Monday, July 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለወጣቶች የቴክኒክና የሙያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ትኩረት እንስጥ!

በበቀለ ማቴዎስ

‹‹ኦሊምፒክ›› የሚለው መጠሪያ ሲነሳ በአብዛኛው ያለው መረዳት በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው ዝግጅት ነው፡፡ በአንፃሩ በየሁለት ዓመቱ በኢንተርናሽናል ደረጃ የሚካሄደው የወጣቶች፣ የቴክኒክና የሙያ ኦሊምፒክ መካሄድ ከጀመረ 60 ዓመታት ያህል አስቆጥሯል፡፡

በአሁን ወቅት ዓለም አቀፍ ይዘቱን ጠብቆ በ78 አባል አገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ነው፡፡ ወርልድ ስኪል (World Skills) የቮኬሽናል ውድድር እንዲስፋፋ የሚሠራ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖትና ከፆታ ተፅዕኖ ውጪ የሆነ ተቋም ነው፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር (International Vocational Training Organization) በመባል ይታወቃል::

ከውድድሩ በተጨማሪ ማራኪና የወጣቱን ልብ እንዲስብ የሚያደርገው የመክፈቻውና የመዝጊያው ፕሮግራም ከስፖርት ሥነ ውበት ጋር እንዲዳመቅ መደረጉ ነው፡፡ ወጣቶቹ በተመልካች ፊት የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ሲያልፉ፣ እንዲሁም በአራቱ የውድድር ቀናት በየመወዳደሪያው ጣቢያ ፊት ለፊታቸው የአገራቸው ባንዲራ እንዲታይ ሲደረግ የበለጠ መስህብ ይኖረዋል፡፡ በመዝጊያው ዕለት ከየሙያ መስኩ የተመረጡ አሸናፊዎች ልክ የስፖርት ተወዳዳሪዎች ቆመው የሚሸለሙበት ደረጃ ላይ ወጥተው፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለወጡ ሜዳሊያ  ይሸለማሉ፡፡ በአኳያውም የአሸናፊ አገሮች ሰንደቅ ዓላማ ወደ ላይ እየወጣ ብሔራዊ መዝሙር ይዘመራል፡፡

ይህ ዝግጅት ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚመጡ ወጣቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ መንግሥታት፣ በትምህርት ላይ የሚሠሩ ተቋማትና ሌሎችንም አግባብ ያላቸውን የሚያገናኝ ነው፡፡ ይህም በአባላት አገሮች በአብዛኛው በቀጥታ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ሲሆን፣ በርካታ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የንግድ ምክር ቤቶች፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የአሠሪ ድርጅቶች፣ የንግድና አምራች ኩባንያዎች፣ ቀጣሪና አስቀጣሪ ኤጀንቶች፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ሌሎችም የኅብረተሰቡ አባላት ይጎበኙታል፡፡

 አባላት አገሮች አዘጋጅነቱን ለማግኘት ቅድሚያ ከሚያገኙበት አንዱ ከዓለም አቀፍ ስፖርት ወይም ኦሊምፒክ ጋር የተያያዘ ዝግጅት ካካሄዱ፣ ወይም ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአገረ እንግሊዝ ዓለም አቀፍ ስፖርት ውድድር ከመካሄዱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ2011 ከኅዳር አምስት እስከ ስምንት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በተገኙበት፣ 42ኛው የቴክኒክና የሙያ ውድድር ለተመልካች ተከፍቷል፡፡ 43ኛው የቴክኒክና የሙያ ኦሊምፒክ በብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 11 እስከ 16 ቀን 2015 ሲካሂድ ከአንድ ዓመት በኋላ ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ በብራዚል ተካሂዷል፡፡ ዱባይ ወይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እ.ኤ.አ. በ2016 የበጋ ኦሊምፒክ (Summer Olympic) ባዘጋጀችበት ማግሥት፣ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 15 እስከ 18 ቀን 2017 ከተማዋ የሙያ ሻምፒዮን አዘጋጅታለች፡፡ መጪው 45ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች፣ የቴክኒክና ሙያ ውድድር የሚካሄደው ባሳለፍነው ሰኔ 2010 ዓ.ም. 21ኛውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ባካሄደችው በሩሲያ ነው፡፡

ይህ ለአራት ተከታታይ ቀናት በጎብኝዎች ፊትና በአባላት አገሮች የሚካሄድ የሙያ ውድድር ዓይነቶች በየሙያ ዘርፉ የሚካተቱ ናችው፡፡ ለግንዛቤ ያህል፣  

 • የኮንስትራክሽንና የሕንፃ ቴክኖሎጂ

የብሎኬት ግንባታ፣ የጡብ ግንባታ፣ የግድግዳና የወለል ንጣፍ (Wall & Floor Tiling)፣ የሳኒቴሪ መስመር ዝርጋታና (Sanitary Installation) ወዘተ፡፡

 • የፈጠራና ፋሽን

የልብስ ስፌት፣ የፋሽን ዲዛይን ሥራ፣ የአበባ አዘገጃጀት (Floristry) የጌጣጌጥ ሥራ፣ ወዘተ፡፡  

 • ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ

ኢንፎርሜሽን፣ ኔትወርክ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም (IT Application) ዌብሳይት ዲዛይን፣ ኅትመት ቴክሎኖጂ፣ ወዘተ

 • ማኑፋክቸሪንግና ኢንጂነሪንግ ቴክሎኖጂ   

ኮንስትራክሽን ሜታል ወርክ፣ መካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ ብየዳ፣ ወዘተ  

 • ለማኅረሰብና ለግል የሚሰጡ አገልግሎቶች     

የዳቦና ጣፋጭ ጋገራ ሥራ፣ የምግብ ዝግጅት፣ የሬስቶራንት ሰርቪስ አሰጣጥ፣ የፀጉር ሥራ፣ የውበት አጠባበቅ፣ ወዘተ፡፡  

 • ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ

የአውሮፕላን ጥገና፣ የአውቶሞቢል ቴክሎኖጂ፣ የመኪና አካል ቅብ፣ ወዘተ፡፡   ሌሎችም ከፍ ባለው ከተዘረዘሩት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡

ዓላማ

ወጣቱ ስለቴክኒክና ሙያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ፣

 • ሠልጣኞችና አሠልጣኞች ዘመኑ የደረሰበት የኢንዱስትሪ፣ የንግድና የአገልግሎት ብቃት ላይ እንዲደርሱ በሁሉም መስክ ለማበረታታት፣
 • በሚዘጋጀው ውድድር ሐሳብና ልምድ መለዋወጥና በዘርፉ ተጓዳኝ የሚሆን ወርክሾፕና ሴሚናር በመሳሰሉት የግንዛቤን አቅም ለመገንባት፣
 • በኩባንያዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ለወጣቶች የቅጥር ዕድል ለማመቻቸት፣
 • ተጨማሪ ትኩረት ሊደረግላቸው የሚገቡትን የሙያ ዓይነቶች ለማሳየት፣
 • የቴክኒክና ሙያ ጥራትና አገልግሎትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ፣
 • የፈጠራና የክህሎት (Innovation & Talent) ሥራዎችን ለማበረታታት፣

የቴክኒክና ሙያ ዕውቀት ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማሳየትና ሌሎችንም መሰል ዓላማዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡

ጠቀሜታ

 • ስለቴክኒክና ሙያ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሊኖር የሚገባውን ግንዛቤ ያሳድጋል፣
 • የሥራ አስተሳሰብና መነቃቃት በባለሙያዎች ዘንድ እንዲሻሻል ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
 • ወጣቶች በያዙት ዕውቀት ላይ ያላቸውን መተማመን፣ እንዲሁም ለሥራቸው የመስጠትና ለሙያው ያላቸውን አክብሮት የማዳበር ልምድ ከፍ እንዲል ይረዳል፣
 • በሙያ የሠለጠኑ በማኅረሰብ ውስጥ ላሉ አክብሮትና ዕውቅና ለመስጠት ያግዛል፡፡

አገር አቀፍ የቴክኒክና የሙያ ኦሊምፒክን በማዘጋጀት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሊኖር የሚገባውን ትስስር ለማሳደግና ሌሎችንም ተዛማጅ ጉዳይዮች ግምት ውስጥ በማስገባት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

በአፍሪካ በጥቂት አገሮች ማለትም በሞሮኮ፣ በቱኒዚያ፣ በደቡብ አፍሪካ ተወስኖ ቆይቶ የነበረውን የሙያ ውድድር ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲገባ ሁኔታዎች ተመቻችተው ነበር፡፡ ይኼውም በስዊዘርላንድ እ.ኤ.አ. 2003 በተካሄደው 37ኛው ዓለም አቀፍ የቴክኒክና የሙያ ውድድር በእንግድነት የተጋብዘው ሊዲንግ ኢንተርፕራይዝ የተባው ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ በማስገባቱ ነው፡፡ ይኼንን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ በ1998 ዓ.ም. አገር አቀፍ ሞዴል የቴክኒክና ሙያ ውድድር ከአቅም ግንባታ፣ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ትምህርት ቢሮና ከሊዲንግ ኢንተርፕራይዝ  ጋር በመሆን ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ክልሎቻቸውን የወከሉ የቴክኒክና የሙያ ወጣቶች በልብስ ስፌት፣ በፀጉር ሥራ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በፈርኒቸር ሥራ፣ በጡብ ግንባታ (Bricklaying) እና በአይቲ (IT Application) ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እጅግ ብዙ ጎብኚዎች ፊት በየሙያ ዘርፍ የሞቀ ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት ለምሥራቅ አፍሪካና ለአካባቢው አገሮች ፈር ቀዳጅ ይሆናል ተብሎ የተገመተው ጭራሽ ለዓመታት ሳይካሄድ ቀረ፡፡ በሌላ በኩል ከዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ2016 ታንዛኒያ የምሥራቅ አፍሪካን የሙያ ውድድር ለማዘጋጀት ባደረገችው መነሳሳት፣ ኬንያና ዛምቢያን ጨምሮ ሦስት አገሮች የተሳተፉበት ውድድር ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበትን ዕድል የወሰደችው ታንዛኒያ ከዓለም አቀፍ የሙያ ኦሊምፒክና የልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን በወጣቱ ላይ የበለጠ ለመሥራት ሁኔታዎችን እያመቻቸች ትገኛለች፡፡

ቀጣዩ 45ኛው የዓለም አቀፍ የሙያ ውድድር በሩሲያ ሦስተኛ ከተማ በሆነችው ካዛን እንዲካሄድ በጠቅላላው ጉባዔ በድምፅ ብልጫ ተወስኖል፡፡ አንድ ሺሕኛ ልደቷን  በ2005 ዓ.ም. ያከበረችው ካዛን ከሞስኮ በስተምሥራቅ 820 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ዓለም አቀፉ ውድድር እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 22 እስከ 27 ቀን 2019 ይህም በእኛ አቆጣጠር በመጪው ነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም. ይሆናል፡፡ ውድድሩ በአማካይ 50 ያህል ሙያዎች፣ ከ70 አገሮች የሚመጡ 1,300 የቴክኒክና ሙያ ወጣቶች፣ ከ60 አገሮች የሚመጡ 2,000 ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡

አንዳንድ አዘጋጅ አገሮች ለየት ያለ ተጨማሪ ድምቀትና ለአገር ፋይዳ የሚሆኑ ዝግጅት ያካሄዳሉ፡፡ ለማስታወስ ያህል ጃፓን በ2007 ዓ.ም. የ39ኛውን የሙያ ውድድር ስታዘጋጅ የአካል ጉዳተኞች ኢንተርናሽናል ውድድር አብሮ እንዲካሄድ አድርጋለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 በዱባይ ዝግጅት ከፍተኛ ኮንፍረስ ሲካሄድ፣ በመከካለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ አካባቢ በዓይነቱ የመጀመርያ ነበረ፡፡ በዚህ ዝግጅት ፖለሲ አውጪዎች፣ አስፈጻሚዎች፣ እንዲሁም ወጣት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተቀናጁበት ውይይቴ ተካሂዷል፡፡  

በካዛን ሩሲያ በሚካሄደው 45ኛው ዝግጅት ላይ ተጨማሪ ሆኖ የሚቀርበው ከአሥር እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች ውድድር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ከሕዝቧ 70 በመቶ የሆነው ወጣት በሥነ ልቦናና በጥሩ የሥራ ባህል ቀርፆ ለኢኮኖሚው አጋር ለማድረግ የተለያዩ ዕቅዶች መነደፍ እንዳለበት በመርህ ደረጃ ሁላችን የምንስማማበት ነው፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚያደርጉት ጥረት ምሥጋና የሚቸረው ቢሆንም፣ ሙያ በዓይነትና በጥራት እንዲያድግ፣ ምርትና አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ፣ የሥራ ባህል ተቀይሮ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶችን እንደ መልካም ዘር ለማውጣት፣ ብዙ የማሠልጠኛ ተቋማትን ከመገንባትና ብዙ ወጣት ባለሙያዎችን ከመቀበል ባሻገር ወጣቱ ቴክኒክና ሙያ ላይ ልቡ እንዲያርፍ ተጨማሪ ሥራዎችን መፈተሽ አንዱ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ በተለይ ብዙ ያደጉ አገሮች ‹‹ተጠቅመንበታል!›› ይበጀናል በሚል የበለጠ እየተጠቀሙበት ያለውን ዓለም አቀፍ የሙያ ውድድርን መሞከር ለነገ የምንለው አይደለም፡፡ ከእኛ በኋላ አባል የሆኑ አንዳንድ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጥቅሙን በመረዳት በትጋት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሙያ ኦሊምፒክ ብትካፈል እንደ ብዙ ጀግኖች አትሌቶቻን ለብዙዎች መበረታታትና ትንሳዔ እንደሚሆን እምነታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በዓለም አቀፍ ውድድር ለመሳተፍ ብቁ ናቸው፡፡ ተቋማቱም እነዚህን ተወዳዳሪዎች ለማብቃት በቂ አቅም አላቸው፡፡ በአገር ደረጃ በዚህ መሰል ዝግጅት ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው የሚገኙበት መድረክ ሲፈጠር ለዕድገትና ለልማት መደመር ይሆናል፡፡ በአኳያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኘው ልምድ የዛኑ ያህል ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ተንቀሳቅሰን ማንቀሳቀስ እንችላለን! ውጤትን አልመን ውጤት ማምጣት አንቸገርም! የዓለም ዓቀፍ የሙያ ኦሊምፒክ አባል በመሆን እንደመር!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles