Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሀብት ፖለቲካና የፖለቲካ ሀብታችን

የሀብት ፖለቲካና የፖለቲካ ሀብታችን

ቀን:

በሉልሰገድ ግርማ

አንድን ሥራ ለመሥራት ወይም ተፈላጊ ውጤትን ለማምጣት የምንጠቀምበት ነገር ሁሉ ሀብት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን በስፋት ከሚታወቁት መሬት፣ የሰው ጉልበትና ካፒታል ባሻገር መረጃን፣ ጊዜን፣ ሙያዊ ችሎታን፣ የአመራር ችሎታንና የመሳሰሉትንም ጭምር ከሀብት ጐራ ይመድቧቸዋል፡፡ ሀብቱን ተደራሽ የማድረግ፣ የመጠቀምና የማስተዳደሩን ሥራ ደግሞ የሀብት ፖለቲካ ብለው ሲጠሩት ፖለቲካዊ ሀብቶችን ደግሞ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ሀብቶችን በመጠቀም፣ የሌሎች ፖለቲካዊ ባህርይ የሚቀረፅበት መንገድ ነው ይሉታል፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአብዛኛው የሀብት ፖለቲካም ሆነ የፖለቲካ ሀብት እጅግ ሲያወዛግቡ የኖሩና በዚሁ የቀጠሉ ጉዳዮች ሆነው ይገኛሉ፡፡ በአገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተተገበሩትና እየተተገበሩ ያሉት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችና ዘላቂ የልማት ግቦች ከሀብት ፖለቲካና ከፖለቲካ ሀብቶች ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ የሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች አረዳዳችንና አተገባበራችን በምን ሁኔታ እያባሉንና እያቆረቆዙን እንደነበሩና አሁንም ያሉ በመሆናቸው ላለፉት ስልሳና ከዚያም በላይ ዓመታት የነበሩትና ያሉት ሁኔታዎች ያስረዱናል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመሬት ሥሪቱና ባላባታዊ ሥርዓቱ ዋነኛ የግጭት መንስዔ ነበር፡፡ ሰው በሰውነቱና በዜግነቱ የሚያገኛቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተጥሰውና ላቡን አንጠፍጥፎ ያመረተው ምርት፣ ሥልጠናቸውን በሥዩመ እግዚአብሔር ተሰጥቶናል ብለው በሚያምኑ ባለሥልጣናት እየተወሰደበት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ጥቂት የኃይለ ሥላሴ ከፍተኛ ወታደራዊ መኰንኖች ሁኔታውን ለመለወጥ ያደረጉት ሙከራ ባይሳካም፣ ምንም መሣሪያ ያልታጠቁ ተማሪዎች ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት ዋነኛ ሀብት የሆኑትን መሬትንና የሰው ጉልበትን ነፃ በሚያወጣ መንገድ ተደምድሟል፡፡

ሆኖም በተማሪው ትግል አስታኮ ወደ ሥልጣን የወጣው ደርግ ኢትዮጵያን ከባላባታዊ የሀብት ፖለቲካ አስተዳደር ወደ ለየለት አምባገነናዊና ወታደራዊ አስተዳደር ቀየራት፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ የሆኑት ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ጭምር በድንጋጌ በመገደብ ወታደራዊ የሀብት ፖለቲካውን ተግባራዊ አደረገው፡፡ በወቅቱ የነበሩትና የተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶችም በትውልዱ ዕልቂትን ያስከተለ ሌላ ዘይቤ ተከተሉ፡፡ ይኼንኑ ሁኔታ ተቃውመውና ጠንካራ አቋም ወስደው ጫካ የገቡ ወጣቶችም ተሳክቶላቸው 1983 .ም. ሥልጣን ተረከቡ፡፡ ወደ ጫካ የገቡበት ዋነኛ ምክንያትም በወቅቱ የነበረው የሀብት አስተዳደር በኢፍትሐዊነት ላይ የተመሠረተና እኩልነትን ያላመጣመሆኑ እንደነበር ማንም ያስታውሰዋል፡፡

ኢሕአዴግም ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን በማሰባሰብ የሽግግር መንግሥት ካቋቋመ በኋላ፣ ኢትዮጵያን ወደ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አሸጋገራት፡፡ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የፖለቲካ ሀብቶቻችንና እሴቶቻችን በፌዴራላዊ የሀብት አስተዳደር ዘይቤ መዘወር ጀመሩ፡፡ ከኢሕአዴግ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን አንቀጽ 39 የአገር መበታተኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ ነው በማለት ሲቃወሙት ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌዴራላዊ ሥርዓቱ የክልሎች ወሰን በዋነኛነት ቋንቋን መሠረት ያደረገ መሆኑን ይቃወሙታል፡፡

 

የፌዴራላዊ ሥርዓቱ የቆመበት መርህ ችግር ባይኖረውም በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃኖች (ከገዢውም ሆኑ ከተቃዋሚው ወገን) አጣመው ማቅረብና መጠቀም ጀመሩ፡፡ በተለይም ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለው የፌዴራሊዝም ፖለቲካዊ ሀብት ተገቢ ባልሆነ የሀብት ፖለቲካ ወይም አስተዳደር ይቤ ሥር ወደቀ፡፡ ሁለት የተለያዩ የትውልድ ሥፍራ ያላቸው ግለሰቦች በሚያነሱት አምባጓሮ የሁለት ክልሎች ፀብ እንደሆነ በማድረግ ወይም እንደሆነ ተደርጎ መደበኛና መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሠራጨት ጀምረ፡፡ አንዳንዴም የዚህ ክልል ነዋሪዎች ከዚህ ክልል እንዲፈናቀሉ ሆኑ፣ ተዘረፉ፣ ተገደሉ መባል ጀመረ፡፡ የባለሀብቶችን ሀብትና ንብረትም በደቂቃዎች ውስጥ ዶግ አመድ ማድረግም አልፎ አልፎ ሲከሰት ዓይተናል፡፡

ለመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ተስፋን ሰንቆ የነበረው ምርጫ 97 በበርካታ ባለድርሻ አካላት አማካይነት እንደ ሒደቱ ሳይሆን ቀረ፡፡ ባለድርሻ አካላቱ ሕገ መንግሥታዊ ፖለቲካዊ ሀብቶች አትራፊ ባልሆኑ የሀብት ፖለቲካኞች ባክነው ቀሩ፡፡ እንደ ተፈጥሮ ሀብት ሁሉ የፖለቲካ ሀብቶችም በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ካልዋሉ እርግማንን እንደሚያስከትሉ ከራሳችን ተምረናል፡፡ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የፕሮግራምና የመርህ አልባዎች ጐራ አድርጎ መፈረጅ፣ በተቃዋሚው ጎራ ኢሕአዴግን በትጥቅ ትግል የማውረድና የፖለቲካ ትግላቸውንም በአብዛኛው በኢሕአዴግ ህፀፆች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

የሀብት አስተዳደራችን ወይም ፖለቲካችን በፈጸመው ስህተት ምክንያት ባለፉት ሦስት ዓመታት የዘመኑ ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ዘርማዎች ከ1960ዎቹ ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ዘርማዎች የወጡትን የዘመኑ መሪዎች አምርረው ተቃወሙ፡፡ ወደ አደባባይም ወጡ፡፡ ጉዳትም ደረሰ፡ቁጣውንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመገደብ ተሞከረ፡፡ ኢሕአዴግም ኩላሊቱ ውስጥ ጠጠር በመገኘቱ ቀዶ ጥገና አስፈለገው፡፡

 

አሁን እየተካሄደ ያለው ነገር ሁሉ ከእነ ችግሩም ቢሆን ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ከማመን ጨምሮ ኢሕአዴግ ከእስር ነፃ አውጥቷቸዋል፡፡ የምሕረት አዋጅ ታውጇል፡፡ ትጥቅ ትግልን እንደ ዋንኛ የትግል ሥልት ሲያራምዱ የነበሩ ተቃዋሚዎች ሸብረክ ብለዋል፡፡ ከኤርትራ የነበረን ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ ሁኔታ ተስፋንና መርህን ወደ ሰነቀ ግንኙነት ተቀይሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች ተዋህደዋል፡፡ የማስተካከያ ዕርምጃዎችንም ወስደዋል፡፡ ቀፍዳጅ የሚባሉትን የሽብርተኝነት፣ የሚዲያና የሲቪል ማኅበራት ሕጎችን ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወሳኝ የሆኑ የኢኮኖሚ ተቋማቷን ወደ ግሉ ሴክተር ለማሸጋገር ተፍ ተፍ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ ድና ጀርባ ሆነው የቆዩት የኢትዮጵያ መንግሥትና ዳያስፖራውም አዲስ ፍቅር ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀብቷን የማስተደደር አቅሟን ከምንጊዜውም በላይ ማሳደግ አለባት፡፡ በተለይም  የሰው ኃይሏን፡፡ በአግባቡ ያልተያዘ የሰው ኃይል ከመደጋገፍ ይልቅ፣ ውስን በሆነ ሌላው ሀብት ላይ መጋጨትን ይመርጣል፡፡ ትምህርትን በጥራት ለማስኬድ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቢሆንም፣ እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ግን በቂ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ሕጎች ሀብቶች ናቸው፡፡ ሕጎች የኅብረተሰብንና የአገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ልጓሞች ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ አካልን ለመጉዳት ወይም እንቅስቃሴውን ለማቀብ ብቻ የሚቀረፁ ከሆነ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በመሆኑም ሕጎች ፖለቲካዊ ሀብት በመሆናቸው ለአገርና ለአገር ጥቅም ብቻ እንዲውሉ ሊቀረፁና ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡

 

ፖለቲካዊ ባህርያችንንና የፖለቲካ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንድንችል የሚያስችለን የሀብት ፖለቲካ ዕውቀት በእጅጉ ጎድሎናል፡፡ ለዚህም የገነባናቸውን ተቋማትንና ሌሎችን በመጨመር ሀብትን ለአገር ግንባታና ለትውልድ ጥቅም ማዋል ይገባናል፡፡ እንደኛ ባሉ ጀማሪ ዴሞክራሲዎች የፖለቲካ ልሂቃን የሚገነቧቸው ተቋማት፣ እነርሱንና በዙሪያቸው ያሉ ቅርቦቻቸውን ብቻ ለመጥቀም የተቀረፁ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን ስለሚችል ቆም ተብሎ ፍተሻ የሚካሄድበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ በየአቅጣጫው እየተፈጠረ ያለውን መቀራረብ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በማደራጀት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ተገቢ ነው፡፡ ተቋማት የፖለቲካ ሀብቶችና የሀብት ፖለቲካ የሚሳለጡባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፣ ተገቢ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችና ሀቀኛ የሰው ሀብት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሰው ሀብታችን የፖለቲካ ሀብቶችንም ሆነ ሌሎች ሀብቶችን የሚዘውበመሆኑ፣ ተገቢውን አመላካከት መያዙንና ተገቢውን የትምህርትና የሥልጠና ዝግጅት ማድረጉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ከዕቅድ ጀምሮ መሳተፍ ሲችልና የልማት ሥራዎችን ጥራት በተደራጀ ሁኔታ ሲከታተል ብቻ ነው፡፡ የበጀት ዕቅድን ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመለጠፍ ብቻ ግልጽነትና ተጠያቂነት አሰፍናለሁ ማለት ቀልድ ብቻ ይሆናል፡፡ በግብርና፣ በመንገድ ሥራ፣ በጤናና መሳሰሉት መሠረታዊ አቅርቦቶች ኅብረተሰቡ ሊያቅዳቸው፣ ሊከታተላቸውና ሊገመግማቸው ይገባል፡፡ በልማት ሒደት ኅብረተሰቡን ማሳተፍ የፖለቲካና ሌሎች ሀብቶችን ጥቅም ላይ የሚያውል የሀብት ፖለቲካ መኖሩን ከመጠቆሙም በላይ፣ ጠንካራ የአገር ግንባታ መሠረት በመጣል ከራሷ አልፋ ለአካባቢውም ጭምር መመኪያ የሆነች አገር ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ዜጐችን ማክበር፣ እንዲከባበሩ ማድረግ፣ በልማት ማሳተፍና የበኩላቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ማድረግ የበሰለ የሀብት ፖለቲካ አራማጅ መንግሥትና ተቋማቱ ባህርይ ሊሆን ይገባል፡፡

ለውዝግብ መንስዔ የሆኑ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችም ገና አልተነኩም፡፡ ዘርን መሠረት ያደረጉ ጭፍን የጥላቻ አመለካከቶች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ በርካታ ጥናቶች የተሠሩባቸው ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ከመደርደሪያ ላይ አልወረዱም፡፡ ያልተግባባንባቸው አንድ ሺሕ አንድ መፍትሔ የሚፈልጉዳዮች አሉ፡፡ መደማመጥ የተሞላበት መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ አገራዊ መግባባት ያስፈልገናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ወጣቱን አሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችልና የአገሪቱን ፖለቲካዊና ሌሎች ሀብቶች በአግባቡ ማስተዳደር የሚችል የሀብት ፖለቲካ ያስፈልገናል፡፡ ቀጣይነት፣ እኩልነትና ደኅንነት የሚረጋገጡት የልማት ዕቅዶቻችንን ለማረጋገጥ በምንከተለው የፖለቲካ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በሚያውል የሀብት ለቲካዊ አስተዳደር ብቻ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡ጸሐፊው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ የጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...