በምድር ላይ ታላቁ ፍጡር ሰው ነው፡፡ ታዲያ ታላቁ ፍጡር በዚህ ዘመን ወርዶ መደረግ የማይገባውን ተግባር ሲፈጽም እናያለን፡፡ አገር ማለት ሰው ነው፡፡ ተራራው፣ ወንዙ፣ በውስጡ ያለው ማዕድንና ብርቅዬ ሀብት ብቻ አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ከዚህ ቀዬ ውጣልን ብሎ ሰው መግደልና ንብረት ማቃጠል የሰውኛ አስተሳሰባችንን ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለው፣ ‹‹ነብር ዥጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም፡፡››
በዘሁኑ ጊዜ የምናየው ኢትዮጵያዊ እሴታችን ሲቦረቦር ነው፡፡ አብረን መኖራችን ቀርቶ መገፋፋታችን አይሏል፡፡ ለሁላችን የምትበቃውን ኢትዮጵያንን ለማፍረስ የተነሳን ይመስላል፡፡ ግን ለምን? ሰው ከሰው ወዲያ ማን ሊመጣለት? በራስ ወዳድነትና በጥላቻ ተሞልተን መልካሙንና ቀናውን እንዴት ማየት ተሳነን? ለአንዳችን የሚያስፈልገውን ለሌላውም እንደሚያስፈልገው እንዴት ጠፋብን? እኔ ብቻ ትክክለኛ ነኝ፣ እኔ ተበድያለሁ፣ ለእኔ ይገባኛል በማለት ታውረን ማየት ያልቻልነው እውነትና መልካምነት ለሁላችንም ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ራሳችንን ቆም ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ጥላቻን ማራገቡ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ሲቻል ሰውን ያህል ታላቅ ፍጡር፣ ያውም የአገር አለኝታዎችን ለምን መግደል አስፈለገ?
ያሳዝናል፡፡ ይኼ ከኃቀኝነት ያፈነገጠ እኩይ ድርጊት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችን ናትና ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን እሾህና አሜኬላ አናውርሳቸው፡፡ አንዳችን ከአንዳችን አንበልጥም፡፡ ሁላችንም እኩል እንጠቀም፡፡ በልፋታችንና በዕውቀታችን እንበልፅግ፡፡ እኩል እንደግ፤ እኩል እንኑር፡፡ ታዲያ ይኼ ሁሉ የሚሆነው ግን በመግደል፣ በማጥፋት አይደለም፡፡ ለአገር የሚሠሩ ሰዎችንም ብንገድል በሟቾች ደም ላይ ሚሊዮን ጀግና ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ቂም አንዝራ፡፡ የእኔ ሐሳብና የእኔ ፍላጎት ብቻ ይጠበቅ የሚለውን ትተን፣ መጽሐፉ እንዳለው መልካችን ዥንጉርጉር ቢሆንም አንድ ኢትዮጵያዊ ነንና በፍቅርና በሰላም እንኑር፡፡ ሐሳብን በሐሳብ እናሸንፍ፡፡ ተሸናፊው ሐሳብ የአሽናፊውን ሐሳብ ያክብር፡፡ ሕዝብ የወደደው ይሁን፡፡ አንድ ጀግና ሲሞት በሺሕ እንደሚተካ ለኢትዮጵያውያን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡
በየምክንያቱ መበጣበጥ ከጀመርን ለኢትዮጵያ ጠላቶች ተመችተን አገራችንን እንደምንገላት እንወቅ፡፡ ትዕግሥት ይኑረን፡፡ ረጋ እንበል፡፡ ነገሮችን በማስተዋል እንይ፡፡ አለዚያ ለውጡን ወደ ጥፋት እንዳንቀይረው ያሠጋል፡፡ ያለችን አንዲት አገር ነች፡፡ ሁላችንም በትዕግሥትና በመቻቻል እንራመድ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ተደጋጋሚ ጥፋት እየተካሄደ ነው፡፡ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ያረፉት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፣ የህዳሴውን ግድብና እሳቸውን ነጥሎ ማየት ይከብዳል፡፡ ለህዳሴው ግድብ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው እንዲሁም የሠራዊቱ አባላት ለኑሮ አስቸጋሪ በሆነው ቆያ ውስጥ የከፈሉት መስዋዕትነት ምንጊዜም በሁሉ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ሥራቸውን፣ አገራቸውን፣ ከቤተሰባቸው የበለጠ በመውደድ በበረሃ ለሰባት ዓመታት ሲንገላቱ መቆየታቸው ሳያንስ በጥይት ተመተው መሞታቸው የኢትዮጵያዊያንን ልብ ሰብሯል፡፡
የዘመናት ቁጭታችን ዓባይ መላ ተበጅቶለት ከድህነት ማምለጫ አንዱ መንገድ ይሆናል ተብሎ ለኤሌክትሪክ ማመንጫነት ለሚገነባው ግድብ ከመሠረቱ ጀመሮ በሥራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉ የነበሩት ታላቅ አርበኛ፣ በመገባደጃው አፋፍ ወቅት አሳዛኝ ሞት መሞታቸው እጅግ ልብ ይሰብራል፡፡ ሆኖም የኢንጂነር ስመኘውን ደም የምንመልሰው በሕግና በሕግ ብቻ፣ የጀመሩትንም ከፍጻሜ በማድረስ መሆን አለበት፡፡ ግድቡ ለስንት ትውልድ የሚጠቅም ነውና ትውልድ እንዳይረሳቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ በግድቡ መግቢያ ሐውልት በማቆም ለሁሌም ህያው እናድርጋቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው የተበተነበት፣ እሳቸውም የሞቱለት ዓላማ በመሆኑ፣ የኢንጂነር ስመኘውን አርዓያ በመከተል ግድቡን በርብርብ ለመጨረስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና እንደሳቸው ሁሉ በእሳት የሚፈተኑ ሺሕ ኢንጂነሮች እንደሚተኩ አልጠራጠርም፡፡ ሁላችንም ግን ትዕግሥት፣ ፍቅርና አንድንነት ሊኖረን ይገባል፡፡
አምላካችን ነፍሳቸውን ይማርልን፡፡ ለቤተሰባቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይስጥ፡፡
(ከገነት ዘውዴ ወልደ ዮሐንስ፣ ከአዲስ አበባ)
* * *
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎ ሰው ተኮር አይሁኑ!
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰላም፣ ስኬትና ፍቅር ፈጣሪ አብዝቶ ይሰጥዎት፡፡ ቤተ መንግሥት ከገቡ ሦስት ወራት አለፉ፡፡ በእዚህ ወራት ውስጥ ልገልጽልዎ የፈለግሁት ጉዳይ ቢኖረኝም፣ በለውጥ ወጀብ ወቅት ላለመናገር ራሴን ቆጥቤ መቆየቱን መርጫለሁ፡፡
መናገር ያለብኝ ጊዜ መቼ እንደሆነ ሳስብ ጊዜው አሆን እንደሆነ አመንኩ፡፡ እንደ አሁኑ ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊባል በሚችል መልኩ ሳያውቅዎ በፊት፣ ዓለም ሳያውቅዎ ቀድሞ፣ ጥቂቶች በሚያውቁዎ ጊዜ ከጥቂቶቹ መካከል ተደምሬ አውቄዎታለሁ፡፡፡ እርስዎ አያውቁኝም፡፡ ብዙ ሕዝብ ቢውቅዎትም እርስዎ የሚያውቁት ግን ውስን ሰዎችን ነው፡፡ በአካል ያወቅሁዎ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ውስጥ እንደማር የሚጥመውን የበጎ አሳቢነት ንግግርዎን ባስደመጡን ጊዜ ነበር፡፡፡ ስብሰባ መሳተፍ ከተውኩ ብዙ ዓመታት አልፎኛል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› እንደሚባለው ስብሰባው ሌላ፣ የሚሠራ ሥራ ሌላ እየሆነ ጊዜዬን ለአልባሌ ነገሮች ከማዋል በራሴ ሐሳብ ውስጥ ብቆዝም ይሻላል ብዬ በማመኔ ነው፡፡ እርስዎ በተገኙበት ስብሰባ ግን ሳላስበው ተገኘሁ፡፡ የመሰብሰቢያ አዳራሹን ለማየት ግን አልነበረም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ገብቼ አይቼዋለሁ፡፡ በስብሰባው የተገኘሁትም አውቄዎት አልነበረም፡፡ እርስዎ እንደ አሁኑ ባለዝና ስለነበሩም አይደለም፡፡
እንደማንኛውም የሚኒስትሮች ሹመት በኢሕአዴግ የተሾሙ ሚኒስትር መሆንዎና ከማውቃቸው ሚኒስትሮች የተለዩ ነዎች በሚል መነሻም አልነበረም በስብሰባው የታደምኩት፡፡ የተለየ አዲስ ነገር ያሰሙኛል ብዬ ጓጉቼም አይደለም፡፡ ብቻ እርስዎ በጠሩት ስብሰባ ምንም አስገዳጅ ነገር ሳይኖርብኝ ተገኘሁ፡፡ በስብሰባው ደቂቃ እንኳ ሳያልፈኝ ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ተሳተፍኩ፡፡ ነገሩ ሁሉ ካሰብኩት በላይ ሆነብኝ፡፡ ከእርስዎ ጋር በቆየንባቸው ጊዜያት ሁሉ ስላቀረቧቸው በጎ ሐሳቦችዎ ስናጨበጭብ ነበር፡፡ ማድነቅና ማጨብጨብ የማልወድ ሰው ነበርኩ፡፡ ለእርስዎ ግን አጨበጨብኩ፡፡
‹‹በጫጩት መሐል ስለፈንግል አይወራም›› እንዲሉ፣ በጎ ነገርን መናገር ብርቅ በሆነበት ጊዜ በጎ ሐሳብ ያውም ከሚኒስትር መነገሩ ልዩ ነገር ሆኖብኝ ነው፡፡ እርስዎ የነገሩን በጎ ሐሳብ የእርስዎ ሰብዕና ያፈለቀው እንጂ፣ እንደ ኢሕአዴግ ፓርቲ ሹመኝነትዎ እንዳልሆነ ተረዳሁ፡፡ እርስዎ ከኅብረተሰቡ የወጡ የሕዝብ ልጅ ነዎት፡፡ በብዙ ሕዝብ ልብ ውስጥም ገብተዋል፡፡ ሕዝብ ይወድዎታል፡፡ ሠይጣን ግን መዋደድን አይወድም፡፡ የሕዝብ ውዴታዎ እንዳይሸረሽር ግን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ጥንቃቄውን ስለሕዝብ ብለው በሚሠሯቸው ሥራዎች ያድርጉ፡፡ ለሕዝብ ተብሎ በሚሠራ ሥራ ውስጥ ሕዝባዊ ወገንተኝነት እንጂ፣ ግለኝነት መንገሥ የለበትም፡፡ ግለኝነት የግል ጥቅምን ለማግበስበስ የግለኞች ቡድን የሚመሠረትበት ሥርዓት ነው፡፡
የግለኞች ቡድን ሲመሠረትና በቡድተኞች ጉቦ ሕዝብ ሲማረር ነው ስናይ የከረምነው፡፡ ስለዚህ እርስዎም ግለሰብ ተኮር ሳይሆኑ፣ ሕዝብ ተኮር ይሁኑ፡፡ በመስዋዕትነት የተገኘሁ፣ ከዚህ ደረጃም የደረስኩት ሕዝብ ተኮር በመሆኔ ነው ይሉ ይሆናል፡፡ ልክ ነዎት፡፡ ግን የአገራችንን የኋላ ታሪክን ስናስታውስ፣ የወደፊቱንም ስናስብ ያስፈራናል፡፡ ለመማርያ ካልሆነ በስተቀር፣ ያለፈውን እርሱት ብለዋል፡፡ ግን ደግሞ ያለፈው በጉልበት እንዳይደገም እንፈራለን፡፡ ጨለምተኛ እንዳይሉኝ አደራ እልዎታለሁ፡፡ ‹‹እባብ የሚፈራ በልጥ ይደነግጣል›› እንደሚባለው ነው እንግዲህ፡፡ በባለጉልቶች ብቻ ተይዞ የቆየው የመሬት ሀብታችን የንጉሣዊ ሥርዓታችን መገለጫ ነበር፡፡ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ተብሎ የንጉሡ ሥርዓት ሲወገድ ደርግ ተተካ፡፡ አምባገነንነት ተከትሎት ወደ ቤተ መንግሥት ገባ፡፡ ደርግም ወደቀ፡፡ አምባገነንነት በኢሕአዴግ ተደመሰሰ ተባለ፡፡
ዴሞክራሲን ይዤ መጥቻለሁ ያለው ኢሕአዴግም ሥልጠናን በያዘበት የሽግግር ጊዜ፣ የአንድን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሥራ አስኪያጅ በሠራተኛው እስከማስመረጥ ተደረሰ፡፡ ዴሞክራሲው ግን ዕድሜው አጭር ነበር፡፡ እንደ ጉም በነነ፡፡ አሁን ካለንበት ደረጃም ደረስን፡፡ ሥራ ተኮር ካልሆንን፣ ወደፊትስ ምን ይምጣ ይሆን? እያልን እንሠጋለን፡፡ ለማንኛውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎ ሥራ ተኮር ይሁኑ፡፡ ሥራ ተኮር መሆንም ሥራን በሥርዓት ማስኬድ ማለት ነው፡፡ ሥርዓት ደግሞ ሕግ፣ ደንብ፣ መመርያ፣ በግልጽነት የተቀመጠና በግልጽነት የሚተገበር መሠረት ሲኖረው የሚከወን ነው፡፡ ሥራ ለመሥራት ሥርዓት ይኖራል እንጂ ግለሰቦችን ለመጥቀም ሥርዓት ልናበጅ አይገባም፡፡ ለመጉዳትም እንዲሁ፡፡ ሥራ ሰው ተኮር ሳይሆን፣ ሥራን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ሰው ተኮር ሲባል ሥራን የሚሠራው ሰው በመሆኑ፣ ሥራው ዞሮ ዞሮ ሰው ተኮር መሆኑ አይቀርም ሊባል ይችላል፡፡ ሥራው ማዕከል ከሆነ፣ የሥራውና የአመራሩ ሒደት በሥርዓት የሚመራ ከሆነ፣ ሰው ተኮርነቱ ቀርቶ ሥራ ተኮር ይሆናል፡፡
ሥራ ሲስተምን ተከትሎ የሚከወን ከሆነ፣ በሲስተም ብዙ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ሰዎች ሰዎችን ፈልገው ከሚያቀርቡ ይልቅ ሲስተሙ ፈልጎ ቢወስዳቸው ስኬቱ ሰዎች ሰዎችን ከሚፈልጉበት መንገድ የላቀ ይሆናል፡፡ ከሰዎች ዕይታ ይልቅ የሲስተም ዕይታ የላቀ ነውና፡፡ ሰዎች የሚያውቋቸውን ወይም በሌሎች ሰዎች የቀረቡላቸውን የሚሾሙ ሲሆን፣ ሲስተም ግን የተደበቀውን ፈንቅሎ የሚያወጣ፣ በሰዎች ከሚቀርቡት ጋር ደምሮ ለሥራው ብቁ የሆነውን ይጠቁማል እንጂ አይሾምም፡፡ ሰዎች በተለያዩ ሰዋዊ ምክንያቶች አድሏዊ በሆነ ዕይታ ፕሮፌሰር፣ ሳይንቲስት፣ ዶክተር፣ በትምህርቱ ጎበዝ፣ የተማረው ከዚህ ትልቅ ቦታ ነው፣ የዚህ ቦታ ተወላጅ ነው፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፣ የዚህ ብሔር ተወላጅ ነው ወዘተ. እያልን አድሏዊነትን እናገነትረዋለን፡፡
ሥራውን የሚሠራው ሰው የብቃት መለኪያው፣ በያዘው የምስክር ወረቀት የማይኮፈስ፣ የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም የኑሮው መሠረት አድርጎ የማያይ፣ በስጦታና ድግድጋት የማሸነፍ፣ አገልጋይ የሚመርጥ ሥርዓት ማበጀት የሚችል ሲሆን ነው፡፡ ሥራን ከሠሪውና ከሕዝብ አገልጋይነት ጋር የማያቆራኝ ሰው ተኮር ከሆነ ግን፣ ያደራጀውን የቡድን መሪ ትዕዛዝ መቀበል እንጂ፣ ለሥራና ለሕዝብ ደንታ ቢስነትን ያነግሣል፡፡ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን የቡድን አባላት እከሌን አውጣው፣ እከሌን ከቦታው አንሳው በማለት ቡድናዊ ቁርኝትን ያጠናክራል፡፡
(ተመስገን ታረቀ፣ ከአዲስ አበባ)