Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተራርቆ ፍቅር

ተራርቆ ፍቅር

ቀን:

የቅርብ ጓደኛው ሠርግ ላይ ነው፡፡ ኃይሎጋው ሽቦ እየተባለ ይጨፈራል፡፡ በጭፈራው መሀከል ከተዋወቃት ሴት ጋር ጨዋታ ጀመረና ተግባቡ፡፡ ከዚያም ስልክ ተለዋውጠው ተለያዩ፡፡ በትልቅ ሠርግ ትንንሽ ሠርጎች ይፈጠራሉ እንዲሉ ከወራት በኋላ ግንኙነታቸው ጠንክሮ እነሱም ተሞሸሩ፡፡ ለዓመታት ፍቅራቸው እንደሞቀ ዘለቀ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ የትምህርት ዕድል አግኝቶ አብረው ተጓዙ፡፡ ትምህርቱን እየተከታተለ ባለቤቱ ወለደች፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ትምህርቱ ላይ ሲያጠፋ እሷ ከልጃቸው ጋር ታሳልፍ ጀመር፡፡ ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ሐሳብ ቢያቀርብም ባለቤቱ አልተስማማችም፡፡ እዛው አገር ቆይታ መሥራት እንደምትፈልግ አሳወቀች፡፡ ሕይወታቸውን መምራት የሚፈልጉበት መንገድ መለያየቱ ጫና ቢያሳድርባቸውም ትዳራቸው ሳይፈርስ መቀጠል የሚችሉበት መንገድ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር እንደሆነ ተስማሙና እሱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡

የመጀመርያዎቹ ጥቂት ወራት ቀላል ነበሩ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የሰዓት ልዩነትና የሥራ ውጥረት ችግር አልሆነባቸውም፡፡ ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ዘወትር ያወራሉ፤ ይጻጻፋሉ፡፡ ከስልካቸው አይርቁም፡፡ ፎቶ ይላላካሉ፡፡ ቪዲዮ ቻት ያደርጋሉ፡፡ ጊዜው ሲገፋ ግን ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፡፡ እስከ መቼ ተነጣጥለን እንኖራለን? አኗኗራችን ለልጃችን ምቹ ነውን? የሚሉና ሌሎችም ጉዳዮች ይረብሿቸዋል፡፡ ሲለያዩ ያልተነጋገሩባቸው እነዚህ ጉዳዮች ትዳራቸውን ይበጠብጡ ጀመር፡፡ ሁለቱም በያሉበት አገር ለመኖር መወሰናቸው ደግሞ ፀባቸውን አባባሰው፡፡ ሳይደዋወሉና ሳይጻጻፉ መዋልና ማደር ለመዱት፡፡ ትዳራቸው መፍረሱ ወይም መቀጠሉ ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ሳለ ሚስትየዋ ያልጠበቀችውን ዜና ሰማች፡፡ ለካስ ባለቤቷ ከሌላ ሴት ጋር ፍቅር ጀምሯል፡፡ የዓመታት ትዳር እንዲህ በቀላሉ ይበተናል ብላ ለማመን የተቸገረችው ሚስት ነገሮችን ለመለወጥ አሁን እየተጣጣረች ቢሆንም ባለቤቷ ግን ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡

በሥራ፣ በትምህርት ወይም በሌላ ምክንያት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተራርቆ መቆየት የማንኛውም ጥንዶች እውነታ ሊሆን ይችላል፡፡ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች በአጠቃላይ የነዚህ ጥንዶች ዕጣ ፈንታ ባይገጥማቸውም ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ብዙዎች የሩቅ ፍቅር ፈታኝ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ መነፋፈቅ፣ ስለቀጣይ ሕይወት አቅጣጫ እርግጠኛ አለመሆን፣ አለመተማመንና የትስስር መላላት የግንኙነቱን መሠረት የሚሸረሽሩ ናቸው፡፡ የፍቅር አጋራቸው ርቆ የሚሄድበት አጋጣሚ ሲፈጠር የሩቅ ለሩቅ ፍቅርን በመፍራት አስቀድመው ግንኙነቱን የሚያቋርጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ፍቅራቸው በርቀት እንዳይከስም የሚጣጣሩት ይጠቀሳሉ፡፡ ነገሮች መልካም ሆነውላቸው ወደነበራቸው ግንኙነት የሚመለሱ ጥንዶች እንዳሉ ሁሉ ርቀት ፍቅራቸውን ያሳጣቸውም ገጥመውናል፡፡

በርግጥ ቴክኖሎጂ ምሥጋና ይግባውና ጥንዶች የሚገናኙባቸው መንገዶች መበራከት ነገሮችን ያቀለለ ይመስላል፡፡ ስልክ፣ ፌስቡክ፣ ስካይፕ፣ ቫይበር፣ ዋትስአፕና  አይኤምኦ ርቀትን በመጠኑም ቢሆን ያጠባሉ ማለት ይችላል፡፡ ጥያቄው የድምፅ፣ ጽሑፍና ምስል መገናኛዎች ምን ያህል ያዘልቃሉ የሚለው ነው፡፡ አካላዊ ቅርርብ በፍቅር ግንኙነት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለ ሩቅ ለሩቅ ፍቅር ሲነሳ ጥንዶች በርቀት ሳቢያ ግንኙነታቸው ላይ ስለሚጋረጡ ችግሮች አስቀድመው ይነጋገራሉ ወይ? የሚለው ጥያቄም ይሰነዘራል፡፡ ከምን ያህል ጊዜ በኋላ እንገናኛለን? አንዳችን በሌላችን ሕይወት ያለን ቦታ ምን ይመስላል? ለሚሉት ጥያቄዎች በግልጽ መልስ መስጠት ስለ ቀጣይ ሕይወታቸው እንዲያውቁ ሊረዱ ይችላሉ፡፡ የጥያቄዎቹ መመለስ ብቻ ግንኙነታቸውን ጤናማ ባያደርግም በርቀት ምክንያት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

አንዳንድ ጥንዶች ተራርቆ አለመለያየትን የፍቅራቸው ጥንካሬና የመተማመናቸው መጠን መለኪያ አድርገው ይወስዱታል፡፡ የፍቅር አጋራቸውን ለዓመታት መጠበቅ ሲኖርባቸው ሰዋዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩ አይታጡም፡፡ ይህም ቢሆን ግን ተነጋግረው ከሌሎች ሰዎች የነበሩ ቢሆንም ሲገናኙ ወደ ፍቅር ግንኙነታቸው  የሚመለሱም ቁጥር የዚያኑ ያህል ነው፡፡

ከተሞክሯቸው ተነስተው የሩቅ ለሩቅ ፍቅር የጥንዶችን ባህሪ እንደሚለውጥ የነገሩን ሰዎች ነበሩ፡፡ ‹‹የሚወዱትን ሰው በአካል አለማግኘት ከባድ ነው፡፡ እያንዳንዱን ቀን ለብቻ ማሳለፍና ትዝታ የሚጥል ቅጽበትን አለመጋራት ያበሳጫል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ዓለም ሰመረ ናቸው፡፡ የ23 ዓመታት ባለቤታቸው በተደጋጋሚ ለሥራ ከኢትዮጵያ ስለሚወጡ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ይለያዩና ይገናኛሉ፡፡ ሲለያዩ በስልክ አሁን ደግሞ በፌስቡክ ይገናኛሉ፡፡ የተጋቡ ሰሞን ተለያይቶ መቆየት ይከብዳቸው ስለነበር፣ ባለቤታቸው ኢትዮጵያን ከለቀቁበት ቅጽበት ጀምሮ ፀባያቸው እንደሚለወጥ ያስታውሳሉ፡፡ ያለምንም ምክንያት ይበሳጫሉ፡፡ ሆድ ይብሳቸዋል፡፡ አሁን ግን ሁለት ልጆቻቸውና ሥራቸው ናፍቆታቸውን እንደሚያስረሳቸው ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ ዓለም እንደሚሉት፣ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ቢከብድም መወጣት ይቻላል፡፡ ጥንዶች በተናጠል ማድረግ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ተራርቀውም ቢሆን አሳክተው ወደ ግንኙነታቸው መመለስ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ እሳቸውና ባለቤታቸው በሁሉም ነገር ይደጋገፋሉ፡፡ የየቀን ውሏቸውን ከመጋራት በተጨማሪ በየፊናቸው የሚገጥሟቸው ነገሮች ላይ የጋራ ውሳኔ ያሳልፋሉ፡፡ ‹‹እርስ በርስ መግባባት ያስፈልጋል፤ አንዳችን ለሌላችን ጊዜ ባንሰጥ በትዳር አንቀጥልቅም ነበር፤›› ይላሉ፡፡ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ከየትኛውም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት የበለጠ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅም ይናገራሉ፡፡ ቀድሞ በጥቃቅን ነገሮች እልህ እየተጋቡ ከባለቤታቸው ጋር ይጋጩ ነበር፡፡ ‹‹እሱ ይደውል እሷ ትደውል እየተባባልን ሳንነጋገር ቀርተን የትዝታ ዘፈን እየሰማሁ እያለቀስኩ ያነጋሁባቸው ምሽቶች ብዙ ናቸው፡፡ አሁን የዕድሜ መጨመርም ሊሆን ይችላል ሁለታችንም ኃላፊነታችንን እንወጣለን፤›› ይላሉ ወይዘሮዋ፡፡

ኤፍሬም ኃያል የተለየ ሐሳብ አለው፡፡ ሰዎች በጊዜ ሒደት አመለካከታቸውን መቀየራቸው የሩቅ ለሩቅ ፍቅርን ከባድ እንደሚያደርገው ያምናል፡፡ ከአንድ ዓመት የሩቅ ለሩቅ ፍቅር በኋላ የተለየችው ፍቅረኛውን የተዋወቃት ድሬዳዋ ለሥራ በሄደበት ወቅት ነበር፡፡ እንደተዋወቁ ቢለያዩም የስልክ ወሬዎችና የቫይቨር መልዕክቶች ተጧጧፉ፡፡ ተዋደዱም፡፡ ድሬዳዋ ትከታተል የነበረውን ትምህርት ስታጠናቅቅ ወደ አዲስ አበባ መጥታ አብረው ለመኖር ቢስማሙም ከአንድም ሁለት ሦስቴ እመጣለሁ ባለችበት ወቅት ቀረች፡፡ መጨረሻም አዲስ አበባ መኖር እንደማትፈልግና እሱ ወደ ድሬዳዋ መሄድ እንዳለበት አሳወቀችው፡፡ በዚህ ስላልተስማሙ ከዓመት በኋላ ተለያዩ፡፡

ኤፍሬም በሩቅ ለሩቅ ፍቅር የሚያምን ሰው አይደለም፡፡ ‹‹እንኳን የተለያየ አገር እየኖሩ አንድ አገር ሆኖም ለብዙ ቀናት ካልተገናኙ ግንኙነቱ ትርጉም ያጣል፤›› ይላል፡፡ ከዛሬ ነገ ትመጣለች ብሎ ይጠባበቃት የነበረችው ፍቅረኛው አዲስ አበባ እንደምትመጣ ባያምን ኖሮ ፍቅር እንደማይጀምር ይናገራል፡፡ በእሱ እምነት፣ ሰዎች ምንም ያህል ቢደዋወሉና ቢጻጻፉ አብረው ካልሆኑ ግንኙነታቸው ጠንካራ አይሆንም፡፡

ጥንዶች ስሜታቸው ሳይቀዘቅዝ የሚዘልቁት አንድ ላይ ሲኖሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ምንም ያህል ጥረት ቢደረግ የሌላኛውን ሰው አኗኗር በርግጥ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ግምቶች ደግሞ አንዳንዴ ስህተት ላይ ይጥላሉ፤›› ይላል፡፡ ለፍቅረኛው ታማኝ ሆኖ እሷን ቢያምናትም፣ ከሌላ ሰው ጋር እየተኛ እንደሆነ ትጠራጠር ስለነበር ዘወትር ይጣላሉ፡፡ አብረው ቢኖሩ በመካከላቸው ያሉት ችግሮች  እንደሚቀረፉና በፍቅር እንደሚቀጥሉ ያምናል፡፡ በአካል መራራቃቸው ፍቅራቸውን እንዳያደፈርሰው በሚል ብዙ ነገር መሞከራቸው ግን አልቀረም ነበር፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው ጥልቅ ስልክ የፍቅር ወሬዎቻቸውን ሲሆን፣ ወሬዎቹ ወደ ስልክ ወሲብ (ፎን ሴክስ) የሚያመሩባቸው ጊዜዎችም ነበሩ፡፡ ሁሉም ጥረታቸው ግን በመጨረሻ ፍቅራቸውን አላዳነውም፡፡

ወዴት እያመሩ እንደሆነ ለማወቅ የሚያዳግቱ የሩቅ ለሩቅ ግንኙነቶችም አሉ፡፡ ጥንዶቹ ደስተኛ ባይሆኑም ግንኙነታቸውን እንዳያቋርጡ የሚያደርጓቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከባለቤቷ ጋር ባላት የሩቅ ለሩቅ ፍቅር እየተፈተነች የምትገኘው ፀዳለ ቢቂላ፣ ‹‹የሚያስተሳስረን ልጃችን ብቻ ነው፤›› ትላለች፡፡ ባለቤቷ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ስዊዘርላንድ ካቀና ዓመት አልፎታል፡፡ ጥሩ ሥራና ገቢ ካገኘ ቤተሰቡን ጠቅልሎ እንደሚወስድ ቢስማሙም አሁን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ነገር የለም፡፡ በየጊዜው ሐሳቡን መቀያየሩ እሷም እንዳትወስን አድርጓታል፡፡ መንስዔአቸውን ለማስታወስ የሚያስቸግሯት ጥሎች ብዙ ናቸው፡፡ ለወራት ይጣሉና ይታረቃሉ፡፡ መልሰው መጣላታቸው እንደማይቀር ግን ትናገራለች፡፡ አንድ ላይ ቢኖሩ ሲጣሉ አኗኗራቸው አስገድዷቸውም ቢሆን ይታረቃሉ፡፡

‹‹እንደ ድሯችን መሆን አልቻልንም፡፡ አሁን ያለን ግንኙነት ልጃችንን ታሳቢ በማድረግ ብቻ ነው፤›› የምትለው ፀዳለ፣ ተጣልተዋል አልተጣሉምም ለማለት የሚያስቸገር ሁኔታ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚገቡ ትገልጻለች፡፡ ግንኙነታቸው ግራ ቢያጋባትም ለልጃቸው ስትል የመጣውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነች ታክላለች፡፡

ጥንዶች ቃል ቢገባቡም የመጠበቁ ጉዳይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ርቀት ዳግም የመገናኘት ዕቅዳቸውን ያስለወጧቸው ጥንዶች እንዳሉ ሁሉ፣ ርቀት ፍቅራቸውን ያጠናከረላቸውም አይታጡም፡፡ ሚስጥር ኃብተአብ ጓደኛዋ ካናዳ እየተማረ ነው፡፡ ስለእያንዳንዱ እንቅስቃሴአቸው መረጃ ይለዋወጣሉ፡፡ ለፍቅረኞች ቀን በዲኤችኤል ስጦታ ይቀያየራሉ፡፡ ሁለቱም ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ይደዋወላሉ፡፡ ሲተኙም ይሰነባበታሉ፡፡ ‹‹ፍቅራችንን ርቀት አልቀነሰውም፡፡ የወደፊት ሕይወታችንን በጋራ ማቀዳችን ተስፋ ይሰጠናል፤›› ትላለች፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በጋራ ስለሚኖራቸው ሕይወት ስለ ልጆች ጭምር ያወራሉ፡፡ ያልተጠበቁ ስጦታዎች መለዋወጣቸው እንዳይሰለቻቹ እንደሚያደርጋቸው ታምናለች፡፡ ለጓደኞቿ ደውሎ ቀይ አበባ ገዝተው እንዲሰጡለት ያደረገበትን ወቅት አትዘነጋውም፡፡ ‹‹መነፋፈቁ ቢያምም ስለምንገናኝበት ጊዜ በተስፋ እያወራን እርስ በርስ እንጽናናለን፤›› ትላለች፡፡ የሩቅ ፍቅር ስኬታማ የሚሆነው ጥንዶች ስለፍላጎታቸው በግልጽ ሲነጋገሩ እንደሆም ታምናለች፡፡

በሌላ በኩል ጥንዶች የሚገናኙባቸው ቴክኖሎጂዎች ለጥንዶች ፍቅር መጠንሰስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በፌስቡክና ሌሎችም የማኅበረሰብ ድረ ገጾች ተዋውቀው ፍቅራቸውንም በርቀት ጀምረው በነዚሁ መገናኛዎች የሚቀጥሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ትዳር መመሥረትና ቤተሰብ ማፍራት ላይ የደረሱ ሰዎችን ታሪክ ማጣቀስ ይቻላል፡፡ የድረ ገጽ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ሁልጊዜ ይሳካል ማለት ግን አይደለም፡፡ ማንነታቸውን ለውጠው ሰው የሚተዋወቁና ጊዜ ማሳለፊያ የውሸት የፍቅር ግንኙነቶችን የሚጀምሩም አሉ፡፡ ከኮምፒውተር አልያም ከስልክ ጀርባ ያለውን ሰው ትክክለኛ ገጽታና ማንነት ለማወቅ አዳጋች መሆኑ ግንኙነቶቹን ፈታኝ ያደርጋቸዋል፡፡

በፌስቡክ ከተዋወቃት ሴት ጋር በፌስቡክ ብቻ የጦፈ ፍቅር የጀመረ አንድ ወጣት ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ፌስቡክ ላይ የምትልክለትን ፎቶግራፎች በመመልከትና የሚጻጻፉትን ተመርኩዞ ፍቅረኛው አደረጋት፡፡ ልጅቷ ግን ግንኙነታቸውን የጀመረችው እንደቀልድ ነበር፡፡ ፍቅሩ እየበረታበት መሆኑን ስትገነዘብ ጓደኞቿ እንደሞተች አድርገው ፌስቡክ ላይ እንዲጽፉለት አደረገች፡፡ ወጣቱ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ ገባ፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖም ደርሶበት ነበር፡፡

የኔነሽ ደጄኔ የቀድሞ ጓደዋኛዋን የተዋወቀችው በፌስቡክ ነበር፡፡ ነዋሪነቱን ፊንላንድ ካደረገው ወጣት ጋር ፍቅር የጀመረችው ተራርቀው ስለሚኖሩ ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት አልነበራትም፡፡ የጓደኞቿና የሌሎች ሰዎችን ተፅዕኖ ለመቋቋም ብላ ግን ግንኙነቱን ጀመረች፡፡ በሩቅ ፍቅር ስለማታምን ራሷን ሙሉ በሙሉ አልሰጠችውም ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት ፍቅር  በኋላ ኢትዮጵያ መጥቶ ተገናኙ፡፡ ወጪ ሳለ ስለመጋባት ያወራ ስለነበር ቀለበት እንድትመርጥ ይገፋፋት ነበር፡፡ እዚህ ሲመጣ ግን ጠንካራ ፍቅር እንደሌላት ተረዳ፡፡ እሷም ትሸሸው ጀመር፡፡

‹‹ግንኙነቱን የጀመርኩት ሰው አለኝ ለማለት ብቻ ነበር፡፡ በርግጥ ፌስቡክ ላይ ስናወራ እንግባባለን፡፡ በአካል ሳገኘው ግን ፍፁም የተለየ ሰው ሆኖ አገኘሁት፡፡  መጣጣም አለመቻላችን ከኔ የፍቅር ግንኙነት አለመፈለግ ጋር ተደማምሮ በስተመጨረሻ ተለያየን፤›› ትላለች የኔነሽ፡፡ የሩቅ ለሩቅ ፍቅር ከፍተኛ ጥረት ስለሚጠይቅ እንደሚያከብድ ትናገራለች፡፡ ፍሬዘር ሐጎስ ግን ተቃራኒ ሐሳብ አለው፡፡ የረዥም ዓመታት ጓደኛውን ለሥራ በተለያዩ የክልል ከተሞች ስለሚዘዋወር ለወራት ይለያታል፡፡ ‹‹በመለያየታችን ብዙ ችግሮች ይገጥሙናል፡፡ ችግሮቹ ግን የግንኙነቱ አንድ አካል ናቸው፡፡ አብረን ብንሆንም ፈተናዎች ይኖራሉ ጥንዶች አንዳች ግብ እስካላቸው ድረስ ፈተናዎች ይታለፋሉ፤›› ይላል፡፡ ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል የሚለው ፍሬዘር፣ ለወራት በስልክና አይኤምኦ ብቻ ያገኛት ለነበረችው ጓደኛው የጋብቻ ቀለበት እንደገዛና በቅርቡ እንድታገባው ሊጠይቃት እንደሆነም ተናግሯል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...