Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል31 ቀናት በሩሲያ ምድር

31 ቀናት በሩሲያ ምድር

ቀን:

በዳዊት ቶሎሳየአውሮፕላኑ ካፕቴን በሩሲያዋ ዋና ከተማ ሞስኮ ከተማ ለማረፍ የደቂቃ ዕድሜ እንደቀረ ሲለፈፍ፣ ሁሉም ከእንቅልፉ መንቃት ጀመረ፡፡ በበረራ ቁጥር 1428 ግዙፉ የኳታር አውሮፕላን ውስጥ የነበረው ተሳፋሪ ሁሉ በጠባቧ መስኮት ብዙ የተነገረላትን ኃያል አገር ሞስኮ ለማየት ይንጠራራ ጀመር፡፡ በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን መለያ የደመቁ ተመልካቾች፣ የኢራን፣ የሞሮኮና ጥቂት የሩሲያ ተወላጆች ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ ትውልድ ቀያቸው ለመመለስ በዚህ አውሮፕላን ውስጥ ተገኝተዋል፡፡

ከአሥር ሺሕ ጫማ ከፍታ ላይ ሞስኮ ቁልቁል ስትታይ በጫካ የተከበበችና ዙሪያዋን እንደ መቀነት የከበባት ወንዝ መለስ ብሎ ይታያል፡፡ ምድሯ ፍፁም አረንጓዴና ለደቂቃዎች ያህል እንኳ ዝናብ አጥቶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ እንደ እኔ ላለው እንግዳ ደግሞ በሕንፃ ጫካ ያልተከበበችና ከሰማይ ጠቀስ ፎቆች ነፃ የሆነችውን ሞስኮ ዓይቶ  አውሮፕላን ማረፊያው ከከተማው ርቆ ስለሚገኝ ይሆናል የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደርገዋል፡፡

ከሞስኮ ከተማ ከአንድ ሰዓት በላይ ርቆ በሚገኘው የዶሞዴዶቮ አየር ማረፊያ የቪዛ አጣሪ መስኮት ላይ በሠልፍ ቆመናል፡፡ አንድ መንገደኛ ለማስተናገድ ከሃያ ደቂቃ ያላነሰ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ፖስፖርት ከጠየቁ በኋላ አገላብጦ ማየት፣ ፎቶ ኮፒ ማድረግ፣ ድጋሚ ስካን ማድረግ እንግዳን በተደጋጋሚ ከፎቶ ጋር የማስተያየት ሥራ ሲሠሩ ብዙ  አቆዩን፡፡ እነዚህ ፍተሻዎች በአፍሪካውያን ላይ ጠንከር ያሉ ነበር፡፡

በፊፋ ጋባዥነት ወደ ሥፍራው ያመሩት ሦስት ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ከሪፖርተር፣ ከአዲስ አድማስና ከሊግ ስፖርት ነበሩ፡፡ እንደደረስን በሩሲያ የማስተርስ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ኤርፖርት ጠብቀውን ከወሰዱን በኋላ ስለሞስኮ ከተማ አንዳንድ ነገሮችን እየነገሩን ወደ ኢትዮጵያውያን ቤት አመራን፡፡ በአውቶሞቢል ውስጥ በነበርንበት ወቅት መንገዶቿ በመብራት ያሽቆጠቆጠችውን የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በመስኮት እየቃኘን እነሱ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች እያወጉን ነበር፡፡ በጎዳናዎቹ ላይ ሰው የማይታይባት ሞስኮ እንደ እኔ ላለው እንግዳ ትንግርት ሆናለች፡፡ በከተማዋ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ነዋሪ እንደሚኖርባት የሚነገርላት ሞስኮ በጎዳናዎቿ ዝር የሚል አለመኖሩ እንዴት ነው ነገሩ ማስባሉ አይቀርም፡፡

ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያዊ የአቬኑ ካፌ ባለቤት አቶ ተፈራ የኋላ ጋር ለማረፍ ተገደድን፡፡ አቶ ተፈራ በሩሲያ ኑሯቸውን ካደረጉ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ከአንዲት ሩሲያዊት ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አቶ ተፈራ ከተለያዩ ከአፍሪካ አገሮች የትምህርት ዕድል ላገኙት ተማሪዎች መናኸሪያ የሆነችውን ካፌ ከከፈቱም ቆይተዋል፡፡

በሩሲያ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው በሚክሉማካያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የምትገኘው አቬኑ ካፌ ኢትዮጵያዊያንን ታሰባስባለች፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በሩሲያ ኑሯቸውን ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም ስለአገራቸው የሚወያዩባት፣ የተለያዩ የሐባሻ ምግቦችንና መጠጦችን የሚያገኙበት ሥፍራም ነች፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለሌሎች አፍሪካውያን መሰባሰቢያ ነች፡፡

እኛም ሩሲያ ከደረስንበት ጊዜ ጀምሮ ማረፊያችንን በዚህ አቬኑ ካፌ ውስጥ አድርገን ነበር የከረምነው፡፡ በቆይታችንም አማርኛ ቋንቋ ማውራት የናፈቃቸው ኢትዮጵያዊያን ከሩሲያኛው ቋንቋ ጋር እየተቀላቀለባቸውም ቢሆን ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ይጠይቁን ጀመር፡፡

በሶቪየት ኅብረት ወቅት በሩሲያ የሚኖሩ የኢትዮጵያን ቁጥር ከ20 ሺሕ በላይ እንደነበር፣ አሁን ግን ቁጥሩ ወደ 300 መውረዱን ነገሩን፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት አገሪቱ ለውጭ ዜጋ ያላት ጥብቅ የሆነ ሕግና ያለባት የኢኮኖሚ መላሸቅ ነው፡፡

ኑሮዋቸውን በሩሲያ ካደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል 20ዎቹ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በሩሲያ ለረዥም ጊዜ የኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ነዋሪዎች ጥቂቶቹ ከሩሲያውያን ጋር ትዳር የመሠረቱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ የአገሪቷን ቋንቋና ባህል በማወቃቸው በተለያዩ ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የመሥራት ዕድል ያገኙ ናቸው፡፡ ከሩሲያዊያን ጋር በትዳር ተጣምረው አብረው የዘለቁ ጥቂቶቹ ብቻ እንደሆኑ ይነገራል፡፡

በየዓመቱ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ሩሲያ የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር ከ13 እንደማይበልጥ በሩሲያ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ሞስኮና ሩሲኪዎች

በጥቅጥቅ ደን የተከበበችው የሩሲያዊያን መሰባሰቢያ ከተማ ሞስኮ፣ ለማያውቃት ግር ትላለች፡፡ ሕዝቦችዋ በዋዛ ፈዛዛ ሰዓት የሚያባክኑ ዓይነት አይደሉም፡፡ በፍጥነት ሲራመዱ ማየትም አግራሞትን ያጭራል፡፡ አብዛኛው የሞስኮ ነዋሪ የከተማዋን ሜትሮ (የመሬት ውስጥ ትራንስፖርት) ተጠቃሚ ነው፡፡

ከምድር በታች  ፈጣን ባቡር የሚጠባበቁበት ጣቢያ በተለያዩ ታሪካዊ ቅርፃ ቅርፆች የተሞላ ሲሆን፣ ውበቱም የቤተ መንግሥት ይመስላል፡፡

በ15 ቀለማት የተለየው የከተማዋ መዳረሻ በሞስኮ ከተማ የሚኖረው 75 በመቶ ኅብረተሰብ ይጠቀማቸዋል፡፡ ወደ አንዱ የከተማዋ አካባቢ ለማቅናት ብዙም ሳይቸገሩ ለአካባቢዎቹ የተሰጡትን መለያ ቀለሞች መከተል በቂ ነው፡፡ ከአንድ ጣቢያ ጫፍ ወደ አንደኛው ጫፍ ጣቢያ ለማምራት ከአንድ ሰዓት በላይ ይወስዳል፡፡ የባቡር አገልግሎት ኤሌክትሮኒካል የክፍያ ዘዴ የሚጠቀም  ሲሆን፣ ባቡሮቹ ከ45 ሴኮንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቶሎ ቶሎ ከአንድ ጣቢያ ወደ ሌላኛው ይደርሳሉ፡፡ ይህ የባቡር አገልግሎት 56 ብር ለአንድ ጉዞ የሚያስከፍል ሲሆን፣ የወርና የዓመት ትኬት ለሚገዛም ቅናሽ ይኖራል፡፡

በፈጣኑ የሜትሮ ትራንስፖርት ውስጥ ሩሲያዎችና መጻሕፍት አይለያዩም፡፡ ማንበብ ባህላቸው ነው፡፡ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎችና አዛውንቶች በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ይዘው በአንደኛው የባቡር እጀታ ተደግፈው ማንበብ የሚያቆሙት የመውረጃ ቦታቸው ሲደርሱ ብቻ ነው፡፡

የሜትሮ ባቡሮች ከጠዋቱ 11 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት ያለምንም መታከት ሕዝባቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብም ያለምንም ሐሳብ ወደፈለገበት ሲንሸራሸር ይውላል፡፡

ከ40 ዓመታት በፊት የተሠሩት እነዚህ የከተማ ሜትሮ ባቡሮች ማገልገል ከጀመሩ አምስት ዓመት እንኳን የሞላቸው አይመስሉም፡፡ በባቡር ውስጥ ቆሻሻ መጣልና ለአዋቂ አለመነሳት ነውር ነው፡፡ የከተማው ሕዝብ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ በየሰፈራቸው በርከት ያሉ ብስክሌቶች አሏቸው፡፡ ብስክሌቶች በቅርብ ርቀት ላይ ቁጥራቸው ከ15 ያላነሰ ለሕዝቡ ይቀመጣሉ፡፡ አንድ ተገልጋይም እጁ ላይ ባለውና እንደ ቁልፍ በሚያገለግለው ካርድ በመጠቀም ወደፈለገበት ሥፍራ ካመራ በኋላ በአግባቡ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

ከተሰመረላቸው መስመር ውልፍት የማይሉት ሩሲያውያን ለሌላ አገሮች ቋንቋና ባህል ቦታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ አሌክሳንድራ ፒቱርካን ተወልዳ ያደገችው ሞሰኮ ነው፡፡ ስለአገሯ ሥነ ጽሑፍ፣ ጥበብና ታሪክ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ እንደ እሷ ያሉን ከራሳቸው የሩሲያ ቋንቋ ውጪ የሌላ አገር ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች በሩሲያ ማግኘት መታደል ነው፡፡ አሌክሳንድራ እንግሊዝኛ አቀላጥፋ ታወራለች፡፡ ሩሲያ ስለሌላ አገሮች ባህል ወይም ጥበብ የማታተኩረው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ሲቀርብላት፣ ቆፍጠን ብላ ሩሲያኖች በሙዚቃም በፊልምም እንዲሁም በጥበብ ሀብታም ስለሆኑ የሌላን አገር ባህልና ቋንቋ ማወቅ ግዴታ አይደለም ትላለች፡፡

31 ቀናት በሩሲያ ምድር

 

ሞስኮ 2,511 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ትገኛለች፡፡ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንደሚኖርባት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለስደተኞችም ፊት የማይሰጠው የሩሲያ መንግሥት በከተማዋ ያለፍቃድ መኖር የማይታሰብ ነው፡፡ ትውልደ ኤርትራዊ የሆነው አብርሃም ገብረዮሐንስ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል ከጀመረ አንድ ዓመት እንዳለፈው ይናገራል፡፡ አብርሃም በኤርትራ 14 ዓመት በእንግሊዝኛ መምህርነት አገልግሏል፡፡ በአገሪቷም የነበረው የኑሮ አለመመቻቸት ወደ ሩሲያ እንዲሰደድ አስገድዶታል፡፡

‹‹ከመጣሁ አንድ ዓመት አልፎኛል፡፡ የተለያዩ ምክንያት እየሰጡኝ ከመመላለስ ውጪ ምንም ዓይነት መፍትሔ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ከእኔ ጠበቃ ጋር ጨርሰናል ያልነውን ሒደት እነሱ ትክክል አይደለም እያሉ ያመላልሱኛል፤›› በማለት አብርሃም ፍቃድ ለማግኘት ያለውን አሰልቺ ሒደት ይናገራል፡፡ እንደ አብርሃም ያሉ ግን የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው እንደ ሌባና ፖሊስ እየተደባበቁ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡

ሞስኮና ታሪካዊ ቅርፆቿ

ሞስኮ በታሪካዊ ሀውልቶች ሀብታም ነች ቢባል ድፍረት አይሆንም፡፡ ሞስኮ ብቻ ሳትሆን የሩሲያ ሌሎች ከተሞችም በቅርፃ ቅርፅ የተሞሉ ናቸው፡፡ ጥበብን፣ ባህልን ፖለቲካን የሚያሳዩ ቅርፆቻቸውንና የጀግኖቻቸውን ሐውልቶች በተለያዩ የከተማ ቦታዎች ላይ በክብር ያኖራሉ፡፡

እ.ኤ.አ. 1937 የተቀረፁና ወንድና ሴት ማጭድና መዶሻ በመያዝ በጊዜው የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍና የሚያመለክተው ሐውልት ሩሲያን የሶቪየት ዘመን ያስታውሳል፡፡ ሩሲያዊያን ያላቸው ጥበባዊ ሐውልቶች ከአገር ወዳድነታቸው ጋር እንደሚያያዝ ይገልጻል፡፡ በሩሲያ ከሚገኙ ታሪካዊ ሐውልቶች የላባደሮች ሕይወት ተምሳሌት የሆነው ሐውልት 24.5 ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ በሩሲያው ቀራፂ ቬራ ሞኪና መቀረፁ ይነገራል፡፡ ከሥነ ጽሑፍም ዘርፍ የፌዲዮር ዶስቶቮስኪና አሌክሳንደር ፑሽኪን ሐውልቶች ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ናቸው፡፡

በፖለቲካውም መስክ አገሪቷን የራሷ የሆነ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም እንዲኖራት ትልቀ አስተዋፅኦ ያደረገው ቭላድሚር ሌኒን፣ በከተሞቹ ዓይን በሆኑ ቦታዎች ሐውልቶቹ ተቀምጦለት በቱሪስቶች ሲጨናነቅ ይስተዋላል፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂውም ቢሆን እነሱ የደረሱበትን ደረጃ የሚገልጽ የጠፍር ጅማሮና ሮኬትን በሌላኛው የሩሲያ ከተማ ሰማራ ይገኛል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሩሲያውያን የናዚን ሠራዊት የጣሉበትን ‹‹ማዘርላንድ ኮል›› በመባል የሚታወቀው ታሪካዊ ቀን ለማሰብ ከተማውን የሚወክል ሐውልት አኑረዋል፡፡

የሩሲያ ሠዓሊያን በየጎዳናው ጥቂት ሳንቲም እየተከፈላቸው የሚሥሉት ሥዕል፣ ከፎቶ ግራፍ ያልተናነሰ የራስን ምሥል በብሩሻቸውና በቀለማቸው በመታገዝ ማስታወሻ ለመስጠት ደቂቃ አይወስድባቸውም፡፡ በፒተርስበርግ፣ ሰማራ፣ ሶቺ እና ቮልጎግራድ ከተሞች ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችን መመልከት ወደ ኋላ 40 እና 50 ዓመታት በትዝታ ይወስዳል፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች ታዲያ ቢያረጁ እንኳን ቀድሞ የነበራቸው ዲዛይን ሳያልቁ እንዲታደሱ ይደረጋል፡፡

ሌላኛው በሞስኮ የቱሪስት መስህብ የሆነው የሞስኮ የክሬሚሊን ቤተ መንግሥት ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ እ.ኤ.አ. 1937 ዓ.ም. እንደተገነባ ይነገርለታል፡፡ ሞስኮ 45 በላይ ብሔራዊ ሙዚየም አላት፡፡ እነዚህም ሙዚየሞች በየቀኑ ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥርን ያስተናግዳሉ፡፡ ሩሲያዊያን በሁሉም ነገር ቀዳሚ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ በዚህም ራሳቸውንና ራሳቸውን ብቻ ይዘው መኖር ይፈልጋሉ፡፡ በዓለም ዋንጫውም ፕሮግራም ወደ ሩሲያ የተመሙ የዓለም ሕዝቦች ይህንን እውነታ ለመረዳት አልተቸገሩም፡፡ ይኼን ነገር ለመረዳት ውድድሩ ሲጠናቀቅም በቋንቋቸው ‹‹ኢስባሲባ›› እናመሠግናለን ብለው እንግዶቻቸውን ሸኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...