Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየመድረክ ፈርጡ ፍቃዱ ተክለ ማርያም (1948-2010)

  የመድረክ ፈርጡ ፍቃዱ ተክለ ማርያም (1948-2010)

  ቀን:

  በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ አንጋፋ አርቲስቶች መካከል ፍቃዱ ተክለ ማርያም አንዱ ነው፡፡ ትህትናውንና ሰው አክባሪነቱን የሙያ አጋሮቹ፣ በአጋጣሚ ያገኙትና አድናቂዎቹም የሚመሰክሩለት ትልቁ አርቲስት ፍቃዱ፣ በዚህ ሙያ ለ43 ዓመታት ያህል አገልግሏል፡፡ የተወለደው 1948 ዓ.ም. አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ሲሆን፣ ትምህርቱንም በሚያዝያ 27 እና አፄ ናሆም በተባሉ ትምህርት ቤቶች ሲከታተል ቆይቶ ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ ወደ ጥበብ መንደር ጎራ ብሏል፡፡

  ገና በልጅነቱ የተቀላቀለው የጥበብ ሙያ እንደ ፍቃዱ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች አንጥሮ ለማውጣት ጊዜ አይፈጅምና ፍቃዱ በልጅነት ዕድሜው ዕውቅና ማትረፍ እንደቻለ ይነገራል፡፡ በ1967 ዓ.ም. ማዘጋጃ ቤት ተቀጥሮ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህር አዳራሽ በርካታ ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡ ወደ ብሔራዊ ቴአትር የተዘዋወረው በ1985 ዓ.ም. ነበር፡፡

  በሥራዎቹ ከፍተኛ ዕውቅናን ማትረፍ የቻለው አርቲስቱ የተለያዩ ቴአትሮችን በምሥራቅ በጀርመን፣ በስዊድን፣ በካሜሩንና ሌሎች አገሮች ተንቀሳቅሶ አቅርቧል፡፡ በ1996 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የሥነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ድርጅት በትወና ዘርፍ ረዥም ጊዜ በማገልገል ሽልማት ተቀብሏል፡፡ በሙያው በቆየባቸው 43 ዓመታት 150 የሚሆኑ ቴአትሮችን፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ድራማዎችን ሠርቷል፡፡

  አብዛኛውን ጊዜ የንጉሥ ገፀ ባህሪን የሚጫወተው ፍቃዱ በንጉሥ ዓርማህ፣ በቴዎድሮስና በሐምሌት ቴአትሮች የንጉሥ ካባ ተጎናጽፎ በተለያዩ መድረኮች ተንጎራዷል፣ የንጉሥን ክብር ከፍ በሚያደርግ ግርማ ሞገስ መድረክ አንቀጥቅጧል፣ ሎሌዎቹንም አራውጧል፡፡ የአፄው ሕይወት መቋጫ የሆነውን የመቅደላን ጦርነት በቃሉ እያነበነበ እንደ ንጉሡ ሁሉ የገዛ ሽጉጡን ጠጥቶ በወደቀባቸው መድረኮች የንጉሡን አገር ወዳድነት ሲያጎላ፣ የእሱንም የተውኔት ብቃት አሳይቷል፡፡

  ኦቴሎ፣ መርዛማ ጥላ፣ የቃቄ ውርዶት፣ ቤቱ፣ ባለካባና ባለዳባ በተሰኙ ቴአትሮችም ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ገመና በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም  ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ የሰው ልብ ውስጥ ከከተቱት ዋነኛ ሥራዎች መካከል ግን ‹‹ባለጉዳይ›› ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው ባለጉዳይ የተሰኘው በሰማኒያዎቹ ይታይ የነበረ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ፍቃዱ ወንደ ላጤ ሆኖ ነበር የሚሠራው፡፡ የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹ ችግሮቹን ለመፍታት ማዘጋጃ ቤት በመመላለስ ከጉበኛ ኃላፊዎች ጋር የሚያደርገውን ፍጥጫ ያሳያል፡፡

  ፍቃዱ ከመጽሐፍት ዓለም በተሰኘው የሬዲዮ ትረካ ፕሮግራም የተለያዩ መጽሐፍቶችን ተርኳል፡፡ ሳቤላ፣ ጥቁር ደምና የነበረው እንዳልነበር የተሰኙ መጽሐፎች በተረኮቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ለወትሮ በሥራዎቹ የሚያዝናናው ፍቃዱ አሳዛኝ ዜና የተሰማው ከወራት በፊት ኩላሊቶቹ ሥራቸውን ሲያቆሙ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኝ የሚያስችለውን ወጪ ከሕዝቡ ተሰባስቦ ነበር፡፡ ይሁንና ለሕክምና የተዋጣውን ገንዘብ በተመሳሳይ ሕመም ለምትሰቃይ የ18 ዓመት ወጣት ሕክምና እንዲውል ሰጥቶ ነበር፡፡ መንግሥትም ለአርቲስቱ የሚያስፈልገውን ሙሉ የሕክምና ወጪ ሸፍኖ ለማሳከም መዘጋጀቱን አስታውቆ ነበር፡፡

  በኩላሊት ሕመም ሲቃይ የከረመው አንጋፋው አርቲስት በቅድስት አርሴማ ገዳም ፀበል ሲከታታል ቆይቶ ማክሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ የዚህ አስደንጋጭ ዜና በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንደተሰማ በርካቶች ሲደነግጡ፣ ሐሰት ነው የሚል ጥርጣሬም ፈጥሮ ነበር፡፡ የአርቲስት ፍቃዱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ሐሙስ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አጋሮቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡ አርቲስት ፍቃዱ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...