Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተጋረጡባቸው ፈተናዎች በምርታማነታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን አስታወቁ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ውስጥ ሲሚንቶ አምራቾች የተጋረጡባቸው የተለያዩ ፈተናዎች፣ በምርታማነታቸውና ትርፋማነታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደሩባቸው አስታወቁ፡፡

ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከፈተው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ የኮንክትሪትና የኢነርጂ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የደርባ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ በበቂ ሁኔታ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ እየጨመረ በመጣው የኃይል ወጪና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለኢንዱስትሪው ከፍተኛ ማነቆ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ መስፋፋቱን፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሲሚንቶ ከውጭ ስታስገባ የነበረች አገር  ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ የሲሚንቶ አምራቾችን እየተገዳደሩ ያሉ ችግሮች በጋራ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

አቶ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የውጭ ባለሙያዎች ቀጥረው ለማሠራት ተገደዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች ሥልጠና የሚጀምሩት በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ ነው፡፡ በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የሠለጠኑ ኢንጂነሮች የሉንም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ባለሙያዎችን ከቻይና፣ ከህንድና ከሌሎች አገሮች እናመጣለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ደርባ፣ ዳንጎቴና ናሽናል ሲሚንቶ ያሉ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚንቀሳቀሱት በአብዛኛው በውጭ ባለሙያዎች ስለሆነ የውጭ ምንዛሪ ወጪያቸውን እንደሚያንረው ተገልጿል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ እንደሆነ አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ማሠልጠኛ ማዕከል በማቋቋም ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ በሦስት ዓመት ውስጥ የውጭ ባለሙያዎችን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለመተካት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

ሌላው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን እየተፈታተነው ያለው ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ እንደ አቶ ኃይሌ ገለጻ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት አንድ ጊዜ ሙሉ  ዕድሳት ያደርጋሉ፡፡ ዓመታዊ ጥገና በሚካሄድበት ወቅት በርካታ መለዋወጫዎች ከውጭ ተገዝተው ይገባሉ፡፡

‹‹ዓመታዊ ጥገና ከመጀመሩ በፊት መለዋወጫዎቹ ተገዝተው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠመን ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ ጥገናው በአግባቡ ካልተካሄደ በፋብሪካው ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው ውይይት ቢያካሂድም፣ የውጭ ምንዛሪ ጥረት አገራዊ ችግር በመሆኑ መፍትሔ የሚሰጠው በመንግሥት በሚቀመጠው አቅጣጫ ስለሆነ በሒደት እየተቀረፈ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ሲሚንቶ አምራቾች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተለየ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እንዲኖራቸው ቢደረግም፣ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በማሽኖች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ፣ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ኢንዱስትሪ እመርታ እንዳሳየ  ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት አንደኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ካጋጠመው ችግሮች መካከል አንዱ ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ እጥረት እንደነበር የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ አጠቃላይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የማምረት አቅም 2.3 ሚሊዮን ቶን እንደነበርና ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ቶን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

መንግሥት በወሰዳቸው ጠንካራ ዕርምጃዎችና ባመቻቸው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተጠቅመው በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በሲሚንቶ ዘርፍ ኢንቨስት በማድረጋቸው፣ ሁኔታዎች እንደተለወጡ አስረድተዋል፡፡ ደርባ፣ ዳንጎቴ፣ መሰቦና ናሽናል ሲሚንቶ ባካሄዱዋቸው መጠነ ሰፊ የፋብሪካ ግንባታዎች የሲሚንቶ ገበያውን ማረጋጋት እንደተቻለ የገለጹ አቶ ሳሙኤል፣ እ.ኤ.አ. በ2017 አጠቃላይ አገራዊ የሲሚንቶ ምርት 15.1 ሚሊዮን ቶን ሊደርስ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ እንደሆኑ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎች ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች ሥልጠና የሚሰጡበት የዕውቀት ሽግግር መርሐ ግብር ተቀርፆ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና የፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ የሲሚንቶ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሚያፈሩበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲሚንቶ ቴክኖሎጂ የሠለጠኑ ኢንጂነሮች በማፍራት የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንደሚኖርባቸው፣ የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር አስታውቋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረትን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት አቶ ሳሙኤል ያለውን ውስን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ማከፋፈል ላይ ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አገሪቱ ውስጥ ተከስቶ ከነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ግንኙነት አለው፡፡ አዲሱ አመራር እየወሰዳቸው ባሉ የለውጥ ዕርምጃዎች ችግሩ እየተቀረፈ በመሆኑ፣ በመጪው ዓመት አምራቾች የውጭ ምንዛሪ እጥረት አይገጥማቸውም የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንደሌለ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ እየተከሰተ ያለው ከኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮችና ከኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ችግር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ አገልግሎት ችግሩን ለመቅረፍ ሰፊ የኤሌክትሪክ መስመርና የማከፋፊያ ጣቢያዎች ግንባታዎች በማካሄድ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲታመሱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ማጓጓዝ ተስኗቸው የነበረ ሲሆን፣ በተካሄዱት ሕዝባዊ አመፆች የጭነት ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች እንደተቃጠሉባቸው አይዘነጋም፡፡ የሲሚንቶ ማምረቻ ግብዓቶች ከሆኑ ማዕድናት ምርት ጋር በተያያዘም ከአካባቢ ወጣቶች ጋር ግጭቶች መፈጠራቸውና ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች በአብዛኛው መፈታታቸውን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመካከር ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሲሚንቶ ማከፋፈል፣ ስክራፕ በማስወገድና በመሳሰሉ ሥራዎች የተደራጁ ወጣቶች እንዲሳተፉ አድርገን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን ያለው የሥራ አጥ ወጣት ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ፣ ለተወሰኑ ወጣቶች ሥራ ስንፈጥር ሌላው መጥቶ ተመሳሳይ ዕድል እንዲሰጠው ይጠይቃል፤›› ያሉት አቶ ኃይሌ፣ ይህንን ችግር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ብቻቸውን የሚወጡት ባለመሆኑ ሌሎችም ፋብሪካዎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ የኮንክሪትና የኢነርጂ ጉባዔ በሰው ኃይል ልማትና አማራጭ የኃይል ምንጭ ላይ ትኩረት አድርጎ ለሁለት ቀናት ተወያይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች