Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ላይ የመጨረሻ ብይን ለመስጠት የሁለት ወራት ቀጠሮ...

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ላይ የመጨረሻ ብይን ለመስጠት የሁለት ወራት ቀጠሮ ተሰጠ

ቀን:

– ተጠርጣሪዎቹ የቀጠሮውን መርዘም ተቃውመዋል

– ፍርድ ቤቱ ሰፊ መዝገብ መሆኑን ጠቅሶ ባነሰ ጊዜ አይደርስም ብሏል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት ሦስት ዓመታት በእስር ላይ በሚኙት በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የመጨረሻ የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ላይ ብይን ለመስጠት፣ የሁለት ወራት ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ ጊዜው መርዘሙን በመግለጽ ተከሳሾቹ ተቃውመዋል፡፡ በመዝገቡ ከመቶ በላይ ምስክሮች የሰጡት የምስክርነት ቃል ሰፊ መሆኑን፣ ማለትም በአንድ ምስክር ከ12 ቀናት በላይ የተሰጠን የምስክርነት ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ከዚያ ባነሰ ጊዜ ሊሠራ እንደማይቻል በማስታወቅ ለሰኔ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመጨረሻ ብይን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

- Advertisement -

ተከሳሾቹ ሌሎች ሁለት የክስ መዝገቦች ያሉዋቸው ቢሆንም፣ የመዝገብ ቁጥር 141354 ለሚያዚያ 20 የመዝገብ ቁጥር 141356 ለሚያዚያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ለብይን ቀጠሮ ተይዘዋል፡፡ ለሁለት ወራት በተቀጠረው የክስ መዝገብ አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ መርክነህ ዓለማየሁ፣ አቶ አስመላሽ ወልደማርያም፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ከተማ ከበደ (ኬኬ)፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ፣ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤልና ሌሎችም የተካተቱበት የክስ መዝገብ 141352 ሲሆን፣ የሕገ መንግሥት ጥያቄም ተነስቶበታል፡፡

የክስ መዝገቦቹን በማየት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ አዲስ የወጣውን የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006ን ተከትሎ፣ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚቃረን በመግለጽ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የላከው ቢሆንም፣ አጣሪ ጉባዔው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) ጋር እንደማይጋጭ ገልጾ ለፍርድ ቤቱ መልሶለታል፡፡

ነገር ግን ተከሳሾቹ አቤቱታቸውን በድጋሚ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማቅረባቸው፣ ምክር ቤቱ ከወር በፊት ተሰብስቦ ባደረገው ክርክር ለሁለት በመከፈሉ ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ለቋሚ ኮሚቴው ተመርቶ ውጤቱ በመጠበቅ ላይ ነው፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አዋጅ ቁጥር 622/01ን ሙሉ በሙሉ እንደሻረው በአንቀጽ 181(1) ላይ ስለተደነገገና በአዋጅ ቁጥር 622/01 ወንጀል የነበሩ በአዋጅ ቁጥር 859/2006 ወንጀል መሆናቸው ቀሪ እንደሆነ ስለተደነገገ፣ ተከሳሾቹ ተከሰው የሚገኙበት ወንጀል እንዲሰረዝላቸው መጠየቃቸው ተገቢ መሆኑን በተደጋጋማ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ አዲሱ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ከወጣበት ዓላማ አኳያ እንጂ፣ በቀድሞ አዋጅ ቁጥር 622/01 ለተከሰሱ ወይም ለተቀጡ ሰዎች እንደሚጠቅም ወይም እንደማይጠቅም ተደርጎ መታየት እንደሌለበት አብራርቷል፡፡

ተከሳሾቹ ግን ባቀረቡት መከራከሪያ ነጥብ እንዳስረዱት፣ አዋጅ ሲወጣ የሆነን ቡድን ወይም ግለሰብ ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ተብሎ አይወጣም፡፡ እንደዚያ የሚወጣ ከሆነ የሚያደላ (አድሎአዊ) አዋጅ ስለሚሆን ‹‹ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግባቸው በሕግ ፊት እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል›› የሚለው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 25 ድንጋጌን እንደሚጥስ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2)ን ስለሚቃረን፣ ምክር ቤቱ ሊያርመው እንደሚገባ ጠቅሰው አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ አዋጅ ቁጠር 859/2001ን በመጠቀም በተመሳሳይ ፍርድ ቤትና ተመሳሳይ ወንጀል ተከሰው የነበሩ በርካት እስረኞች፣ ወንጀል መሆኑ ቀርቶላቸው ከእስር መፈታታቸውን በመግለጽ ሕጉ ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዲተገበር በማሳሰብ አመልክተው ነበር፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከወር በፊት ባደረገው ክርክር ከፊሎቹ ሕጉን መሠረት አድርጎ ፍርድ ቤቱ መሥራት እንዳለበት በመግለጽ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጋጭ ሲከራከሩ፣ ከፊሎቹ ደግሞ አዋጁ በአንቀጽ 182 መሸጋገሪያ አንቀጽ ላይ ቀደም ብለው የተጀመሩ ጉዳዮችን እንደማይመለከት ስለሚገልጽ ‹‹በሕጉ መሠረት›› የሚለው እንደማይሠራና ጭራሽ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደማይጋጭ በመግለጽ መከራከራቸውን፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና መብቶች ዳይሬክተር አቶ ተወልደ ወልዱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች የሕገ መንግሥት ትርጉምን በሚመለከት የሚናገሩት ነገር ተመሳሳይ ቢሆንም ለተወሰኑት፣ ‹‹ሕጉን መሠረት አድርጎ ፍርድ ቤቱ መሥራት አለበት›› የሚለው ምን ማለት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ጉባዔው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምክር ቤቱ ውሳኔ ምንም ይሁን ምንም የፍርድ ቤቱን ሥራ ሊያቆመው እንደማይችል የተናገሩት አቶ ተወልደ፣ እየሠራ ውሳኔውን መጠበቅ እንደሚችል ውሳኔው ‹‹አይመለከታቸውም›› ከተባለም የተላለፈባቸው ውሳኔ ውድቅ ሊደረግላቸው እንደሚችል፣ ወይም ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብይን እንደሚፀና አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ በግንቦት ወር ውስጥ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱን ሪፖርተር አነጋግሮ፣ ‹‹እኛ ሥራችንን እየሠራን ነው፡፡ ባለን ጊዜና መሄድ ባለበት ፍጥነት እየሠራንና እየጨረስን ነው፡፡ ወደ ምክር ቤት መሄዱ ሥራችንን እንድናቆም አላደረገንም፤›› ሲሉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የተከሳሾችን የክስ ሒደት በሰብሳቢ ዳኝነት የሚመሩት አቶ በሪሁ ተወልደ ብርሃን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...