በአሸናፊ ዋቅቶላ (ዶ/ር)
ሰሞኑን ዋና ዋና የዓለም አቀፍ ጤና ተቋማት ከዚካ ቫይረስ በሽታ ወረርሺኝ ጋር በሽሎችና በአዲስ ተወላጆች ውስጥ የሚታየው የጭንቅላት መጠን ማነስን (ማይክሮኬፋሊ)፣ ጉሊያን ባሬ ሲንድሮምንና ሌሎቹን የነርቭ ሥርዓት ችግሮችን ቫይረሱ እንደሚፈጥር አውጀዋል። እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሷቸው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በተለያዩ ዕውቅ ጆርናሎች ውስጥ የታተሙት የምርምር ውጤቶች እንደሆኑ ገልጸዋል። በተጨማሪም የበሽታ ፈጣሪነት መመዘኛ ነጥቦችን ዘርዝረዋል። ስለበሽታው ብዙ የታወቀ ቢሆንም በውል ያልተተነተኑ አያሌ ጉዳዮች እንደሚቀሩ ስምምነት አለ። ይህም ቢሆን አንዳንድ ተመራማሪዎች ከነጭራሹ የዚካ ቫይረስ ለአሳሳቢ ውስብስቦቹ መንስዔነት በዋነኛነት መጠቀሱን እንደ ችኩልነት የሚቆጥሩ አሉ።
የዚካ ቫይረስ በሽታ መገለጫዎች
እስካሁን በተለያዩ ጊዜያት ከተጠቀሱት ዋና ዋና ውስብስቦች ሌላ አደም (አኪዩት ዲሰሚኔትድ ኢንስፋሎ ማየላይቲስ) በሚባል ምኅፃረ ቃል የሚታወቀውና ሰውነት በራሱ ላይ የሚመጣን ጥቃት ለመከላከል አንጎልንና ኅብለ ሰረሰርን (ስፓይናል ኮርድ) በስፋት የሚጎዳበት መቆጣት (ኢንፍላማሽን) ነው። በብራዚል ውስጥ የሚሠሩ የነርቭ ሐኪም (ኒሮሎጂስት) ከዚካ በሽታ ጋር ተያይዞ ሁለት ሰዎች ላይ የዘገቡት ይህ በሽታ በተለይም ኋይት ማተር የተባለውን የአንጎል ክፍል እንደሚያጠቃ አሳይተዋል። የዚህ በሽታ አቀራረብ መልቲፕል ስክሌሮሲስ የተባለ የነርቭ በሽታን እንደሚመስል ተዘግቧል። ስድስት ወራት ድረስ ሊቆዩ የሚችሉ የነርቭ ሥርዓት እክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተጠቅሷል። ጥናቱ ሊቀርብ የታቀደው ቫንኩበር ካናዳ ውስጥ ከአፕሪል 15 እስከ 21 ቀን 2016 በሚደረገው የአሜሪካን አካዴሚ ኦፍ ኒሮሎጂ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ኮለምቢያ ውስጥ በፌብረዋሪ 2015 አራት ሰዎች በዚካ ቫይረስ መዘዝ መሞታቸው በአፕሪል 7 ቀን 2016 በታተመው ዘላንሴት ጆርናል ውስጥ ተዘግቧል። ዕድሜያቸው ሁለት ዓመት፣ 30 ዓመት፣ 61 ዓመትና 72 ዓመት የሚሆናቸው አራቱ ሰዎች ከታዩባቸው የበሽታ መገለጫዎች ውስጥ ትኩሳት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የፕላትሌቶች ቁጥርን መቀነስ፣ ያንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ፣ የነጭ የደም ቁጥር መቀነስ፣ ማንቀጥቀጥ (ሲዠር)፣ የሰውነት ውኃ ማነስ (ዲሐይድሬሽን) ይገኙበታል። ይህም ቢሆን የዚካ ቫይረስ በሽታ እስካሁን ሞት የሚያደርሰው እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ ወይም የኢቦላ ቫይረስ በሽታ ሳይሆን አልፎ አልፎ ብቻ እንደሆነ መታወቅ አለበት።
የበሽታው ስርጭት
በማርች 2016 መጨረሻ ላይ ሁለት የቬትናም ሰዎች እዚያው አገራቸው ውስጥ በቢንቢ የተላለፈ የዚካ ቫይረስ በሽታ ተገኝቶባቸዋል። ይህ እንግዲህ ሠፈራዊ (ሎካል ወይም ኦቶክቶኖተስ) መተላለፍ ነው። ቫይረሱን ማስተላለፍ የሚችሉ የኤዲስ ቢንቢዎች ባሉበት ቦታዎች ሁሉ የዚካ ቫይረስ በሽታ የመከሰት ችሎታ እንዳለው ያስታውሳል። በ1950ዎቹ ውስጥ የተሠሩት የደም ፀረ አካል ምርመራዎች ዩጋንዳንና ሌሎቹን የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጨምሮ ቫይረሱ በሰዎች ውስጥ መቆየቱን እንዳሳዩ ያስታውሷል፡፡ በሽታው በተስፋፋበት የደቡብ አሜሪካ ክልል የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ፓሆ (ፓን አሜሪካን ሔልዝ ኦርጋናይዜሽን) በቅርቡ በድረ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው ከ2015 እስካሁን ድረስ 35 አገሮችና ግዛቶች በቢንቢ አማካይነት የሚሰራጭ ሠፈራዊ ትልልፍ አሳይተዋል። ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የሽሎችና አዲስ ተወላጆች የዚካ ቫይረስ በሽታ 98 በመቶ የተዘገበው በብራዚል ውስጥ ነው።
በመጪው ነሐሴ ወር ብራዚል ውስጥ በሚደረገው የኦሊምፒክና የፓራሊምፒክ ውድድሮች ሳቢያ ብዙ ሰው ወደ ብራዚል እንደሚሄድ ይጠበቃል። በዚያ ወቅት ብራዚል ውስጥ የብርድ ጊዜ ስለሆነ የቢንቢዎች ቁጥርና እንቅስቃሴ በጣም ይቀንሳል ይባላል። ስለሆነም በሽታው የስፖርቱ እንግዶችን በከፍተኛ ደረጃ አያጠቃም የሚሉ አሉ።
የዚካ ቫይረስ በሽታ ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ በኤዲስ ኤጂፕቲ አማካይነት መሆኑ ቢታወቅም የሌሎቹ ቢንቢ ዝርያዎች ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። በተለይ ኤዲስ አልቦፒክተስ የተባለው የቢንቢ ዘር በከፍተኛ ደረጃ ማስተላለፍ ቢችል ወደ ቀዝቃዛ ዓለም ክፍሎች የመተላለፉን አደጋ ይጨምራል ይባላል።
በግብረ ሥጋ ግንኙነት መተላለፍ
በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን አፕሪል 13 ቀን 2014 የታተመው ዘገባ ለዚካ በግብረ ሥጋ መተላለፍ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነበር፡፡ ሕመምተኛ 1 የ24 ዓመት ሴት ሲሆኑ፣ ሕመምተኛ 2 የ46 ዓመት ወንድ ናቸው። ሰውዬው ለሁለት ወራት ብራዚል ቆይተው ወደ ፈረንሣይ ከመሄዳቸው በፊት ለጥቂት ቀናት ሕመም ነበራቸው። ሰውዬው ተሽሏቸው ፈረንሣይ እንደደረሱ ከሕመምተኛ 1 ጋር ተደጋጋሚ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶችን አድርገው ነበር። ሴትዬዋ ከታመሙ በኋላ ሽንትና ምራቃቸው ውስጥ የዚካ ቫይረስ ሲገኝ፣ ደማቸው ውስጥ ዚካ በፒሲር ባይገኝም በዚካ ቫይረስ ምክንያት የተፈጠረ አይጂኤም የተባለ ፀረ አካል (አንቲቦዲ) ታይቷል። የወንዱ ሽንትና የወንድ ዘር ፍሬ ፈሳሽ (ሲመን) ውስጥ ቫይረሱ ሲገኝ በምራቃቸውና በደማቸው ውስጥ ግን አልታየም ነበር። ከሴትዮዋ ምራቅና ከሰውዬው ዘርፍሬ ፈሳሽ ውስጥ የተገኘው ቫይረስ ጂኖሞች ሲተነተኑ እጅግ በጣም ተቀራራቢ ነበሩ፡፡ መቼም በሽታ ስለመጣ ብቻ ሰዎች ፍቅርን፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነትንና እርግዝናን እርግፍ አድርገው ስለማይተዉ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ከፍተኛ የትምህርት ዘመቻ ማድረግ ያስፈልጋል። በፀረ ኤችአይቪና ኤድስ ዘመቻዎች የተገኘው ልምድ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል።
ቅድመ ዝግጅት
በቅርቡ የተደረገ ጥናት የሚያሳየው የአሜሪካ ሕዝብ ስለዚካ ቫይረስ በሽታ ያለው ዕውቀት አነስተኛ መሆኑን ነው። በተጨማሪም በሽታው በክፍተኛ ደረጃ የመሰራጨቱን አደጋ ለመመከት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመመደብ እንዳይቻል የዋሽንግተን ዲሲ ፖለቲካ ማነቆ ሆኖበታል። የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር የዚካ በጀት እስኪፈቀድ ድረስ ለኢቦላ መከላከያና ሕክምና የተመደበውን ገንዘብ መጠቀም እንደተገደደ ገልጿል። ይህ ሁኔታ ባለፉት ዓመታት የነበረውን የፀረ ኤችአይቪና ኤድስ ትግል ያስታውሳል። የኤችአይቪ በዓለም ላይ መስፋፋት ይበልጥ ያጠቃው የጤና ሥርዓቶችንና አጠቃላይ ልማታዊ ዕድገታቸው ዝቅ ባሉ አገሮችና ሕዝቦች ላይ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ከሆነ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ከፍተኛ የዚካ ወረርሽኝን ለመጋተር ብቃት እንደሌላት ሥጋት አለ። መነሳት ያለበት ጥያቄ ሌሎች አገሮችስ ከአሁን ጀምሮ ምን ማድረግ ይገባቸዋል? የሚለው ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡