Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቦምብ ፍንዳታው ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቀቀ

የቦምብ ፍንዳታው ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቀቀ

ቀን:

ለዓቃቤ ሕግ የክስ መመሥረቻ ጊዜ ተፈቀደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመደገፍና ለማበረታታት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሠልፍ በወጡ ዜጎች ላይ በደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት፣ ኃላፊነትን ባለመወጣትና ቦምብ ወርውረው በማፈንዳት ተጠርጥረው ላለፉት 42 ቀናት (እስከ ዓርብ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ) ሲደረግ የነበረው ምርመራ ተጠናቀቀ፡፡

ቦምብ እንዲወረወር በማቀበል፣ የፋይናንስ ድጋፍ ከሌሎች አካሎች በመቀበልና ኦፕሬሽኑን በስልክ በመምራት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመሥረት 15 ቀናት ለከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተፈቅዷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የቀድሞ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ አሥር የፌዴራል ፖሊስ አባላት ደግሞ፣ በዕለቱ ሊፈጽሙ ይገባቸው የነበረውን በአግባቡ ባለመፈጸም፣ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣትና ክፍተት በመፍጠር የተጠረጠሩበት የምርመራ ጊዜ በመጠናቀቁ፣ ክስ የመመሥረቻ አሥር ቀናት ለዓቃቤ ሕግ ተፈቅዷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሁለት የምርመራ መዝገብ የተከፈሉ ሲሆኑ፣ ዓርብ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት የቀረቡት ከቦምብ ውርወራውና ፍንዳታው ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት አቶ አብዲሳ ቀነኔ፣ አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ፣ አቶ ጌቱ ግርማ፣ ወ/ሪት ሕይወት ገዳ (በአማኑኤል ሆስፒታል በመታከም ላይ ያለች) እና አቶ ባህሩ ቶላ ናቸው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን በዕለቱ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያደርግ የነበረውን የምስክሮችን ቃል መቀበልና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብ አጠናቆ፣ የምርመራ መዝገቡን ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስረክቧል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ከምርመራ ቡድኑ ከአንድ ቀን በፊት ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የምርመራ መዝገብ እንደደረሰው አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የምርመራ መዝገቡ በርካታ ምስክሮች የተሰሙበትና በርካታ ሰነዶች የተሰበሰቡበት መሆኑን ጠቁሞ፣ ‹‹በማን ላይ እነማን መሰከሩ? በእነማን ላይ ምን ዓይነት የሰነድ ማስረጃ ቀረበ?›› የሚለውን መርምሮ ተጠርጣሪዎች ያላቸውን ተሳትፎ በመለየት፣ እንደ ወንጀል ድርሻቸው በሚመሠረትባቸው ክስ የሚጠቀስባቸውን የወንጀል ሕግ አውቆ ክስ ለመመሥረት፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) መሠረት 15 ቀናት ክስ የመመሥረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን አጠናቆ ለከሳሽ ዓቃቤ ሕግ መዝገቡን ማስተላለፉንና ዓቃቤ ሕግም ክስ ለመመሥረት የጠየቀውን 15 ቀናት በሚመለከት ተጠርጣሪዎች ያላቸውን አስተያየት እንዲናገሩ ፍርድ ቤቱ ዕድል ሰጥቶአቸዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹መርማሪ ቡድኑ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ አቆይቶናል፡፡ ምርመራውን ከጨረሰ ክስ ያቅርብብን እንጂ ለምን 15 ቀናት ይጠይቃል? እኛ 24 ሰዓት ተዘግቶብንና ሰብዓዊ ክብራችን ተገፎ ነው ያለነው፡፡ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰብን ነው፡፡ በሕገ መንግሥትና በሕግ በምትተዳደር አገር ለምን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን እንደማይከበርና የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እየተጣሰ መሆኑ አልገባንም፤›› በማለት፣ የዓቃቤ ሕግንና የመርማሪ ቡድኑን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡ የዋስትና መብታቸውም እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት የአያያዝ ጉድለት ላይ በሰጠው ምላሽ እንደተናገረው፣ ተጠርጣሪዎቹ የሰጡት አስተያየት ትክክል አይደለም፡፡ ስላያያዛቸው በቪዲዮ ጭምር ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል ብሎ፣ ሦስተኛና ገለልተኛ አካል ሄዶ ሊያይ እንደሚችል በመግለጽ ያቀረቡት አቤቱታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ እንዳስረዳው፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በደረሰው አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፎ ከ100 በላይ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ መዝገቡን መርምሮ የሚያቀርበውን ክስና የሚጠቅሰውን የሕግ አንቀጽ አሁን ማወቅ ስለማይቻል፣ የዋስትና ጥያቄውን እንደማይቀበል አስረድቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚጠቀስባቸው የሕግ አንቀጽ ዋስትና ሊከለክላቸው ስለሚችል መሆኑንም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን 15 ቀናት ፈቅዶ ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በቀጠሮው ቀን ስለተጠርጣሪዎቹ አያያዝ የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በተመሳሳይ ቀን ከቀትር በኋላ ያየው የምርመራ መዝገብ፣ በምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ፣ በኮማንደር ገብረ ኪዳን አሰግዶም፣ በኮማንደር ገብረ ሥላሴ ተፈራ፣ በኮማንደር ግርማይ በርሄ፣ በኮማንደር አንተነህ ዘነበ፣ በምክትል ኮማንደር አባቡ ዳምጤ፣ በምክትል ኢንስፔክተር ሀገሬ ቀኔሳ፣ በዋና ሳጅን ድራር ታረቀኝ፣ በዋና ሳጅን ከድር ዓሊ፣ በምክትል ኮማንደር አብዲሳ ጋዲሳና በምክትል ኮማንደር ጫኔ ጠቋሬ ላይ የቀረበውን ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከላይ እንደገለጸው የምርመራ ሥራውን አጠናቆ ለፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግም የምርመራ መዝገቡን መረከቡን አረጋግጦ ከላይ በቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረበውን አስተያየት በመግለጽ፣ ክስ ለመመሥረት የሚያስችለውን የ15 ቀናት ጊዜ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) መሠረት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ጠንከር ያለ ተቃውሞ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ በተቃውሟቸው እንዳስረዱት፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) ክስ መመሥረቻ አይልም፡፡ ዓቃቤ ሕግ የክስ መመሥረቻ ሊል የሚችልበት የሕግ መሠረት የለውም፡፡ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ከመጀመርያው ጀምሮ ምርመራ የሚያደርጉት አብረው ነው፡፡ እያቀረቡ ያለው ጥያቄ የሕግ የበላይነትን የጣሰ ነው፡፡ ሰዎች ሊታሰሩ የሚችሉት በሁለት ነገር ብቻ ነው፡፡ አንደኛው በምርመራ ወቅት ምርመራውን ሊያደናቅፉ ይችላሉ ተብሎ ሲታመን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና የሚከለክል ሲሆን ብቻ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ባልተመሠረተ ክስ ላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ያባብላሉ ማለቱ ከማስገረምም በላይ የሕግ መሠረት እንደሌለውም ተናግረዋል፡፡ አንቀጽ 109(1) የሕግ ትርጉም የማያስፈልግው ግልጽ ሕግ መሆኑንና ዓቃቤ ሕግ ከመርማሪ ቡድኑ ጋር አብሮ እንዳልሠራና መዝገቡን እንደማያውቀው መናገሩን፣ ፍርድ ቤቱ የሕግ ግምት (Judicial Notice) እንዲወስድላቸው አስታውሰዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ንፁህ ዜጎች መሆናቸውን ሊደመጡ እንደሚገባ፣ ኢትዮጵያ የእነሱም አገር መሆኗንና ሕግ ቢኖር ኖሮ በ48 ሰዓታት ውስጥ ሊለቀቁ ይገባ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በእነሱ ላይ እንዲፈጸም የማይፈልጉትን በሌላ ሰው ላይ መፈጸም እንደማይፈልጉ ተናግረው፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸውን ፍርድ ቤቱ እንደዲያስከብርላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው የቀረቡትን ተቃውሞና የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡ በመዝገቡ ላይ የሚያውቀው እንደሌለ ለችሎቱ ገልጾ፣ ማን ምን ወንጀል እንደፈጸመ የሚያስረዳውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ውሳኔ በመስጠት ክስ ስለሚመሠርት፣ የሚመሠረተው ክስ ላይ የሚጠቅሰው ሕግ ዋስትና የሚከለክል ወይም የማይከለክል መሆኑን አሁን ማወቅ እንደማይችል በመግለጽ፣ የጠቀሳቸውን ሥራዎች ለማከናወንና ክስ ለመመሥረት 15 ቀናት በሕጉ መሠረት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የተጠርጣሪዎችን ተቃውሞና ዋስትና ጥያቄ በማለፍ፣ ዓቃቤ ሕግ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ ለነሐሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...