Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየተግባር ክትትልና ቁጥጥር የሚሻው የስፖርቱ ዘርፍ ብሔራዊ ስሜቱን ማደስ ጀምሯል  

የተግባር ክትትልና ቁጥጥር የሚሻው የስፖርቱ ዘርፍ ብሔራዊ ስሜቱን ማደስ ጀምሯል  

ቀን:

በአልጀሪያ በተካሔደው ሦስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ከተሳተፈባቸው ስድስት ስፖርቶች በሦስቱ 25 ሜዳሊያዎችን አስመዝግቦ ተመልሷል፡፡

በሌሎችም የስፖርት ዓይነቶች ላይ ወጥነትና ተከታታይነት ያለው ሥልጠናን መሠረት ያደረገ ዝግጅትና ክትትል ማድረግ ቢቻል፣ ከዚህም የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ ይሁንና በቃል የሚነገረው ሁሉ በተግባር እስካልተተረጎመ ድረስ አንድ ዕርምጃ መራመድ ከባድ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በአልጀሪያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ውድድሮች ወቅት ውጤት ላስመዘገበው ቡድን፣ ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ለውጤታማ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡ ከ820,000 ብር በላይ ወጪ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ዕርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶችና  የስፖርት ባለሙያዎችና ሌሎችም አካላት በፕሮግራሙ ተገኝተዋል፡፡ ለአገሪቱ ስፖርት ውድቀትም ሆነ ትንሳዔ በተለይም በአሁኑ ወቅት አንዱ በሌላው ላይ ጣት መጠቋቆሙ ቀርቶ ከመንግሥታዊ አካሉ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚመለከታቸው ሁሉ በጋራ መሥራታቸው ያለውን ጠቀሜታ በማውሳት፣ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች የኅብረተሰቡን የድል ጥማት ለመመለስ መረባረብ እንደሚገባ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹መድረክ ስናገኝ የምንናገረውን ሳይውል ሳያድር ወደ መሬት በማውረድ መሥራት ካልቻልን፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ አገሮች ለስፖርቱ እየሰጡት ካለው ትኩረትና ክትትል አኳያ ልንፎካከራቸው ቀርቶ ልንከተላቸው እንኳ ይቸግረናል፡፡ በሦስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ቁጥርም ሆነ በተሳትፎ የበለጧት አገሮች፣ በአብዛኛው አትሌቶቻቸው ቀጣይነት ባለው ሥልጠናና ዝግጅት የሚሠሩት ናቸው፤›› በማለት የዘላቂ ሥልጠናን አስፈላጊነት አጉልተዋል፡፡ አያይዘውም የተቋሙ ፕሬዚዳንት የሚከተለውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእኛ አሠራርም ሆነ ተሞክሮ ውድድር ሲቃረብ ካልሆነ በቀር፣ ለሥልጠናም ሆነ ለዝግጅት በቂ ጊዜ ሰጥተን አንዘጋጅም፡፡ ውጤት ሲጠፋ ካልሆነ በቀር ድክመቶቻችንን ምንድናቸው፣ ጥንካሬዎቻችንስ? ብለን መድረኮችን የማመቻቸት ባህል የለንም፡፡ ውጤት የምንፈልግ ከሆነ የግድ ይህን አሠራር መቀየር መቻል ይኖርብናል፡፡››

በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በአርጀንቲናዋ ቦነስ አይረስ ከተማ ለሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲጀምሩ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው መወሰኑን አስታውቋል፡፡፡፡

የአቅም ችግር ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ ያሳሰቡት አሸብር (ዶ/ር)፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ በመሆናቸው በሁሉም ረገድ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ከተቻለ፣ በተለይም ከማዘውተሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ችግሮች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ተናቦና ተቀናጅቶ በመንቀሳቀሱ ረገድ በዘርፉ አሁንም ሆነ ወደፊት ክፍተቱ ካልተቀረፈ ግን ሁሉንም ነገር ዋጋቢስ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዕርስቱ በበኩላቸው፣ ‹‹በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ የሆነ ለውጥ እየተካሄደ ነው፡፡ ስፖርቱም የዚሁ አካል ስለሆነ በምክንያት የምናባክነው ጊዜ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ዋንጫ እንድታዘጋጅ፣ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዕድሉን አግኝታለች፡፡ ከዚያ ቀደም ሲልም የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ ከአኅጉራዊው ተቋም ጋር ስምምነት ተደርሷል፡፡ ሌሎችም በርካታ ዝግጅቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ መጪውን ጊዜ በቀላሉ አንመለከተውም፤›› በማለት ሁሉም በየድርሻው መሠረት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ የስፖርቱ ተዋንያን ከእንግዲህ ውጤት ለማምጣት በአንድነት መሥራት ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን በማውሳት፣ እንደ አሸብር (ዶ/ር) ሁሉ እሳቸውም ከንግግር ባለፈ ዕቅዶችን ወደ መሬት በማውረድ በአንድነት መሥራትና መንቀሳቀስ ሲቻል ውጤት እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ማዘውተሪያዎች ለስፖርቱ ዕድገት ከመትጋት ይልቅ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጓደል ምክንያት የሚሆኑበት አካሄድ ፍጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው አፅንኦት ሰጥተውበታል፡፡

የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የወጣቶችና ስፖርት ኃላፊዎችም ይኼንኑ በማጠናከር በሁሉም ስፖርቶች ወጣቶች ተገቢውን ሥልጠናና ዝግጅት እንዲሁም ክትትልና ትኩረት ካገኙ፣ የክህሎትም ሆነ የአቅም ችግር እንደሌለባቸው ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ያደረጉትም በአልጀሪያ ሜዳሊያ ከተገኘባቸው ስፖርቶች ቦክስና ወርልድ ቴኳንዶን ነው፡፡ እነዚህ ስፖርቶች ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠናና ዝግጅት ሊያገኙ ቀርቶ የሚዲያ ሽፋን እንኳ እንደማይሰጣቸው በመግለጽ፣ ለወደፊቱ በዕቅድ መንቀሳቀስ ከተቻለ እ.ኤ.አ. በ2020 ለሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በሌሎችም ስፖርቶች ውክልና ብቻ ሳይሆን፣ ውጤት የማይመዘገብበት ምክንያት እንደማይኖር በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ውጤት ያስመዘገቡ አሠልጣኞችም ሆኑ አትሌቶች ለስፖርቱ ውድቀት ምክንያት ተብሎ በቀረበው ነጥብ ላይ ሙሉ በሙሉ  እንደሚስማሙ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባልና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በየበኩላቸው፣ አትሌቲክሱን ጨምሮ ለሁሉም ስፖርቶች ውድቀት የመርኅና የዕቅድ ክፍተት ካልሆነ በቀር የአቅም ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ አሠልጣኟ የዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ (ነፍስ ኄር) የውጤታማነት ምስጢር ምን እንደ ነበር በማስቀደም አስተያየቷን ያከለችው ኮሎኔል ደራርቱ፣ ቀናነት በተመላበት ሁሉም የድርሻውንና የአቅሙን ማበርከት ከቻለ፣ ኢትዮጵያ በሁሉም ስፖርት የወላድ መካን እንዳልሆነች ለማሳየት ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በአልጀርሱ ውድድር ላመጡት ውጤት ዕውቅና ከተሰጣቸው ታዳጊ ወጣቶች መረዳት እንደሚቻል ተናግራለች፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁሉም ስፖርቶች ማለት በሚቻል መልኩ ማዘውተሪያዎች ከመዝናኛነታቸው ይልቅ የውዝግብና የጠብ አደባባይ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይ በአትሌቲክሱ መስክ ቀደምቶቹ የሚታወቁበትን የብሔራዊ ቡድን ስሜት እየጠፋው መምጣቱን የሚናገሩ አሉ፡፡ ይኼንን ሥጋት ከሚጋሩት መካከል የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ አንዱ ነው፡፡ በመድረኩ ያስተላለፈው መልዕክትም ይኼንኑ ሥጋቱን ያመላከተ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡

ሻለቃ ኃይሌ ከውጤቱም በላይ በአልጀርሱ ተሳታፊ ልዑክ ውስጥ ቀደም ሲል ጠፍቶ የነበረው ብሔራዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ተመልሶ ማየቱ እጅጉን እንዳስደሰተው ተናግሯል፡፡ በዚህ ላይ የሚመክር መድረክ ወደፊት እንደሚኖር ያስረዳው ኃይሌ፣ ዝርዝሩን ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ አብራርቷል፡፡

ከውጤቱ ጋር በተያያዘ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ብሔራዊ ቡድን በሆቴል አስቀምጦ ዘለቄታ ያለው ዝግጅት ማድረግ እንደሚያዳግት፣ ከዚህ ይልቅ አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሜ ከብክሌት ጋር የሚያያዝ ችግር ለማይነሳባቸው ስፖርቶች አገልግሎት እንዲሰጥ ቢደረግ፣ አትሌቲክሱን በተመለከተም አሰላ የሚገኘውን ጥሩነሽ ዲባባ የወጣቶች ማሠልጠኛ ማዕከልን መጠቀም እንዲቻል የሚያግዙ አሠራሮች መፈጠር እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውና ሌሎች ፌዴሬሽኖችም ይኼንኑ አስተያየት እንደሚጋሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ስፖርት አካዴሚ ዋና ዳይሬተር አቶ አምበሳው እንየው በበኩላቸው፣ አካዴሜው በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት ኢትዮጵያን በሚወክሉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ብሔራዊ አትሌቶችን በማውጣቱ ረገድ ትልቁን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ በአልጄሪያው ቡድን ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያህሉ አትሌቶች የአካዴሜው ውጤቶች ስለመሆናቸውም አስረድተዋል፡፡ አካዴሜው ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ያለውን የቅንጅት አሠራር አስመልክቶ በጋራ ለመሥራት በገቡት ስምምነት መሠረት ሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በተቋሙ እየተገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም አሁን ላይ እየፈሰሰበት ያለውን መዋዕለ ንዋይና የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ አሠራሩን ፈትሾ በውጤት መስክ ተስፋ እያሳዩ ከሚታዩት ስፖርቶች ጎን እንዲሠለፍ ክልሎች ጠይቀዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የታደሙት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ይኼንኑ ሐሳብ እንዲቀበሉ ክልሎቹ ጠይቀዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከወትሮው በተለየ መልኩ ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳድሮች፣ ለአትሌቶችና ለሙያተኞች የሚያደርገውን የገንዘብና የዓይነት ዕገዛና ድጋፍ በጀመረው መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥልበት የክልል ተወካዮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...