጆርዳን ከአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ፣ ይገኙበታል፡፡ በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ የሪሰርች አፕቴክ ኤንድ ኢምፓክት አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ አበበ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴና ያስገኘውን ውጤት አስመልክቶ አስተባባሪውን አቶ ወርቅነህ አበበን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጀንደር ኤንድ አዶለሰንስ ግሎባል ኢቪደንስ አወቃቀሩ ምን ይመስላል?

አቶ ወርቅነህ፡- ጂኤጂኢ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የዳሰሳ ጥናት ሲሆን፣ የቀሩት ሁለቱ ደግሞ የፖሊሲና ጥልቅ ጥናቶች ናቸው፡፡ የመጀመርያውን ጥናት የሚመራው የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕሮፌሰር) ደግሞ ዋና ተመራማሪ ናቸው፡፡ የፖሊሲው ጥናት የሚንቀሳቀሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና የሕግ ምርምር ማዕከል ሆኖ ጥልቅ ጥናቱ የሚሠራው በነፃ ተመራመሪዎች ነው፡፡ በአጠቃላይ ምርምሩን በዋናነት የማስተባብረው እኔ ነኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- ጥናቱ መቼ እንደተመጀመረና በየትኛው የአገሪቱ ክፍሎች እንደተካሄደ ዘርዘር ባለ መልኩ ቢያስረዱን?

አቶ ወርቅነህ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያው የመነሻ ጥናት በዚህ ዓመት ጥር ላይ ተጠናቅቋል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በአማራ ክልል ጎንደር ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በአፋር ክልል በሚገኙ አምስት የተለያዩ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በድሬዳዋ፣ በደብረ ታቦርና በአዳሚቱሉ ከተሞች ነው፡፡ ጥናቱ ወደ 6,800 የሚጠጉና ዕድሜያቸው ከአሥር እስከ 12 ዓመት የሆኑ ታዳጊ ሴቶችንና ወንዶችን ያካተተ ነው፡፡ ጥናቱ ካካተታቸው ታዳጊዎች መካከል የአካል ጉዳት በተለይም ዓይነ ሥውራን፣ የመስማትና የመንቀሳቀስ ጉዳት የደረሰባቸው፣ በውስን መልኩ ደግሞ የአዕምሮ ችግር ያለባቸው ሕፃናት ይገኙባቸዋል፡፡ ጥናቱ የተጠናቀቀ ስለሆነ ውጤቱ ከአንድ ሳምንት በፊት በለንደን በተካሄደው ኢንተርናሽናል ግሎባል ዲሰብሊቲ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ቀርቧል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ተገኝተው ኢትዮጵያ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ፖሊሲ ቀርፃ ሰፊ ሥራ እየሠራች መሆኑን፣ በተለይ የልዩ ፍላጎትና የአካትቶ ትምህርቶች በአገሪቱ እየሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ የእኛም ጥናት የሚሳየው መንግሥት በተለይ በከተማ አካባቢ የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ለማስፋፋት እየሠራ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በገጠር ብዙ ይቀረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ግሎባል ዲሰቢሊቲ ስብሰባ ላይ የቀረበው የጥናት ውጤት ምን ዓይነት ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ነበር?

አቶ ወርቅነህ፡- በስብሰባው ላይ የቀረበው የጥናት ውጤት በዓለም ላይ ያሉ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ የገንዝብ ችግር እንዳለባቸው፣ ችግሮቻቸውንም ለመወጣት የገቢ ማስገኚያ ፕሮግራም መካሄድ ግድ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ በርካታ የዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ በተደረገበት በዚህ ስብሰባ የአቅም ችግር መኖሩን ለማስረዳት የተሞከረ ሲሆን፣ ገቢ በማሰባሰብ ሥራ ላይ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያ ከዚህ ፈንድ ተጠቃሚ የምትሆንበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ የእኛም የጥናት ፕሮግራም የማመቻቸቱ ሥራ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በከተማና በገጠር ያለው የልዩ ፍላጎት ትምህርትና አካል ጉዳተኞችን ከልማት የማግለሉ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ጥናቱ ያመላከተው ነገር አለ?

አቶ ወርቅነህ፡- ጥናታችን በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በገጠር አካባቢ የሚገኙ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት ለአካል ጉዳተኞች አመቺ የሆነ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ነው፡፡ በተለይ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው ትምህርት ቤት ለመግባት አይችሉም፡፡ የልዩ ፍላጎት ትምህርትም በከተሞች አካባቢ አልፎ አልፎ ነው እንጂ እንደ መደበኛ ትምህርት በሁሉም አካባቢዎች አይገኝም፡፡ ከዚህም ባሻገር የኅብረተሰቡ አመለካከት በተለይ አካል ጉዳት ያለባቸውን ወገኖች በሚመለከት ያለው ግንዛቤ አሁንም አላደገም፡፡ ስለዚህ አካል ጉዳት ያለባቸው ልጆች ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውም ጭምር የመገለል ሁኔታ እየገጠማቸው መሆኑን ጥናቱ በሰፊው ያሳያል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ተሸማቅቀው እንዲኖሩ መደረጉም ተደርሶበታል፡፡ በአካል ጉዳት በማንኛውም ወቅትና ሰው ላይ ሊደርስ እንደሚቻል ኅብረተሰቡ ገና አልተገነዘበም፡፡ ከዚህም ሌላ የተፈጥሮ አካል ጉዳተኞችን ከእርግማን ጋር ያገናኙታል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ኃጢያት ሠርተው ሊሆን ይችላል የሚል እምነቱም በኅብረተሰቡ ዘንድ አሁንም ድረስ እንደሰርፀ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በተለይ በአማራ ክልልና በሌሎችም የክልል ገጠር አካባቢዎች ሰፊ የመገለል ሁኔታ ይታያል፡፡ በከተሞች አካባቢ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቢኖርም የተቋም፣ የጥራትና የመሣሪዎች ችግር እንዳለባቸው ጥናቱ ደርሶበታል፡፡ የተመደቡትም መምህራን አጫጭር ሥልጠና የወሰዱ እንጂ፣ በትክክል በሙያው ሠልጥነው ሰፊ ድጋፍ ለመስጠት የሚችሉ አይደሉም፡፡ ገጠር አካባቢ ደግሞ አልፎ አልፎ በተጨናነቁ አካባቢዎች የልዩ ፍላጎት ትምህርት እንዳለ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ተደራሽነቱ በጣም ገና ነው፡፡ ዕድሉን አግኝተው የሚማሩም የተወሰኑ አካል ጉዳተኞች ብቻ ናቸው፡፡ ልዩ ፍላጎት ትምህርት ደግሞ ሦስተኛ ክፍል ላይ እንዲሚያበቃ ጥናታችን ያሳያል፡፡ ሦስተኛ ክፍልን የጨረሱ ተማሪዎች በአካትቶ ትምህርት ወዳለበት አራተኛ ክፍል ይቀላቀላሉ፡፡ በአካትቶ ትምህርቱ ደግሞ እንደማንኛውም ተማሪ የሚማሩበት እንጂ ለአካል ጉዳተኞች ተብሎ የሚደረግ ድጋፍ የለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ካለመኖሩ የተነሳም ብዙዎቹ አካል ጉዳተኞች የጀመሩትን ትምህርት ማቋረጥ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ቢቀጥሉበትም በውጤቶቻቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደሩ አያጠያይቅም፡፡ በጥናቱ ምክረ ሐሳቡ መሠረት የአካትቶ ትምህርት ጥራቱን የጠበቀና ድጋፍ የታከለበት መሆን አለበት ብሎ ነው የጠቆመው፡፡

ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኛ የሆኑ ወጣቶች ጤንነትን በተመለከተ ጥናቱ ምን ይላል?

አቶ ወርቅነህ፡- በጥናታችን ከተካተቱት ወጣቶች መካከል ብዙዎቹ አካል ጉዳታቸው ቢታከሙ ሊድን ወይም ሊሻሻል የሚችል መሆኑን ዓይተናል፡፡ ነገር ግን ወላጆቻቸው ደሃ በመሆናቸውና የኢኮኖሚ ችግር ስላለባቸው ወይም ደግሞ በአቅራቢያቸው የሚፈለገውን ሕክምና ሊሰጥ የሚችል የጤና ተቋም ባለመኖሩ ብቻ ለጉዳቱ ተጠቂ በመሆን እየኖሩ ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸውና በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ጭምር ስለጤና አጠባበቃቸውና አገልግሎት በቂ የሆነ መረጃ የላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ በጤና አጠባበቃቸውና በተለይ በወጣት ልጃገረዶች ዘንድ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ሰፊ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የፅዳት መጠበቂያ (ሞዴስ) የላቸውም፡፡ እንዴት እንደሚጠቀሙ የሚገልጽ መረጃም የለም፡፡ በዚህ የተነሳ ሊደርስባቸው የሚችል መገለል በጣም ከፍተኛ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- የአካል ጉዳት ያለባቸው ወጣቶች የሥነ ልቦና ችግሮቻቸውን ለማቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ወርቅነህ፡- በዘላቂ የልማት ግቦች ከተቀመጡት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ‹‹አንድም ሰው ወደኋላ መቅረት የለበትም፤›› የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት የተጠቀሱት ግቦች ሲጠናቀቁ አንድም ሰው ወደ ኋላ መቅረት እንደሌለበት የሚጠቁም ነው፡፡ ወደ ኋላ ይቀራሉ ተብለው ሥጋት ከተጣለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አንዱ አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ወገኖች ከችግር ለማውጣት ሰፊ ሥራ ይጠይቃል፡፡ በተለይ ጥናታችን እንደሚያሳየው ከሆነ አካል ጉዳት ያለባቸው ወጣቶች የአካል፣ የፆታና የሥነ ልቦና ጥቃት በሰፊ ይደርስባቸዋል፡፡ ጥቃት ሲደርስባቸው ለማንና እንዴት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም አያውቁም፡፡ በተለይ የመስማት ችግር ያለባቸው ወጣቶች ፖሊስ ጣቢያ ሄደው እንኳን ማስረዳት አይችሉም፡፡ ፖሊሶችም ብዙ ጊዜ እነሱን ለመርዳት ፍላጎት እንዳማያሳዩ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ስለዚህ ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ የአካል ጉዳተኛ ወጣቶችን ከጥቃት ለማዳን ወይም ለመጠበቅ የሚያስችል ዕርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡ ወጣቶች ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በተለየ መልኩ የምክር አገልግሎት ማግኘት አለባቸው፡፡ ስለአኗኗራቸው፣ ስለትምህርታቸውና ስለማንኛውም ነገር ምክር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን በገጠርም በከተማም በሄዱባቸው አካባቢዎች ይህንን አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ተቋም የለም፡፡ ስለዚህም ወላጆች፣ መምህራን፣ የጤና ኤክስቴንሽንና የማኅበራዊ ሠራተኞች የምክር አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመቅረፍ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ እነዚህን ወገኖች በመተው ስለልማት፣ ስለእኩልነትና ስለፍትሐዊነት ማውራት ከባድ ይሆናል፡፡      

ሪፖርተር፡- በወጣቶች ላይ የሚታዩ ሌሎች ችግሮች ምንድናቸው? እንደተቋምስ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ወርቅነህ፡- በሁሉም ወጣቶች ዙሪያ ትኩረት አድርገን እያጠናን ያለነው ‹‹ቮይስ ኤንድ ኤጀንሲ›› የሚል ነው፡፡ የዚህም ትርጉም ሲታይ ስለመብት መናገርና መግለጽን፣ ወይም በቤተሰቡና በኅብረተሰቡ ውስጥ በውሳኔ ሰጪነት መሳተፍ መቻልን፣ ወጣቶቹን በሚመለከት ውሳኔዎች ላይ የራስ የሆነ ልምድ እንዲኖራቸው ማድረግን ይመለከታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዙሪያ ወጣቶችን በተለይ ደግሞ ልጃገረዶችን  የማሳተፍ ሁኔታ ሲታይ ሰፊ ክፍተት አለበት፡፡ ወደ አካል ጉዳተኞች ሲመጣ ደግሞ ችግሩ ወይም ክፍተቱ ይብሳል፡፡ አካል ጉዳት ያለባቸው ወጣቶች በተለይ ወጣት ሴቶችን በቤተሰባቸው ጉዳይ ውሳኔ መስጠት ወይም ውሳኔ ላይ የመሳተፍ አቅም እንዳላቸው አይረዱም፡፡ እንዲያውም ከቤት አካባቢ እንዳይርቁ ወይም እንዳይወጡ ማዕቀብ ይጣልባቸዋል፡፡ ስለዚህ ተንቀሳቅሰው በማኅበራዊ ጉዳይ ላይ በተለይ ሠርግና በማኅበረሰቡ ዘንድ በሚከናወኑ ጉዳዮች እንዲሳተፉ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች ተሸማቅቀው፣ ቤት ውስጥ ተገልለውና ኅብረተሰቡም ሳያውቃቸው እንዲኖሩ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የእነዚህን ወገኖች ድምፆች ሊሰማና ሊያዳምጣቸው ይገባል፡፡ በውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ መሳተፍ አለባቸው የሚለውን ነገር ግንዛቤ ለማስጨበጥም በመንግሥት፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ባላቸው ወገኖች በኩል ሥራዎች እንዲሠሩ እናመለክታለን፡፡

ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኛ ወጣቶችን በኢኮኖሚ የማብቃት ጉዳይን እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ወርቅነህ፡- በኢኮኖሚ የማብቃት ጉዳይ የሚመለከታቸው ዕድሜያቸው እስከ 19 ዓመት የሆኑትን ወጣት አካል ጉዳተኞችን ነው፡፡ ዕድሜያቸው 17 እና 18 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከሌሎች እኩል የማይታዩበት ሁኔታ በተለይ በገጠር አካባቢ በሰፊው ይንፀባረቃል፡፡ በብድር አገልግሎትና በጥቃቅንና አነስተኛ ውስጥ ተሳትፎ ላይ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል አመለካከት ስለሌለ እነሱን የማካተት ችግር በሰፊው ይታያል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በተለይም የክህሎት ሥልጠናዎችንም በሚመለከትም ክፍተት አለ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ችግሮች ይንፀባረቃሉ፡፡ አንደኛው የአመለካከት ችግር ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ ወጣቶች ራሳቸው ከመጀመርያው የትምህርት ተደራሽነት ያልነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እያደጉ ሲሄዱ ወይም ወደ ጎልማሳነት በሚሸጋገሩበት ጊዜ በኢኮኖሚ ደሃ ሆነው የሚቀሩበት ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ በጥናታችን ላይ በግልጽ ለማየት ችለናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ ወርቅነህ፡- አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ልጆቻቸው ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቤተሰቦቻቸው አያውቁም፡፡ ማኅበረሰቡም በወላጆቻቸው ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ወላጆች አካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ማግለል ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው የሚያስወግድዱበት ሁኔታ በሰፊው ተንፀባርቋል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ በይበልጥ የተንፀባረቀው በደቡባዊ ጎንደር አካባቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከደብረታቦር ከተማ ራቅ ባለ የገጠር አካባቢ የሚኖሩ ባልና ሚስት የመስማት ችግር ያለባቸው አራት ልጆች አሏቸው፡፡ ከልጆቹም መካከል ሦስቱ ወንዶች ሲሆኑ፣ አንዷ ሴት ነች፡፡ የልጆቹም ቤተሰቦች ከኅብረተሰቡ በሚደርስባቸው የመገለል ተፅዕኖ የተነሳ አራቱንም ልጆቻቸውን ከተማ አምጥተው ጣሏቸው፡፡ ልጆቹም እየለመኑ በጎዳና ላይ መኖሩን ተያያዙት፡፡ ከጊዜ በኋላም ሚዛን እየመዘኑ፣ ሊስትሮ እየሠሩና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ ዕድሜያቸው ትልልቅ ቢሆንም ገና ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል እየተማሩ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ አሁንም ጭምር መገለሉ እንዳለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሜሪካ ከዳያስፖራ ሊሰበሰብ የታቀደው የባለአደራ (ትረስት ፈንድ) እንቅስቃሴ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ያለው ፋይዳ እስከምን ድረስ ነው ይላሉ?

አቶ ወርቅነህ፡- የትረስ ፈንዱ ስምምነት ክፍተቶቹን ለመሙላት ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለአካል ጉዳተኛው ትልቅም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የእኛም ጥናት ለዚህ ሥራ ትልቅ ግብዓት ሆኗል ብለን እናስባለን፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...