Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከረቫት ያሰሩ ረሃብተኞች

በዕዝራ ኃይለ ማርያም መኮንን

ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ ቤቴ አካባቢ ቆሜ ሰው ስጠብቅ ጎን ለጎን የተቀመጡ ጉልት ቸርቻሪዎች ሲነጋገሩ የሰማሁት ነበር፡፡ አንደኛዋ ‹‹ልጅሽ አሁን እንዴት ነው?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹የመንግሥት ሥራ ከለቀቀ በኋላ ለእኔም ተርፏል፤›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹‹የአንቺስ? አሁንም የመንግሥት ሥራ ላይ ነው?››  

‹‹ምን እባክሽ የመንግሥት ሥራ አለቅ ብሎ፣ አሁንም ከእኔ ጋር ነው የሚኖረው፤›› አሉ በተሰበረ ድምፅ፡፡ ሌላም፣ ‹‹ሌላ ሥራ አልሞከረም?››

‹‹መሞከሩማ መቼ ይቀራል? አልሳካ ብሎት ነው እንጂ፤›› አሉ ፊታቸው ክስክስ እንዳለ፣ ‹‹እግዚአብሔር ይርዳው፣ አንቺንም ይርዳሽ፤›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ ‹‹ከእኔው ጋር እየኖረ ዕድሜውም ገፋ፣ በእዚህ ኑሮና ደመወዝ ሚስት አግባ ማለትም ከበደኝ፤›› አሉ በቁዘማ፡፡ ‹‹ከመንግሥት ሥራስ የእኛ ጉልት ሳይሻል አይቀርም፣ እኛስ ዕድሜያችንን እየጨረስን ነው፡፡ አወይ የልጆቻችን ነገር!›› አሉ እጃቸውን እያጣቡ፡፡  ይኼን በመነጋገር ላይ እያሉ የምጠብቀው ሰው ስለመጣ ሄድኩኝ፡፡ እነሱ ጨዋታቸውን ቀጠሉ፣ ውስጤ ተነካ፡፡ ፊቴ ላይ እስኪነበብ ድረስ አዘንኩ፣ ቆዘምኩ፡፡

ጠያቂና አስታማሚ አጣ እንጂ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ከታመመ ቆይቷል፡፡ ለሲቪል ሰርቪሱ በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ ከፍላ በምላሹ በስብሰባና በተለያዩ የሥራ አመራር ፍልስፍናዎች (ውጤት ተኮር፣ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ ካይዘን፣ አንድ ለአምስት. . . ) መሞከሪያ በማድረግ የምታስጨንቅ አገር ኢትዮጵያ ትመስለኛለች፡፡

ይህ ጽሑፍ የአገራችንን ሲቪል ሰርቪስ ችግር በሙሉ የሚገልጽና የሚተነትን አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሲቪል ሰርቪሱ የሚከፈለው ደመወዝ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የዋጋ ግሽበት የሚቋቋም ባለመሆኑ ምን ይሻላል? መንግሥት ወዴት ነው? የሚለውን የሚያመለክት ነው፡፡

በሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሥር በሚተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የዲግሪ ምሩቅ መነሻ ደመወዝ 2‚748.00 ብር ነው፡፡ በዚህ ደመወዝ ቤት ኪራይ ተከፍሎ፣ ተመግቦና ሌሎች አስገዳጅ ወጪዎችን ሸፍኖ መኖር ከባድ ነው፡፡ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎችስ በፍጥነት እየጋሸበ የሚመጣውን የኑሮ ውድነት እንዴት ያደርጉታል? የብር ምንዛሪ ከቀን ቀን እየወደቀ የመግዛት አቅምን ሽባ በማድረጉ የኑሮ ወጪ (Cost of Living) ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ በዚህም ዋናው ተጎጂ የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ ነጋዴውማ ‹‹እዚያው ሞላ፣ እዚያው ፈላ›› እንዲሉ የዋጋ ግሽበቱ በጨመረ ቁጥር እሱም ዋጋ ይጨምራል፡፡ ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን የመሥሪያ ቤት ካፌ ከፍሎ መብላት አቅቷቸው ምሳ ሳይበሉ የሚውሉ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ሞራል ከሁሉም የሚልቅ ኃይል ቢኖረውም የብዙዎች የመንግሥት ሠራተኞች ሞራል ወድቋል፡፡ ሞራሉ ከወደቀና ለዕለታዊ ጥቅሙ ብቻ ከሚያዘነብል ሠራተኛ ውጤት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕመሙም የኅብረተሰቡም ጭምር ነው፡፡  

ብሩ እየወደቀ፣ ኑሮ እየጋሸበ ሲሄድ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ባለበት በመሆኑ ሠራተኞች ሕይወታቸውን ለመምራት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡፡ የደመወዝ ዝቅተኛነትና የሁኔታዎች አለመመቻቸት ሠራተኛው ከልቡ እንዲሠራ ባለማድረጉ፣ በአገር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡

ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ ያሉ አብዛኛው ወጣት የመንግሥት ሠራተኞች ቤት ተከራይተውና ራሳቸውን ችለው ለመኖር ደመወዛቸው ስለማይበቃ፣ ከቤተሰባቸው ጋር ለመኖር ተገደዋል፡፡ ትዳር ለመያዝም ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡

አንዳንድ የመርካቶ ነጋዴዎች የመንግሥት ሠራተኛን ‹‹ከረቫት ያሰረ ረሃብተኛ›› እንደሚሉ ሰምቻለሁ፡፡ መርካቶዎች ይኼን ስያሜ ያወጡት ሞራሉን ለመጠበቅ አለባበሱን ያሳመረ ሠራተኛ ኪሱ ባዶ እንደሆነ አሳምረው ስለሚያውቁ ነው፡፡ በእርግጥ አፋዳሽ፣ ዕውቀት አጠርና ሁሉም ቦታ አለሁ ባይ ደላላ የመንግሥት ሠራተኛ ከረቫትም አስሮ ኪሱ ባዶ እንደማይሆን ይገነዘባሉ፡፡

ማን የማን አቀባባይና ኮሚሽን ተቀባይ እንደሆነ ከሥራቸው ተሞክሮ አበጥረው ያውቃሉ፡፡ በመርካቶ የሀብት መለኪያው ልብስ ባለመሆኑ ጭርንቁስ የለበሰ ነጋዴ ሚሊየነር ሊሆን ይችላል፡፡ ዕቃ ለመግዛት የሚከራከራቸውን ሠራተኛ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ ነህ እንዴ?›› በማለት ዝቅ አድርገው የሚያዩ አንዳንድ ነጋዴዎች እንዳሉ በራሴ ደርሶብኝ አይቻለሁ፡፡ ገንዘብ እንደ አምላክ በሚታይበት ዓለም ውስጥ ይህ ቢባል አያስደንቅም፡፡ ‹‹ይሁና›› ከማለት ውጪ፡፡

ተቀባይነትና መከበርን የማይሻ የለም፡፡ መነሳት የሚገባው ቁም ነገርም ይኼው ነው፡፡ ‹‹ሞሰብ ሃይማኖቱ›› እና ‹‹ላንቃ አዳሪ›› ካልሆነ በቀር ሰው መብቱን፣ ክብሩንና ሰብዕናውን ከሚመገበውና ከሚለብሰው በበለጠ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሲቪል ሰርቪሱ ያጣው ይኼን ክብር ነው፡፡ የሥራ አመራር ባለሙያዎች እንደሚሉት ተገቢ ባልሆነ ክፍያ ማሠራት ቅጣት ነው (Service without a fair reward is punishment)፡፡ 

የሚከፈላቸው ውሎ አበል ዝቅተኛ በመሆኑ ለሥራ መስክ ሲወጡ መኪናቸው ውስጥ የሚያድሩ ሾፌሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ አልጋ በሌለው መኪና ውስጥ ኩርምት ብሎ አድሮ በማግሥቱ ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ መገመት አይከብድም፡፡ በአንድ ወቅት መስክ ይዞን የተጓዘ ሾፌር መኪና ውስጥ እንዳያድር ብር አዋጥተን ራሳችን በያዝንበት ሆቴል አሳድረነዋል፡፡  

የጡት አባት ያላቸው መሥሪያ ቤቶች እንደ ልጅ፣ ሌላው ደግሞ እንደ እንጀራ ልጅ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የደመወዝ ደረጃ ከፍተኛ ሲሆን፣ የሌሎች ደግሞ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ወጥ የሆነ አሠራር እንደሌለ አመልካች ነው፡፡ ልዩነት ለምን ተፈጠረ የሚል ሐሳብ የለኝም፡፡ መሥሪያ ቤቶች እንደ ተቋቋሙበት ዓላማና ተልዕኳቸው መጠን አንዱ መሥሪያ ቤት ከአንዱ ሊለይ ቢችልም፣ ሰፊ የደመወዝ ልዩነት መፈጠር የለበትም ባይ ነኝ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሠራተኛው የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ እየፈለሰ ነው፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ አራት መሥሪያ ቤቶችን የሚቀያይሩ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ይህን ችግር ያቃልላል ብሎ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን መመርያ ቢያወጣም፣ ተግባራዊ ለማድረግ ከስምንት ዓመታት በላይ ፈጅቶበታል፡፡ ምደባው በየመሥሪያ ቤቱ እየተካሄደ ቢሆንም፣ ምደባ ለተደረገላቸው ሠራተኞች ከወረቀት አልፎ በደመወዝ ላይ ያመጣው ለውጥ ባለመኖሩ ‹‹ደረቅ ቼክ›› ለመባል በቅቷል፡፡

ሌላው አስገራሚ ነገር ደመወዝ ሳይጨመር ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በሚዲያ በሚሰጡት መግለጫ የኑሮ ግሽበቱን ከማናር ውጪ ለሠራተኛው የሚሰጠው አንዳች ጥቅም አለመኖሩ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን በአምስት ክፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

  1. የትምህርት ዕድል ለማግኘት ብቻ የሚሠሩ ሠራተኞች (የሚፈልጉትን ትምህርት ካገኙ የሚለቁ)፣

  2. ከመንግሥት ያልተገባ ጥቅም የሚያገኙ ከዝቅተኛ የሥራ መደብ እስከ ከፍተኛ አመራር ያሉ (ከአነስተኛ ደመወዝተኝነት በብርሃን ፍጥነት ቢጠሯቸው ወደማይሰሙ ባለሀብትነት የተቀየሩ) መኖራቸው፣     

 3. ለጡረታ የተቃረቡ፣ የኑሮ ደረጃቸው ሻል ያለና ከሥራ ይልቅ ለጊዜ ማሳለፊያነት የሚጠቀሙ፣

 4. ሌላ አማራጭ ያጡና በሥራቸው ደስተኛ ያልሆኑ አብዛኛውን ቁጥር የያዙ፣

 5. በሙያቸው ለአገራቸው የበኩላቸውን ለማበርከት የሚተጉ፣ ሆኖም በቁጥር በጣም ጥቂት የሆኑ ናቸው፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው ምደባዎች የግሌ አስተያየት እንጂ በጥናት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በመሆኑም ለአገር ዕድገት ቁልፍ ሚና ያለውና ቁጥሩም ከሚሊዮን በላይ የሆነው ይህ ዘርፍ ተረጋግቶ ካልሠራ በአገር ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው፡፡

ይህች ዓለም ደሃ በረሃብ፣ ሀብታም በሙስና የሚሞትባት ለብርቱው እንጂ ለደካማው የማትሆን ነች፡፡ ከፍተኛ አመራሮች ካለባቸው ኃላፊነት አንፃር ደመወዛቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በውጭ ጉዞ፣ በቦርድ፣ በነፃ ቤት፣ በመስተንግዶና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ተጠቃሚ በመሆናቸው የበታች ሠራተኞች ሕመም ላይሰማቸው ይችላል፡፡  የሠራተኞች ደመወዝ ዝቅተኛ የሆነው የአገራችን የመክፈል አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት?

መቼም የአገራችን ሲቪል ሰርቪስ ችግር አሁን ይባባስ እንጂ ካለፉት ሥርዓቶች ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ዕብድ እንዳደራው ድር ውትብትብ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ በሙሉ ይቃለላል ተብሎ አይታመንም፡፡ ሆኖም ቀዳሚ ችግሮችን በመለየት ትኩረት ተሰጥቶ በሙሉ ኃይልና ጉልበት ከተሠራ የመፍትሔውን መሠረት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ሲቪል ሰርቪሱ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂ አስፈጻሚ በመሆኑ ለመንግሥት የጀርባ አጥንት ያህል ነው፡፡  በገቢውና በሌሎችም ምክንያቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ ክብሩ ያሽቆለቆለውን ይኼን ዘርፍ ከወደቀበት አንስቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ የማድረግ ኃላፊነት ትግልን ይጠይቃል፡፡ መንግሥት የታመመውን ሲቪል ሰርቪስ በማከም ሲቪል ሰርቪሱን ‹‹ከረቫት ያሰረ ደስተኛ›› ሊያደርገው ይገባል፡፡

መድኃኔ ዓለም ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራ [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles