Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከአክሱም የፈለቀው የሆሣዕና አከባበር

ከአክሱም የፈለቀው የሆሣዕና አከባበር

ቀን:

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና የጁሊያን ቀለንቶንን (ካሌንደር) የሚከተሉ የምሥራቅ ዓለም ኦርቶዶክሳውያን የፋሲካ በዓልን ለማክበር አንድ እሑድ ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ ከርሱ በፊት ዛሬ ሚያዝያ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.  የሆሣዕና በዓልን ያከብራሉ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ምዕራባውያኑ (ካቶሊክና ፕሮቴስታንት) የግሪጎሪያን ቀለንቶን ተከታዮች ፋሲካውን ማክበራቸው ይታወሳል፡፡

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፋሲካን የምታከብረው ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣12 ሰዓት ከሚሆንበትና መጋቢት 25 ቀን ላይ ከሚውለው የፀደይ ዕሪና/ እኩሌ (Spring Equinox) ቀጥሎ፣ ከምትታየው ሙሉ ጨረቃ (የአይሁድ ፋሲካ/ፍሥሕ የሚውልበት) በኋላ በሚመጣው የመጀመሪያ እሑድ ነው፡፡ ዘንድሮ የሚያዝያ ወር ሙሉ ጨረቃ (የጨረቃ ሚያዝያ 14 ማለት ነው) በፀሐይ አቆጣጠር የሚውለው ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ማክሰኞ ሲሆን፣ በድንጋጌው መሠረት ቀጣዩ እሑድ ሚያዝያ 23 ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ፋሲካ (ትንሣኤ) ይውላል፡፡

‹‹የዘንባባ እሑድ››

እንደ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ከፋሲካ በፊት የሚውለው እሑድ የሆሣዕና በዓል ይከበርበታል፡፡ ‹‹የዘንባባ እሑድ›› ይባላል፡፡ በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ እንደያጥቢያቸው ትውፊትና ሥርዓት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ኢየሩሳሌም የገባበትና ሕፃናትን ጨምሮ ኅብረተሰቡ፣ የዘንባባና የወይራ ዝንጣፊ ይዞ በደስታና በዝማሬ፣ ‹‹ሆሣዕና የዳዊት ልጅ›› እያለ ያደረገውን የምስጋና አቀባበሉን በልዩ ልዩ መንገድ ያከብሩታል፡፡

‹‹ሆሣዕና›› የአራማይስጥ (አራማይክ) ቃል ሲሆን፣ ፍችውም ‹‹አድነን›› ማለት ነው፡፡ በዕብራይስጥም በግእዝም ተመሳሳይ ፍቺ አለው፡፡ በዚያ ዘመን አይሁዶች በሮማውያን ቀንበር ውስጥ ወድቀው ነበርና ምድራዊ ንጉሥ መጥቶ ነፃ እንደሚያወጣቸውና እንደሚያድናቸው ይጠብቁ ነበር፡፡ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፣ በዚሁ ቀን እንዲሁ እግዚእ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቶ ሃይማኖት የንግድ ቦታ አይደለም በማለት ቁጣውን ያሳየበትና ነጋዴዎችንና ቀራጮችንም ያባረረበት ነበር፡፡

ቤተመቅደሱ የጸሎት ቤት መሆኑን ያወጀበትና ክብሩንም የገለጸበት ነው፡፡ የሆሣዕና ሥርዓት ዐቢይ ጾም በተጀመረ በስምንተኛው ሳምንት፣ ከትንሣኤ (ፋሲካ) አንድ ሳምንት በፊት የሚከበረው ሆሣዕና ከዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሆሣዕና እሑድ በሁለት ነገሮች ይዘከራል፡፡ አንደኛው በቅዳሴ ጊዜ ‹‹ያለ ሕማምና ያለ ደዌ፣ ያለ ድካምም ለከርሞም ያድርሰን ያድርሳችሁ›› እያሉ ካህናቱ ዘንባባ የሚያድሉበት ሲሆን፣ ሁለተኛው ካህናቱና ምዕመናኑ በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የሚያደርጉት ዑደት ነው፡፡ ‹‹በታወቀችው በዓላችን መለከቱን ንፉ›› እያሉ፣ የስድስተኛው ምእት ዓመቱ ቅዱስ ያሬድ መዝሙር እየተዘመረ በአራቱም ማዕዘናት ዕለቱን በተመለከተ ምንባባት እየተነበቡ ይከበራል፡፡

ከሆሣዕና በኋላ ከትንሣኤ በፊት ያሉት ሰሙነ ሕማማትና ዓርብ ስቅለት በተለይ በጾምና በስግደት የሚከበሩ ናቸው፡፡ በወይራ ቅጠል ጥብጠባ በማሳረጊያው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ከሆሣዕና ሰኞ እስከ ጸሎተ ኀሙስ ያሉት ቀናት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን 5,500 ዓመታት (አምስት ተኩል ቀናት) ‹‹የዓመተ ፍዳ›› መታሰቢያ ሆነው ተሠርተዋል፡፡ እርሱም ‹‹የዓመተ ምሕረት›› አንፃር ነው፡፡

ከአክሱም የፈለቀው አከባበር

 የሆሣዕና በዓል ባህላዊ ገጽታዎች የሚታዩበት ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ምእመናኑ እየተገኙ የዘንባባ ዝንጣፊ ከመያዝ ባሻገር፣ ከአዋቂ እስከ ሕፃን በዘንባባው ቅጠል ለጣታቸው ቀለበት፣ ለእጃቸው እንደ አልቦ፣ ለራሳቸው እንደ አክሊል የሚጠለቅ አድርገው ያዘጋጃሉ፡፡ ምዕመናኑም የመስቀል ምልክት በመሥራት በቤታቸው ይሰቅሉታል፡፡

በዕለቱም ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁነት በማስታወስ በአንዳንድ አድባራት ተመሳሳይ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርዒቱ የተካሄደው ከ110 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የሐያኛው ክፍለዘመን መባቻ፤ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922›› በሚለው የትዝታ ድርሳናቸው እንደጻፉት፣ የሆሣዕና በዓል በአክሱም ሥርዓት ዓይነት ሆኖ እንጦጦ ላይ መከበር የተጀመረው በ1898 ዓ.ም. መጋቢት 30 በሆሣዕና ዕለት ነው፡፡ ከአክሱም የመጡ አንድ መምህር ከበዓሉ ቀን ቀደም ብለው ጀምረው የሥነ ሥርዓቱን አፈጻጸም ለደብሩ ካህናትና ለሕፃናት መዝሙር አስጠንተዋል፡፡

‹‹… እንግዲህ በበዓሉ ቀን በሆሣዕና እንዲህ ሆነ፡፡ አንዲቱን የበቅሎ ግልገል በወርቅ ጥልፍ የተጠለፈ ባለመረሻት (የበቅሎ የማዕርግ ልብስ፣ በልዩ ልዩ ሐሮች ተጠልፎ የተዘጋጀ ወርቀ ዘቦ) ኮርቻ ጫኑባት፡፡ ቀጥሎም ድባብ ደብበውላትና አጅበዋት ከከንቲባ ወልደ ጻድቅ ቤት ወደ ቤተ ክርስቲያን አመጡዋት፡፡ ከንቲባ ወልደ ጻድቅ የሆሣዕናን በዓል ድግስ እንዲደግሱና በቅሎዪቱን ጠብቀው ቀልበው እንዲያኖሩ፣ ግብሩ ይኸው የሆነ 12 ጋሻ መሬት የቀላድ ርስት የተተከሉ የደብሩ ትክለኛ ናቸው፡፡ የበዓሉም ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ሆኖ ተፈጸመ፡፡

‹‹ለሕፃናቱ ከነጭ ሐር የተሰፋ ቀሚስ አጠለቁላቸውና ያቺን ያጠኑዋትን መዝሙር ቄሮስ ሜሮስ እያሉ እየዘመሩ በቅሎይቱን አጅበው ይጓዙ ጀመር፡፡ በቅሎይቱ ከቤተ ክርስቲያን እስክትደርስ ድረስ ‹‹አርእዩነ ፍኖተ ወንሑር ቤቶ›› (መንገዱን አሳዩን፣ ወደቤቱም እንሂድ) የሚለው የያሬድ መዝሙር በየምዕራፉ እየተመራ ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል ይነበብ ነበር፡፡ ቃጭልም ይቃጨል ነበር፡፡ በቅሎይቱ ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ ስትደርስ በስተውጪ ዑደት ተደረገና የበቅሎዋ ጣጣ አልቆ ወደ መኖሪያዋ ተመለሰች፡፡

‹‹ይህ ዓይነት ሥርዓት መፈጸሙም ክርስቶስ በሆሣዕና ዕለት በአህያ ግልገል ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ሽማግሎችና ሕፃናት አጅበውት ነበርና የዚያን ምሳሌ ለመከተል ወይም ለማዘከር ነው፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ የመዘምራኑ ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ቀሳውስትና ዲያቆናት በዐውደ ምሕረቱ (በስተውጭ ያለው የቤተ ክርስቲያኑ አደባባይ) ላይ ከመዘምራኑ በስተኋላ ተሰለፉ፡፡ መዘምራኑ በድርብ (ጨርቁ በእጥፉ ሆኖ የተሰፋ ቀሚስ፣ የሹመት ልብስ) እና በአብደላከኒ ቀሚስ (የመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚለብሱት ዥንጉርጉር የሹመት ቀሚስ) አጊጠውና ተሰልፈው በስተፊት ቆሙ፡፡ የቀሩት ካህናት ግን በዐውደ ምሕረቱ በምንጣፍ ላይ ተቀመጡ፡፡ ቆመው ያሉትም መዘምራን ‹‹ተጽዒኖ ዲበ ዕዋል›› የሚለውን የያሬድን ዜማ በዝማሜ (ከሰውነትና ከመቋሚያ ውዝዋዜ ጋር እየተቀናጀ የሚዜም የአቋቋም የዜማ ስልት) እያቀነቀኑና በዝግታ እርምጃ እየተራመዱ ወደ ተቀመጡት ካህናት መጡ፡፡ በየዜማውም መጨረሻ መቋሚያቸውን ደቅ እያደረጉና እጅ እየነሱ ቀረቡ፡፡ በዐውደ ምሕረቱ በምንጣፍ ላይ የተቀመጡት ካህናት ለመዘምራኑ የዜማ መልስ ይሰጡዋቸው ነበር፡፡

‹‹ከአክሱም የመጣው ያ የሆሣዕና በዓል ሥነ ሥርዓት በዚያ በመጀመሪያው ጊዜ ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ፣ መኳንንትም ሁሉ ባሉበት በዚህ አኳኋን ደምቆ ተከበረ፡፡ ሥነ ሥርዓቱ በሸዋ የመጀመሪያ ጊዜና እንግዳ ነገር ስለሆነ ዕፁብ እየተባለ ተደነቀ፡፡ በኋላ ግን ሌሎቹም የአዲስ አበባ አድባራት ይከተሉት ጀመረ፡፡ ለምሳሌ በአራዳ ጊዮርጊስ ይኸው ሥነ ሥርዓት ገብቶ ይሠራበት ጀመር፡፡››

በዓሉ በዚህ ዘመን

የሆሣዕናን በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ትርዒት በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማክበር ከተጀመረ ከ110 ዓመት ወዲህ የአከባበር ፈለጉን ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መከተል ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳምና የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ይጠቀሳሉ፡፡

በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ሳይቋረጥ በዐውደ ምሕረትና በአደባባይ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ያለበት መንገድ የውጭ አገር ቱሪስቶችንም ሆነ ያገር ቤት ተወላጆችን የሚስብ ሆኗል፡፡ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ሥፍራውን ይዟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...