Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውስጣችን ሲጨመቅ ውጪያችን እንዳይደርቅ!

ሰላም! ሰላም! አቤት እነ አዶርኖ ያላዩት ጉድ። መዓት ካልወረደብን ቤትሆቨንንና ሞዛርትን የማናዳምጥ ሰዎች ሆነናል ለካ? “ወይ አለማወቅ!” አሉ ባሻዬ። ሰው ሲሞት ቤተሰብ ሲያዝን ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ቢያንስ አርባው እስኪወጣ አይከፈትም። ይኼው ዛሬ አገር ሲያዝን አንቺ ባለጋሜ ልበሽ ካባሽን … እናዳምጣለን። ዋናው ‘ኢንስትሩመታል’ ሙዚቃ መሆኑ ነዋ አሉኝ። “አስደመጡን እንዴ?” ስላቸው ‘በክላሲካል ስም አንቺ ሆዬ ለእኔው ለጉድ አልበር እንዴ?’ ብለው አፈጠጡብኝ። መፋጠጡም እንደሌላው ነገራችን የይስሙላ ባይሆን አልቆልኝ ነበር። ለነገሩ ያለነው የፈረደባት አፍሪካ ውስጥ ነው። እኛ ላይ ይፈረድ ምድሪቷ ላይ ገና እያጣራን ስለሆነ ለጊዜው የምንለው የለንም። ብቻ አንዳንዴ ሲደላን ከሰሐራ በታች መኖራችንን እንረሳውና ቀን ቆጥሮ እንደ ሰሞኑ የአስታጣቂና የታጣቂ ፖለቲካ ሲያሳዝነን በክላሲካል ሙዚቃ ደረት እንደቃለን።

አንዱ ወዳጄ እኮ ነው፣ “የኮንጎ ብትሆን ወይ ከብሩንዲ አሊያም ከኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ እስከሆንክ ድረስ ያልታሰበ ድንገተኛ አደጋ ያለ ነው፤” ብሎ ገረመኝ። ‹‹በፓሪስ፣ በብራስልስ፣ በኢስታንቡል የተጠቁትን ምን ልትላቸው ነው?” እለዋለሁ “እሱን እነሱ ያመጡት እነሱ የሚያሮጡት የሽብር ተረት ስለሆነ ሆድ ይፍጀው። ብቻ ፖለቲካ አስቀያሚ ጨዋታ ነው፤” ብሎ አድበሰበሰው። ድሮስ ማድበስበስ እንጂ ማጥራት አንችል። “ካሮት! ካሮት!” እያለ አንዱ በሠፈራችን ባለፈው ሰሞን ቢጮህ፣ ‹ሱፍ  ሽንኩርትና መወልወያ እያሉልህ እንዴት ካሮት ካሮት አልክ ተብሎ ጀርባው ይጠና ተባለ። ይኼን ከወዲኛው ምን ያገናኘዋል ካላችሁኝ መልስ የሚኖረኝ አይመስለኝም፡፡ አንዳንዴ እኮ የሚያስፈልገን መነሻውም መድረሻውም አይታወቅማ፡፡ ህማማት ነው ብዬ እንጂ በመጪው ሳምንት ብዙ የማናግራችሁ ነበረኝ። ፋሲካ ከደረሰብን አይቀር አንድያውን ሥጋን እያሰብን ሥጋ መዘልዘል አይሻልም? ምረጡ እናንተ።  

በፆሙ በሥጋ ቴክኒክ ጨዋታዬን ልቀጥል ስለሆነ ይፍታህ በሉኝ እንግዲህ። መቼ ዕለት አንድ ሎቤድ እየደለልኩ ደንበኛዬ ወደ አገልግሎት መስጫ ክልል እስኪመለሱ፣ የሰርክ መሰባሰቢያችን ወደሆነችው ካፌ አመራሁ። ሦስት ሰዎች ጠረጴዛ ከበው የቀለጠ ክርክር ይዘዋል። በነገራችን ላይ በፆም ወቅት መከራከር በራሱ ከመፈሰክ አይተናነስም፡፡ ካላመናችሁ ባሻዬን ጠይቁ። አንደኛው ተከራካሪ፣ “እኔ አሁን መታወቂያዬ ላይ ብሔሬ ተጻፈ አልተጻፈ ምን ይሠራልኛል?” ይላል። አላረጀም እንዴ ይኼ ጭቅጭቅ እያልኩ ማዳመጤን ቀጠልኩ። አንዳንዱ ነገር ያስረጃል እንጂ መቼ ያረጅና? “በብዝኃነት ላይ ለተመሠረተ አንድነት መሠረት ያለው አሠራር ነው፤” ይላል ተጋጣሚው። “በነገራችን ላይ” ብሎ ሦስተኛው ጣልቃ ይገባል። “እንኳን ደስ ያላችሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ ከመቶ ወደ አራት መቶ ዓመት ታሪክ ከፍ ብሏል። እንኳን ደስ ያለን፤” አለ። “እሱን ሄደህ ሐበሻና ሐበሻነትን መነገጃ ላደረጉት ንገራቸው፤” ብሎ የመጀመርያው ቱግ አለ።

ይኼኔ በባሻዬ ዕድሜ ክልል የሚሆኑ አዛውንት ሰምተው፣  “እናንተ ልጆች ኧረ ባካችሁ ዓይናችሁን ግለጡ ተው! ተው! የሰው ልጅ እኮ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አይኖርም። ምናልባት ከትናንቱ ይማራል። እሱንም ጥሩ ተማሪ ከሆነ ነው። ካለፈው መማር ካልቻለ ከራሱ ታሪክ እየተማረ ይሄዳል። ይህቺ አገር አታሳዝናችሁም? ልጆቻችሁን አታስቡም? መጀመርያ እስኪ የካፒታል ክምችታችንን በሚገባ  አገባደን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንሸጋገር። ከዓለም የንግድ ማኅበረሰብ ጋር መሽቀዳደም እንቻል። ከዚያ እኮ ጉሮሯችንን እያራስን ሆዳችን ሳይጮህ ቁጭ ብለን መነጋገር እንችላለን። ዛሬም እኮ ለነገ ታሪክ ነው፤” ቢሏቸው፣ “አንዳች የሚያህሉ አዛውንት አባል የሆኑት ቆይ ለየትኛው ዕድሜያቸው ብለው ነው?” ብለው ሦስቱም ሲንሾካሾኩ ሰማሁ። እኔ ምለው ሀቅም በካድሬነት ተመለመለች እንዴ? መቼ?

‘ወዬው እኔና እኔ’ ያለው ማን ነበር እባካችሁ? በምን አመጣኸው ብትሉኝ ያ ደንበኛዬ ወደ አገልግሎት መስጫ ክልል ተመልሶ ከደወለልኝ በኋላ በሆነው ነው። መቼም ዘንድሮ በቀላሉ መገልገልም ማገልገልም አስቸጋሪ ሆኗል። ክልሉ ውስጥ መገኘትማ ለታደለው ካልሆነ እንዲሁ ባለሲም ካርድ ስለተሆነ ብቻ አይሠራም። የባሻዬ ልጅ ይህን አገላለጽ ሰምቶ ወደደውና “ትንሽ ማሻሻያ ላደርግበት ፍቀድልኝ፤” አለኝ። መብትህ ነው ስለው ‘ባለሲም ካርድ ስለተሆነ ብቻ’ የምትለዋን ‘ባለመታወቂያ ስለተሆነ ብቻ’ ብሎ ቀየራት። በገዛ እጄ መብቱን ሰጥቼ የተበላሁት ራሴው። ለነገሩ የሰማው ሰው የለም። ቢኖርም መንግሥታችን በአገልጋይና በተገልጋይ ጦስ የጠፋ ስሙን ለማደስ ቆርጦ የተነሳበት ጊዜ ስለመሰለኝ አባባሉ አያስከፋም። ‘ብለን ተስፋ እናደርጋለን’ ብላችሁ የማሻሻልና የመጨመር እንዲሁም የማሸሞር መብት አላችሁ፡፡

ለባሻዬ ልጅ የሰጠሁትን መብት ለእናንተ ከነፈኩትማ እውነትም አገሩ በወገንተኝነት ተይዟል። እዚህ ጋ ማሳሰቢያ አለ፡፡ ከላይ በተናገርኩት ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያሉትን የመጨረሻ ስድስት ቃላት ለይቶ ማንበብ አይቻልም። ኋላ የለሁበትም ዋ! “የለንበትም እያልን ስንቱን ጎተራ አዘረፍነው፤” አለኝ ደንበኛዬ ገና መኪናው ላይ ከመሳፈሬ። “ማናችሁ እናንተ የሌላችሁበት? ከምኑ ነው የሌላችሁበት?” አልኩት። እኔ ድፍንፍን ያለ ነገር አልወድ። “ሁላችንም፤” አለኝ ኮስተር ብሎ። “እኔም አለሁበት?”  ብዬ ዓይኔ ሲፈጥ፣ “አንተም! እኔም! እሷም! እሱም! (አላፊ አግዳሚውን እየጠቆመ) ያለችሎታ፣ ያለሙያ፣ ያለሥነ ምግባርና ዕውቀት ለሚሠራው ዕድሉን አሳልፈን ሰጥተን ዛሬ ግቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ ሆነ። እኔም፣ አንተም፣ እሷም፣ እሱም የለንበትም አያገባንም ብለን፤” ሲለኝ ስለቢሮክራሲና ጣሩ እንደሚያወራ ገባኝ።  አይመስለንም እንጂ ለካ ያዋጣነው ለህዳሴው ግድብ ብቻ አይደለም!

እንዳልኳችሁ ገዥና ሻጭን አስማምቼ ሳበቃ ደንበኛዬ ባገኘሁለት ሁነኛ ንብረት ተደስቶ ሊጋብዘኝ ቦሌ አካባቢ ወሰደኝ። መቼም ኋላ እንደታዘብኩት ወዳጁ ብዙ ነው። ያንንም ሰላም ሲል ለአንዱ ሲነሳ ለአንዱ ሲቀመጥ ይኼ አሁን የሰው ፍቅር ነው የአየር መበከል ነው ብዬ አሰብኩ። ሁለት ምግብ ለየብቻ አዘዝን። ከፋይ እሱ እንደሆነ ስለነገረኝ ወግ ይድረሰኝ ብዬ መነሻ፣ ሀተታና መደምደሚያ እንደሚባለው ሦስት ምግብ አዘዝኩ። ቦሌ ደስ የሚለኝ ለአውሮፓ ቅርብ ለኢትዮጵያችን የቅርብ ሩቅ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ሩቅም ቅርብም ሳይሆኑ ጠላት ማሳፈሪያ ወዳጅ ማኩሪያ ሠፈር በመሆኑ ጭምር ነው። ለምሳሌ በሰላጣ ጀምሬ ስሙን የማላስታውሰው የጣሊያን ምግብ በልቼ ለመደምደሚያ ዓሳ አክዬበት ግማሽ ብርጭቆ ወይን ስጠጣ፣ የሚያየኝ ጠላቴን አስቡት ምን እንደሚያስብ። የዛሬ ጊዜ ጠላት በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው ካየዎ የሚያስበው የታወቀ ነው። ወይ ‘ጥገኛ ባለሀብት’ ወይም ‘ኪራይ ሰብሳቢ’ ቢልዎት ነው። ሁለቱም አንድ መሰለኝ።

‘ኤኒ ዌይ’ . . . ውይ ውይ  በጣም ይቅርታ። ቦሌ በቀን ሦስት ጊዜ  መብላት ያቃተው ወገኔ እያለ፣ አንድ ውድ የአውሮፓ ሬስቶራንት ውስጥ ሦስት ምግብ አዝዤ በአንዴ ስበላ የዳያስፖራ ስሜት ተሰምቶኝ እንግሊዝኛ ቀላቀልኩ። አልነገርኳችሁም  ታዲያ ስለቦሌ የቅርብ ሩቅነት? ሆዴ ተቆዝሮ ደንበኛዬን አመስግኜ ደግሞ ለትኩስ ነገር የት እንሂድ ስንባባል አንድ ለማኝ መጥቶ ተነጠፈልኝ።  እንደ እኔው ሠፈር ለማኝ መስሎኝ አሥር ሳንቲም ብሰጠው አነጣትሮ በዓይኔ ትይዩ ወረወራት። ደንግጨ ሳየው “አዝለሃት ዙር” ብሎኝ ወደሚቀጥለው ተለማኝ ሄዶ በትህትና አጎነበሰ። ንዴቴን ተቆጣጥሬ አሥር ሳንቲሜን ከወደቀችበት ቦታ ስፈልግ ነው ከእኔ ይልቅ የቦሌና የአካባቢው ለማኝ ስለገንዘብ የመግዛት ዋጋ ማሽቆልቆል በቂ ግንዛቤ እንዳለው የገባኝ። አሁን አሥር ሳንቲም ምኗ ይታዘላል በፈጠራችሁ?!

በሉ እንሰነባበት። የድለላ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ቤቴ ትዝ ሲለኝ ለማንጠግቦሽ ‘እራት ስለምዘል አስቤዛ ቆጥቢ’ ብዬ የጽሑፍ መልዕክት ላኩኝ። ቤት ስገባ ሦስት ሰዎች የሚያጠግብ ማዕድ ተዘርግቷል። ማንጠግቦሽ አቀራርባው ሳትከድነው ‘ዛራና ቻንድራ’ የሚል የህንድ ፊልም በአማርኛ ትከታተላለች። “እራት አልበላም ብዬ እኮ መልዕክት ልኬሽን ነበር፤” ስላት ዓይኗን ከቴሌቭዥኑ ላይ ሳትነቅል፣ “አንተ መሆንህን በምን ልወቅ? ቴሌ አርባ ጊዜ መልዕክት ይልካል። በጽሑፍና በቃል መነጋገርም መግባባትም የቻለው ጥቂቱ ብቻ ነው አንበርብር። ቆይ ፊልሙ ይለቅና ግድ የለም ትንሽ ታባላኛለህ፤” አለችኝ። የህንድ ፊልምና የአገራችን የታሪክ ንትርክ ደግሞ ማለቂያ ያለው አይመስልም። እንቅልፍ እንቅልፍ ሲለኝ፣ “ኧረ በፈጠረሽ ተነሽና ብይ ምግቡ ቀዘቀዘ። ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ፊልም አፍቃሪ የሆንሽው?” ስላት፣ “ይልቅ አንተም ያጠራቀምከውን አውጣና አንድ የቲቪ ቻናል ክፈት። ያን ጊዜ ወጡም አይቀዘቅዝም እንጀራውም አይደርቅም፤” አትለኝ መሰላችሁ? “እንዴት? እንዴት?” ስላት፣ “አይዞህ ዘመኑ የቅጂ ስለሆነ አሁን የተናገርኩትን መርካቶ ሄደህ ብትፈልገው አታጣውም፤” ብላ ጨመረችልኝ። የህንዱ ሲያልቅ የቱርኩ ጀመረ። ቢቸግረኝ ተነስቼ የተከፋፈተውን ሽሮ፣ ፎሶልያና ቆስጣ ከደንኩ። በነጋታው የማንጠግቦሽን ፊልም አፍቃሪነት አንስቼ ከባሻዬ ልጅ ጋር ስንጫወት፣ “አይዞህ ገና ሁላችንም ቁጭ እንላለን፤” አለ። “ምን ማለት ነው?” ስለው “ሠራተኛና ምርታማ ዜጋ ከመሆናችን ቀድሞ መዝናኛና ማዋዣ ፕሮግራሞች፣ በሰፊው አማራጭ እያሰፉ ከሄዱ ከመቀመጥ በቀር ምን ትጠበቃለህ?” ብሎ አፈጠጠብኝ። እኔም ወደ እናንተ ላፍጣ። ሚዛን ካልሠራን ተቀምጠን መቅረታችን ነው ጎበዝ። ይዘትና ጊዜ እየመረጥን ሠርተን ብንዝናና ምን ይመስላችኋል? ልንበላ ያሞቅነውን እያቀዘቀዝን በኢኮኖሚ ዕድገቷና በሀብቷ ሞዴል ስናደርጋት ህንድስ ምን ትለናለች? እስከ መቼ በቁጭ በሉ ተቀምጠን ኋላ እንቅር? ‘ሳሩን ስናይ ገደሉን ሳናይ’ እንዳይሆን ኋላ። ውስጣችን ሲጨመቅ ውጪያችን እንዳይደርቅ! መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት