Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉድህነት ዕጦት ሳይሆን ያለንን መጠቀም ያለመቻል ነው

ድህነት ዕጦት ሳይሆን ያለንን መጠቀም ያለመቻል ነው

ቀን:

በአንድነት ኃይሉ

ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም ምክንያት መስጠት አያስፈልግም ነበር፡፡ ዛሬን ትናንት ላይ እንሠራው ነበር፡፡ በድህነታችን ላይ ባለመግባባታችን የገጠመን ችግር ድህነትን መሻገር አለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ ከቀን ወደ ቀን ሁሉም የራሱን ምክንያት ማስቀመጡ ነው፡፡

ወጥ ፍላጎት አለመኖር፣ ለአንድ ግብ አለመቆም፣ ወዘተ. . . ሁሉም ድህነትን ያየበት መንገድ የተለያየ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ ከምንም በላይ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ያለመቻል ለድህነታችን የሰጠነው ምክንያት የተሳሳተ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ተፈጥሮ ሀብት ይዘን፣ የሚያለማ ጉልበትና የሚመግብ ሕዝብ ይዘን ደሃ ነን ካልን፣ ነፃ አገር ነን ብለን ገንዘብ የለንም ካልን፣ አስተምረን የተማረ ሰው የለንም ካልን፣ ሐሳብና ዕውቀት ይዘን ደሃ ነን ካልን ድህነትን እንኖረዋለን እንጂ አልገባንም፡፡  ድህነታችን ቢገባን ዕውቀትና ተፈጥሮን ይዘን የሰው ገንዘብ ባልናፈቅን ነበር፡፡ ድህነታችን ቢገባን ይኼንን ሁሉ ሕዝብ ይዘን በርካታ ምርት፣ በርካታ ገበያና ጠንካራ ግብይት በኖረን ነበር፡፡

ድህነታችን ስላልገባን ገንዘብ ይዘን ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ ድህነታችን ስላልገባን የትምህርት መሠረት የሆነው ተፈጥሮ ላይ ቆመን ዕውቀት እንናፍቃለን፡፡ ድህነታችን ስላልገባን ሥራ ውስጥ ሳንገባ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንፈልጋለን፡፡

እውነት እኛ የሚታዘንልን ወይስ የሚታዘንብን ሰዎች ነን? በቅርቡ እህቴን ለማስመረቅ ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ አቅንቼ በመንገዴ ላይ ያየሁት የተረሳ ተፈጥሮ ፍላጎትና ግብይት ያስደነግጣል፡፡ እንኳን ለአገሪቱ ለሌላ አካባቢ፣ በአካባቢው ለሚኖሩትም የጠቀማቸው ነገር የለም፡፡ ለአካባቢውም ሁሉም ፀጥ ያለ ነው፡፡ አካባቢው በምንም መመዘኛ ከአገሪቷ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር ያልተሳሰረ ነው፡፡ በእዚህም ምክንያት በርካታ ምርቶች፣ ገበያዎች፣ ገንዘቦች፣ ሥራዎች፣ ወዘተ. . . መባከናቸው በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ተፈጥሮ አለ፣ ሕዝብ አለ፡፡ ድህነት አለ ምን ማለት ነው? ገበያ አለ ግብይት የለም ተፈጥሮ አለ፣ ሥራ የለም፣ ምርት አለ ገንዘብ የለም፣ ሕዝብ አለ ግብይት የለም፡፡ ምን ማለት ነው? ሁሉም ሙሉ ሆኖ የጎደለው ያለንን ነገር ያየንበት ዕውቀት ነው፡፡

ባየሁት አካባቢ ተፈጥሮ፣ ጉልበት፣ ዕውቀት፣ ገበያ፣ ፍላጎት፣ ወዘተ. . .  ሙት ነው፡፡ ሲጠቃለል ለኢኮኖሚው ተፈጥሮው ሙት ነው፡፡ መኖር ያለብንን ሕይወት ሳንኖረው ማለፍ በሚገባን መንገድ ሳናልፍ ድህነትን ልንሻገረው አይደለም፣ ድህነት ምን እንደሆነ ሳይገባን ዘመን ያልፍብናል፡፡ ድህነት የገንዘብ ዕጦት አይደለም፡፡ ድህነት ያለህን መጠቀም ያለመቻል ነው፡፡ ዕድገት በገንዘብ አይመጣም፡፡ ያለህ ነገር ለግብይት እንዲበቃ ማስቻል ግብይትን መፍጠርና መምራት ዕድገትን ያመጣል፡፡ ይኼንን ለማድረግ የሚጠይቀው ያለህ የራስህ የሆነ ሀብት ብቻ ነው፡፡ ያንተን ነገር ከማንም ጋር የምታወዳድረው ከሆነ፣ ነገ ውስጥ የራስህ የሆነ ምንም ነገር አይኖርህም፡፡

ትናንት ለድህነታችን መሠረት የጣልነው የራሳችንን በመተዋችን ነው፡፡ ዛሬ የምንኖረው የሰው ስለሆነ፣ የራሳችን የሆነን ምንም ነገር ማድረግ ባለመቻላችን ያቃተን ከድህነት መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ድህነት ተምታታብን፡፡ ድህነት ስለተምታታብን በድህነቱ ውስጥ መኖርን መለማመዳችን ሳያንስ፣ ሀብት የሆነውንም ተፈጥሮንም እያደኸየነው ነው፡፡

ያየሁት የተፈጥሮ ሀብት እስካሁን ድረስ እንደተፈጠረ ለመቆየት ምክንያቱ ድህነትን ያየንበት ዕውቀት ነው፡፡ ዕውቀታችን ይኼንን ሀብት ከማድረግ ይልቅ በቀጥታ የሚበላ የሰው ሀብት እያስጠበቀን ነው፡፡ በእዚህ በተሳሳተ ዕውቀት ሰውም ተፈጥሮም ደሃ ሆነ፡፡ ይኼንን ሁሉ የተፈጥሮ፣ የገበያ፣ የገንዘብና የፍላጎት ብክነት እየፈጸምን ደሃ ሆነን መኖር መቻላችን በራሱ ተዓምር ነው፡፡

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዘን የተደራጀ ገበያ፣ ገቢ፣ ግብይት ግን የለም፡፡ በአንድ በኩል እናስተምራለን፣ ኢንዱስትሪ እንገነባለን፣ ነገር ግን ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል ፍላጎት፣ ገበያና ግብይት አልተዘጋጀም፡፡ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ማለት ይኽው ነው፡፡

እንዳየሁት ተፈጥሮን በጥቂቱ ለመጠቀም የሞከሩ ሰዎች አሉ፡፡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የገበያ ችግር አለባቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች የገበያ ችግር ሳይቀረፍ በአካባቢው ያለ ማኅበረሰብ አካባቢውን ባለው አቅም ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ የአካባቢው ኅብረተሰብ አካባቢውን ባለው አቅም ተጠቃሚ መሆን ባለመቻሉ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የትኛውም አምራች በቀጥታ ተጎጂ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ መንደር ውስጥ ጠንካራ ግብይት የለም፡፡ በአገራችን ድህነት ጮክ ብሎ የሚናገረው ያልተሳሰረ ሀብት በመኖሩ ነው፡፡ ያየሁትም ተፈጥሮ ለአገሪቱ ሕዝብ ግብይት ሙት ነው፡፡ አገር የገዛ ሀብቷን ለማስተሳሰር የማንም ዕርዳታና ድጋፍ አያስፈልጋትም፡፡ ሁሉንም በገዛ ሀብቷ የምታከናውነው ነው፡፡ ነገር ግን ድህነትን ከውጭ ምንዛሪ ጋር ስላስተሳሰርነው ድህነት ተምታታብን፡፡ በዚህ ምክንያት በእጃችን ያለውን ሥራ፣ ገንዘብ፣ ግብይትና ተፈጥሮ እያባከን እየኖርን ነው፡፡ አወዛጋቢ የሆነ ዕውቀትና ፍላጎት ውስጥ ገብተን ድህነትን እንኳን ልንሻገረው ድህነት የበለጠ ይወሳሰብብናል፡፡

ለአገራችን ዕድገት መዘግየት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ስለድህነት ያለን ዕውቀትና ፍላጎት ቢሆንም፣ የበለጠውን የሚያባብሰው ከግለሰብ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ተቋማት አለመተሳሰራቸው ነው፡፡ በዚህ የተፈጥሮ ገነት የገጠር ከተማ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ሀብት እያለ፣ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ምንም አሻራቸውን አለማስፈራቸው የሚያመላክተው ብዙ ነገር አለ፡፡ ይኼንን ሁሉ ዘመን ያልተሳሰሩና ተመጋጋቢ አለመሆናቸው መሪ ሳያይ የማያዩ፣ ሳያነሳ የማይነሱ፣ የራሳቸው የሆነ ዕይታ፣ ዕውቀትና ፍላጎት ላይ ያልተመሠረቱ ወይ ሲጠሩ አልያም ሲገፉ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ነው፡፡

በዚያ አካባቢ ያየሁት ችግር በሙሉ ሰው ሠራሽ ነው፡፡ ድህነት ስላልገባን አላወቅነውም አልተሰማንም እንጂ፣ እዚያ መንደር ውስጥ ያየሁት ሰው ሠራሽ ችግር በአገሪቱ በሙሉ ተዳርሷል፣ ሁላችንም እየኖርነው ነው፡፡ የዚህ መንደር ሀብት ለአካባቢው ሙት የሆነ ቢመስልም፣ በአካባቢው ጠንካራ ግብይት ባለመኖሩ ሁሉም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ ተጎጂ ነው፡፡ በአገራችን ያሉ አብዛኞቹ ተቋማት አለቆቻቸው፣ ዕቅዳቸው፣ ውጤታቸው፣ ዕውቀታቸው ሆነው ስለማይቀረፁ ቢሠሩ የማያተርፉ፣ ባይሠሩም የማይከስሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለውጤት ብዙም አይጨነቁም፡፡ ላለብን ችግር የመፍትሔ አካል መሆን ሲገባቸው እንደማይመለከታቸው፣ ተመልካች የሆኑት ድህነታችን ስላልገባን ነው፡፡

በአንድ አገር ውስጥ ማንም ምንም የመሆን መብት እስካልተረጋገጠ፣ እንኳን የተፈጥሮ ሀብታችን እኛም ምንም እንደሆንን ዘመን ያልፋል፡፡ የሕዝብ የዕውቀት መሠረቱ የግለሰብ ስህተት ድምር ውጤት ነው፡፡ ግለሰብ ከስህተቱን መማር ሲችል ነው፡፡ ሕዝብ ከግለሰብ ውጤት በመማር ነው ዕውቀትን ማደራጀት የሚችለው፡፡ በዚያ አካባቢ ጠንካራ ሠራተኞችን አይቻለሁ፡፡ ገበያና ገንዘብ ግን ብርቃቸው ነው፡፡ እነሱን እያየ ማን ጠንካራ ሠራተኛ መሆን ይችላል? በአካባቢው ካየኋቸው ወጣቶች ጋር መሥራት የሚገባቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሉም፡፡ በአገራችን በተለምዶ ለትርፍ የማይቋቋመው ብሔራዊ ባንክ ብቻ ነው፡፡ ስህተት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ በርካታ ለትርፍ የማይቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አገር መሠረቷ ገንዘብ አይደለም፡፡ አገር ገንዘብ አታተርፍም፣ ገንዘብ አትከስርም፡፡ ገንዘብን ግን በሚገባው መንገድ በሥራ ላይ ልታውለው ካልቻለች፣ እንዳየሁት የተፈጥሮ ሀብቷን፣ ሕዝብ ውስጥ ያለ ፍላጎትና ሊፈጠር የሚገባውን ግብይት ትከስራለች፡፡

በዚህ መንደር ውስጥ ያየሁትም የተፈጥሮ፣ የገበያ፣ የፍላጎት፣ የገንዘብና ግብይት ኪሳራ ነው፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ፣ የአገር ውስጥ ገቢ የመሠረተ ልማት፣ ወዘተ. . .  መሥሪያ ቤቶች ትርፋቸው በሥራ ላይ መዋል ያለበትን ተፈጥሮ፣ ዕውቀት፣ ፍላጎት፣ ገንዘብ፣ ገበያና ግብይት በሥራ ላይ ማዋል ነበር፡፡ እነዚህ መሥሪያ ቤቶችን ስንፈትሻቸው ትርፍና ኪሳራቸውን በምን እንደሚለኩት ባላውቅም እስከማውቀው ድረስ ተፈጥሮን፣ ገበያን፣ ገንዘብን፣ ወዘተ. . . ከሕዝብ ጋር ሊያስተሳስሩት ይቅርና እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ አይደሉም፡፡ እንደምናውቀው አንዱ የገነባውን ሌላው ሲያፈርሰው ማየት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች የአንዱ ውጤት የሌላው ግብዓት፣ የአንዱ ግብዓት የሌላው ውጤት ሆነው ካልተሳሰሩ እንኳን ለአገር እርስ በርሳቸውም መግባባት ይከብዳቸዋል፡፡

መሠረተ ልማቱን ገንዘብ ተቀብሎ የሚሠራው ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገው ወይም ግብዓት የሚሆነው የተፈጥሮ ሀብት፣ ዕውቀት፣ ወዘተ. . . በሥራ ላይ እንዲውል ለሠራተኛው የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ታስቦ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ውስጥ ገቢ በሥራ ላይ ሊያውለው የተዘጋጀው ዕቅድ የስኬታማ ለማድረግ ሆኖ ነው መሥራት ያለብን፡፡ የአገር ውስጥ ገቢ ዕቅድ መሠረተ ልማት ተቋም በሥራ ላይ የዋለው ገንዘብ የሚፈጠረውን ግብይት ለመቆጣጠርና ለመምራት ተብሎ ነው፡፡ በውስጡ ለሚሠሩ ሠራተኞች ሥራ የሚፈጥረው መንገድና የትራንስፖርት አገልግሎት ስላለ ነው፡፡ ገቢዎች የተቋቋመው እንደ ማለት ነው፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቻችን ያለመተሳሰራቸውን ለማየት የሚባክነው ተፈጥሮ፣ ፍላጎት፣ ገንዘብ፣ ወዘተ. . . ብቻ ሳይሆን፣ በየቢሮዎቻቸው የተለጠፉት ዓላማና ዕራያቸው ነው፡፡ ሁሉም ራሱን ችሎ የቆመና አንዱ ለአንዱ ባዕድ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ እንኳን የሰው ልጅ ተፈጥሮን ያስተሳሰረው ልዩነት ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ተቋም የተቋቋመው ያለውን ልዩነት ወደ አንድነት ለማምጣት እንጂ፣ ልዩነትን ሰብስቦ ለመያዝ እንዳልሆነ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ያየሁት ግን እንዲሁ ነው፡፡ ሁሉም ተቋም ምንም ዝምድና የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ሥራ እያባከንን ነው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት ያለውን ለመስጠት ገንዘብን ሲጠቀም አንዱ መሥሪያ ቤት የሚፈልገውን ለመቀበል ገንዘብ ሲያወጣ፣ አንዱ ለመስጠት አንዱ ለመቀበል እኩል ገንዘብ ሲጠቀም፣ የሚፈጠረው መስተጋብር ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብና ከሀብት ጋር የሚያስተሳስረው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ይኼንን የመሰለ የተፈጥሮ ሀብት፣ ይኼንን የሚያህል የሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት ይዘን ደሃ ነን እንላለን፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮም፣ ፍላጎቱም፣ ግብይቱም ባክኗል፡፡ አገር በሕዝብ ውስጥ ያለውን ዕውቀት፣ ሀብት፣ ልዩነትና ፍላጎት ተጠቅማ ግብይት ሳትፈጥር መኖር ትችላለች ብሎ ማለት ዓሳ ከውኃ ወጥቶ መኖር ይችላል ማለት ነው፡፡ የሚደንቀው ግን እንዴት መኖር ቻልን? የሚለው ነው፡፡ መልሱን ሳስበው በድህነት የኖርነው በራሳችን ዕውቀት፣ በራሳችን ገበያ፣ በራሳችን ገንዘብ፣ በራሳችን የተፈጥሮ ሀብት ላይ ስላልሆነ ነው፡፡ ይኼንን የሰው ዕውቀት፣ ገበያ፣ ገንዘብና ተፈጥሮ ያጣን ዕለት ምን እንሆን ይሆን? እናስብበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...