Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርያልተዳሰሱትን ዳሰሳ

ያልተዳሰሱትን ዳሰሳ

ቀን:

በሁሉሰው ታጀበ

የብዙዎቻችን ሰሞነኛ ጉዳይ ‹‹አመራር!››. . .  ‹‹አመራር!››. . . ‹‹አመራር!››. . . የሚል ነው፡፡ ይህ ያለምክንያት የተፈጠረ ሳይሆን አየሩን ክፉኛ ካሞቀው ብሔራዊ ትኩሳትና አገር አቀፍ ጥያቄ ጋር ተቆራኝቶ ለችግሮች ሁሉ ምላሽ ነው እየተባለ የተሰነዘረ የመፍትሔ ቋት በመሆኑ ነው፡፡

ከአንድ ባልደረባዬ ጋር ስለአስቸጋሪው ሙስና ከዚህች ምድር መወገድ ስንወያይ፣ ለመሆኑ ሙስና እዚህ አገር አለ ወይ? ተባብለን የብዙ አገሮችን ተሞክሮ እያወጣንና እያወረድን ከሌሎቹ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ትንሽም ቢሆን/ብትሆን አለ/አለች ተባባልንና እሱኑ/እሷኑ ማን ያጥፋው ያጥፋት? እያልን ስንከራከር መረታታት ተሳነን፡፡ ውድድሩ ሊያጠፋው በሚችለው ወገን ማንነት ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡ ሙስና ውስጣዊ አንድምታው መሰጣጣት ነውና ሊያጠፋ የሚችለው ሰጪው ነው? ወይስ ተቀባዩ? እያልን ተከራክረናል፡፡ ጉዳዩን ለማደናቀፍ የሠለጠነና በተጠያቂነት የተቧደነ አደናቃፊ ባይኖር ኖሮ የሰጪዎች ሠራዊት አይፈጠርም ነበር፡፡ ሰጪ ከሌለም ተቀባዩ ሙሰኛ ከእነ መጥፎ ተግባሩ ይጠፋልና ነው፡፡ ከዚሁ ሐሳብ ሳንርቅ ሌላ ትዝታ ውስጥ ገባንና ሁለታችንም ሆዳችንን እስኪያመን ሳቅን፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ በቀድሞው መንግሥት የደርግ አመራር ልክ እንደ ዛሬው ሙስና እያቆጠቆጠ ነው በሚል እምነት ችግሩን ከሥር መሠረቱ ነቅዬ አጠፋዋለሁ ተብሎ ተፎከረና ለዚሁ የሚረዳ ተቋዋም ተመሠረተ፡፡ ‹‹የሠርቶ አደሩ የቁጥጥር ኮሚቴ›› የሚባል አካል በየደረጃው ተዋቀረና ሰፊው ሕዝብ የራሱን ንብረት (የመንግሥትን መሆኑ ነው!!) ራሱ መቆጣጠር ይችላል በሚል እሳቤ በመንግሥት ሹመት የሥራ ኃላፊዎች ተመደቡ፡፡ ከዓመታት በኋላ ጥረቱ ሁሉ ጉንጭ አልፋ ሆነና ምክንያቱ ምን ይሆን ተብሎ ሲጠና፣ በምርጫም ሆነ በሹመት የተደረደሩት አብዛኞቹ የሠርቶ አደሩ ቁጥጥር ኮሚቴ አባላት ራሳቸው በከፍተኛ ሙስና የተዘፈቁ ዋልጌዎች ሆነው ተገኙና ተቋሙ የተሽመደመደ ሆኖ የብዙዎች መሳለቂያ ሆኖ አረፈው፡፡

ሌላ ዳሰሳ ለማድረግ በብሔረ ፖለቲካዊ ሥርዓት አጥፊውን ለመለየት አመራር ወሳኝ ነውና ከዘመኑ የዳበረ ሥርዓት ሕይወት መሪው ማነው? ብሎ ውይይት ተከተለ፡፡ የታችኛው የላይኛውን ይመራል? ወይስ የላይኛው ብቻ የመሪነት ባለቤት ነው? የግራው ቀኙን? ወይስ የቀኙ ግራውን? የትኛው ነው የአመራር ጉድለት የፈጸመው? ዕውን ለመልካም አስተዳደር ወይም ለታየው የአመራር ጉድለት ተጠያቂው ማነው? ጉዳዩ ያነጋግራል፣ ያጠያይቃልና እንተነፋፈስበት ተባባልን!! ሌላ ዳሰሳ ነበር!! መፍትሔውን ያነገቡ እነ ዶ/ር ዓብይ አህመድ ብቅ አሉና ገላገሉን፡፡

በዘመናዊ አስተዳደር ቋንቋ አመራር ከላይ ወደታች የሚደረግ ፍሰትና ከታች ወደ ላይ የሚዘልቀው ግብዓት ውሁድ ሥርዓት ነው፡፡ አቅጣጫ አመላካች መመሪያዎች ከላይ ወደ ታች ሲፈሱ ውጤት ተኮር የሥራ ሒደቶች ከታች ወደ ላይ ቢዘልቁ የተሻለ ዕድገት እንደሚገኝ አዋቂዎች ያመላክታሉ፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ግራና ቀኝ ተደጋግፎ፣ ተመካክሮና ተረዳድቶ የሚራመዱት ጉዞ ብቻ ነው ከግብ የሚያደርሰው፡፡ አመራር መምራት ሲሳነው ተመሪ መመራት ሳይሆንለት አራምባና ቆቦ ይኮንና ሜዳው ላይ ተበትኖ፣ የታሪክ መዘባበቻ ነውጥ ውስጥ መዘፈቅና የዕድገት ጎታች መሆን ይከተላል፡፡ ለለውጥ አስፈላጊ የሆነውን የሕዝቦችን ጤናማና ምርታማ ግንኙነት ቸል የሚል አመራርም ሆነ ለተቀናጀ ጥረት ስኬታማነት ሊኖር ከሚገባ ማዕከል የሚያፈነግጥ ተመሪ የኋላ ኋላ ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ እናም በጋርዮሽ የተጠያቂነት ዘውግ ማን ማንን ይምራ? ቢባል ማን በማን ይጠየቅ ነውና አባባሉ አወያይ ነው፡፡

ከታች እስከ ላይ ያለውን አካባቢያችንን ስንቃኝና የምንኖርበት ሥርዓት ለለውጥና ለማኅበራዊ ፍትሕ የቆመ አመራር ይኑረው አይኑረው ለመለየት ከሚታወቁት ሦስት የመሪዎች የለውጥ አመራር ውስጠ ጉዳዮች ጋር አገናዝበን ማየት ይጠቅመናል፡፡ ለለውጥ የቆሙ ፍትሐዊ መሪዎች ሕዝብ ምን ከማድረግ መቆጠብ እንዳለበት ለይተው የሚያውቁ፣ ሕዝብ ምን ለመሥራት መነሳት እንዳለበት ለይተው የሚያሳውቁ፣ እንዲሁም ሕዝብ ሳያቋርጥ መሥራት ያለበትን ለይተው የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው፡፡ መመዘኛ ነጥቦቻችን እነዚሁ ይበቁናል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የተገላቢጦሽ ብንመዛዘን መሪዎች ምን ማድረግ መጀመር እንዳለባቸው፣ ምን ከመሥራት መቆጠብ እንዳለባቸውና የትኛውን ተግባር መቀጠል እንደሚኖርባቸው መረዳት የሚሳነው ሕዝብ ለአመራር አስቸጋሪና ለጥፋት የተጋለጠ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከእነዚህ ከላይ ወደ ታች ከሚፈሱና ከታች ወደ ላይ ከሚዘልቁ የዘመናዊ ሥርዓት አመራር ሒደት ውህድነት ያፈነገጠ ሁኔታ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመተንበይም ሆነ ለመቆጣጠር አዳጋች ይሆናል፡፡

ዛሬ አልፎ አልፎ ኅብረተሰባችን እየከፈለ ላለው መስዋትዕነት የዳረገውን ችግር በእነዚህ መሥፈርቶች ብንመዝናቸው፣ የመፍትሔ ቋቱን የሚሞላ ሥልትና ፍትሐዊነቱ የማያጠራጥር ማኅበረ ፖለቲካዊ ቁርኝት መገንባት አይሳነንም፡፡ እነዚህ ሲሟሉ የገዘፈ ግልጽነትና መተማመን፣ የበለፀገ ሁሉን አቀፍ ዕውቀት መዳበር፣ ፈጣን የመወሰን አቅም፣ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች የማያቋርጥ መሻሻል፣ ትክክለኛ ነገሮችን ለመሥራት በራስ የመተማመን ብቃት ዕድገት፣ የሕዝቦችን ችሎታ የመጠቀም አቅም መፋጠን፣ የተሻሻለና የዘመነ የሕዝብ ውክልና መሥፈንና የማያቋርጥ የሕዝቦች እርካታ መረጋገጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ ነባራዊ ህልውናቸው ጎልቶ ይታያል፡፡

ስለአመራር ሲወሳና የአመራር ሚና ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ የሚገባን የወቅቱ የአገራችንን ሁኔታ በአትኩሮት ስንመለከት ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከችግሮቻችን ብዛትና ስፋት ብቻ ተነስተን እጅግ አስደናቂና ተዓምራዊ በሚባል ቅጽበት የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ልብ ማርከው፣ በአንዲት አገር ጥላ ሥር ለማሰባሰብ 90 ቀናት ያልፈጀባቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ90 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን የኅብረተሰብ ችግሮች በአንድ ጊዜ ፈነቃቅለው በመጣል በድልና በሙሉ ስኬት ሊያስደምሙን ይገባል ብለን የምንጠብቅ የዋሆች ቁጥራችን ጥቂት ላይሆን ይችላል፡፡ ይልቁንም አምላክ ፈቃዱ ሆኖ ከመቶ ሚሊዮን በላይ በምንሆን ሕዝቦች መሀል የተናጠል ምኞቶቻችንን ሁሉ እየደረደርን፣ ይህ ቢሆን ያ ባይሆን የምንለውን በየፊናችን ከተከተልንና የሆነውን ሳንቆጥር ያልሆነውን እያሰላን ወዲያና ወዲህ የምንል ከሆነም በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት ከሚፈልገው ባለሁለት እግር ጎልማሳ ወይም ከቀንድ ነካሹ የጅብ ችኩል የምንሻል አንሆንም፡፡ ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት የሚፈልግ አንድም ተላላ ነው፣ ብዙም ሳይርቅ ወድቆ ይከሰከሳል፣ አሊያም የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል የሚባለው ዓይነት ይሆንና የማይታኘከውን ለማመንዠግ ጥርሱን ይሰባብራል፡፡ የአገራችን ብሂል አስተምህሮቱ ብዙ ብዙ ነውና ነገሮችን ለማስተዋል የተዘጋጀ አዕምሮ ካለ መንገዶቻችን ቀና ሆነው እንደ ልብ የሚያራምዱና ወደ ፈለግንበት የሚያደርሱን ከመሆን የሚገታቸው የለም፡፡ በአሸናፊ የፍቅር ጉዞ ከእዚያ መልስ ከእዚህ መልስ ሳይባል በይቅር ባይነት ስሜት እየተደማመርን ወደፊት መራመድ ያሻናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፍቅር ያሸንፋል መርሆ የይቅር ባይነትን ማኅበረሰባዊ ራዕይ ሲያንፀባርቁና በፈጣን ሒደት የለመለመ የኢትዮጵያዊነት መታደሻ ዘር በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲዘሩ፣ ሁሉንም በአንድ ጀንበር የመዳሰስ መለኮታዊ ብቃት እንዳላቸው ግዙፍ ኃይል ሁሉንም ዛሬውኑ እንዲያከናውኑ ሳንመኝ ጊዜውንና ወቅቱን የጠበቀ ሊታለፍ የማይገባውን አቅጣጫ መጠቋቀሙም አይከፋም፡፡ ያልተዳሰሱ ዳሰሳዎችን በማድረግ ወቅትና ጊዜ ጠብቀው የሚያገረሹ፣ ችግሮችን ከሥራቸው መንግሎ ለመጣል የብልህና አስተዋይ ዳሰሳዎችን በማድረግ ሁሉም የበኩሉን ቢያበረክት ይበጀናል፡፡ ይህ አስተዋጽኦ አላስፈላጊ የሆኑ ቅራኔዎች እንዳይፈጠሩና በዘዴ የተዋቡ ድርጊቶች ከሚፈለገው ግብ በእርጋታ እንዲያደርሱ ሰው ያለውን ቢሰነዝር ጠቀሜታው የትየለሌ ነው፡፡ በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝባዊ ድጋፍን ለመግለጽ በተደረጉት ማዕበላዊ ሠልፎች የአዲስ አበባዎቹ አዘጋጆች ሊታለፉ የማይገባቸው ማሳሰቢያዎችን ሲሰጡ፣ ያልተዳሰሱ ዳሰሳዎችን እያደረጉ እንደነበር የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ ልብ ብለዋል፡፡

በሠልፉ ላይ የማንንም የፖለቲካ ድርጅት የማሞገስም ሆነ የመዝለፍ መፈክሮች እንዳይሰሙ፣ ከምሥጋናና ከፍቅር ያሸንፋል ያፈነገጡ የጥላቻ ፉከራ ሰሌዳዎች እንዳይያዙ የተሰጠው የጥንቃቄ ማሳሰቢያ የነበረውን ጠቀሜታ ብዙዎቻችን አስተውለናል፡፡ በአንዳንድ ከተሞች ተከታትለው በተካሄዱት መሰል ሠልፎች ተመሳሳዩን ማሳሰቢያ ያላጤኑ ሰዎች እንቅስቃሴ ከእንግዲህስ መሰል ሠልፎች እየተቀዛቀዙ መሄድ ይኖርባቸዋል ወደሚል መደምደሚያ ማስደረሳቸው አይዘለሌ አቋም ይሆናል፡፡ ይህም ያልተዳሰሰው ዳሰሳ አካል ነው፡፡ በብዙ ጎጂ ትውስታዎቹ ብቻ ዘወትር በምናብጠለጥለው የደርግ ሥርዓት ወቅት በአንደኛው የዓለም አቀፍ ወዛደሮች ቀን (ሜይ ዴይ) አከባበር በተጠራ ዓመታዊ የመስቀል አደባባይ ሠልፍ ላይ፣ አንደኛው ድርጅት ፈንገጥ ብሎ ከሌሎች ሁሉ ገዝፎ ለመታየት የእንቧይ ካብ ከመረና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ ከአርቲስቶች ጋር ባደረጉት ውይይት በጨረፍታ ያስታወሱን፣ በማቸነፍና በማሸነፍ ቃላት ዙርያ የተፈጠረውን የመተላለቅ ፖለቲካ አጡዞት ተከትሎ የመጣውን ዕልቂት በሕይወት የነበርን ሁሉ የማንዘነጋው አሰቃቂ ወቅት ላይ እንድንደርስ አስችሎ ነበር፡፡ ያ ከንቱ የእሳት መለኳኮስ ድርጊት ዋናውን በዓል ጥላሸት ቀብቶት አለፈ፡፡

በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ዘንድ ታምቆ ያለ ስሜት ሲፈነዳ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችም ሆኑ የሚዘነጉ ድርጊቶች መዘዛቸው ዞሮ ዞሮ ያልተፈለገ መንታ መንገድ ላይ ሕዝብ ቆም እንዲል የሚያደርጉ፣ የለውጥ አደናቃፊና የፍጥነት ዕንቅፋት ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ቀላል ያልሆነ ነገር ግን ባለፉት ሦስት ወራት ከተወሰዱት ግዙፍ የአዲሱ የአገር አመራር ድርጊቶች ሲነፃፀር አንፃራዊ ቅለት ሊኖረው የሚችል ከአገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ጋር የተያያዘ አንድ ያልተዳሰሰ እውነታ ማንሳት ይቻላል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሆነ የደርግ መንግሥታት በሥልጣን ዘመናቸው ወቅት በአገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሥርዓታቸው መለያ የሆነና የሚመሩበትን ሥርዓት አገዛዝ ባህሪ የሚያንፀባርቅ ምልክት ለጥፈውበት እንደነበር ያየነው ሁሉ ምስክሮች ነን፡፡ ሞአ አንበሳ ለንጉሣዊው ሥርዓት፣ በአበባና በሐረግ የተከበበ አስተራረስ ለደርግ ናፍቆተ ኅብረተሰባዊነት በምልክትነት የዋሉበትን አንዘነጋም፡፡ ያም ሆኖ እነዚያ ምልክቶች ከፕሮቶኮል ዕይታና ከየሥርዓቶቹ ደጋፊዎች ማንገብ የተሻገረ እንደ የአሁኑ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ምኞታዊ ምልክት፣ ሕገ መንግሥታዊ አስገዳጅነት በእያንዳንዱ ዜጋ ጫና ላይ አሳርፈው አልነበረም፡፡

እናም ባልተዳሰሱት ዳሰሳዎች አቀራረብ እነ እገሌ ሕገ መንግሥቱን ተዳፍረዋል የሚል አጓጉል ቅራኔን የሚፈጥር ቀዳዳን ለመድፈንና ሁሉን አቀፍ አገራዊ ተቀባይነትን ለመጨበጥ፣ የዚያን ምልክት ሕገ መንግሥታዊ አስገዳጅነት ሥልጣን ባለው አካል ከባንዲራው ላይ እንዲነሳ ቢያንስ የምሥሉ ደጋፊዎች በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ለፕሮቶኮላቸው ዕይታ ብቻ ቤተ መንግሥት ወይም የመሪዎች መኪናዎች ላይ ከማውለብለብ ያለፈ በዜጋዎች ላይ የተጣለው፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዳጅ ቶሎ እንዲነሳ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ አለመኖሩን ሕዝባዊው የፖለቲካ ከባቢ አየር በግልጽ የሚያመለክተው ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ሕዝብ የወደደውን በመተግበር ላይ መሆኑን እናጢን፡፡

የፍቅር ያሸንፋል መርሆ አራማጅ የሆኑትና የይቅርታ አድራጊነት አመራር ባለቤት ጠቅላይ ሚኒስትር  ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ባደረጓዋቸው ንግግሮች እንዳመለከቱት፣ የይቅርታ አድራጊነት ዕርምጃቸው የእስከ ዛሬውን ጥፋት ሁሉ ያጠቃለለ ለመሆኑ ብዙ ምርምር አያሻውም፡፡ የብርታታቸው ብርታት የቀድሞው መንግሥት ኮሎኔልም ቢሆኑ ወደ አገራቸው መመለስ ይችላሉ እስከ ማለት አድርሷቸዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ የቀድሞው መሪ የቀኝ እጅ የነበሩ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር  አገር ቤት እየገቡና እየወጡ መሆናቸውን በይፋ ተዘግቧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ያልተዳሰሰና መዳሰስ የሚገባው ታሪካዊ ክስተት እንደ ፖለቲካ አጀንዳነቱ መቋጫ ያልተበጀለት ነውና መወሳቱ ይበጃል፡፡

የቀድሞው መንግሥት በተለወጠ ማግሥት ለተለያዩ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ስያሜ ሲሰጥ፣ ከእዚያ በፊት በነበረው የአገር ትርምስና ብዙ ቡድኖችንና ወገኖችን በየዘርፉ አሠልፎ የእርስ በርስ መተላለቅ ባስከተለው የቀይና የነጭ ሽብር በታሪካችን አሳፋሪ የሆነ የትውልድ ዕልቂት ይወሳል፡፡ ለአንደኛው ወገን ብቻ ተለይቶ የተሰጠው የፖለቲካ ስያሜ ዛሬ በብዙ አገሮች ተበትነውና እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአንድ ወቅት አኃዛዊ መረጃ ከ33 ሺሕ በላይ ለሚገመቱ ዜጎች የሥጋት ምንጭ የሆነ፣ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ ታፔላ ሊነሳላቸው የሚገባ መሆኑ ያልተዳሰሰ ዳሰሳ ነው፡፡ ያ በጦር መሣሪያ የታጀበውንና የእርስ በርስ ዕልቂት ያስከተለውን ፖለቲካዊ ክስተት በብዙ መጣጥፎች፣ እየተጠቀሱ ካሉ ምሳሌዎች ደግመን አንስተን ብንቃኝ እንኳን በሕግ ምሁሩና የቀበሌ ተመራጭ በነበረው አቶ ዮሐንስ ህሩይና ኮትኩቶ ባሳደገው ወንድሙ የኢሕአወሊ ወጣት ቲቶ ህሩይ መካከል፣ በመኢሶኗ ዶ/ር ንግሥት አዳነና በወንድማቸው የኢሕአፓው አቶ ዮሴፍ አዳነ መካከል ስለነበረው የእርስ በርስ ጦርነት አንዱን ነጥሎ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ የተደረገበት የፖለቲካ ውሳኔ መሰል ዕርምጃ፣ ብዙ ክርክር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡

ለዓመታት በአገራችን በተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ምክንያት በፍርድ ቤቶች የተካሄዱት ክርክሮችና ውጤታቸው በቂ ሰነዶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ የበላይነት በነበረው ኃይል ከሳሽነት በተካሄደው ክርክር የእነ ቲቶንና ዮሴፍን ትግል ከእነ ዮሐንስና ንግሥት ትግል በተፃራሪነት የፈረጀው የፍትሕ አካል፣ ለኋለኞቹ አቋም የተለጠፈውን ስያሜ እንዴት እንደ ተመለከተው፣ ልክ በተመሳሳይ የፖለቲካ የበላይነት የነበረው ከሳሽ ኃይል በደርግ መንግሥትና ደጋፊዎች ከተፈጁት ባላነሰ ጫካ ውስጥ በነፃ አውጪዎቹ ድርጅቶች ያለቁበትን ድርጊት ተመሳሳይ መጠሪያ መስጠት ባልቻለበትና ዕልቂታቸውንም እንደ በጎ ነገር ከቁብ ያልቆጠረበት የእርስ በርስ ትልልቅ ስያሜ ብዙ ታዝበናል፡፡ ያም አልፎ ዛሬ ቆም ብለን ሁሉንም በይቅርታና በይቅር ባይነት በምንመካከርበት መድረክ የታሪክን ለታሪክ ማስተማሪያነት ትተን በፖለቲካ ፍላጎት ብቻ አንዱን ወገን በተናጠል የታሪክ ተጠያቂ ማድረግን ትተን፣ በአዲስ የፍቅር ያሸንፋል የይቅር ባይነት ጎዳና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ወገን ተደማምረን ለአገር በሚበጀው የአንድነት ጎዳና መጓዙ ይመረጣል፡፡

ላልተዳሰሰው ዳሰሳ በማሳረጊያነት የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ የሕይወት ገጠመኝ  እንይ፡፡ ጸሐፊው ለአሥራ አንድ ዓመታት በአዲስ አበባ እስር ቤት በመማቀቅ፣ የሕይወት ዘመኑን ክሬም ዓመታት አቃጥሏል፡፡ ለአምስት ዓመታት በተራዘመ የፍርድ ቤት ክርክር የተለጠፈበትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ለፍርድ ቤት አቅርቦና ዳኞችን አሳምኖ ከሳሽ ኃይልን በመርታት፣ ከአሥራ አንድ ዓመታት እስራት በኋላ በሕግ አሸናፊነት በነፃ ለመለቀቅ ችሏል፡፡ ያም ሆኖ ዛሬ የወቅቱ ርዕሰ ጉዳይ ከመሆኑ በፊት ጀምሮ ከሳሾቹን በጠላትነት ላለማየትና የይቅርታ ሕይወት ለመለማመድ በመወሰን ከኅብረተሰቡ ተቀላቅሎ፣ ባለፉት አሥራ ምናምን ዓመታት ሰላማዊ ኑሮን በመምራት ላይ ነው፡፡ እናም ለሁሉም አይበጅምና ያላግባብ የተለጠፉ ፖለቲካዊ ስያሜዎችን ፍቀንና አንስተን በፍቅር ያሸንፋል ይቅር ባይነት በውጭው ዓለም የሚገኙና በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አገራቸው በምሕረት እንዲገቡ ዕድል ይሰጣቸው!! ይኼም ያልተዳሰሰው ዳሰሳ አካል ነውና የሁሉንም ትኩረትና በጎ አሳቢነት ይጠይቃል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን መዝጊያ ቋንቋ ፈጣሪ አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ!! በቸር ይግጠመን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...