Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፈጣሪዎችን ማብቃት

ፈጣሪዎችን ማብቃት

ቀን:

ሙሴ በዕውቀቱ የ15 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ወላጅ አባቱ የተለያዩ የቴክኒክ ሥራዎችን በተለይም የፈጠራ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር፡፡ ይህም ሙሴ ለፈጠራ ሥራዎች ቅርብ እንዲሆን፣ የተለያዩ ሙከራዎችንም እንዲያደርግ ዕድል ሰጥቶታል፡፡

የልዩ ልዩ ማሽኖችን ሞዴል መሥራት ያስደስተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የፈጠራ ሥራዎችም አሉት፡፡ በተለይም የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት በተቋቋመው አይከን ኢትዮጵያ ወርክሾፕ መማር ከጀመረ በኋላ የተሻሉ ነገሮችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ የመፍጠር ክህሎቱ ከፍላጐት በዘለለ አደባባይ ላይ እንዲወጣና እንዲሸለም በር ከፍቷል፡፡

ከዓመታት በፊት በአንድ በሮቦቲክስ ፈጠራ ውድድር ላይ ተሳትፎ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በወቅቱ በተወዳደረበት የፈጠራ ሥራ፣ ክሬን የመጀመሪያውን ዙር ውድድር አሸንፎ ወደ ሁለተኛው ዙር ተሸጋገረ፡፡ በሁለተኛው ዙርም እግር ኳስ የሚጫወት ሮቦት ሠራ፡፡ በዚህም ከ2,000 ተማሪዎች መካከል አንደኛ በመውጣት ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቀቀ፡፡ ከዚያም ህንድ አገር በመሄድ ከስምንት አገሮች ከተውጣጡ ታዳጊዎች ጋር ተወዳድሮ ዳግም ለማሸነፍ በቃ፡፡

በውድድሩ አሸናፊ የነበሩት እሱና ሌሎች አምስት ኢትዮጵያውያን ጓደኞቹ አሜሪካ አገር ሄደው ዓለም አቀፉን የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳን የመጐብኘት ዕድል አገኙ፡፡ ‹‹የጐበኘነው የኬኔዲ ስፔስ ሴንተር የሚባለውን የናሳ ክፍል ነበር፡፡ ናሳ ሲባል በዓይነ ህሊናዬ የምስለው መጠነኛ ቦታ ላይ ያረፈ የምርምር ተቋም ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ግዙፍ ሆኖ ነበር ያገኘሁት፡፡ ከተለያዩ አስትሮኖውቶች ጋር ምሳ መብላት ችለናል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንድንወያይ ዕድሉ ተሰጥቶናል፡፡ ይህም የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎችን እንድሠራ ሞራል ሆኖኛል፤›› ይላል፡፡

በቅርቡ በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት ውስጥ በሚካሄደው የሮቦቲክ ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድሉን አግኝቷል፡፡ ውድድሩን ያዘጋጀው ቬክስ ሮቦቲክስ ተወዳዳሪዎች ኳስ የሚጫወቱ ሮቦቶችን እንዲያዘጋጁ፣ የተሻለ የሚጫወትና ጐል ማስቆጠር የሚችል ሮቦትም እንደሚሸለም አስታውቋል፡፡ ሙሴም የተሻሉ ቴክኒኮችን ተጠቅሞ ሌሎቹን ሮቦቶች ይረታልኛል ብሎ ያሰበውን ሮቦት አዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ውድድር ላይ መሳተፉም እንደሚጠቅመው ያምናል፡፡

ሙሴንና ሌሎች ተመሳሳይ ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊዎች ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና የሚታይ ነገር እንዲሠሩ የሚያግዛቸው አይከን ኢትዮጵያ የተባለው ድርጅት ነው፡፡ ተቋሙ እንደ ሙሴ ያሉ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች መጠነኛ ገንዘብ ከፍለው የበለጠ መሥራት እንዲችሉ፣ በወርክሾፑ አስፈላጊውን ቁሳቁሶች እንዲሁም መምህራን፣ በዚህም ጥቂት ለማይባሉ ታዳጊዎች ክህሎታቸው እንዲዳብር፣ ልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩም የማይናቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሚዛን ተፈሪ አካባቢ የመጣው ሔኖክ ወንድሙ በድርጅቱ ከሚማሩት መካከል ነው፡፡ የ22 ዓመቱ ሔኖክ በሚዛን ተፈሪ ቲቪቲ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበር፡፡ ገና ሕፃን ሳለ ነበር ነገሮችን መፈታታትና መገጣጠም የጀመረው፡፡ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ስድስት እግር ያላት ስፓይደር ሮቦት የተሰኘች የተለያዩ መሰናክሎችን ማለፍ የምትችል በሪሞት የምትሠራ ሮቦት ሠርቷል፡፡ ከዚያ በኋላም ጥቂት የማይባሉ ፈጠራዎች ሠርቷል፡፡ ለዚህም የሥዕል ችሎታው ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ‹‹ማንኛውንም ነገር እሥል ነበር፡፡ ይህም ነገሮችን ዲዛይን ወደ ማድረግና በቅርጽ ወደ ማስቀመጡ እንዳዘነብል አደረገኝ፤›› ሲል የነበረው የሥዕል ዕውቀት ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ መሠረት እንደሆነው ይናገራል፡፡

እንደ ሰው በሁለት እግር የሚራመዱ፣ አራት እግር ያላቸው፣ መብረር የሚችሉና ሌሎችም ባህሪ ያላቸው ሮቦቶችን ሠርቷል፡፡ ነገር ግን የሚያስፈልገውን ግብአት ለማግኘት ብዙ ይቸገር ነበር፡፡ ‹‹በእኛ አካባቢ ለፈጠራ ሥራዎች የሚሆኑ ግብአቶችን ማግኘት በጣም ችግር ነው፡፡ አብዛኞቹን ለመሥራት ከኤሌክትሮኒክስ ቤቶች የሚወጡ አንዳንድ ዕቃዎችን እጠቀም ነበር፡፡ ነገር ግን በቂ ባለመሆኑ ሌላ አዲስ ሮቦት ለመሥራት ስል የሠራሁትን አፍርሼ ዕቃውን ለመጠቀም እገደዳለሁ፤›› ሲል በዚህ መልኩ ችግሮቹን ለመቅረፍ ቢሞክርም አንዳንድ እንደ ሴንሰር ያሉ ዕቃዎችን ለማግኘት ፈታኝ እንደሆነ በዚህም አንዳንድ ሥራዎቹ ሳይጠናቀቁ ይቀሩ እንደነበር ይናገራል፡፡

አይከን ኢትዮጵያ ያወጣውን የትምህርት ዕድል ማስታወቂያ እንደ ሰማ ነበር የተመዘገበው፡፡ ጥሩ ችሎታ ስለነበረውም ዕድሉን ለማግኘት ብዙ አልተቸገረም፡፡ ወዲያው ነበር የተቀበሉት፡፡ አሁን ተቋሙን ከተቀላቀለ መንፈቅ ሆኖታል፡፡ ከመደበኛ ትምህርቱ ጐን ለጐን ቅዳሜና እሑድ በወርክሾፑ ይማራል፡፡ ግብአት ለማግኘት ይገጥመው የነበረው ችግር አሁን በመጠኑም ቢሆን ተቀርፏል፡፡ ሙሴ በሚሳተፍበት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሔኖክም ይሳተፋል፡፡

ሌላዋ በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሰብለወንጌል ብርቁ ነች፡፡ 17 ዓመቷ ሲሆን በትምህርቷ ከጠንካራ ተማሪዎች ተርታ ትሠለፋለች፡፡ አይከን ኢትዮጵያ ከመግባቷ በፊት ሮቦትም ሆነ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎች ሠርታ አታውቅም፡፡ ይሁን እንጂ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የማታውቀው እንደሌለ ትናገራለች፡፡ ቤት ውስጥም የተለያዩ ቴክኒካል ሥራዎችን መሥራት ያስደስታታል፡፡ ‹‹ቤት ውስጥ ላፕቶፖች ሲበላሹ እሠራለሁ፡፡ ቧንቧም ሲበላሽ እጠግናለሁ ሌሎችም ነገሮች ሲበላሹ ማስተካክለው እኔ ነኝ፤›› ስትል በቴክኒካል ሥራዎች ረገድ ችግሮችን በራሷ የመፍታት ልምዱ እንዳላት ትናገራለች፡፡

አይከንን መቀላቀሏ በኋላ በጽንሰ ሐሳብ የምታውቀውን በተግባር እንድትሠራ እንደረዳት፣ በጥቂት ወራት ውስጥ የተለያዩ ሮቦቶችንና ማሽኖችን መሥራት መቻሏን ትናገራለች፡፡ በአሜሪካ በተዘጋጀው ሮቦቲክስ ውድድር ላይም ትሳተፋለች፡፡

በፕሪስቲጂየስ ዩዝ አካዳሚ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የ18 ዓመቱ ሳሙኤል መርጋም ተመሳሳይ ዝንባሌ አለው፡፡ ዘወትር ቅዳሜና እሑድ ከወርክሾፑ አይጠፋም፡፡ የተለያዩ እንደ ወኪንግ ሮቦት፣ ሄሊኮፕተር፣ ሮቦቲክ አርምና ሌሎችም ዓይነት ሮቦቶች ሠርቷል፡፡ ከሥሩ ተሽከርካሪ ተገጥሞለት አንድን ዕቃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርስ ሮቦቲክ አርም የተሰኘ ሮቦትም ሠርቷል፡፡

በተጨማሪም በወታደራዊው ዘርፍ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጐ የተሠራ ስኔክ ሮቦትም (እባብ ሮቦት) ሠርቷል፡፡ ሮቦቱ ሚኒካሜራዎች ተገጥመውለት በፕሮግራሚንግ ክትትል እየተደረገበት ነገሮችን የመሰለል ባህሪ አለው፡፡ ከሌሎች መሰል ሮቦቶች የሚለየውም ሮቦቱ በቀላሉ ቀለሙን በመቀያር ያለበትን አካባቢ የመምሰል ባህሪ በመላበሱ፣ በቀላሉ በተቃራኒ ቡድኖች ዕይታ ሊገባ ባለመቻሉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሮቦቱ አገልግሎት ለመስጠት ገና ብቁ አይደለም፡፡ የሚቀረውን ፕሮግራሚንግ እውን ለማድረግም ከፍተኛ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ሳሙኤል ይናገራል፡፡

ለሮቦቲክ ሥራ ልዩ ፍቅር ያለው ሳሙኤል ሙያውን አሳድጎ ለስኬት ለመብቃት የበኩሉን እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹የራሴን ቡድን መሥርቻለሁ፡፡ አባላቱንም እያስተማርኳቸው እገኛለሁ፡፡ መሠረታዊ የሮቦት አሠራር ዕውቀት የሚያስጨብጥ መጽሐፍም እየጻፍኩ ነው፤›› ይላል፡፡   

‹‹አሁን ላይ በርካታ አገሮች ተማሪዎችን በጽንሰ ሐሳብ ከማስተማር ይልቅ ተግባር ላይ አተኩረዋል፡፡ ይህም ተማሪዎቹን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል፤›› የሚሉት የአይከን ኢትዮጵያ መሥራች አቶ ሰናይ መኰንን ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ተማሪዎች ጽንሰ ሐሳብን በተግባር እንዲማሩ ማድረግ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ተቋሙም በሒሳብ፣ በኢንጅነሪንግና በሌሎች የሳይንስ ዘርፎች 50 የሚሆኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ አስፈላጊውን ግብአት እያቀረበ ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲማሩ ያደርጋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጠውም እንደ ደጋፊ ትምህርት ቅዳሜና እሑድ ሲሆን ተማሪዎቹን ለማበረታታት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የሳምንቱና የወሩ ምርጥ ተማሪ በሚል ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዓመታዊ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ሲያሸንፉም አሜሪካ ሄደው ዓለም አቀፉን የጠፈር ምርምር ተቋም እንዲጐበኙ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡

አቶ ሰናይ እንደሚሉት፣ የተቋሙ ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ አራተኛ ጊዜያቸው ነው፡፡ በዚህኛው ውድድር ከ25 አገሮች የተውጣጡ ከ20,000 የሚበልጡ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ በውድድሩም የተሻለ መጫወትና ጐል ማስቆጠር የቻለውን ሮቦት የሠራ ተሸላሚ ይሆናል፡፡

በዚህኛው ዙር ለተጠየቁት ሥራ ወርክሾፑ በቂ ግብአቶችን ማቅረብ ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች የተሻሉ ሥራዎችን ለማቅረብ የአቅም ውስንነት እንደሚይዘው፣ በተጨማሪም ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን ‹‹ዕቃዎችን በገፍ ማስገባት እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ግብአቶች ተደራሽ ቢሆኑ ልጆቹ የበለጠ እንዲሠሩ ይረዳቸዋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአቅም ውስንነት ምክንያት ጥቂት ተማሪዎችን ለመቀበል እንደሚገደዱም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...