– ከውጭ አሥር ትልልቅ ኩባንያዎች የማምረቻ ቦታ ይዘዋል
መንግሥት በተለየ አኳኋን የባንክ ማስያዣን ሳይጨምር እስከ 85 በመቶ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ ልዩ ማበረታቻዎችን ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያቀረበበት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የአሜሪካ ኩባንያዎችን ጨምሮ አሥር ትልልቅ የውጭ ኩባንዎችን እንዳካተተ ተገለጸ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ ዓርብ ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ባለሀብቶች ባደረጉት ገለጻ፣ መንግሥት ለረጅም ጊዜና ለሥራ ማስኬጃ የሚውል ከወትሮው የተለየ የብድር አቅርቦት ማዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ በሚሰጠው የረጅም ጊዜ ብድር መሠረት መንግሥት ያለምንም ማስያዣ እስከ 75 በመቶ የፕሮጀክቱን የገንዘብ መጠን የሚሸፍን ሲሆን፣ ቀሪውን 25 በመቶ ባለሀብቶች ከራሳቸው መዋጮ በጥሬ ገንዘብ እንዲሸፍኑ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለሥራ ማስኬጃ የሚቀርብ የፋይናንስ ጥያቄ እስከ 85 በመቶ በመንግሥት እንደሚመለስና ቀሪው 15 በመቶ ግን የኢንቨስተሮች ድርሻ መሆኑን ዶ/ር አርከበ አብራርተዋል፡፡ ፋይናንሱን የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሲሆን፣ ወደፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚቀላቀለውም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የራሳቸውን መሣሪያና ማሽነሪዎች ይዘው ለሚቀርቡም በጥሬ እንዲከፈለው ከተጠየቀው ገንዘብ በተጨማሪ፣ ዓይነት የሚቀርብ መዋጮም በመንግሥታ ታሳቢ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህ ከሌሎች ማበረታቻዎች ጋር ሲደመር መንግሥት በብድር ማበረታቻ እስከ 90 በመቶ ሊደርስ የሚችል ዕድል ማመቻቸቱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡
ከፋይናንስ ባሻገር መንግሥት ሁሉንም አገልግሎቶች ወደ ፓርኩ በማምጣት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ይኸውም የባንክ አገልግሎት፣ የጉምሩክ አገልግሎት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮምና ሌሎችም አገልግሎቶች ተሟልተው እንደሚቀርቡ ያብራሩት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ለማውጣት፣ መሬት ለማግኘትና ግንባታ ለማካሄድ ይወስድባቸው የነበረው ጊዜና ይደርስባቸው የነበረው እንግልት ሙሉ ለሙሉ እንደሚወገድ አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ያቀረባቸው ማበረታቻዎች ገዘፍ ብለው ከታዩባቸው መካከል ከዚህ ቀደም የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ለመክፈት ይከፈል የነበረው የ3.5 በመቶ ኮሚሽን፣ አሁን ወደ 0.5 ከመቶ ዝቅ መደረጉን ያብራሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ ናቸው፡፡ አቶ ታደሰ ባደረጉት ማብራሪያ መሠረት ከዚህ ቀደም የነበረው ክፍያ ተጠንቶ ከብዙ አገሮች አኳያ ውድና የተጋነነ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ ማበረታቻ ግን ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባሻገር ወደ ውጭ ለሚልኩ አምራቾች ብቻ እንደሚውል ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፣ መንግሥት እስከ አሥር ዓመት የሚደርስ የግብር ዕፎይታ ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መፍቀዱን፣ ከቀረጥ ነፃን ጨምሮ ወደ ውጭ ከተላከ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ እስከ 28 ቀናት ባለሀብቶቹ እጅ እንዲቆይና ለሚያስፈልጋቸው ተግባር እያገላበጡ እንዲጠቀሙበት ለማገዝ ተብሎ የተሰጠ ማበረታቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ሁሉ ማበረታቻ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሰጠበት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ እስካሁን ከውጭ አሥር ያህል ኩባንያዎችን ማካተቱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን ባለፈው ወር ለባለሀብቶች ቀርቦ የነበረው ጥሪ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ይኼውም መንግሥት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶች በጨረታ እንዲሳተፉ የሚያስችል ጥሪ ቀርቦ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አርከበ፣ ለጨረታ ሰነድ የገዙ ዘጠኝ ብቻ ቢሆኑም አንዳቸውም ለመዋዋል እንዳልመጡ ተናግረዋል፡፡
ይህ በመሆኑም መንግሥት ስብሰባ በመጥራት ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ዕድል ማመቻቸቱንና ስለሚሰጣቸው ማበረታቻዎች ገለጻ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ቢሆን ይመጣል ተብሎ ከተጠበቀው ያነሰ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች በሸራተን አዲስ በተካሄደው ስብሰባ መገኘታቸው ታይቷል፡፡
ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ባሻገር ግን በዓለም ትልልቅ የተባሉ አሥር ኩባንያዎች በሐዋሳ ኢንዲስትሪ ፓርክ ውስጥ የማምረቻ ቦታ በመያዝ ፓርኩ ሥራ እስኪጀምር እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአሜሪካዎቹ ፒቪኤች ኩባንያና ቫኒቲ ፌር ይጠቀሳሉ፡፡ ካልቪን ክሌን፣ ቶሚ ሂልፊንገርና ሄሪቴጅ ብራንድስ የተባሉትን ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ብራንዶች በሥሩ ያቀፈው ፒቪኤች ኩባንያ በየዓመቱ ከስምንት እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ የሚያከናውን ትልቅ ኩባንያ ነው፡፡ ራንግለር፣ ቫንስ፣ ቲምበርላንድ፣ ሊ የተባሉትን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ምርቶችን ያካተተው ቫኒቲ ፌር ኩባንያም በሐዋሳ ሥራ ለመጀመር ከሚጠባበቁት መካከል ይጠቀሳል፡፡ የህንዶቹ አርቪን፣ ሬንሞንት ኩባንያዎችን አካቶ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከሆንግ ኮንግ፣ ከስሪላንካ፣ ከማሌዥያና ከኢንዶኔዥያም ቦታ የያዙ መኖራቸውን ዶ/ር አርከበ አስታውቀዋል፡፡
የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ በጀመረ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ለ60 ሺሕ ሰዎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ ሆኖም ለ60 ሺሕ ሰዎች መኖሪያ ቤት በሐዋሳ ማግኘት ባለመቻሉ፣ መንግሥት ለሐዋሳ ነዋሪዎች ብድር በማመቻቸት በየግቢያቸው በአነስተኛ ወጪ 12 ሺሕ ቤቶች እንዲገነቡ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡
ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግሥት የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉን እያስከተለባቸው ሠራተኞች በሥራ ላይ ለማቆየት መቸገራቸውን፣ የሠራተኞች የሥራ ባህል፣ ሥነ ምግባር፣ የምርታማነት አቅምና መሰል ጉዳዮች ላይ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ድንገተኛው የመንግሥት ማበረታቻ እንዳስደስታቸው በርካቶች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡