Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከአሜሪካ ከመጡ ወዳጆቼ ጋር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርን ስንዝናና ነበር፡፡ ለረዥም ጊዜ ዓይቻቸው የማላውቃቸውን መስቀል ፍላወርን፣ ሃያ ሁለትን፣ ቺቺኒያን፣ ቦሌንና መሰል አካባቢዎች የመጠጥና መዝናኛ የሚባሉ የተለያዩ የንግድ ሥፍራዎችን ጎበኘኋቸው፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ይታደሙባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ሙሉ ናቸው፡፡ ለእኔ ዓይነቱ በትዳር ከታሰረ ዓመታት ለተቆጠሩበት ሰው፣ እነዚህ ያየኋቸው ቦታዎች በጣም ለየት ይላሉ፡፡ ለየት ይላሉ ብቻ ሳይሆን በጣም ያስፈራሉ፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቹ መጠጥ ቤቶች በወጣት ሴተኛ አዳሪዎች የተሞሉ በማለት ብቻ አይገለጹም፡፡ ሃያ ሁለት፣ ካዛንቺስና ቺቺኒያ ደግሞ እጅግ በጣም ይብሳሉ፡፡ ይኼ እንግዲህ እንጀራ ፍለጋ መንገድ ላይ የተሰማሩትን እህቶቻችንን አይጨምርም፡፡ በአጠቃላይ ግን ሁኔታው ያስፈራል፡፡

ለገጠመኜ መነሻ የሆነችው በአንደኛው ሆቴል ውስጥ ያጋጠመችኝ ወጣት ዕድሜዋ ከ16 አይበልጥም፡፡ የታሸገ ውኃዋን እየጠጣች የተስተናጋጆችን ቀልብ ለመሳብ ወዲህና ወዲህ እያለች ስትውረገረግ በሥራው ጥርሷን የነቀለች ትመስላለች፡፡ በዓይኔ ጠቀስ አድርጌ አጠገባችን እንድትቀመጥ ጋበዝኳት፡፡ በደስታ እየተፍለቀለች መጥታ ተቀመጠች፡፡ ከሁኔታዋ መጠጥ እንደማትፈልግ በመረዳትና ለዚህች ታዳጊም መጋበዝ አስፈላጊ ባለመሆኑ ያለ ግብዣ አዋራት ጀመር፡፡ የተለመደው ማን ነሽ? ከየት ነሽ? ለምን እዚህ ሥራ ውስጥ ገባሽ? ማለት አስፈላጊ ባለመሆኑ፣ ‹‹የተስማማሽ ትመስያለሽ ሥራ እንዴት ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹የእኛ ሥራማ በኃጥያት የተሞላ ነው፤›› አለችኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኳት፡፡ ‹‹አልሰማህም? ኑሮ ካሉት ፍሪጅ ይሞቃል ማለቷን ኮካ?›› ብላኝ፣ ‹‹እባክህ ተወኝ ካንተ ጋር ስለፋለፍ ቢዝነስ እንዳያመልጠኝ፤›› ብላ ተነሳች፡፡

ልጅቷ በአልባሳትና በጌጣጌጥ ብትዋብም ውስጧ የታመቀ ቁጭት ያለ ስለሚመስል ልለቃት አልፈለግኩም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲገኝ የሰዎችን ብሶት ማዳመጥ ስለሚያስፈልግ አንድ መላ መታሁ፡፡ ‹‹ለአንድ ቢዝነስ ልክፈልሽና እዚህ ሆነሽ አዋሪኝ?›› ስላት አላመነችም፡፡ ‹‹ሁለት መቶ ብር አምጣ ሃያ ደቂቃ ይፈቀድልሃል፤›› ብላኝ ለመሄድ ተነሳች፡፡ ወዲያውኑ ኪሴ ገብቼ ሁለት ባለመቶ ኖቶች አስጨብጫት ወሬ ጀመርን፡፡ ጓደኞቼ መጠጣቸውን እየተጎነጩ የጦፈ ወሬ ስለያዙ የእኔና የልጅቷ ወሬ አልሳባቸውም፡፡ ልጅቷ፣ ‹‹በእርግጥ ብሩን የሰጠኸኝ ልታዋራኝ ብቻ ነው?›› በማለት አላምንህም በሚል ስሜት ጠየቀችኝ፡፡ መዋሸት ስለነበረብኝ፣ ‹‹ከቆንጆ ጋር ከመዳራት ይልቅ ዓይን ዓይኗን እያየሁ ማውራት ስለምወድ ነው፤›› ብዬ እያሳሳቅኳት ወሬያችንን ቀጠልን፡፡ ልጅቷ እዚህ ሥራ ውስጥ ከገባች ሁለት ዓመት እንዳለፋት፣ በእነዚህ ዓመታት ከታዳጊ እስከ አዛውንት ድረስ አንሶላ መጋፈፏን ነገረችኝ፡፡ ‹‹አብረውኝ የተኙ ቢሠለፉ ከፒያሳ ቦሌ ይደርሳሉ፤›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ መጠጥ እየጠጣች የደረሰባትን ስቃይ ስታስታውስ ስለሚያንገሸግሻት ላለፉት ሦስት ወራት መጠጣት እንዳቆመች ነግራኝ፣ ከዚህ ሕይወት ውስጥ ለመውጣት ብትሞክር ግን እንዳልቻለች አወጋችኝ፡፡

እሷ እንደምትለው ፒያሳ፣ ካዛንቺስ፣ ሃያ ሁለትና ቺቺኒያ ድረስ ትናንሽ ሴት ልጆች በሴተኛ አዳሪነት ይተዳደራሉ፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ አነሰ ቢባል ከሃያ በላይ ሴቶች ይገኛሉ፡፡  ሁሉም ለመኖር ሲሉ ሥጋቸውን ሸጠው ያድራሉ፡፡ ሥነ ምግባር ከጎደለው ባለጌ ጀምሮ የተከበሩ የተባሉ ድረስ ይጎበኙዋቸዋል፡፡ እሷ ለምሳሌ ባለትዳርና የትልልቅ ልጆች አባት የሆኑ ደንበኞች አሉዋት፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ግንኙነት የሚያምራቸው ከጠጡ በኋላ ነው፡፡ ከመጠጥ በፊት አንዳንዶች ቢመጡም፣ አብዛኞቹ ጠገብ ካሉ በኋላ ስለሚመጡ የሚያቀርቡት ጥያቄ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ያለ ኮንዶም መገናኘት ከሚፈልገው ጀምሮ ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካልሆነ ብለው ድርቅ የሚሉ በሽ መሆናቸውን ነገረችኝ፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ምክንያት ውድድሩ አንገት ለአንገት በመሆኑ ሕይወት ጥቀርሻ ሆናባታለች፡፡ ‹‹እኔ ዛሬ እንቢ ካልኩ ደንበኞቼ ወደሌላ ስለሚሄዱ ሳልፈልግ በግድ የታዘዝኩትን መፈጸም ጀምሬያለሁ፤›› ስትለኝ ውስጤ ተቃጠለ፡፡

ይህቺ አንድ ፍሬ ልጅ በሕፃንነቷ በስቃይ ያለእናት አባት ማደጓን፣ የረባ እንኳ ትምህርት ሳትቀስም ወደ ሴተኛ አዳሪነት በልጅነቷ መግባቷን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ምድረ ሰካራም እየረገጠ፣ እየደበደበና አስገድዶ እየደፈራት፣ ከዚያ አልፎ ተርፎም ይኼንን መራራ ኑሮ ለመቋቋም የታዘዘችውን እየፈጸመች እንደምትኖር ነገረችኝ፡፡ ‹‹አንዳንድ ብርቱዎች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኞቹ ሴትኛ አዳሪዎች ገንዘብ ይዞ በሚመጣው ሰው ፍላጎት ተፅዕኖ ሥር ናቸው፤›› ስትለኝ በጣም አዘንኩ፡፡ ልጅቷ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ‹‹ባለትዳር ነን›› የሚሉ ጅንኖች ጭምር ናቸው ትላለች፡፡ ‹‹አንዳንዱ ሚኒስትር ወይም የአገር አስተዳዳሪ ይመስል ዝንጥ ብሎ ተኮፍሶ ሲጠጣ ስታየው ሰው ይመስላል፡፡ ክላስ ውስጥ ሲገባ ግን ወይ አውሬ አሊያም ሰይጣን ሆኖ አስደንጋጭ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ አለበለዚያም በጉልበት አስገድዶ የልቡን አድርሶ ይሄዳል፤›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ ይህች ልጅ ብዙ የምትለው ነገር ቢኖርም አንዱ ጠቀሳት መሰለኝ፣ ‹‹በል ሰዓቱ አልቋል ልሂድ፤›› ብላኝ ተነሳች፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ይህ ሕይወት ምን ይመስላል?›› በማለት ስጠይቃት፣ ‹‹የምንኖርበት ሕይወት ገሃነም ነው፣ እኛ ሸሌዎቹና ደንበኞቻችን ደግሞ የተኮነኑ ነፍሶች፤›› ብላኝ ተሰናበተችኝ፡፡

ወገኖቼ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማስወገድ የመፍትሔ ያለህ ማለት አይገባንም? ወገኖቻችንን ለመታደግ ስንል መስዋዕትነት ብንከፍልስ? እስቲ በምሽት የአዲስ አበባን ጎዳናዎች እንመልከታቸው፡፡ በተለይ ደመቅ ያሉትን ሥፍራዎች ስንቃኝ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሴቶችን ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ አንድ ምሽት ከአሜሪካ ከመጡት ወዳጆቼ ጋር ዞር ዞር ስንል ከፊታችን በዝግታ የሚጓዝ ላንድክሩዘር ከመንገድ ዳር ወጣ ብሎ ሲቆም፣ በግምት 18 ዓመት የሚሆናት  በጣም አጭር የሚባል ሚኒ ስከርት የለበሰች ብስል ቀይ ወጣት በሩን ከፍታ ስትገባ፣ መኪናው ከአካባቢው በፍጥነት ተፈተለከ፡፡ ይህችን የመንገድ ላይ ሴተኛ አዳሪ ጭኖ የከነፈው ሰው ደግሞ በከተማው ውስጥ አንቱ ተብለው ከሚታወቁ የንግድ ሰዎች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት የሆነው ይህ ሰውና መሰሎቹን ሳስብ ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ ቢያንስ በዚህ ዘመን ሜዳ ላይ የወደቁ ወገኖችን አንስቶ ለቁምነገር ማብቃት ሲገባ፣ ጨለማን ተገን አድርጎ መርመጥመጥ ያሳፍራል፡፡     

(ዘውዱ አውራሪስ፣ ከኦሊምፒያ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...