Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአስለቃሹ የግብር አወሳሰንና የአገር የገቢ ፍላጎት

አስለቃሹ የግብር አወሳሰንና የአገር የገቢ ፍላጎት

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

የሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴን እንግዳ አድርጎ ነበር፡፡ የሥራ ኃላፊው  በቀደመው አደረጃጀት ጨምሮ በተለይ በመዲናዋ የ233 ሺሕ ግብር ከፋዮች ቅሬታዎች ተመልሰው የዜጎች ጥቅም እንደተከበረ ቢገልጹም፣ እዚያው ላይ በግብርና መሰል አመቺ ያልሆኑ ሁኔታዎች 30 ሺሕ የሚደርሱ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ መመለሳቸውን፣ ይኼንኑ ያህሉም የግብር ከፋይነት ክሊራንስ አለመውሰይቸውን በመግለጫቸው ማውሳታቸው፣ የዘርፉን ፈተና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥም የመንግሥትን ምሕረትና እፎይታ ወይም የቅጣትና ማሳደድ አካሄድ መቅረት የሚጠብቀው ዜጋ (በተለይም አነስተኛ ነጋዴ) ቁጥሩ ትንሽ አይመስለኝም፡፡

ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለፓርማው ቀርበው ባቀረቡት የበጀት ማብራሪያ መሠረት አገሪቱ ወደ 347 ቢሊዮን ብር  የሚደርስ በጀት ለ2011 ዓ.ም. የሥራ ዘመን አፅድቃላች፡፡ ይህ በጀትም እንደተለመደው በዋናነት ከሕዝቡ ግብር እንዲሰበሰብ መጠበቁ ዕሙን ቢሆንም፣ ግን ግብርና ታክስ ፍትሐዊና በሕዝቡ የውዴታ ግዴታ የሚከፈል የአገር ሀብት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብን የማያማርር ይሆን ዘንድ የሚጠብቁ ሥራዎች ገና የትየለሌ መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡

የግብር ሥርዓት ለአንድ አገር ዕድገትም ሆነ የመልካም አስተዳዳር ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ግብር የሠራና ገቢ ያገኘ ማንኛውም ሰው ባገኘው ልክ የሚከፍልበት፣ የሌለውም በዜግነቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት (መንግሥት ግብር በመሰብሰብ በሚሠራው የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የመሠረተ ልማት ወይም አገራዊ ደኅንነትና መልካም አስተዳደር) የአገር እሴት ነው፡፡ ለዚህም ነው ግብር መክፈል ማለት አውራ መንገድና የባቡር ትራንስፖርት መዘርጋት፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ማቋቋም ወይም የአገር ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደርን በአገር ላይ ማስፈን ማለት ነው፡፡

ግብር መክፈል ማለት የነገው ትውልድ የሚታከምበት የጤና ተቋም፣ የሚማርበትን ትምህርት ቤት፣ የሚጠጣውን ውኃ፣ የሚያስፈልገውን መብራት፣ የቴሌ አገልግሎት፣ የሚኖርበት ቤት፣ ሀብት የሚያፈራበትን የሥራ ዕድል፣ የውስጥና የውጭ ሥራውን የሚያስከብርበትን ሥርዓት መዘርጋት ማለት ነው የሚሉትም አሉ፡፡  ግብር ‹‹ያለው ለሌለው›› የሚያስከፍልበት ፍልስፍና ነው፡፡ ግብርና ታክስ መክፈል ማለት የሕዝብንና የአገርን ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም  አገርና ሕዝብን ከፍ ወደ አለ ሥልጣን ማድረስ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ  ዕውን ሊሆን የሚችለው ግን ፍትሐዊ የግብር ሥርዓትና ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ አከፋፈል በመዘርጋቱ ብቻ ሳይሆን፣ በግብር መክፈል ስም ከሥራ መፈናቀል፣ ስደትና እንግልት ሲቆም ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን እየታየ ያለው የተለጠጠውን የመንግሥት የልማት ዕቅድና ፍላጎት ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ለማሟላት (አሁን ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ከአፍሪካ አማካይ ያነሰነ 11 በመቶ ብቻ ነው የሚሰበስበው የሚለው ሥሌት አጭበርባሪውንና ግብር ሳይከፍል የሚያግበሰብሰውን የመንግሥትና የኢንዶውመንትና የኮንትሮባንዲስት ለማስከፈል ከሆነና ያው መልሶ ደሃው ላይ ጫና ለመፍጠር ከታሰበበ አደጋው የከፋ ነው)፣ መንግሥት ከብድርና ከዕርዳታ ከሚያገኘው በላይ ከዜጋው ገቢ ለመሰብሰብ ከመፈለጉ የተነሳ ከፍተኛ ጫጫታ እየተቀሰቀሰ ይገኛል፡፡

ባለፈው ዓመት ሁላችንም ደጋግመን ከሕዝብ ወገን በመቆም እንደጮህነው  ሁሉ በቀን ገቢ ግምት ስም በርካቶች ከሥራ ወጥተዋል (በድንጋጤ ሕይወቱ ያለፈም ትንሽ አልነበረም)፡፡ የመንግሥት ዕዳ በመፍራትና በመሸሽ ከአገር የተሰደዱትም ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንድ በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ (በተለይ በአገልግሎት ሰጪ መስክ) ወገኖችም ሠርተህ ያላገኘኸውን ገንዘብ እንድትከፍል ከመገደድ ልመናና ሴተኛ አዳሪነት ወይም በምሬት መሰደድና መሸሽ በእጅጉ ይሻላል ብለው ኑሯዋቸውን ቀይረዋል፡፡ አስደንጋጩ ነገር ደግሞ በአንድ ዓይነት ሥራና ቦታ ወይም በተቀራራቢ የወጪና የገቢ መስክ አንዱ ግብር ብቻ ሳይሆን ቅጣትና ወለድ እየተጫነበት ሲገፈግፍ፣ ሌላው በኢፍትሐዊነትና በማናለብኝነት በሕዝብ ሀብት የግል ኪሱን ሲያደልብ መመልከት፣  አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ በተለይ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ መጠጥ ቤቶችና በመሳሰሉት የግል ድርጅቶች ላይ የሚጣለው ግብርም ሆነ እንዲሰበስብ የሚፈለገው ተጨማሪ እሴት ታክስ ( ቫት)  የተጋነነ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ በተቃራኒው በአሥርና 20 ሚሊዮን ብር ካፒታል የመኪናና ልዩ ልዩ ማሽነሪዎች መለዋወጫ የሚያስመጣ ሰው ግን ካፒታሉ ከ50 ሺሕ ብር ባይበልጥም (በአሠራሩ ክፍተትና በአድሎአዊነቱ መዘዝ)  የሚናገረው የለም፡፡  በመቶ ሺዎች ብር ለሚፈጽመው ሽያጭም ደረሰኝ ቆረጠ አልቆረጠ አተኩሮ የሚያስተውለው የለም፡፡ እንዲያውም በገቢዎች መሥሪያ ቤት እየሠሩ ደመወዝና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ያመቻቸላቸው ጥገኛ ሠራተኞች አማካይነት መረጃና ድጋፍ ስለሚደረግለት እያጭበረበረ በብልፅግና ይኖራል፡፡ ምንም እንኳን በፈጸመው ድርጊት  ህሊናው  አርፎ ሊተኛ ባይችልም፡፡

ለዚህ አብነት ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የመርካቶው ደረሰኝ አልባና ሕገወጥ ንግድ ብቻ ሳይሆን በፒያሳ፣ በልደታና መሰል አካባቢዎችም እየተባባሰ መምጣቱ ነው፡፡ በቅርቡ የንግዱን ማኅበረሰብና የገቢ ሰብሳቢ አካላትን ለመከታታል ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ በመሆኑም ውድ የሚባሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ አንዳንድ ጌጣጌጦችና ቁሳቁሶች ካለደረሰኝ  በሥውር አይሉት በይፋ በሚቸበቸቡበት አገር ስለምን ምግብና መጠጥ ወይም ቅመማ ቅመምምና አልባሳት መሠረታዊ ፍላጎት ሆነው ሲያበቁ፣ ይኼን ያህል ተዘመተባቸው መባል አለበት፡፡ ይኼ ነገር በሕዝቡ ላይስ የሚያደርሰው ጫና የለምን ስል መጠየቄ አልቀረም፡፡ መልሱ ግን መንግሥት ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› የሚል የገቢ አሰባሰብ ብሂሉን ካልፈተሸ፣ ሕዝቡ ከማልቀስ እንደማይድን የሚመለከታቸው አካላት ሳይቀሩ አረጋግጠውልኛል፡፡ ከሁሉ በለይ በቅጣት ያውም በተደራራቢ ቅጣት ከዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰበሰብ ከሕዝብ የተነጠቀ ገንዘብ  ለመንግሥትም ቢሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ማመዘኑ አይቀሬ ነው፡፡ ለአገርም የማይበጅ ነው፡፡

በቅርቡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራዎች ላይ አንድ አነስተኛ ጥናት ያካሄደው ዘሪሁን ተክሉ የተባለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ክፍል ተማሪ ባካሄደው መለስተኛ ጥናት፣ አሁንም ኢፍትሐዊ የግብር አወሳሳንና ገቢ የማያስገቡ ትልቅ ሀበት የሚያንቀሳቅሱ ወገኖች አሉ፡፡ በአዲስ አበባ እንደ ቄራና ጎፋ እንዲሁም አብነት፣ ሶማሌ ተራ፣ መርካቶና ልደታ አካባቢዎች (አሁን አሁንማ ሥራው እየተስፋፋ በለቡ፣ ጀሞና ሃና ማርያምም ተባብሷል) የመሳሰሉ ሠፈሮች በጨረታም ሆነ ከዚህ ቀደም አገልግለው ከተወገዱ ወይም የኢንሹራንስ ‹ሪከቨሪዎች› በየቀኑ ከ20 እስከ 50 ተሸከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎችና ከፍተኛ ካሚዮኖች ታርደውና ተቆራርሰው ሲቸበቸቡ ይውላሉ፣ ያድራሉ፡፡ የድልድይና የግንባታ ግብዓቶች፣ ባዶ ኮንቴይነሮችና ተንቀሳቃሽ ቤቶች ሳይቀሩ እንደ ጉድ የገንዘብ ልውውጥ ሲደረግባቸው መንግሥት ተገቢ ድርሻውን እንዲሰበስብ አለመደረጉ፣ እነዚህ ሰዎች (በዘርፉ የተሰማሩት) እነማን ናቸው የሚያስብል ነው፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አራጆችና ትልልቅ አጥር ግቢዎች ከፍተኛ ሀብት ባይንቀሳቀስባቸው (አንዱን ግቢ ከ60 ሺሕ  እስከ 100 ሺሕ ብር በየወሩ እንደሚከራዩት  ልብ ይሏል) በምንም ታምር እዚህ ሥራ ላይ ሊሰማሩ አይችሉም ነበር፡፡ በተመሳሳይ በከተማዋ እጅግ በርካታ ሊባሉ የሚችሉ አነስተኛና ከፍተኛ ጋራዦች፣ የቶርኖና የማለስለሻ ሥራ የሚሠሩ ወርክ ሾፖች ሁሉ አንድም ግልጽ የገቢና የወጪ ማስታወቂያ ሆነ በደረሰኝ የሚያከናውኑት ሥራ የላቸውም፡፡ ለሠራተኛም በተለምዶ  በሳምንት ደመወዝ የሚከፍሉ እንደ መሆናቸው የሥራ ግብርና የጡረታ ሲሰበስቡም ሆነ ገቢ ሲያደርጉ የሚታዩት እጅግ ጥቂቱ ብቻ ናቸው፡፡ ይህን የኢፍትሐዊነት ሰፊ በር መንግሥትና የመንግሥት አካላት እንዳላየ እያዩ አልፎዋቸዋል ወይም እንዲያልፉዋቸው ታስቦ እየተሠራ ነው፡፡

 በተቃራኒው በጥቃቅንና አነስተኛ ሳይቀር የተደራጁ የእንጨትና የብረታ ብረት ሥራዎች ወይም የደረቅና ፈሳሽ ምግብ አዘጋጆች፣ ወይም የባልትና ዕቃ አምራቾች ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ግብይት ደረሰኝ እንዲቆርጡና ከደሃው ሸማች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሰበስቡ ይገደዳሉ፡፡ ባልታሰበ የቀን ገቢ ግምት ተብየም አከርካሪያቸው ይመታል፡፡ ሥርዓቱ ለደሃውና ለመካከለኛ ገቢ ተርታ ዜጎች የወገነ ነው እየተባለ በተቃራኒው ጥገኝነትን እያስፋፋ የሚሄድበትን መንገድ መዝጋት ካልተቻለ፣ ሁለንተናዊ ዕድገትን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት አድርጎ ነው መንግሥት የግብር መረቡን ለማስፋት የሚችለው? ከ11 በመቶ ዓመታዊና አገራዊ ገቢስ ማለፍ የሚሞከረውና አገርስ ልትጠቀም የምትችለው ብሎ ዙሪያ ገባውን መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ ሕጋዊውንና ታግሎ አዳሪውን ከፋይ በማቆርቆዝ!

ሌላው እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት የኢፍትሐዊነት መገለጫ የቤትና የሕንፃ ኪራይ ግብር ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጥናትም እንደተረጋገጠው አሁን ያለው የአዲስ አበባ የቤትና መሬት ይዞታ ባለቤትነት ከ27 ዓመታት በፊት ከነበረበት በመሠረታዊነት ተቀይሯል፡፡ ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው በአገራችን በትጥቅ ትግል የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ወደ መዲናዋ የገባው የዚህ ኃይል ዘመድ አዝማድና ዕውቂያ ያለው ሁሉ ተጠቅሟል፡፡ ከዚያም አልፎ  ዛሬ በመዲናዋ አብዛኛው ባለሕንፃ፣ ትልልቅ ግቢና መለስተኛ ቤት አከራይ የሆነው የዚሁ ሥርዓት ማኅበራዊ መሠረት የሚባለውና በቀድሞው ሥርዓቶች ሰፋ ያለ ቦታና ሀብት ይዞ አንዳንዱ የወቅቱን ጫና የተቋቋመው ኃይል ብቻ ነው፡፡

ይህ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የኢፍትሐዊነትና የተዛባ ሀብት ክፍፍል መገለጫው ይህ አብዛኛው ቤት አከራይ ተገቢውን የመንግሥት ግብርና ቀረጥ የማይከፍል፣ በከተማ የኪራይ ዋጋ ጣሪያና ምጣኔ ሕግ ለማውጣት ቢሞከር እንኳን ሥርዓቱን እንደ መነቅነቅ ስለሚቆጠር የማይደፈር ሆኖ የቆየ ነው፡፡ ስለዚህ ባለጥቅምና ባለጊዜ ከሚነካ የደሃውና መካካለኛ ገቢ ባለቤቱ ወገብ እየተቆረጠ ወይም በብዙኃኑ ለፍቶ አደር ብታድግ ትደግ ካልሆነም ትንፏቀቅ እየተባለ ይመስላል፡፡ በእውነቱ በመዲናችን እንደ አሸን እየፈሉ ካሉ ሕንፃዎች፣ ዘመናዊ ‹‹ገስት ሐውሶች››፣ አፓርትመንትቶችና ቪላዎች ኪራይ በውል ማጭበርበር ወይም ራሱ የገቢ ሰብሳቢ መሥያ ቤቱ ጋር በመሞዳሞድ ኪራዩ ባይሸሸግ ምን ያህል ግብር ሊሰበሰብ ይችልና ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ሁሉም ሊገነዘበውና ሊመረምረው የሚገባ ነው፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው ግብር አሰባሰብ ልዩነቱ በዘርፍና በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ ከክፍለ ከተማ ወይም ከወረዳ አንፃር ወጣ ገባና የተዘበራራቀ አሠራር የሚታይበት መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ቂርቆስ የሚባለው ክፍለ ከተማ ገቢ በመሰብሰብ አንደኛ እየተባለ አይዞህ ቢባልም፣ ተገልጋይን በገፍ ግብር በመጠየቅ፣ በመቅጣትና በማማረር የተዋጣለት የከተማዋ ከፋይ መሆን ብቻ ሳይሆን ቅሬታ እንኳን በወጉ የማይደመጥ በለሙያዎቹም ከላይ እስከ ታች ለድርድርና ለሙስና ያሰፈሰፉበት ነው፡፡ በልደታና በቦሌም ተመሳሳይ ቅሬታ እንደሚነሳ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገልጻሉ፡፡ ለነገሩ በተጠቀሱት ቦታዎች ይባስ እንጂ፣ የመዲናዋና በአገሪቱ የአንዳንድ ከተሞች ዝንባሌ አስፈሪና ሕዝብ አማራሪ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንዲህ ዓይነት ቦታዎችን እየለቀቁ ወደሌላ ክፍለ ከተማ መሰደድ አልያም ሁሉንም ነገር ትቶ እጅ እግር አጣጥፎ መቀመጥ ግድ እየሆነባቸው ነው፡፡ ለወደፊቱም ከተማዋን ኮንትሮባንድና የንግድ ውንብድና እንዳጥለቀለቃት እየታወቀ ሕጋዊውን ለማቆርቆዝ ወይም አነስተኛውን ግብር ከፋይ ወገብ ለመቁረጥ፣ በተለይ በአንዳንድ የገቢዎች መሥሪያ ቤት ሙያተኞችና ኃላፊዎች የሚፈጸመው አሻጥርና ደባ ልዩ የመንግሥትን ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ በተለይ እንደ ዜጋ አስተምህሮና ግንዛቤ ማስጨበጥን ከማስቀደም ይልቅ፣ በትንሽ በትልቁ ቅጣትን መሣሪ ማድረግና የቅጣት ወለድን ለመሰብሰብ በመሞከር ዕዳን ከራስ አልፎ በትውልድ ላይ ለመጫን መታተር መዘዙ ጉድጓድ የሚከት ነው፡፡ ለማንም ሊበጅም አይችልም፡፡

ግብር ለሥልጣኔ የሚከፈል ዋጋ ማለት ነው፡፡ ግብር ዕዳ አይደለም ከተባለ ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብም ይህን ዓላማ በትክክል እንዲያውቅ ሁልጊዜ የመማማር፣ የመመካከርና የመጠያየቅ ባህል መዳበር አለበት፡፡ ይህም በሒደት  ግብር ከፋዩ ሕዝብ የራሱን ገቢ ራሱ አሳውቆ፣ በራሱ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት በወቅቱ ቀርቦ እንዲከፍል የሚያስችለውን ግንዛቤ ለመጨበጥ የሚረዳው ከመሆኑ ባሻገር፣ ግብር በመሸሸግና በኮንትሮባንድ የሕዝብ ሀብት ለመንጠቅ የሚሞክረውን ለመታገልና ለማጋለጥም ያበረታታዋል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎች መሠራታቸው የማይካድ ቢሆንም፣ በቂ ሊባሉ ግን የሚችሉ አይደለም፡፡ እስካሁን ከማስገደድ በመለስ ከግብር ከፋዮችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ምን ያህሉ ለግብር ከፋዩ ግልጽ እንደሆኑና ወደ ተግባር እንደተቀየሩ ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ፈጣን አገራዊ ዕድገት ሲባልም፣ ጥገኝነትና ሌብነትን ወደ ዳር የሚገፋ የሕዝብና መንግሥት መተማመን መፈጠርም አለበት፡፡ ይገባልም!

ይህን ማድረግ ከተቻለ በአንድ በኩል ግብር ሸሻጊውና ደረሰኝ ዕርሙ ሁሉ ይጋለጣል ወይም ከድርጊቱ ይቆጠባል፡፡ በሌላ በኩል የግብር ዓላማና አስፈላጊነት ላይ ሕዝቡ ሲተማመን፣ ግብር ከፋዩ በራሱ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት በዓመት ያገኘውን የሽያጭ ገቢ አሳውቆ፣ በፈቃደኝነት ግብር ከፋይነት አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አምኖ ሕጋዊውን ተግባር ከመፈጸም አይቆጠብም፡፡ በቅንንነትና በታማኝነት ሒደት ውስጥ ተገቢውን ባለማድረጉ ምክንያት ሊገጥሙት ስለሚችሉ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችም በግልጽ አውቆ ለመማር የሚረዳው ዕርምጃ ሲወሰድበት ከችግሩ ከመውጣት የሚቆጠብ አይሆንም፡፡

 በመሠረቱ ሕግ ያከበረውን ያከብራል፣ ያላከበረውን ደግሞ እንደ ጥፋቱ መጠን ቅጣቱን ይሰጠዋል፡፡ ግብርና ታክስ አለመክፈል እጅግ በጣም ከፍተኛ አገራዊ ጥፋት ነው፡፡ ግብር ያልከፈለ ወይም የሰወረ ወይም ያጭበረበረ ሰው ይፍጠንም ይዘግይም ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡ ግብር ያልከፈለ ሰው ማንም ይሁን ማን የትኛውንም ዓይነት ሥልጣንና የሀብት መጠን ቢኖረው፣ የቱንም ያህል ተወዳጅና ዝነኛ ቢሆን ሕግ ፊት ከመቅረብ አይድንም፡፡ ይሁንና ሕጉን እንደ ሰው ሁኔታ እየጠመዘዙና እያዛቡ ለመተግበር መሞከር ከወንጀልም በላይ ወንጀል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሱ መንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጡን መፈተሽና ሕዝቡንም ያሳተፈ ትግል ማድረግ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ሴክተሩ ሊስተካከልና ከሕዝብ ጋርም ሊታረቅ ካለመቻሉም በላይ እንደ መንግሥም ወደ  ችግር የሚወስደው ነው፡፡ 

 በአጠቃላይ  ለታክስ ሕጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለብን እያልን ለግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ስንናገር የግብር ሰብሳቢዎች ተቋማትን ኃላፊነት መዘንጋት የለብንም መባሉም ከዚሁ እውነታ በመነሳት ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያሉ ተቋማት  ግብር ወይም ታክስ ፍትሐዊ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው፡፡ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኘውን ሰው ዝቅተኛ ግብር ማስከፈል ወይም ዝቅተኛ ያገኘውን ሰው ላይ ከፍተኛ ግብር መጣል፣ በግብር ከፋዩ ዘንድ የተቋሙን ተዓማኒነትና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ ይጥላል፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ተመሳሳይ ካፒታልና ሽያጭ ያለውን ግብር ከፋይ በቦታ ልዩነት የተጋነነ ታክስ መጣል ወይም በአንድ ቦታም ጉቦ በመስጠትና ባለመስጠት የተጋነነ ልዩነት መጫን እየታየ ነው፡፡ በደረጃ ‹‹ሀ›› መመዝገብ ያለበትን በደረጃ ‹‹ለ›› ወይም በደረጃ ‹‹ለ›› መመዝገብ ያለበትን በደረጃ ‹‹ሐ›› መመዝገብ ትክክል አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡

በተመሳሳይ በግብር ወይም በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ መግባት ያለባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወሰኑትን አስገብቶ ሌሎችን ችላ ማለት አይገባም፡፡ በአዋጁ መሠረት ማንኛውም ነጋዴ፣ አገልግሎት ሰጪ፣ ኢንዱስትሪያሊስት፣ ቀጣሪ ወይም ተቀጣሪ…አከራይ …ካገኘው ዓመታዊ ገቢ ላይ መክፈል ያለበትን ግብር ወይም ታክስ ማስገባት አለበት፡፡ መንሻፈፉ የትም አያደርስም፣ ኢፍትሐዊነትን ያነግስ እንደሆነ እንጂ፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊነት በጣም ግዙፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚያው ልክ የዜጎች ኃላፊነትም ከባድ ነው፡፡ ለአገሪቱ ልማት የሚሆነው ገንዘብ በዋነኝነት የሚሰበሰበው በዚህ ተቋም አማካይነት ነው፡፡ ገቢ የሌለው መንግሥት ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የለም፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ  ባለሥልጣን ሥራ የአንድ ቀን ወይም የአንድ ዓመት አይደለም፡፡ የሁልጊዜም አገራዊ ሥራ ነው፡፡ ተቋማት ግብር ከፋዩን ማኅበረሰብ በተገቢው መንገድና በቅልጥፍና ማስተናገድ እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ቅድሚያ ሰጥተው ማሟላት አለባቸው፡፡ እኛ ዜጎችም ግዴታችንን መወጣት አለብን የሚለው መርህና አሠራርም መዘንጋት የለበትም፡፡ ግን በየደረጃው ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊዳብር ይገባል፡፡ 

ግብር ወይም ታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች፣ ቅርንጫፎች ውስጥ የመብራት መጥፋት ወይም መቆራረጥ ችግር በተቻለ መጥን መኖር የለበትም፡፡ ችግር ሲፈጠር ግብር ከፋዩ የሚጉላላበት ሁኔታም ሊቆም ግድ ይላል፡፡ ሁልጊዜ ጀማሪ መምሰል አይጠቅመንም፡፡ ግብር ከፋዩ ካገኘው ገቢ ላይ ለመንግሥት መክፈል ያለበትን ግብር ሊከፍል መጣ እንጂ፣ ገንዘብ ሊጠይቅ ወይም ሊለምን አልመጣም፡፡ ስለዚህ ፈጣንና አርኪ አገልግሎት እንዲያገኝ በተቋሙ ውስጥ ሊታዩ የሚችሉ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎች አጥብቆ መታገል፡፡ ይህ ደግሞ ከትልልቅ ነጋዴና ባለሥልጣን አንስቶ እስከ ባለሙያውና ሱቅ ቸርቻሪው ድረስ ያለው ግንኑነትና የጥቅም ትስስር ተመርምሮና ተመንጥሮ መበጠስ አለበት፡፡

በእኔ እምነት የሚዲያው ማኅበረሰብም ግብር የአንድ ጊዜና ወገን ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ተረድቶ ቀጣይነት ባለው አስተማሪና ተወዳጅ አቀራረብ የተቋሙን ተልዕኮ በስኬት ለማስቀጠል መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በጋዜጣም ሆነ በሬዲዮና ቴሌቪዥን ተራ የወሬ ሪፖርት ከማነብነብ በላይ የሕዝቡን ብሶት፣ በግብር ላይ የሚፈጸም ሙስናን፣ ማጭበርበርና ኢፍትሐዊነት ዳፋውን ዘክዝኮ ንፋስ ማስመታት ግድ ይለናል፡፡ ሁላችንም የጉዳዩን አገራዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን አዋጁን፣ ደንቡን መመርያውን በተደጋጋሚ የማሳወቅ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡ በዚህም አገርና ሕዝብ በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...