Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ (የነፍስ አድን ዕርምጃ)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ (የነፍስ አድን ዕርምጃ)

ቀን:

ክፍል አንድ                             

በኤርሚያስ አመልጋ

አጭር ቅኝት

ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው አስደናቂ ኢኮኖሚ፣ ዕድገትና ልማት የመቀልበስ አደጋ ላይ የሚጥል የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ መላ አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር በፖለቲካ የቀውስ ማዕበል ክፉኛ ተመታ በተዋጠችበት ፈታኝ ወቅት፣ ኢኮኖሚው አሽቆልቁሎ የድቀት አፋፍ ላይ ደርሷል፡፡ እጅግ ሚዛኑን የሳተና የተፍረከረከ ኢኮኖሚ ዓይነተኛ ምልክቶችን ሁሉ አንድም ሳይቀር እያሳየ ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥልቅና ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በፍጥነት የሚጋልብ የዋጋ ንረትና የሚያሽቆለቁል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይገኙባቸዋል፡፡

በተለይ  የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ኢኮኖሚውን አንቆ እስትንፋስ እያሳጣው ነው፡፡ የደም ግፊትና የስኳር በሽታ መድኃኒቶችን የመሳሰሉ ወሳኝ ጉዳዮች ከገበያው ላይ በመጥፋታቸው የተነሳ በርካታ ሰዎች እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ የቢዝነስ ተቋማትና ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሪ ጠይቀው በማጣታቸውና ጥሬ ዕቃ ከውጭ ማስገባት ባለመቻላቸው ሥራቸውን እየዘጉ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባ የግንባታ ብረታ ብረት በመጥፋቱ ሳቢያ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ ዋጋ ከታሪካዊ አማካይ አሥር በመቶ ገደማ በታሪክ ከፍተኛ ወደ ሆነው 25 በመቶ ተተኩሷል፡፡ በባንክ ዘርፍ የብድር ውዝፍና ቀልጦ የሚቀር ብድር አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ባንኮችም በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ኪሳራ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ በፍጥነት እየጋለበ ነው፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ የሥራ ዕድል እየተመናመነ ይገኛል፡፡ የመንግሥት  ካዝና ተራቁቷል፡፡ የመንግሥት ዕዳ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኢትዮ ቴሌኮምን በመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት ጭምር በጊዜ እየተከፈለ አይደለም፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እግር ከወርች ታስረዋል፡፡ ቻይና እንኳን ተጨማሪ ብድር መስጠት አቋርጣለች፡፡

እነዚህ መዛነፎች የመፈንዳት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሰው በሁሉም  ዘርፎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እግር ከወርች ታስሯል፡፡ በሌላ በኩል የዋጋ ንረቱ አገርሽቶበት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጋለበ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ድንዛዜና የዋጋ ንረት (ስታግፍሌሽን) ገጥሞናል፡፡ ይኼ ክስተት ለመፍታት እጅግ ፈታኝ የሆነ የኢኮኖሚ ጠንቅ ነው፡፡ ለምን ቢሉ አንዱን ችግር አስታሞ ለማዳን የሚቀመሩ የፖሊሲ መፍትሔዎች ሌላኛውን በማባባስ፣ ኢኮኖሚውን መውጪያ ወደሌለው የድቀት አዙሪት ውስጥ ይዶሉታል፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹ አሁኑኑ መጠነ ሰፊና ሁሉን አቀፍ  ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጋቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚህ በታች የተጠቆሙት  ማሻሻያዎች ወይም ሌሎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መለወጣቸው ግን የግድ ነው፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ቀውስ በጣም ለረዥም ጊዜ የዘለቁ፣ በመዋቅራቸው የተዛነፉና የተዛቡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ የአሁኑ የፋይናንስ ቀውስ እንደሚከሰት ቀደም ብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ ይህም አገግሞ ለመውጣት አስቸጋሪና ረዥም ጊዜ ወደሚወስድ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያመራ የሚችልበት ግልጽ አደጋ አለ፡፡ በአክሰስ ካፒታል ሪሰርች የታተመው እ.ኤ.አ. የ2012 ዓመታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪቪው ኢኮኖሚው ይኼን መሰል ቀውስ እንደሚገጥመው ተንብዮ ነበር፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድና ሁለት ወጪን ለመሸፈን የሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅም ቀደም ብሎ ያልተዘጋጀ ሲሆን፣ ይኼ የገንዘብ አቅርቦት ከየት እንደሚመጣ የተቀመጠ ፍንጭ የለም፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ይኼንን የፋይናንስ ዕቅድ ያለመዘጋጀት የሚያሳይ፣ የለየለት ምሳሌ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ የተገመተ ሲሆን (ከሞላ ጎደል ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አሥር በመቶ ገደማ)፣ ይህም እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ለዚህ ሜጋ ፕሮጀክት የተዘጋጀ የፋይናንስ ዕቅድ እንዳልነበረ አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ የፋይናንስ ዕቅድ አለመኖሩ ፍርኃትና ሥጋት ግን አልፈጠረም፡፡ ይልቁንም ወደ ብሔራዊ ክብር መግለጫነት ነው የተቀየረው፡፡ ሁሉም ዜጋ ማናቸውንም መስዋዕትነት የሚከፈልለት የአገራዊ ኩራት መፈተኛ ይህን ብሔራዊ ሐውልት ለመገንባት ሁሉም ‹‹የድርሻውን›› እንዲያዋጣ እየተጠየቀ፣ የግድቡ ግንባታ፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የጦር ሠራዊቱ፣ የፋብሪካ ሠራተኞችና ሊስትሮዎች ጭምር በሚያደርጉት መዋጮ እየተንፏቀቀ ነው፡፡ የለየለት ምሳሌ ቢሆንም የአስተሳሰብ ቅኝትን ያሳያል፡፡ ለግንባታው ከሚያስፈልገው ግዙፍ የኢንቨስትመንት ካፒታልና የዚያኑ ያህል ተስፋ አስቆራጭ ከሆነውና በውል ከሚታወቀው የመንግሥት የአፈጻጸም አቅም ክፍተት አንፃር፣ የፋይናንስ ዕቅድ ሳይዘጋጅ መቅረቱ እንቆቅልሽ ነው፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ የዛሬ ስምንት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ ሀ . .  ተብሎ ሲጀመር በርካታ የውስጥና የውጭ መልካም አጋጣሚዎች ተጠራርተው የተሰባሰቡ ይመስል፣ ለኢትዮጵያ ቢመኙት የማይገኝ ዕድል ፈጠሩላት። ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ለማዞርና ለኢኮኖሚ ቀድመው የሚገሰግሱ የአኅጉሪቱንም አንበሶች ለማየት፣ የአበዳሪዎች ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በዚያ አጋጣሚ ኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ዓይን ውስጥ የመግባት ዕድል ቀናት። በአዲሶቹ ገስጋሽ አንበሶች ዝርዝር ውስጥ የቀዳሚነት ደረጃ የነበራት ኢትዮጵያ እንደ ልቧ በነፃነት ለመበደር ችላለች፡፡ በተለይም ደግሞ ከቻይና በእነዚህ ምቹ ሁኔታዎችም ለዓለም ገበያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዮሮ ቦንድ በመሸጥ ብድር የማግኘት ዕድል አግኝታለች፡፡ የማታ ማታም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 1 እና 2 ከፍተኛ መጠን ባለው የውጭ ብድር ላይ የተንጠላጠለ ሆኖ አረፈው፡፡

በብድር ላይ ተመርኩዘው የሚንቀሳቀሱ ስትራቴጂዎች ስኬታማነት የሚወሰነው በዘላቂነታቸው ላይ ነው፡፡ ዘላቂነታቸውም የሚወሰነው የሚከናወኑት በርካታ መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውና በተያዘላቸው ጊዜ ትርፍ አመንጭተው ብድር መክፈልና የዕዳ ጫናን ከልክ እንዳያልፍ በመቆጣጠር፣ ለወደፊቱ መበደርና ኢንቨስት ማድረግ ማስቻላቸው ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም የውጭ ዕዳን ለመክፈል የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሪ ወደሚያመነጭ ኤክስፖርት ተኮር የአምራች ኢኮኖሚ ሽግግር ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡

ክፋቱ ግን ይህ የመዋቅር ሽግግር በኢትዮጵያ ዕውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ቁልፍ በሆኑ ቁሳዊና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ሜቴክ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ወዘተ ባሉ የመንግሥት ተቋማት ላይ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ያዋለው ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር፣ የኢኮኖሚውን የዕዳ  ጫና የመቋቋም አቅም ጠብቆ ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ትርፍና ውጤት ማመንጨት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳ በሚያሠጋ ሁኔታ ተወጥሮ ሊፈነዳ የደረሰ ሲሆን፣ አሁን አገሪቱ ዕዳዋን የመክፈልና እየተበደረች የመቀጠል አቅሟ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ የተከሰተውን ዕድገት ለማስቀጠል ቀጣይ ግዙፍ ኢንቨስትመንት በሚያስፈልግበት ወቅት ነው፡፡ በተጨማሪም በኢኮኖሚው ውስጥ ጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያዛባና የሚያውክ ሥር የሰደደ የመዋቅር ዝንፈት ተፈጥሯል፡፡

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ከድንዛዜ አውጥቶ ለማነቃቃትና ሚዛኑን ለማስጠበቅ፣ የማስተካከያ ፖሊሲ ዕርምጃዎችን መውሰድ ዛሬ ነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ ገዳቢ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን የዋጋ ግሽበትንና የውጭ ክፍያ ሚዛንን መቆጣጠር ይገባናል፡፡ ኢኮኖሚው ግዙፍ (ከዕዳ ውጪ የሆነ) የውጭ ምንዛሪ ማነቃቂያና በገበያ የሚመራ የምንዛሪ ተመን አስተዳደር ይፈልጋል (የማይቻል አይደለም)፡፡ አሁን በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ላይ የፈሰሰው ከፍተኛ ወጪ ቀጣይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር መታደግ የግድ ነው፡፡ በመንግሥትና በግል ኢንቨስትመንት መፍረክረክ ሳቢያ የተፈጠረው አጠቃላይ የአገራዊ ፍላጎት መደንዘዝ ሊለወጥ ይገባዋል፡፡ በደሃ ያላደገና ዕዳ የተጫጫነው ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የኢኮኖሚ ድንዛዜና የዋጋ ንረት (ስታግፍሌሽን) ተጋፍጠናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ማረቅ የማይቻል ይመስላል፣ ግን አይደለም፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚህ ቀውስ መውጪያ አስተማማኝ መንገድ አለ፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ከሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹን በከፊልም ቢሆን ወደ ግል ባለቤትነት ማዛወር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦችን በሙሉ ለማሳካት የሚያስፈልገውን የገንዘብ አቅርቦት ሊሸፍን ይችላል፡፡ በራሱ ድንቅ  ስኬት ቢሆንም በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚገኙ ድርጅቶችን  ወደ ግል ይዞታነት ማዛወር፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የገንዘብ ችግር ብቻ አይደለም የሚፈታው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችንም ለመፍታት ያግዛል፡፡ እነዚህም  የአጠቃላይ ፍላጎትን ወጪ መሸፈን፣ ለአጠቃላይ አገራዊ ኢንቨስትመንት የገንዘብ አቅም ማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን መፍታት፣ የውጭ ክፍያ ሚዛን ዝንፈትን ማቃናት፣ የዋጋ ግሽበትን መቀነስና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ማነቃቃትን ያካትታሉ፡፡ እኒዚህ ሁሉ ሊተገበሩ የማይችሉ ይመስላል፣ ግን አይደለም፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በሚያስፈልግበት ድባብ ውስጥ፣ የኢትዮጵያን በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ ድርጅቶች የተከማቸ ሀብት ወደ ገንዘብ ለመለወጥ ፕራይቬታይዜሽን ግሩም መንገድ ነው፡፡ ሀቁን ለመናገር ይኼን የተከማቸ ሀብት ራሱ መንግሥት በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ታላቅ መስዋዕትነት ሊከፈልለት ይገባል ብሎ ለሚያምንበት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከማዋል የበለጠ ምክንያታዊ አጠቃቀም መኖሩ ያጠያይቃል፡፡ ሌላው አማራጭ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ የትም መሄድ ሳያስፈልገን፣ እ.ኤ.አ. በ1970 እና 1980 በላቲን አሜሪካ የታየውን በብድር ላይ የተንጠለጠለ፣ የዕድገትና ድቀት አዙሪት መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ የላቲን አሜሪካ አገሮች ከገቡበት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም አሠርት ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 1 እና 2 የተጠነሰሱበትን ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቶች እገመግማለሁ፡፡ በተጨማሪም ኢኮኖሚውን ለዚህ ደረጃ ያበቁ፣ የስትራቴጂና የፖሊሲ ጉድለቶችንም እፈትሻለሁ፡፡ ከዚያም በመነሳት ተገቢ የሆኑ የማሻሻያ ዕርምጃ ሐሳቦችን እጠቁማለሁ፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ምን ይመስላል?

በዓለም ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ሁሉ የዕድገትና ልማት ጉዟቸውን የጀመሩት ከድህነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ያላደጉ ኢኮኖሚዎች በኋላቀርነትና ብቃት በጎደለው የሀብት አጠቃቀማቸው ይገለጻሉ፡፡ ያላደጉ ኢኮኖሚዎች ዋነኛ አጠቃላይ የልማት ስትራቴጂዎች አንዱ፣ የ‹‹ቢግ ፑሽ›› ወይም ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ስትራቴጂ ነው፡፡ በዚህ የልማት ሞዴል መሠረት ያላደገ ኢኮኖሚ ትልቁ ተግባሩ፣ ከ‹‹ድህነት ወጥመድ›› ወይም ሁሉም ኢኮኖሚዎች መጀመርያ ላይ ከሚገጥማቸው ‹‹የድህነት አዙሪት›› ውስጥ መውጣት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ሊያድግና ሊሻሻል የሚችለው ከዚህ የድህነት ወጥመድ ሲላቀቅ ብቻ መሆኑን የሚያቀነቅነው ሞዴሉ፣ ኢኮኖሚውን በመግፋት ቀጣይነት ወዳለው የዕድገት ዑደት ውስጥ ለማስገባት በተለያዩ ዘርፎች የተቀናጁ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች እንደሚያስፈልጉ ይጠቁማል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቢግ ፑሽ ወይም የልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገራችን እየተካሄደ ያለው የ‹‹ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን›› ዕቅድ ማዕቀፍም ነው፡፡ ንድፈ ሐሳቡ የተመሠረተው በኢኮኖሚው ውስጥ ኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ባለው ሚናና  በኢንዱስትሪ የሚመራ ኢኮኖሚ በርካታ ውጪያዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታዎችን (1 + 1 = 3) ይቋደሳል በሚል እሳቤ ላይ ነው፡፡ እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ለመቋደስ ግዙፍ ኢንቨስትመንት በማከናወን፣ በተመሳሳይ ጊዜ በርካታ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ የዕድገት ቻናሎች ኢንቨስትመንት አስፈላጊ መሆኑን የሚያልመው ንድፈ ሐሳቡ፣ በዚህም እያንዳንዱ ቻናል አስፈላጊውን የፍላጎት ምንጭ በማቅረብ የሌሎችን ዕድገት ያስጠብቃል፡፡ ይህም ሚዛኑን የጠበቀና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ይፈጥራል፡፡ ኋላቀርና በድህነት የላሸቀ ግብርና ዋነኛው ዘርፍ ለሆኑባቸው ያላደጉ ኢኮኖሚዎች ታቅዶ የሚከናወን የኢንዱስትሪ መስፋፋት እንደሚያስፈልግ ንድፈ ሐሳቡ በአጽንኦት ያጎላል፡፡ መንግሥት የገበያውን መጠን ለማስፋት የመሠረተ ልማትና ተመጋጋቢ ኢንዱስትሪዎች ግንባታን ወጪ በመሸፈንና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማከናወን፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው አጠቃላይ ወጪ የመፍጠር የመሪነቱን ሚና ይወስዳል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ አነሳስ ከትልቅ ጃምቦ አውሮፕላን አነሳስ  ጋር ይመሳሰላል፡፡ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የመነሻ ፍጥነትን ይጠይቃል፡፡

ለቢግ ፑሽ ሞዴል አስፈላጊውን የኢንቨስትመንት መጠን ለማከናወን የሚሆን፣ የገንዘብ አቅርቦት ለማግኘት ያላደጉ ኢኮኖሚዎች የአገራቸውን የቁጠባ መጠን ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ ቁጠባን ዘላቂነት ባለውና ውጤታማ በሆነ ምቹ መንገድ ለመሰብሰብና ለኢንቨስትመንት ለመመገብም የተሳለጠ ዘዴ ሊቀይሱ ይገባል፡፡ በቅጡ የዳበረ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ወይም ውጤታማ አማራጭ (በመንግሥት የሚመራ የፋይናንስ ሥርዓት) የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ሁለቱም የላትም፡፡ የሚተገበረው የልማት ስትራቴጂ ዓይነት ምንም ይሁን ምንም ስኬታማ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ሦስት መሠረታዊ ምሰሶዎችን ይፈልጋል፡፡

  1. ቁሳዊ መሠረተ ልማት (መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ውኃ)
  2. ማኅበራዊ መሠረተ ልማት (ትምህርት፣ ጤና፣ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች፣ የሕግ ሥርዓት፣ ወዘተ)
  3. የፋይናንስ መሠረተ ልማት (የተሳለጠ የፋይናንስ ጣልቃ ገብነትና የሀብት አመዳደብን የሚያቀላጥፉ ተቋማት፣ መረጃዎች፣ ቴክኖሎጂዎችና ደንቦች) ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በቁሳዊ መሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር አከናውናለች፡፡ በማኅበራዊ መሠረተ ልማት ግንባታ ከአማካይ በታች የሆነ ሥራ ያከናወነች ሲሆን፣ በፋይናንስ መሠረተ ልማት ግንባታ ግን ምንም አልሠራችም ማለት ይቻላል፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ መሠረተ ልማት ያለ መገንባት ወይም የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ፍሰት በአግባቡ መምራት አለመቻል፣ በዋናነት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትንና ልማትን ጥንካሬና ዘላቂነትን ያዳክመዋል፡፡ ይህ የኢኮኖሚው ስስ ብልት (ከደካማ የፋይናንስ ዕቅድ በተጨማሪ) ሲሆን፣ የፋይናንስ ቀውሱ አንዱ መሠረታዊ መንስዔም ነው፡፡ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዕጦት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ደሃ ተኮር ለማድረግ፣ የተቀመጠውን ትልቅ ግብም ይገዳደራል፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ግንባታ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ልማትና የድህነት ቅነሳ ወሳኝና አይተኬ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ፡፡ የፋይናንስ መሠረተ ልማት፣ የቁጠባ መጠንንና ለኢንቨስትመንት የሚውል የቁጠባ አቅርቦትን ያሳድጋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያቀላጥፍና የሚያበረታታ ሲሆን፣ በተፎካካሪ ዘርፎች መካከል የሀብት አመዳደብንም ያሻሽላል፡፡

የፋይናንስ ዘርፍ መስፋፋት በሀብት ክምችትና በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ፍጥነት ላይ በሚያስከትለው በጎ ተፅዕኖ አማካይነት፣ የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገትና ዕመርታን የላቀ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም መጠኑ ሊለያይ ቢችልም የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት፣ በአጠቃላይ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ተመሳሳይ መስመሮች አማካይነት ድህነትን ሊቀነስ ይችላል፡፡ ኢንቨስትመንትና ምርታማነትን በማሳደግ በከፍተኛ ገቢ ማመንጨት በተገኘ ውጤት፣ እንዲሁም የአደጋ ቁጥጥርን በማመቻቸት ለድንገተኛ ቀውስ  ተጋላጭነትን ይቀንሳል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ብዙውን ጊዜ አሁን ላሉት መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ለዕዳ ሥጋት በሚያጋልጥ፣ አማራጩ ጠባብ በሆነና ውድ መደበኛ ያልሆኑ አገልግሎቶችን እንዲጠቀም ይገደዳል፡፡ ይህም በገበያው ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ገቢውን የማሳደግና ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ የማድረግ አቅሙን ይገድበዋል፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን የገንዘብ ተቋማትን የመሳሰሉ በከፊል መደበኛ የሆኑ ዘርፎች፣ ለደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት የመስጠት ሚና ይጫወታሉ፡፡ የልማት ባንኮች የብድር ማኅበራትና የመሳሰሉት ተቋማት እንደሚያደርጉት፡፡ እነዚህ ሁሉ ተቋማት ግን የባንክ ተጠቃሚ መሆን ከሚችሉት ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብቻ ነው እየደረሱ ያሉት፡፡ ስለዚህም ይህን ችግር በበቂ ደረጃ ለመፍታት በመደበኛ የፋይናንስ ዘርፍ፣ በግል ዘርፍ ተቋማት አማካይነት፣ የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥን ማስፋት አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ስትራቴጂ ምን ይመስላል?

የፋይናንስ መሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ አንጎል፣ ልብና የደም ሥር የመሆኑን ያህል የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዕጦት (ወይም ቁጠባን በመሳብ የሚያስተናብርና ኢንቨስትመንትን የሚመግብ ሌላ አማራጭ መንገድ ማጣት) ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያጨልም ክፉ አደጋ ነው። በገበያ ሥርዓት ላይ የተገነባ የፋይናንስ መሠረተ ልማት በአገሪቱ የልማት ስትራቴጂ ውስጥ መሟላት ከሚገባቸው ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ሳይካተት የታለፈው በአጋጣሚ ሳይታወቅ ቀርቶ ወይም ተዘንግቶ አይደለም። ቦታ ለመንፈግ የተፈለገውና ሆነ ተብሎ የተወሰነው የገበያ ጉድለቶች (እንከኖች) የተሰኘውን ንድፈ ሐሳብ በመንተራስ ነው። የገበያ ጉድለቶች በታዳጊ አገሮች ውስጥ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች ያዳረሱ፣ በተለይ ደግሞ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተንሰራፉ ችግሮች እንደሆኑም በዚሁ ንድፈ ሐሳብ ይታመናል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያሰፈሩት ሐሳብ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹አኅጉሪቱ በዝቅተኛ ብድርና በዝቅተኛ ቁጠባ ወጥመድ አጣብቂኝ ውስጥ ተይዛለች። በቁጠባና በብድር ወለዶች መካከል ያለው ልዩነት ተለጥጦ፣ የተጣራ የወለድ ምጣኔው ከመናሩ የተነሳ የማይቀመስ የሆነባቸው የአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል። በካፒታል ዕጦት እጅግ በተጠሙ አገሮች ውስጥ ለግብይት የሚውል ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ግን ሞልቶ ይትረፈረፋል። ለወትሮም የረባ ቁጠባ በሌላቸው አገሮች ውስጥ ቁጠባን በመሳብና በማስተናበር የሚመጣና ባንኮችን ለትጋት የሚያነሳሳ የገበያ ጥቅም ሲጠፋ፣ አንዳንዴም ለቁጠባ የሚመጡ ደንበኞችን ላለማስተናገድ ጀርባቸውን ሰጥተው ሲመልሱ ይታያል። የፋይናንስ ዘርፉ አገናኝ የፋይናንስ ድልድይ የመሆን ተግባርና አገልግሎቱን መወጣት ጨርሶ አቅቶታል።››

የኒዮ ሊበራል የአስተሳሰብ ቅኝት ግን በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚታዩትንና በመንግሥት ውጤታማ ጣልቃ ገብ ዕርምጃ ብቻ ሊስተካከሉ የሚችሉ መሠረታዊ የገበያ ጉድለቶችን መገንዘብ አልሆነለትም። ገበያው በትክክል ሲሠራ ብቻ ሳይሆን እክል ሲኖርበትም፣ ከጣልቃ ገብ ዕርምጃ መቆጠብ ያስፈልጋል ከሚለው እምነቱ ለመላቀቅ አልቻለም። በመዋቅር ማሻሻያ ዘመን በጅምር መክኖ የቀረውን የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ከቆሞ ቀርነት የሚታደግ ከመድረሻ ቢስነት የሚያወጣ መንገድ መክፈት አልቻለም። የመዋቅር ማሻሻያዎቹ ቀልጣፋና ውጤታማ አገናኝ አገልግሎት የሚሰጥ የፋይናንስ ዘርፍ መፍጠር ተስኗቸው ከመምከናቸውም በተጨማሪ፣ በፋይናንስ ገበያው ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢነትን መግታትም አቅቷቸዋል። እንደ ድሮው ሳይሆን መንግሥት  ዛሬ በመንግሥትነቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ተዋናይ አይደለም። ዋናው ተዋናይ የሆነው የግል ዘርፉ ነው። በእርግጥ ተንፈራጥጦ መፈናጠጥ በበዛበት አፍሪካ ውስጥ የትኛው የት ላይ አብቅቶ፣ ሌላኛው የት እንደሚጀምር ድንበራቸውን በግልጽ ለይቶ ማወቅ እንደ ልብ ቀላል አይደለም። የኒዮ ሊበራል የአስተሳሰብ ቅኝት ትኩረቱን በመንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነት ዙሪያ ላይ ብቻ አጥብቦ በማነጣጠሩ፣ ለግሉ ዘርፍ የኪራይ ሰብሳቢነት በሩን ወለል አድርጎ ከፈተው ማለት ይቻላል። ኪራይ ሰብሳቢነትን የመግታት ጥረት የመንግሥትን የኢኮኖሚ ሚና በመቀነስ ላይ ብቻ ስለተገደበም፣ ሌላኛውን የኪራይ ሰብሳቢነት ገጽታ ማለትም በግሉ ዘርፍ በኩል ያለውን ገጽታ ከሞላ ጎደል ሳይነካ አልፎታል።

በአስተሳሰብ ቅኝታቸው ኒዮ ክላሲካል ተብለው ከሚካተቱት የቅኝት ዓይነቶች መካከል የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ በፋይናንስ ዘርፎች ውስጥ በተለይ በታዳጊ አገሮች፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ የገበያ ጉድለቶች መንሰራፋትን ለመገንዘብ የተሻለ ዕድል ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ በምሥራቅ እስያ ክስተቶች ጉዳይ በዋሽንግተን ኮንሰንሰስ ትንታኔ የገበያ ጉድለቶችን አብጠርጥሮ በመገንዘብ ረገድ እንከን አይወጣለትም፡፡ በማጠቃለያው ግን የመንግሥት ጉድለቶች ከገበያ ጉድለቶች የከፋ ነው፡፡ የገበያ ሥርዓት የቱንም ያህል ጉድለት ባያጣው እንኳን ተንገራግጮም ቢሆን ራሱ ይወጣዋል ወደሚል ድምዳሜ የወረደ ነው፡፡ የገበያን ሥርዓት እንደ ፍጥርጥሩ መልቀቅ ገበያው ከጉድለት የፀዳ በማይሆንበት ወቅት የማይቀረው ውጤት ብርቅና ድንቅ ባይሆንም እንኳን፣ ቢያንስ ቢያንስ የማይናቅ በቂ የዕድገት ውጤት ያስገኛል የሚል መከራከርያም ቀርቦ ነበር፡፡ በተግባር እንደሚታየው የገበያ ጉድለቶች የመንግሥት ጉድለቶች ያህል መጥፎ እንደሆኑና በመጨረሻ ሁለቱም መድረሻ ቢስ ቆሞ ቀርነት እንደሆኑ ነው፡፡ ለጥፋት ያሰፈሰፈ ወሮበላ መንግሥትና ‹‹መንግሥት ገነን›› ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ በተለያየ አቅጣጫ በየራሳቸው መንገድ መጨረሻው በማያምር የመካነ ጉዞ የአፍሪካን የፋይናንስ ዘርፍ መድረሻ ቢስ ቆሞ ቀር አደረጉት፡፡ የዚህኛው ቆሞ ቀርነት ከዚያኛው ቆሞ ቀርነት አይሻልም፡፡ የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ በመካነ ጉዞ መድረሻ ቢስ ሆኖ ቆሞ እንዳይቀርና ከመካነ ጉዞ እንዲወጣ፣ ሁለቱም አቅጣጫዎች ተነቅለው መወገድ እንዳለባቸው ማየት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፋይናንስ ስትራቴጂ ላይ ያላቸው አስተሳሰብ እንዲህ ግልጽ ነው፡፡ የገበያ ሥርዓት በራሱ አሠራር የፋይናንስ ዘርፍ ልማትን እንዲመራ ከመፍቀድ ውጪ ያለው አማራጭ መንግሥት የገበያ አሠራር ቦታን በመውሰድ፣ የካፒታል ፍሰትን እንዲመድብና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እንዲወስን ማድረግ ነው፡፡ አሳዛኙ ግን መንግሥት ከሚመራው የፋይናንስ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ያተረፈችው መከራ ብቻ ነው፡፡ እናም ጥያቄው የትኛው ይብሳል የሚል ይሆናል፡፡ ሊያጋጥም የሚችል የገበያ ጉድለት ይብሳል? ወይስ ያልተቋረጠው የመንግሥት ጉድለት? ተጨባጭ ውጤቶች ራሳቸው አንደበት አውጥተው እስከ መናገር ደርሰዋል ማለት ይቻላል፡፡

ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

በመንግሥት ክትትል ውስጥ የገበያ ሥርዓት አንቀሳቃሽ አቅሞችን ሥራ ላይ በማዋል ለኢኮኖሚው የሀብት ፍሰት መንገድ መሪ እንዲሆኑ ቦታ መስጠት፣ እንዲሁም የአገሪቱ የውጭ ንግድና የውጭ ክፍያ ሚዛን መዛባትን መልሰው እንዲያቃኑ መፍቀድ የግድ ነው። ብድር ነክ ያልሆነ ምንጮችን በመጠቀም ኢኮኖሚውን ከድንዛዜ የሚያነቃና የሚያንደረድር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በፍጥነት ማሟላት የማይታለፍ ተግባር ነው። መንደርደርያው ለዕድገት ጉዞ መነሻ ይሆናል። የገበያ ሥርዓትን የተከተሉና መንግሥት የሚያስተባብራቸው በትክክለኛ ማዕቀፍ የሚተገበሩና የዕድገት ግስጋሴን የሚያረጋግጡ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መተግበር የሚቻለውም፣ በዚህ መንደርደርያ ላይ በመመሥረት ነው። በውጭ ምንዛሪ ቀውስ ሳቢያ ለአጣዳፊና ለብርቱ አደጋ የተዳረገውን ኢኮኖሚ የሚያድን ስትራቴጂ የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥሩን በጥንቁቅ አስተዳደር በገበያ ሥርዓት አቅጣጫ፣ ‹‹ማኔጅድ ፍሎት›› ወደተሰኘው አሠራር ማሻሻል እንደሆነ ከእነ ዝርዝሩ በአባሪ 1 ተብራርቷል።

የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳብ አስረግጦ በግልጽ እንደሚያስገነዝበው የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን ወደ ቦታው የሚያወርድ ጥንቁቅ ማስተካከያ ለውጭ ምርቶች ሳይሆን፣ ለአገር ውስጥ ምርቶች ተጨማሪ ገበያ በመስጠትና ኤክስፖርትን በማበረታታት የውጭ ክፍያ ሚዛንን ለማቃናት ያግዛል፡፡ ለዚህ የሚከፈለውን ዋጋ ለማቃለል ፈጣን ውጤት ለማየት ይረዳል። በእርግጥ አዳዲስ የኤክስፖርት አቅሞች እግር ለመትከል ጊዜ መውሰዳቸው ባይቀርም፣ የውጭ ክፍያ ሚዛን ሳይውል ሳያድር ይሻሻላል (ከውጭ በሐዋላ የሚላክና ወደ አገር ውስጥ የሚገባ የውጭ ምንዛሪ በማሻሻል በኤክስፖርት ዙሪያ የሚንጠባጠቡ ሒሳቦችን በማጥበብና በሌሎች መንገዶች ነው ፈጣን ውጤት የሚታየው)፡፡ የዓለም ገበያ ዋጋዎች ላይ ተፅዕኖ የሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች በዚያው መጠን በዋጋ ጫና ፍንክች አይሉም ካልተባለ በቀር፣ የገንዘብ ምንዛሪ ሲወርድና ሲስተካከል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መቀነሱና የውጭ ክፍያ ሚዛንም መሻሻሉ አይቀርም።

የቅርብ ጊዜ ዓይነተኛ ጥናት በግብፅ

እጅግ በቅርቡና በምሳሌነት የሚጠቀስ ፋይዳ ያለው ስኬታማና በገበያ የሚመራ  የውጭ ምንዛሪ ተመን በአፍሪካ ዕውን የተደረገው እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2016 ነበር፡፡ ግብፅ የሦስት ዓመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሯን የሚደግፍ የ12 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር ስምምነት ላይ ደረሰች፡፡ በገበያው እንዲመራ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን እ.ኤ.አ. በኅዳር 2016 በግብፅ ኢኮኖሚ ላይ ፈጣን አዎንታዊ ተፅዕኖ የፈጠረ ሲሆን፣ ኢኮኖሚውንም ከድንዛዜ አነቃቅቶታል፡፡ የጥቁር ገበያ ዕላፊ የዋጋ ርቀት በከፍተኛ መጠን ተወግዷል፡፡ የዶላር ዋጋ ወርዷል፡፡  የግብፅ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ተመንድጓል፡፡ የግብፅ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2016 መጨረሻ ከነበረበት ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2017 መጨረሻ ወደ 37 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ በ14 ወራት ውስጥ 18 ቢሊዮን ዶላር በመጨመር፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተወግዷል፡፡ ኢኮኖሚውም በአዲስ አቅምና ጉልበት ተጠናክሯል፡፡

ኢትዮጵያ የግብፅን ተሞክሮ መድገም ትችላለች?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ ተሞክሮውን ለመድገም ምን እንደሚያስፈልግ በቅድሚያ እንመልከት፡፡ የሚያስፈልገው የመጀመርያውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት የሚሸፍንና በገበያው የሚመራውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር የሚደግፍ፣ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኝ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በመንግሥት ባለቤትነት ከተያዙት ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹን በከፊልም ቢሆን ወደ ግል ማዛወር፣ ይህን የገንዘብ አቅርቦትና ከዚያም በላይ  ሊያመነጭ ይችላል፡፡ በአባሪ 1 ላይ እንደቀረበው የውጭ ምንዛሪ ቀውሱን ለመፍታትና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ራሱን ችሎ በዕድገት ጎዳና እንዲቀጥል የሚያስፈልገው የመነሻ ገንዘብ (ከተጠቆመው ተገቢ የማሻሻያ ፖሊሲ ጎን ለጎን) በመጀመርያው ዓመት አራት ቢሊዮን ዶላርና በሁለተኛው ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው፡፡ ይህን የገንዘብ መጠን ለማግኘት ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ይዞታነት ማዛወር ብቻውን በቂ ነው፡፡

በራሱ ድንቅ  ስኬት ቢሆንም፣ ፕራይቬታይዜሽን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የገንዘብ ችግር ብቻ አይደለም የሚፈታው፡፡ ሦስት ሥር የሰደዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችንም ለመፍታት ያግዛል፡፡ የዋጋ ንረት፣ መፈናፈኛ ያሳጣው የውጭ ምንዛሪ ቀውስና በግል ዘርፉ ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ የብድር እጥረት ናቸው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በሚያስፈልግበት ድባብ ውስጥ፣ የኢትዮጵያን በመንግሥት  ባለቤትነት የተያዙ ድርጅቶች ሰፊ የተከማቸ ሀብት ወደ ገንዘብ ለመለወጥ ፕራይቬታይዜሽን ግሩም መንገድ ነው፡፡ ሀቁን ለመናገር ይኼን የተከማቸ ሀብት ራሱ መንግሥት በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ታላቅ መስዋዕትነት ሊከፈልለት ይገባል ብሎ ለሚያምንበት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከማዋል የበለጠ ምክንያታዊ  አጠቃቀም መኖሩ ያጠያይቃል፡፡

መንግሥት በባለቤትነት የያዛቸው ሀብቶች ምንድን ናቸው?

ኢትዮጵያ በበርካታ አሥርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተገነቡ እጅግ ሰፊ የሀብት መሠረት ያላቸው ከ100 በላይ የመንግሥት ኩባንያዎችን በባለቤትነት በመያዝ በአፍሪካ አኅጉር የተለየች ናት፡፡ እነዚህ ሀብቶች በአብዛኛው ባለፉት መንግሥታት የተገነቡ ናቸው፡፡ ቀድሞ በግል የተያዙ ንብረቶችን በውርስ ወደ መንግሥት በማዛወር፣ ወይም በሶሻሊስት ተኮር የኢኮኖሚ አስተዳደር ዓውድ ውስጥ በአረንጓዴ መስክ ፕሮጀክትነት የተፈጠሩ፡፡ በመንግሥት ዘርፍ የተያዙ የሀብት መሠረት ያላቸው ኩባንያዎች መንግሥት  በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ተሳትፎ፣ ርቀትና ጥልቀት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም  መካከል በዓለም ስመ ጥር የሆነው አየር መንገድ፣ ከአፍሪካ ግዙፍ የንግድ ባንኮች አንዱ የሆነ ባንክ፣ በአገሪቱ ትልቁ የኢንሹራንስ ኩባንያ፣ ግዙፉ የንግድ መርከብ ድርጅት፣ ብቸኛው የቴሌኮም ኩባንያ፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች፣ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ፋብሪካዎች፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የብረታ ብረት ሥራ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ በመንግሥት ባለቤትነት ከተያዙት ሀብቶች ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡት አምስቱ ትልልቅ የመንግሥት  ድርጅቶች ተብለው ሊሰየሙ  የሚችሉ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ በተለየ ሁኔታ አስደማሚ የአፈጻጸምና የፋይናንስ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ  መድን ድርጅት፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የመንግሥት  የልማት ተቋማት ዕንቁዎች ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳያሰልሱ ከፍተኛ ዕድገትና የትርፋማነት መጠን እያስመዘገቡም ይገኛሉ፡፡

አምስቱ ትልልቅ ድርጅቶች በእርግጠኝነት ምን ያህል ያወጣሉ?

በዓለም ላይ ተቀባይነት ያላቸው የዋጋ መተመኛ  ዘዴዎችን፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ.  የ2018 ገቢና ትርፍ ገመታን በመጠቀም እንደተሰላው፣ እነዚህ አምስት ኩባንያዎች ብቻ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያወጣሉ፡፡ ይኼ አኃዝ ከፍተኛ ግምት ያለው ተጨማሪ ገንዘብ ሊያስገኙ የሚችሉትን ደርዘን የሚያህሉ ትርፋማ የመንግሥት  ድርጅቶች አይጨምርም፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምን በምሳሌነት ብንወስድ ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ግምቱ ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮ ቴሌኮም የአኅጉሪቱ ግዙፉ የሞባይል አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በኅዳር 2017 የሞባይል ደንበኞቹን ቁጥር ከ57 ሚሊዮን በላይ ያደረሰው የኢትዮጵያ ቴሌኮም፣ በሰፊ የሞባይል ደንበኞች ምክንያት የናይጀሪያው ኤምቲኤን በመተካት በአፍሪካ ግዙፉ ኩባንያ ሆኗል፡፡ ከዚህ በገሃድ ከሚታይ ስኬት በተቃራኒ ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ የአገራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ወደኋላ በመጎተት ከሚታወቁት አምስቱ ቀዳሚ የቴሌኮም ሞኖፖሊዎች ውስጥ የአንደኝነት ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ኩባንያውን በከፊል ብቻ ፕራይቬታይዝ ማድረግ ወደ ኢኮኖሚው ሊገባ የሚችል  ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ከማመንጨትም ባሻገር፣ በታክስና በገቢ ድርሻ ረገድ ቴሌኮም በመንግሥት እጅ ተይዞ ከሚያስገኘው የበለጠ ጥቅም ለመንግሥት ያስገኝለታል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮምን ፕራይቬታይዝ ማድረግ ከገንዘብ ጠቀሜታው ባሻገር፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እንቅፋት የሆኑትን ዝቅተኛ የአገልግሎት የጥራት ደረጃና በዓለም ግንባር ቀደሙን የታሪፍ መጠን ለማሻሻልም ያግዛል፡፡ ዛሬ የምንገኘው በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ነው፡፡ ቴሌኮሞች ደግሞ ለአዲሱ ኢኮኖሚ የመሠረተ ልማት የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ በጠንካራና ተፎካካሪ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ አማካይነት በአስደናቂ ፍጥነትና መጠን ከችግር በመውጣትና ሽግግር በማድረግ ረገድ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደሃ ሕዝብ ያላት ህንድ ማለፊያ ምሳሌ ናት፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ቴሌኮምን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መያዟ ‹‹የቴሌኮሙ ዓለም ሰሜን ኮሪያ›› የሚያሰኛት ቢሆንም፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ለሁሉም ለማዳረስና ልዩነት ለማጥበብ የመንግሥት ሞኖፖል ወሳኝ ሚና ይጫወታል የሚለው ነባር መከራከሪያ ሲነገር ይደመጣል። በተግባር ግን በየጊዜው ለመሣሪያ፣ ለቁሳቁስና ለኔትወርክ የሚያካሂዳቸው ግዥዎች ሲታዩ መላቅጥ የራቃቸውና የተተራመሱ ድግሶች ይመስላሉ። ለተቋሙ ከቻይና ብድር እየፈሰሰለትም ጭምር የግሉ ዘርፍ ቢሆን ያስተናግድ ከነበረው እጅግ ያነሰ ደንበኞችን እያስተናገደ ነው፡፡ ዋጋው  አሁንም ከፍተኛ ሲሆን አገልግሎቱ ግን ደካማ ነው፡፡ የገበያ ዕድገቱም ወደኋላ ቀርቷል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምን ፕራይቬታይዝ ማድረግ ከምንም በላይ በዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ሊሆን የሚችል አቅም ያለው ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን መንግሥት  የሚያደርገው ቁርጠኝነት ነው፡፡ (ተከታዩ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይቀርባል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...