Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናፓርላማው በአዲስ አበባ የለያቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለካቢኔው አቀረበ

  ፓርላማው በአዲስ አበባ የለያቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለካቢኔው አቀረበ

  ቀን:

  – የሸራተንና የፓርላማ ማስፋፊያዎች አለመልማት ለፀጥታ ሥጋት እየሆነ ነው

  ፓርላማው በአዲስ አበባ አስተዳደር ያሰማራቸው የቁጥጥርና ክትትል ቡድኖች የለዩዋቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ለከተማው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና ለካቢኔ አባሎቻቸው ይፋ አደረገ፡፡

  ፓርላማው በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ የክትትልና ቁጥጥር ቡድኖቹን ያሰማራው በሦስት ከፍሎ ነው፡፡ እነርሱም በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች፣ እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመለየት ነው፡፡

  በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመለየት የተሠማራው የፓርላማው የክትትልና ቁጥጥር ቡድን ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሙሉ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የከተማ አስተዳደሩ በለያቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ እንቅስቃሴ ቢጀምርም የተቀናጀ አለመሆኑን፣ አመራሮች የወረዳ ምክር ቤት አባላትን ቁጥጥር የማይቀበሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኦዲት የማይደረጉ መሆናቸውን፣ የክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ሠራተኞች በስብሰባ ምክንያት ተገልጋዮችን የማያስተናግዱ መሆናቸውን፣ ለልማት ተነሺዎች የካሳ አከፋፈል ሥርዓቱ ወጥ ያልሆነና ግልጽነት የሌለው እንደሆነ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

  አንዱ ሠፈር ሳይለማ ሌላውን አካባቢ ለልማት በሚል ምክንያት ማፍረስ፣ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መምጣቱን አቶ ታደሰ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

  ‹‹በመልሶ ማልማቱ የነዋሪዎችን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ የማልማት ሥራ ለመጀመር ብቻ አካባቢዎችን ማፍረስ ይጀመራል፡፡ ቶሎ ወደ ልማት ስለማይገባ የፀጥታ ሥጋት ይሆናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

  ለአብነትም የሸራተን አዲስ ማስፋፊያና ፓርላማ ፊት ለፊት ለመልሶ ማልማት የፈረሱ አካባቢዎች ሳይለሙ ዓመታት ከማስቆጠራቸውም በላይ፣ ለፀጥታና ለደኅንነት ሥጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

  በሌሎች አካባቢዎችም ለምሳሌ በአራዳ ክፍለ ከተማ ደጃች ውቤ፣ ወረዳ 9 ግንፍሌ አካባቢ፣ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አካባቢ ለመልሶ ማልማት የፈረሱ አካባቢዎች ፀረ ባህል ተግባራት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

  በመልሶ ማልማት ምክንያት መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጐች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን፣ ማዕድ ቤትና መፀዳጃ ቤት የሌላቸውና እፍንፍን ብለው የሚኖሩ በመሆናቸው ለጤና ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን፣ ወረርሽኝ ቢከሰት አሳዛኝ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

  በጤናው ዘርፍ ላይ ከቀረቡት ችግሮች መካከል የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ችግር ሕሙማንን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑ ይገኝበታል፡፡ በዚህ የተነሳም ሕሙማን ከግል ክሊኒኮችና ከሆስፒታሎች እስከ አንድ ሺሕ ፐርሰንት የዋጋ ጭማሪ ከፍለው ለመገልገል መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

  ከመንግሥት ሆስፒታሎች መድኃኒት እየወጣ በግል ፋርማሲዎች እንደሚሸጥ፣ የጤና ባለሙያዎችም መድኃኒት ሲያወጡ መያዛቸውንም በጤናው ዘርፍ ክትትልና ቁጥጥር ያደረገው የፓርላማው ቡድን ሪፖርት አድርጓል፡፡

  ለአብነት ያህል በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የ25 ሺሕ ብር መድኃኒት ይዞ ሊወጣ የሞከረ የሆስፒታሉ ባልደረባ መያዙን፣ ሌላ አንድ ባለሙያ ደግሞ ኮመዲኖ ውስጥ ቆልፎ መገኘቱን ጠቁሟል፡፡

  ሪፖርቱን ያደመጡት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ የተቀበሉ መሆናቸውንና ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

  አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠትና በቅን ልቦና ማገልገል እንዳለባቸው ከገለጹ በኋላ፣ በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተዳደሩ ለማስተካከል የወሰደውን ዕርምጃ ፓርላማው በድጋሚ እንደሚገመግም አስታውቀዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...