Sunday, June 16, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአሜሪካ ቆይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከመጀመርያው የሲመት ንግግራቸው አንስተው በተለያዩ መድረኮች በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን (ዳያስፖራ) ለአገራቸው በገንዘብ፣ በዕውቀትና በተለያዩ ተሳትፎዎች ማገልገል እንዲችሉ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው። ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁና የትም በሚከተላችሁ የአገራችሁ የጨዋነት ባህርይ የኢትዮጵያና የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ፡፡

‹‹አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው፣ ነገር ግን እጅግ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለአገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። እንደ አገር ያለንን ሀብት አሟጠን ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም። መቆጨትም አለባችሁ። ይኼንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ አገር አለችንና ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ አገራችሁ መመለስና አገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ፣ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን። በውጭ አገሮች ኑሯዋችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በአገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና አገራችንን በሀሉም መስክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋፅኦ መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል፤›› ብለው ነበር፡፡የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአሜሪካ ቆይታ

 

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ዳያስፖራው ከማኪያቶ መጠጫው ላይ አንድ ዶላር ለአገሩ ቢሰጥ ምን ያህል ጥቅም ላይ የሚውል ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረው ነበር፡፡ ይኼንንም ተግባራዊ ለማድረግ ዳያስፖራውን ተማፅነዋል፡፡

ይሁንና እነዚህን ዳያስፖራውን የሚመለከቱ ንግግሮች ሲያደርጉ፣ ከዳያስፖራው ጋር ሳይገናኙ ነበርና በተለይ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎስ አንጀለስና በሚኒሶታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ለማዘጋጀት ታቅዶ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩ ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ እነዚህ ቦታዎች የተመረጡትም በተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማዕከል ለማሰባሰብ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የዝግጅቱ አስተባባሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ ሌሎች ልዑካንንም ያካተተ ነበር፡፡ ጉብኝቱም ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ተጀምሮ ለስድስት ቀናት የዘለቀ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአሜሪካ ያደረጉትን ጉብኝት በዋሽንግተን ዲሲ ሲጀምሩ፣ ከተለያዩ አካላት ጥያቄዎችን በመቀበል ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በዋሽንግተን ከታማኝ በየነ ጋር በመተቃቀፍ በሕዝቡ ፊት ዕርቀ ሰላም ማውረድ እንደሚያስፈልግ ከገለጹ በኋላ፣ ሕዝቡም እርስ በርሱ በመተቃቀፍ አጋርነቱን እንዲያሳይ አድርገዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግብዣ ንግግር ያደረገው ታማኝ በየነ፣ ‹‹በቀን አንድ ዶላር ተጠይቀናል፣ ነገር ግን በማስተባበር አሥር በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለአገራችን እናስገባለን፤›› ብሏል፡፡

ወደ መድረኩ በጥሪ እንደወጣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እግር ሥር የተደፋው ታማኝ፣ ‹‹ቀሪ ዘመንዎን በፈለጉት መንገድ ላገለግልዎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ቃል እገባለሁ፤›› ሲልም ምሏል፡፡

የታማኝን ንግግር ተከትሎ መድረክ የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ብትሆንም ትፀንሳለች እንጂ አትወልድም፣ ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም፣ ማጎርመስ እንጂ ማጎልመስ አልሆነላትም፡፡ እንጀምራለን እንጂ አንጨርስም፡፡ ይህ ሾተላይ መለየት አለበት፡፡ ይህ አጨናጋፊ በሽታ ከውስጣችን ተለይቶ መውጣት አለበት፡፡ ይህ በሽታ ቂም ነው፣ ይህ በሽታ አልሸነፍም ባይነት ነው፣ ይህ በሽታ በቀል ነው፣ ይህ በሽታ መናቆር ነው፣ ይህ በሽታ የጅምላ ጥላቻ ነው፣ ይህ ሾተላይ ራሱን አደራጅቶ በመካከላችን ያለመደማመጥ፣ ያለመቻቻል፣ የባላንጣነት ግንብ ላለፉት 40 ዓመታት ሲሠራብን ቆይቷል፡፡ ዛሬ ከታማኝ በየነ ጋር ስንተቃቀፍ የመጀመርያውን መዶሻ ግንቡ ላይ አሳርፈናልና ይህን አጉዳይ፣ አጠልሽ ግንብ ጡብ ያላቀበለ፣ ብሎኬት ያላቀበለ፣ ሐርማታ ያላቀበለ፣ መክሰስና ከወንጀሉ ነፃ መሆን የሚችል አንድም በመካከላችን ስለሌለ ሁላችንም በርብርብ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት የገነባነውን ከፋፋይ የጥላቻ ግንብ ዛሬ ለማፍረስ ቃል እንግባ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ጉብኝታቸው ንግግር ከማድረግ ባለፈ ጥያቄዎችን እየተቀበሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በሁሉም ስብሰባዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸው ንግግሮችና የሰጧቸው መልሶች በጭብጨባ የታጀቡ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ የተቋማት ግንባታን በሚመለከት ሲሆን፣ በተለይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያስከብሩ ተቋማት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልሳቸው ‹‹ነፃነት፣ ሰብዓዊ መብት፣ ፍርድ ቤት፣ ሚዲያ እንዲህ ባለ መድረክ የሚመለሱ ጉዳዮች አይደሉም፣ ከንግግር በላይ ናቸው፤›› ብለው፣ ከሁሉ በላይ ግን የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት ዋና ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው እንደሆነ በመጠቆም፣ ‹‹አሁን ያሉን ከ80 በላይ ፓርቲዎች አያስፈልጉንም፡፡ አምስትና ስድስት ጠንካራ ድርጅቶች ኖረው መቀመጫ ተከፋፍለው በሐሳብ የሚፎካከሩ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ አሁን በጣም በርካታ ፓርቲዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ የሽግግር መንግሥት ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት ማለት የሥልጣን መጋራትን ያካትታል፡፡ አሁን ያሉት ፓርቲዎች 80 ናቸው፡፡ ሚኒስትሮች ደግሞ 27 ናቸው፡፡ ስለዚህ ሥልጣን ለማጋራት የሽግግር መንግሥት ብናቋቁም የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በዚህ የማያቋርጥ ሒደት ውስጥ ከምናልፍ ሁለት ዓመት ነው የቀረን፡፡ በእኔ እምነት ሁሉም መንግሥት የሽግግር መንግሥት ነው፡፡ ከተርሙ በላይ ማገልገል ስለሌለበት በረጋ በሰከነና በተደመረ መንፈስ እዚህም እዚያም ያላችሁ እንድንዘጋጅ፡፡ በምርጫ ግን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ስንሸነፍ ልክ እንደዚህ አገር አመሥግነን መስጠትም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማትፈቅደው የጥምር ዜግነትም ሌላው በታዳሚዎች የተነሳ ጥያቄ ሲሆን፣ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? አስፈላጊ ነው ወይ? የሚለውን ጊዜ ወስዶ ማየት እንደሚስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ፓስፖርታችሁ ቢወሰድ ኢትዮጵያዊነታችሁ ስለማይወሰድ፣ ለዚያም ስለሆነ እኛም የመጣነው በሚበጀን መልኩ እንጠቀመዋለን፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት የዳያስፖራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይቋቋም ተብለው የተጠየቁ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ዳያስፖራን የሚመለከት ተቋም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን አስታውቀው፣ ‹‹አሁን ያለን ሐሳብ መስከረም ላይ አብዛኛውን ሚኒስቴር ማጠፍ ነው፡፡ ምክንያቱም በጣም ባለሥልጣን በዛ፣ ባለሥልጣን ሲበዛ ውጤታማነት ስላልተለመደ፣ አንዴ ከተሾምክ መውረድም ከባድ ስለሆነ ዕዳው እንዳይበዛ ቢያንስ የዳያስፖራን ጉዳይ ቀስ ብለን እንጀምረዋለን፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎችን በመድረኮቹ ይመልሱ እንጂ፣ መልስ ሳይሰጡ በይደር ያለፏቸው ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ ለአብነት ያህልም ኢትዮጵያ የሕግ፣ የታሪክና የተፈጥሮ የባህር በር ባለቤትነት መብት አላት ብለው ያምናሉ ወይ? የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን መቼ ያናግራሉና እርስዎ የሚሰብኳትን ታላቋን ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ ያውቀዋል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚኒሶታ በነበራቸው ቆይታም በርካታ የሚኒያፖሊስና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙበት ደማቅ ዝግጅት ሲሆን፣ የኦነግ ባንዲራና መሀሉ ላይ ዓርማ የሌለው አረንጓዴ ቢጫ ቀይና ሌላ ባንዲራ በአዳራሹ ሲውለበለቡ ታይቷል፡፡

በተደጋጋሚ በመድረኮቹ ላይ የፕሬዚዳንት ለማና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ስም ሲጠራ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም፣ ‹‹የለማ ቡድን ቢሆን በጣም የሚያኮራ ነው፡፡ ግን ችግር የሚሆነው የለማን ቡድን ስታስቡ ለማና ዓብይን ብቻ ካሰባችሁ ነው፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች እዚያ ውስጥ አሉ የብዙ ሰዎች ውጤት ነው፤›› ሲሉም የለማ ቡድን (ቲም ለማን) አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በሚኒሶታ በነበረው ዝግጅት፣ ‹‹ቲም ለማ ገዱን (የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው) ያካትታል፣ ቲም ለማ ደመቀን (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን) ያካትታል፣ የውጭ ጉዳይና አማካሪ ወርቅነህን (ዶ/ር) ያካትታል፣ ሙፈርያትን (የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል) ያካትታል፤›› ሲሉም ቲም ለማ የእነ ማን ውቅር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሚኒሶታ በነበራቸው ቆይታ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛና በአማርኛ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በኦሮሚኛ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የኦሮሞ ድርሻው መገንባት ነው:: መታገስ ነው:: ሌላውን መውደድና ይቅር ማለት ነው:: በተደረገብን በደል ልክ ማምረርና ለበቀል መነሳት ደግ አይደለም:: እርግጥ ነው ትናንትና ታስረናልተገድለናልተንቀናልተተፍቶብናልተሰድበናልታመናልተገፍተንማል፡፡ እኛ ግን ይኼንን ግፍ የምንመልሰው በፍቅርበማሳደግበታጋሽነትበይቅር ባይነትና አገር የምናፈርስ ሳይሆን አፍሪካን የምናቀና መሆናችንን በማሳየት ነው:: ስለዚህም ሆድን ሰፋ ማድረግ ምንጊዜም ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በትግርኛም ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች የኤርትራን ሕዝብ ከልባቸው እንደሚወዱና አብረው ለማደግ እንደሚያልሙ ገልጸዋል፡፡

በዝግጅቶቹ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ከማቅረብ በተጨማሪም፣ ለደኅንነታቸው ሥጋት ያደረባቸው ሰዎች ለፕሮቶኮል ትኩረት እንዲሰጡና ለደኅንነታቸው እንዲጠነቀቁም አሳስበዋቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር አያይዘው በተለይ በሐዋሳ ከመኪናቸው ድንገት ሲወርዱ የታየውን ክስተት ያብራሩ ሲሆን፣ ሕዝቡ መንገድ ወጥቶ ሳለ ከእሳቸው ጎን ተቀምጠው ይጓዙ የነበሩት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የእኛ በመኪና መሄድ አግባብ አይደለም በማለት በር ከፍተው ሲወርዱ ለመያዝ ቢሞክሩም ሊያስቆሟቸው ስላልቻሉ ተከትለው መውረዳቸውን፣ ሰውም ያንን ብቻ ማየቱን አስረድተው፣ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ወቅት እጅግ ከባድ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡

‹‹በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ ከባድ የሚያደርገው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምንም ባይደርስባቸውም ትንሽዬ ሙከራ ቢኖር ሁለተኛ ሰው፣ ሁለተኛ መሪ ኢትዮጵያ አይመጣም ማለት ነው፡፡ እኔ እየመራሁ ኢትዮጵያ መሪዎች ለመምጣት የሚፈሩባት አገር ከምትሆን ደግሞ … አልጨርሰውም፤›› ሲሉ ክስተቱን አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመደበኛ የጉብኝት መርሐ ግብሮች በተጨማሪ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አየኤምኤፍ) ዳይሬክተር ክሪስቲን ላጋርድ፣ ከዓለም ባንክ ዋና ዳይሬክተር ጂም ያንግ ኪም፣ እርቅ ከፈጸሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም፣ ከበድር ዓለም አቀፍ ጉባዔና ሌሎች ሥፍራዎች ላይ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበድር ባደረጉት ንግግር የኢንጂነር ስመኘው ሞት ልብ ሰባሪ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ሰው በአገሩ በጠራራ ፀሐይ የሚሞትበት አገር ከመምራት በላይ የሚያሳፍር ነገር የለም፤›› ሲሉም ማዘናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የእኛ ሥራ ክፉ ነገር ስናይ ሰው ነንና ማዘናችን አይቀርም፡፡ እዚያ ሐዘናችን ውስጥ ግን አንኖርም፡፡ ጥርሳችንን ነክሰን እንወጣለን፣ ወደፊትም እንሻገራለን፤›› ብለዋል፡፡

በበድር ባደረጉት ንግግር ላይ ማጠቃለያ ላይም፣ ‹‹በቀን አንድ ዶላር ለምናችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዓይነ ሥውራን እስካሁን ማስተማር የቻልነው አራት ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ ለእኔ አትርዱኝ፡፡ ረዳት ያጡ ዓይነ ሥውራንን አስተምሩ፤›› ሲሉም ድጋፋቸውን እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎበኟቸው ከተሞች በዋሽንግተን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ሐምሌ 21 እና 22 በየዓመቱ የኢትዮጵያ ቀን ሆነው እንዲከበሩ የከተሞቹ ከንቲባዎች ወስነዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -