Sunday, October 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የጥላቻና የቂም በቀል ምዕራፍ ይዘጋ!

የኢትዮጵያ የግማሽ ክፍለ ዘመን ፖለቲካ እጅግ በጣም ከመወሳሰቡ የተነሳ፣ በወንድማማቾች መካከል የጥላቻና የቂም በቀል አጥር አበጅቷል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ችግርን ፈቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከማካሄድ ይልቅ፣ በጥላቻና በቂም በቀል በመመራረዝ ለአገር የሚጠቅሙ መልካም አጋጣሚዎች መክነው ቀርተዋል፡፡ ሕዝብንና አገርን ማዕከል ባላደረጉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት በመደረጉ፣ ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ወገኖች የባዕዳን መገልገያ ሆነዋል፡፡ በሸር፣ በሴራ፣ በአሻጥርና በጽንፈኝነት የተተበተቡ ፖለቲከኞች ለሥልጣን በሚያደርጉት ትንቅንቅ ሕዝብ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኗል፡፡ ሥልጣን ላይ የወጡት ንቅንቅ አንልም በማለት የፖለቲካውን ምኅዳር በአምባገነንነት ሲዘጋጉት፣ ከእነሱ በተቃራኒ ያሉ ኃይሎችም እነሱን ለማውረድ በተደረጉ ግብግቦች በርካታ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ በአገር የጋራ ጉዳዮች ላይ መስማማት ጠፍቶ አንዱ ሌላውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያልተፈጸሙ ደባዎች የሉም፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል እየተወራረሱም እዚህ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለሰላምና ለፍቅር ሲባል በይቅር ባይነት ስሜት መቀራረብ በመጀመሩ ዋና ዋና ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአገር ውስጥና በውጭ የተለገሳቸው ድጋፍ፣ ጥላቻና ቂም በቀል ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሱ ያመለክታል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በአሜሪካ ሦስት ከተሞች ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉዋቸው ውይይቶች፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተበድላ እንደኖረች ማሳያ ናቸው፡፡ ለዓመታት የተጋረጠውን መሰናክል አስወግዶ በኢትዮጵያውያን መካከል ግንኙነቱን ለማጠናከር የተደረገው ጥረት እንዲህ በቀላሉ የተገኘ አይደለም፡፡ የሻከሩ ግንኙነቶችን ለማደስ፣ ቂምና ጥላቻን ለማስወገድና በይቅር ባይነት ስሜት አንድ ላይ ለመቆም የተቻለው፣ በከፍተኛ ልፋት በታጀበ ማግባባት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ጎራዎች ተከፋፍሎ የኖረው የዳያስፖራ ማኅበረሰብን አግባብቶ፣ ኢትዮጵያውያንን ለማገናኘት የተደረገው ጥረት አታካችነት የዘመናት ቁስል የፈጠረውን ጠባሳ በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህ ሁሉ አታካች ጥረት ታልፎ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመው ለአገራቸው አለኝታ እንደሚሆኑ በአደባባይ ሲናገሩ ከማየት በላይ ምን የሚያረካ ነገር አለ? ይህ በብዙ ልፋት የተገኘ አመርቂ ውጤት በሁሉም መስክ መቀጠል አለበት፡፡

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ታሪክ መለስ ብለው ሲያስተውሉ የሚያገኙት፣ መልካም አጋጣሚዎች በከንቱ ሲባክኑ እንደነበር ነው፡፡ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በቁጭት በማስታወስ የነገዋን ኢትዮጵያ ዛሬ ለመገንባት መነሳት ይገባል፡፡ በጥላቻና በቂም በቀል የተሞሉ ልቦች ተከፋፍተው በይቅርታና በፍቅር ሲፈላለጉ፣ የባከኑ መልካም አጋጣሚዎች በሚፈጥሩት ቁጭት የበለጠ ለመሥራት መትጋት የጋራ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ትናንት በፅኑ ተቃውሞ ውስጥ ሆነው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመፋለም በረሃ የገቡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ ሲወስኑ፣ ከዚህ በፊት የነበሩ አላስፈላጊ ተግባራትም እንዳይደገሙ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ትናንት በሕግ ዋስትና ያገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጥሰው በደረሰው ጥፋት ከፍተኛ  ጉዳት የደረሰባቸው ቁስላቸው እንዲሽር፣ ተገፍተው የነበሩ እንኳን ደህና መጣችሁ  ተብለው እንዲስተናገዱ፣ በሕጋዊነት ስም ሲፈጸሙ የነበሩ ሕገወጥ ተግባራት ዳግም እንዳያገረሹ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የምታስተናግድ አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለመሳሰሉት ጠቃሚ ጉዳዮች ሲባል፣ ጥላቻና ቂም በቀል ግብዓተ መሬታቸው መፈጸም አለበት፡፡ ለማንም አይጠቅሙም፡፡

አገር የምትገነባው በመላ ልጆቿ ሁለገብ ተሳትፎ እንደሆነ ሁሉም ወገን ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ የነገዋን ኢትዮጵያ ለሚረከቡ ትውልዶች መሠረት መጣል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው፡፡ አንድነት ልዩነትን የሚያከብር የጋራ መስተጋብር ስለሆነ፣ ከምንም ነገር በላይ በአገር የጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስማማት አሁንም መቀራረብና መነጋገሩን መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የጥላቻ ግንብ ተንዶ ፍርስራሹ ተጠርጓል ሲባል፣ አሁንም ያኮረፉና ግራ የተጋቡ ወገኖች ስለሚኖሩ ጥረትን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውም ሆነ ለሰላሙ የሚበጀው በእኩልነት መነጋገር የሚያስችል ዓውድ መፍጠር ነው፡፡ ይህ ዓውድ በጋራ በመመካከር ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስተካከልና ለማዘመን፣ የፀጥታ ኃይሎችን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ፣ የመንግሥት ቢሮክራሲን ከፓርቲ ተፅዕኖ ለማላቀቅ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈንና ለመሳሰሉት መሠረት ለመጣል ያመቻል፡፡ ከዚህ በፊት በተፈጠሩ መቋሰሎች ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ለማከምና እንደገና እንዳይደገሙ መተማመን ለመፍጠር፣ ጥላቻና ቂም በፍጥነት እንዲወገዱ ሳይታክቱ መሥራት የግድ ይሆናል፡፡ ሕዝብና አገር እስካሁን የደረሰባቸው መከራ ይበቃል፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁሉም የሚናፍቀው ዴሞክራሲ ችግኙ ተኮትኩቶ እንዲፀድቅ፣ ለሐሳብ ነፃነት ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የሚኖረው ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳብ ነፃነት ገበያ እንደመሆኑ መጠን፣ ለሐሳብ ልዩነትም ክብር መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የተለየ ሐሳብን ማጣጣል ወይም መደፍጠጥ ጤነኛ ስለማይሆንና ስለማይጠቅም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሐሳቦች በነፃነት እንዲወዳደሩ ዕድል መስጠት ይገባል፡፡ በሐሳብ መለያየት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን የሚያግባባ አማካይ መፍጠር ደግሞ የማይታለፍ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ዴሞክራሲ በስሙ እንጂ በግብሩ ባለመታወቁ ከፍተኛ አፈና ተካሂዷል፡፡ በማናለብኝነት ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች ተዳፍነዋል፡፡ በሐሳብ ገበያው በነፃነት ተሟግቶ መርታት ሲገባ፣ ጉልበት የበላይነት ይዞ አገር ተተረማምሳለች፡፡ በሰላማዊ መንገድ በነፃነት መከናወን ይገባው የነበረ የአገሪቱ ፖለቲካ ሐዲዱን እንደሳተ ባቡር ካገኘው ነገር ጋር በመላተሙ፣ ኢትዮጵያ የጥፋት አረንቋ ውስጥ እንድትዘፈቅ በማድረግ ልጆቿን ደም አቃብቷል፡፡ ይህ አሳዛኝ ምዕራፍ ይዘጋ፡፡

ኢትዮጵያዊነትን ለመድመቅ ተስፋ በተሰነቀበት በዚህ ጊዜ ከስሜታዊነት በመላቀቅ በምክንያታዊነት መመራት ይጠቅማል፡፡ ስሜታዊነት በምክንያታዊነት ካልተገራ አገርን እንደሚያተራምስና ሕዝብን ቀውስ ውስጥ እንደሚከት ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ እንደሚያምርባቸው ምልክቱ እየታየ ነው፡፡ በበቀል መፈላለግና መጠፋፋት ጥቅም እንደሌለው ታሪካችን ይመሰክራል፡፡ ጥላቻና ቂም በቀልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ አንፀባራቂ ኮከብ መሆን ትችላለች፡፡ አገር በሕግና በሥርዓት እንድትመራ ማድረግ የሚቻለው፣ ዜጎች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት እንዲፈጠር ሁሉም የድርሻውን ሲያዋጣ ነው፡፡ ይህ አስተዋጽኦ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በማኅበራዊና በተያያዥ ዘርፎች እንዲከናወን የጥላቻና የቂም በቀል ምዕራፍ መዘጋት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በአንድነት ሲቆሙ፣ ይህ መልካም ምኞት በተጨባጭ ዕውን ይሆናል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...