Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየዴሞክራሲ ጮራ እየፈነጠቀ ነው! ወዴት እንደምናመራ ግን እርግጠኛ ነን?

የዴሞክራሲ ጮራ እየፈነጠቀ ነው! ወዴት እንደምናመራ ግን እርግጠኛ ነን?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

በአገራችን የዴሞክራሲ ጮራ እየፈነጠቀ ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭነት እየተጠናከረ ሆኖ ይታየቸዋል፡፡ ዕውን እንደዚያ ነው? ይኼንን ለማስባል ያደረሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉን ነገር ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ምክር ቤት እያስወሰነ አለመሥራቱ ከሆነ፣ ይህ አድርጎቱ የሚገጥመው ከፈላጭ ቆራጭነት ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ነፃነት ጋር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲውን ፖሊሲዎች ይዞ ከሕዝብ ፍላጎትና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እያገናዘበ በነፃነት ቢሠራ፣ ከሕገ መንግሥቱም ከዴሞክራሲም ጋር  ግጭት የለውም፡፡ ለፓርቲ ፖሊሲ መታመን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንኳ አይደለም፡፡ በፖለቲካ ዓለም እንኳን በግንባር በፓርቲም ውስጥ ብዙ ነገር ይፈጠራል፣ ፓርቲውና ግለሰቡ ሊለያዩ ሁሉ ይችላሉ፡፡ ምንም ተፈጠረ ምን፣ የሥራ አስፈጻሚ መሪው ግለሰብ ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወካዮችን ምክር ቤት መተማመኛ ድጋፍ እስካላጣ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን ሥር መሆኑንን እስካከበረና መተማመኛ ሲያጣም ዘራፍ እምቢኝ እስካለለ ድረስ፣ ከዴሞክራሲና ከሕገ መንግሥት ውጪ አይሆንም፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትን ውሳኔ የሚሹ ሆነው በሥራ አስፈጻሚው አካል ወይም በፓርቲው የተወሰኑ ነገሮች ካሉ የሥልጣን ድርሻውን የማስከበርና ተግባሩን የመወጣት ኃላፊነት ከማንም በላይ የምክር ቤቱ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከትናንት ይልቅ ዛሬ እየተጣሰ ስለመሆኑ ሊናገሩ የሚደፍሩ ካሉም፣ ቀድሞ የነበረው ሥርዓት በዴሞክራሲና ‹‹በሕገ መንግሥታዊነት›› የሚነግድ የጥርነፋ አገዛዝ እንደነበርና ሕገ መንግሥቱ ተጎድቶ የቆየው ከዛሬ ይልቅ በፊት እንደነበር ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ ከጥርነፋ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ጉዞ ውስጥ መግባትም ከበፊቱ ይበልጥ ሕገ መንግሥታዊ የመሆን እንጂ፣ ከሕገ መንግሥት የመራቅ እንዳልሆነ በራሱ የሚመሰክር ነው፡፡ ከዚያም በላይ ዛሬ የሚያንገላታን ቀውስ የቀድሞው ገዢነት ኢሕገ መንግሥታዊ (የስቀዛ) አገዛዝ ለዛሬ ያሳለፈልን ዕዳ ነው፡፡ ሰቃዥና ሁሉ በእጁ በነበረው የኢሕአዴግ ፓርቲ ወይም ግንባር ውስጥ ቀውስ መድረሱም ከስቀዛ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር መፍጨርጨር ውስጥ የመገኘታችን ሌላ መገለጫ ነው፡፡

ቀደም ብሎ የታየው የኦሮሞና የአማራ፣ የኦሕዴድና የብአዴን አንድ ላይ ማበርና ሌሎች ሕዝቦችና ቡድኖች አባሪነቱን እየተቀላቀሉ መምጣትም ለዴሞክራሲ ሲባል የተደረገ መገጣጠም እንጂ፣ አንዳንዶች ሊስሉት እንደሞከሩት በአናሳ ማኅበረሰቦች ላይ ግዙፎቹ የመግነናቸው ክስተት አልነበረም፡፡ ወደፊትም ካወቅንበትና ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ እስከ ሰመረ ድረስ፣ የአናሳዎቹ መብት በግዙፎቹ እንዳይዋጥ ዴሞክራሲው መጠበቂያ ማበጀቱ አይቀርም፡፡ ልክ እንደዚያው መጪው ዴሞክራሲ የፓርቲ አደረጃጀትንም ማረቁ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በፌዴራላዊ ሥልጣን ላይ የብሔር ፓርቲ በኅብረትና በግንባር ሽፋን ውስጥ ሆኖ የመውጣቱ ነገር በቅጡ መፈተሹ አይቀርም፡፡ ግዴታ ነው፡፡ የፓርቲ ከፍተኛ አካል ወይም ሰው ከአዛዥነት ይልቅ የአባላቱ መሪ የሚሆንበት፣ የፓርቲ ኮሚቴ ወይም ምክር ቤት ውሳኔን በማስፈጸም ወንበር ላይ የተቀመጠ ሰው በውሳኔው ባይስማማ ኃላፊነቱን ከመልቀቅ በቀር ውሳኔን ለመቀበል የማይገደድበት፣ በሐሳብ ልዩነት ምክንያት ከፓርቲ ማባረር የማይቻልበት፣ እንዲሁም በፓርቲ ውስጥ በሐሳብ ልዩነትና ክርክር ውስጥ መኖር መብት መሆኑ  የሚረጋገጥበት የፓርቲዎች ሕግም መምጣቱ ተጠባቂ ነው፡፡

በተቀረ በአሁኑ ደረጃ ከጥርነፋ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር እየሞከርንም በኅብረተሰቡም ሆነ በመንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ ከዴሞክራሲያዊነትና ከሕገ መንግሥታዊነት ያፈነገጡ ተገባራት መኖራቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ ገና ሽግግር ላይ ነንና ሁሉ ነገር በዴሞክራሲና በሕገ መንግሥታዊነት ሚዛን ሊመዘን አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ ያዘወትረው የነበረ የተወሰነ የሥልጣን መደብን እንደ ርስት ከየብሔረሰብ ጋር የማያያዙ ልማድ በዴሞክራሲ ገና ያለመተካቱም ጉዳይ ከዚሁ የሽግግር ጊዜ ገጽታ ጋር አብሮ ሊታይ የሚችል ነው፡፡

የአገሪቱን ፀጥታና ሰላም የማስከበር ወቅታዊ ፈተናን የፀጥታ ኃይሎችን ከፖለቲካ ወገናዊነት ከማፅዳት ሥራ ጋር ደርቦ የማካሄድ ተግባር ውስጥ መውደቃችንም በራሱ፣ ዴሞክራሲያዊነትን ቆንጠጥ ጠበቅ አድርገን እንድንራመድ የሚያስገድድ ነው፡፡ እንደምንገኝበት የፈተና ወቅት ከሆነማ በአግባቡ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊነትን የተጎናፀፈች አገር የመገንባት ዓላማ ላይ የሚገናኙ ፖለቲከኞች (በውስጥና በውጭ ያሉት)፣ በቅድሚያ አንድ ላይ ገጥመውና በጋራ ተልዕኮ ላይ ተሰማርተው የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ ከተደራጀ በኋላ፣ ሪፐብሊኩ ራሱ ያፈነገጠ ጥያቄ ካላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጋር የሚደራደርበት ምዕራፍ እንዲለጥቅ ማድረግ የበለጠ ኮረኮንቹ የቀነሰ መንገድ ነበር፡፡

እኛ ግን ዴሞክራሲያዊነቱን አፍጥነን ፖለቲካ ቡድኖችን በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ዕድል እስከ መስጠት ተራምደናል፡፡ ከዚህ ጋር ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያሉ የፀብና የኩርፊያ ጎራዎች የመፈርከስ ሒደት ውስጥ መግባታቸው፣ በለውጡ ዙሪያ ርብርቡ እየጨመረ መሆኑ፣ ግጭትና የማፈናቀል ችግሮችን በኃይል ከመደፍጠጥ ፈንታ በምክክር በይቅርታና በዕርቅ መንገድ ለማብረድ ብዙ ጥረት መደረጉ፣ በእስር ቤቶች አካባቢ የነበሩ ጥቃቶችና በደሎች እየተጎለጎሉ መውጣታቸውና እስረኞች ድምፃቸውን እስከማሰማት ድፍረት ማግኘታቸው፣ የጥርነፋ ገዢነትን ለማስጠበቅ ብዙ የሕዝብ ሀብትን ይፈጅ የነበር የደኅንነት አውታር ባህርዩን እየቀየረ መሆኑ (ቢያንስ ተቃውሞንና አገዛዛዊ ገመናን የሚያጋልጡ የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ለማፈን የሚከሰከስ ሀብት  መቋረጡ)፣ የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመለከቷቸውን መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ አውቀውና ኮንትራት አስፈርመው በደንብ እንዲከታተሉ መወጠኑ ፈላጭ ቆራጭነት እየተጠናከረ ነው ለሚል ድምዳሜ ፈጽሞ መነሻ ሊሆን አይችልም፡፡ ይኼንን እያዩ ስለፈላጭ ቆራጭነት ማውራት ለውጡ ኮሰኮሰኝ ከማለት አይተናነስም፡፡ በቀድሞው ጊዜ በሥልጣን ላይ እያለ እንዲህ ያለ ንግግር የተናገረ ሰው ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል ወይም በሽብር›› የተሳበበ ጥፋት ተሸርቦ ምን እንደሚከተለው ሁላችንም እናውቃለን፡፡ (በነገራችን ላይ ተቺዎች የኢዴሞክሲያዊነትንና የፀረ ዴሞክራሲያዊነትን፣ የኢሕገ መንግሥታዊነትንና የፀረ ሕገ መንግሥታዊነትን ትልቅ ልዩነት በቅጡ ተረድተው በልዋጭነት ከመጠቀም ቢቆጠቡ ተሳስተው ሰው ከማሳሳት ይድናሉ፡፡)

ለዴሞክራሲ እየተሰባሰብን ብንሆንም የቆምነው ረመጥ ላይ መሆኑ ግን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዴሞክራሲ ለውጡ ቁርሾና መኮራረፍን እያፈረሰና ዕርቅንና የፖለቲካ ድጋፍን እየበራከተ ቢሆንም፣ የለውጥ ተቀናቃኞችን የሻጥርና የሴራ አደጋ ገና አልተገላገልነውም፡፡ ዴሞክራሲን ፈላጊው ኅብረተሰብ ራሱ በኢዴሞክራሲያዊ ፍላጎቶችና ፀባያት የሚናውዝ መሆኑ ጉዞውን ዘገምተኛና ቀርፋፋ ከማድረጉም በላይ ለአሻጥረኛ ቅስቀሳዎች አጋልጦታል፡፡ የዚህ አካባቢ ባለቤት (ባለይዞታ) እኛ ነን የሚለው አመለካከት እስካሁን አለመሰበሩና ሁሉንም የአገር ልጅ በእኩል ዓይን ማየት አለመተከሉ፣ ከግለሰቦች አሳሳችነት ይበልጥ የግጭትና የማፈናቀል ተግባራት እናት ሆኖ ዛሬም ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይነቃነቅ እንደነበር የነበረና እስከ ዛሬ ያለ ሕዝብ በአንዳችም ሥፍራ አለመኖሩ (ሁሉም በእንቅስቃሴ፣ በፍልሰትና በመንፏቀቅ ታሪክ ውስጥ አልፎ እዚህ መድረሱ፣ ሒደቱም የዓለም ሕዝብ ታሪክ ባህርይ መሆኑ) ኢትዮጵያ ውስጥ ገና የሚታወቅ አይመስልም፡፡ ይህ እውነት በዘመዳምና በተጎራባች ሕዝቦች መሀል የተደረገ ክንዋኔ አድርጎ ከማሰብ በላይ፣ አልፎም የሚሄድ ‹‹አገር›› ዘለልና አኅጉር ዘለል ክንዋኔ ነው፡፡ የማዳጋስካር የሕዝብ ጥንቅር ከአፍሪካዊ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ከኢንዶኔዥያ ፈላሲዎችና ከዓረቦች የተቀናበረ እንደሆነ፣ ዛሬ የማሌዥያ መጠሪያ ሆኖ ያለው የማሌ ሕዝብም ከኢንዶንኔዥ ጋር ጥንታዊ የአመጣጥ ግንኙነት እንዳለው፣ በአጠቃላይ የሃይማኖቶች መዛመትና የኢምፓየሮች መስፋፋት ከጥንት እስከ ቅርቦቹ የኦቶማንና የአውሮፓ ኢምፓየሮች ድረስ ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴና መደበላለቅ እንደፈጠሩ፣ በዚሁ ምክንያት ልዩ ልዩ አገር ውስጥ የገቡ አኅጉር ዘለል መጤዎች ዛሬ ባለ አገር ወይም ዋና ባላገር ሆነው በአፍሪካ ሳይቀር እንደሚኖሩ እኛ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ በብሔር መብት ስም ከተተከለው አካባቢያዊ የይዞታ ቅርጫ የሚፈልቅ የካርታና የማኅበረሰባዊ ጥቅም ይዞታ የማስፋት ትንኮሳና ግጭት፣ አሁንም አገሪቱን እያወከና ሰዎችን እያፈናቀለ ያለ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ፕሮፌሰር ተሰማ ታአ ኦሮሞ እንደ ሙጫ ሆኖ አነፃት ያሏት ኢትዮጵያ፣ በማፈናቀል ምክንያት ዛሬ ደግሞ በኦሮሞም ሆነ በሌሎች ማኅበረሰቦች የተያያዘችባቸው ድርና ማጎች የመበጣጠስ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፡፡

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ መሰባሰብን እያቀነቀነ ስለመሆኑ፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ውስጥም አቋምን በሰላም ማራመድ ይቻላል ስለመባሉና የአሸባሪነት ፍረጃው ስለመነሳቱ አልሰማ ይሆን እስኪያሰኝ ድረስ፣ የኦነግ አንድ አንጃ አሮጌ የትግል ሥልትን ሙጥኝ ብሎና በግርግር ለመጠቀም ብሎ በአንዳንድ የአገሪቱ ዳርቻ እየተኮሰ መሆኑ ሌላ የእኛ አገር ጉድ ነው፡፡ ተኩሱ ለጊዜው ዳር አካባቢ ቢሆንም ዛሬ የተከሰተው የመሣሪያ ዝውውር፣  የጥፋት ሥራ ነገ መሀል አገር ድረስ ሊመጣ እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ በመሣሪያ ዝውውር ላይ የሚካሄደው መንግሥታዊ ክትትል ምን ያህል ንቁና ብቁ እንደበርና እንደሆነ ባናውቅም አዲስ ዝውውርን ከመከታተል ባሻገር ከዚህ በፊት የተበተኑ መሣሪያዎች ጉዳይም የሚያሳስብ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ነባርና አዲስ ገብ የፖለቲካ ቡድኖች ከለውጡ አኳያ ምን ዓይነት ሚና እየተጫወቱ እንደሆኑ የአደባባይ መረጃ በማናገኝበት ድብስብስ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንም ይጎረብጣል፡፡

የአማራና የትግራይ ሕዝብ እንቆቅልሻዊ ሁኔታ ውስጥ መገኘት ሌላ አሳሳቢ ገመና ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ እንደ ሌላው ሕዝብ የዴሞክራሲ ለውጥ ደጋፊ ከመሆኑ ባሻገር፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ጉልህ የትግል አስተዋፅኦ ያደረገ ሕዝብ ነው፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ መንጓለል የደረሰበት እንደ መሆኑም ለውጡን መደገፍም ሆነ ለለውጥ መታገሉ አያንሰውም፡፡ ለውጡን እየደገፈም፣ ዕርቅና ይቅርታን እየዘመረም ለዓመታት ከተጠራቀመ አሉታዊ ስሜት የመላቀቅ ትግል ያለበት መሆኑም ከሌላው ሕዝብ ሁሉ ጋር የሚጋራው ፈተና ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ኢዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ በዋለው የክልል ሽንሸና ከወሎና ከጎንደር ወደ ትግራይ በዞሩ ይዞታዎች ምክንያት ሲብሰለሰል የኖረበት ቅሬታ ዛሬ ግልጽ ወጥቶ መፋጣጫ ለመሆን በቅቷል፡፡ በብአዴን ውስጥ የዚህ የፍጥጫ ፖለቲካ ተጋሪዎች የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠር ቢቻልም፣ ብአዴን በድርጅትነቱ የዚህ ፍጥጫ አቀንቃኝ ሆኖ አናየውም፡፡ በትዩዩም የአማራ ሕዝብን ከፍጥጫና ከግጭት የሚያወጣና በሁለቱም ክልሎች ተቀባይነት የማግኘት አቅም ያለው መፍትሔ ማቅረብና ሕዝብን ከጎኑ ማሠለፍም አልተቻለውም፡፡ ይህ ክፍተት ከወሎና ከጎንደር ወደ ትግራይ የገባ መሬትን እምብርታዊ ጉዳዩ ያደረገ ድርጀት እንዲወለድ አግዟል፡፡ እናም ከሕወሓት ጋር ያለው ይዞታ ነክ ፍጥጫ ከአማራ በኩልም ድርጅታዊ ቅርፅ ሠርቶ ሊወጣ ችሏል፡፡ ከዚህ ፍጥጫ አኳያ የአማራም የትግራይም ሕዝቦች፣ ከግጭት ይልቅ ወደ ዕርቅና ፍቅር የሚወስድ አካባቢያዊ የለውጥ ፓርቲ ገና የላቸውም ማለት ስህተት አይሆንም፡፡

የትግራይ ሕዝብ የለውጥና የዕርቅ ፓርቲ የለሽ የሆነበት እውነታ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ካለበት ሁኔታ በብዙ ነገር የሚለይ እንደ መሆኑ በጥሞና መጤንን ይሻል፡፡ ከደርግ ጊዜ አንስቶ ለነበረው የትግራይ ሕዝብ የትግል ታሪክ ሕወሓት ብቸኛ መገለጫ ነበር ባይባልም፣ ዋነኛው እንደነበር አይካድም፡፡ እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሕዝብና በሕወሓት መሀል የተፈጠረው መስዋዕትነትን ያዘለ የትግልና የመንፈስ ትስስር የዋዛ አይደለም፡፡ ከትግል ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ ህሊና ላይ የተሠራው ሥራ ከውጪ ሆኖ እንደሚፈርዱት በቀላሉ የሚወገድ አይደለም፡፡ ከ‹‹ድል›› በኋላ እስከ ዛሬዋ ሰዓት ድረስ 27 ዓመታትን የዘለለ ገዢነቱም ከእነ ፕሮፓጋንዳው በሕወሓት እጅ ውስጥ ነው፡፡ ይኸው ድርጅት ሁኔታዎች ተቀያይረው ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ስለመግባቱና ጥፋት ስለመሥራቱ አውስቶ ይቅርታ ቢጠይቅም፣ ወገንተኛ አገዛዝ በመገንባት ረገድም ሆነ ከፓርቲያዊ ኩባንያዎች ግንባታ ጋር የተያያዙ ዋነኛ ጥፋቶችን ተቀብሎ ወደ ለውጥ መግባት እንደቸገረው ያለ ነው፡፡ ዛሬም የቀድሞውን ሕወሓት ገነን ገዥነትን ለማስመለስ የሚሹም ወገኖች፣ ለውጥ ፈላጊዎችና በሁለቱ ክንፎች መሀል የሚወላውሉ ክፍሎች ሁሉ አንድ ላይ እየተሻሹ ይገኛሉ፡፡ ይኼንን ለማለት የደፈርኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ትልልቆቹን ጥፋቶች በመቀበልና በማራገፍ ረገድ ዛሬ ከተድበሰበሰ ድርጅታዊ ዝምታ በቀር የተሰማ ነገር የለም፡፡

ከብሔረተኛነት ጋር የተያያዙ የሕወሓት ጥፋቶች በ27 ዓመታት ልምድ ድርጅቱን ከማስጠመድ ባሻገር ጦሳቸው ለብሔሩም መትረፉም እውነት ሆኖ ሳለ (ገና ቀደም ባሉ ጊዜያት የብሔረተኛ ስብስብና አካሄድ ጠንቀኛነቱ ተተንትኖ ሳለ) ዛሬም ድረስ ከሕወሓት በኩል ትልቁን የድርጅቱን ጥፋት ጠንቀኝነት ያስተዋለ ግምገማ ተፈልቅቆ ሲወጣ አላየንም (ትግራዊ ላይ የደረሰውን ጥላቻ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የተካሄደ የፀረ ሕዝቦች ዘመቻ ውጤት አድርጎ ከማቅረብና የግለሰባዊ ማጋጣነትን ቁንጣሪ ሀቅ ከማመን በቀር)፡፡  ሌላ ሌላው ቀርቶ የፌዴራል ምርመራና የእስረኛ አያያዝ ብዙ ጉድ በወጣበት በአሁኑ ሁኔታ ውስጥ እንኳ፣ ለአሰቃይነት ሳይቀር ትግራዊን የመጠቀም ጥፋት ምን ያህል ጦሰኛ ውጤት እንዳስከተለ አስተውሎ የተቆጨ ድምፅ ሹክሹክታን ጥሶ አልወጣም፡፡

ይኼንን ያህል ድፍንፍን ካለ ሁኔታ ጋር በሕወሓት አስተዳደር ውስጥ የሕዝቡ ኑሮ እንደመቀጠሉ ያለፈው የጥላቻ ጥላ ገና ተገፍፎ አልወደቀም፡፡ ለወህኒ ቤት እስረኛ ሮሮ ምላሽ ሰጪ ሹም ትግራዊ ሆኖ ሲታይ ሌላው አጀብ እንደሚል ሁሉ፣ ትግራዊም ከመሳቀቅ አያመልጥም፡፡ ርካሽ ድጋፍ ፈላጊዎች ወይም የፖለቲካ ሰዎች ጥንቃቄ የጎደለው የቃላት አጠቃቀም ዛሬም ይቧጭሩታል፡፡ የአማራ ክልል የንብረትና የሕይወት ጉዳት የደረሰባቸውን ተፈናቃዮችን በተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ መልሶ ለማቋቋም የወሰነው ውሳኔ፣ ከመንግሥት አቋምነት አልፎ የአማራ ሕዝብ የዕርቅና የመተሳሰብ እንቅስቃሴ (የመፈናቀል መድረቅ ማረጋገጫ) ሆኖ ባለመከሰቱ እሰይታ የመፍጠርና ወደ ተግባር የመለወጥ አቅም አልነበረውም፡፡ በትግራይ ተፈናቃዮች ላይ ያለው ሥጋት አሁንም እንዳረበበ ነው፡፡ እናም ትግራዊ በጥቅሉ የሚገኘው በመኮርተም ውስጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

የአልጀርስ ስምምነት ከመሳበያ ወጥቶ ለኢትዮ ኤርትራ ዕርቀ ሰላም ሲውል እንኳ ቀና ውጤት በሚገኝበት አቅጣጫ፣ የትግራይ ሕዝብ የዕርቁ ንቁ ተጋሪ እንዲሆን አለኝታህ ነን ባዮቹ አላገዙትም ነበር፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች (አበበ ተክለ ሃይማኖትና ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ) በናሁ ቴሌቪዥን ቀርበው በሕወሓት ጥፋት ዳፋ የትግራይ ሕዝብ ያለኃጢያቱ እየደረሰበት ስላለው ጉዳት፣ በማያፈናፍን አገዛዝ ውስጥ ሌላው ሕዝብ የኖረበትን ፖለቲካዊ መቆራመድ የትግራይ ሕዝብም የኖረበት ስለመሆኑና ጭርታው ከሥጋትና ከአገዛዝ ጫና እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን ያለመናፈቅ ላለመሆኑ ያተቱት የለውጥ መሪነት መጓደሉ አሳስቧቸው፣ ያንን ክፍተት የመሙላት ሚና ላፍታ መጫወታቸው ነበር፡፡ በእርግጥም ለለውጥ መፈራገጥ ትግራይ ውስጥ ስለመኖሩ የሚጠቁሙ ፍንጮች እንዳሉ ይታወቀል፡፡ ፍንጭ ማነፍነፍ ውስጥ ሳይገባ፣ በሥጋትና በጥላቻ መኮራመትን በዕርቅና በፍቅር አሸንፎ እየተሳሰቡ አብሮ የመጓዝ ተስፋ ውስጥ መግባት ለትግራይ ሕዝብ ተፈጥሯዊ ጥቅሙ መሆኑና ለዚህም እንደማያቅማማ ዕውቅ ነው፡፡ ይኼን እውነት ማወቅ ብቻ ግን ፋይዳ አያመጣም፡፡ አጣብቂኙ መፍረስ አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የትግራይ ሕዝብ ያለበትን አጣብቂኝ በማስተዋል የሌሎች አካባቢ አስተዳደሮችና የለውጥ ቡድኖች የትግራይ ሕዝብ የለውጡ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያደፋፍር አጥጋቢ ዕገዛ አለማድረጋቸው አንዱ የለውጡ ጉድለት ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉትን የትግራይ ሰዎች ወደ ንቁ ተሳታፊነት መሳብና የተፈናቀሉትን በልባዊ ዕርቅ መጥራት ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ፣ ይህ በራሱ የትግራይ ሕዝብ ሆ ብሎ እንዲንቀሳቀስ ብርቱ መልዕክት በረጨ ነበር፡፡ በሕወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ ወገኖችም ሆኑ ከደጅ የገቡ ትግራዊ የዴሞክራሲ ወገኖች ባዶ የሆነውን የለውጥና የዕርቅ መሪነት ሚና ለመሙላት መዘግየታቸው ሌላ ክፍተት ነው፡፡

በእርግጥ ጄኔራሎቹ በ‹‹ናሁ›› ቲቪ አስተያየት ከሰጡና እነሱንና እነ ‹‹አረና ትግራይ››ን፣ የ‹‹ትዴት›› ሰዎችን፣ ወዘተ ያካተተ ስብሰባ ሕወሓቶች በመቀሌ ካደረጉ ወዲያ፣ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሰላም ድጋፍ መስጠትን አንድ ዋነኛ ጉዳዩ ያደረገው የሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የመቀሌ ስታዲዮም ትዕይንተ ሕዝብ መዘጋጀቱ የእነሱንም ጥረት ይጠቁማል፡፡ ይሁን እንጂ የስታዲዮሙ ትዕይንት የኢትዮ ኤርትራን ዕርቅ ከመደገፍና በኢንጅነር ስመኘው በቀለ አሳዛኝ አሟሟት ከመቆጨት ውጪ፣ እምብዛም አዲስ ነገር የሌለበት (ሕወሓት ለጥላቻ መፍትሔ ከማዋጣት ይልቅ ዛሬም ያለነው እኛው ነን ያለበት ከመሆን ያላለፈ) ነበር፡፡

‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር! የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በሰላም ሠርቶ የመኖር መብት ይከበር! ማንኛውም የብሔር ጥቃት ይቁም!›› የሚለው ጥያቄ ቀደም ብሎ በእነ መለስ ጊዜ ሁሉ የነበረና በአግባቡ ያልተመለሰ፣ እንዲያውም የጥላቻ መዛመት በመንግሥት እየተካደና እየባሰበት ሄዶ ዛሬ ላይ የደረሰ ችግር ነው፡፡ ዋናው ጉዳይም የ‹ይከበር› መፈክርን ማስተጋባቱ ሳይሆን ይህ እጅግ ተፈላጊ ውጤት እንዴት እንደሚገኝ የመመለስ ጉዳይ ነው፡፡ ሰብዕና በጥላቻ መንጨፋረሩና ለመጠቃቃት መዳረጉ የ27 ዓመት አገዛዝ ፍሬ እንደ መሆኑ ሕወሓት መብት ይከበር ብሎ ከማስፈከር በላይ ጥላቻን በመፈረካከስ ትግል ላይ ዕዳ አለበት፡፡ ይኼንን ግዴታ በማየትና በመወጣት ፈንታ ተከባብሮ መኖር ላለመቻል መበታተን አማራጭ እንደሆነ አድርጎ መናገር አሳዛኝና ጥፋት አያልቅበት መሆን ነው፡፡ የቀጣናችንን ወጀባምነት እንተወውና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወጀብ ራሱ ተበታትኖ ከመጨራረስ ይልቅ እየተረገጡም መትረፍን እስከ ማስመኘት ድረስ አስፈሪ መሆኑን፣ ማለትም ዛሬ ባለንበት እውነታ ውስጥ ያለን ዕድል እንደ ምንም ችግሮችን አቃሎ መከባበር የሰፈነበት ቤት ከማደራጀት በቀር አማራጭ የለሽ መሆኑን ማስተዋል ዕውን እንቆቅልሽ ነው?

የትግራይ ሕዝብ ይኼንን ልብ ብሎ ሊፈታው የሚገባ እንቆቅልሽ ግን አለ፡፡ የለውጥና የዕርቅ ንቁ ታሳታፊ መሆን ከሕወሓት ጋር ያለ የትግል ቁርኝትን መሰረዝ ወይም ሕወሓትን መኮነን የሚጠይቅ አይደለም (እንኳን የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ ቀሪው ሕዝብም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ሕወሓት የተጫወተውን በጎም ሆነ አሉታዊ ሚና እንዳልነበረ ሊያደርገው አይችልም)፡፡ የትግል ቁርኝትን ማክበርና መጠበቅ ግን ጥፋትን አለማየት ወይም የአመለካከት ቁራኛ ሆኖ መቀጠል ማለት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የትኛውንም ምድር አገሬ ብሎ የመኖር ረዥም ታሪክ ያለው የትግራይ ሕዝብ ትግራይን እንዲያበልጥ፣ የተሟሸበትን ርዕዮተ ለዓለም ሰብሮ መውጣት እንዳለበት አስተዋሽ ይሻ ይሆን!? አገር ምድር ኢትዮጵያዊ ከውስጥ እስከ ውጭ ያነሳውን ‹‹የእርቅ፣ የይቅርታና የመደመር›› መፈክር  ከፍ አድርጎ መጋራት ከሌሎቹ ሕዝቦች ጋር እንደሚያስተቃቅፈው፣ መሬት ላይ ካለ ፍጥጫም የሚገላግል ሰላማዊ መፍትሔ ወደ መፈለግ እንደሚወስደው ማየትም ከባድ አይመስለኝም፡፡

ሁላችንም አበክረን ልናጤነው የሚገባንን አንድ ነገር አጠንክሬ ልናገር፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝቦች ከመሬት ጋር በተያያዘ ፍጥጫ ራሳቸውን እስከ አስጠመዱ ድረስ፣ በዴሞክራሲና በሰላም ውስጥ የመኖር ናፍቆታቸው ከቃልና ከምኞት ማለፍ እንደማይችል ይወቁት!!! ቀሪዎቹ የአገሪቱ ሕዝቦችና የፖለቲካ ቡድኖችም የትግራይን ሕዝብ የዘነጋ የዕርቅና የይቅርታ ጩኸት ጥልቀት የለሽ ከመሆን እንደማይዘልና ጥላቻን ድል የመምታት ፈተናንም ማለፍ እንደሚከሽፍበት ይወቁት!!! የትግራይ ሕዝብ የይቅርታና የዕርቅ መፈክርን ማስተጋባት እንደቸገረው ከቆየ፣ አስተዳደሩም ተስፋ ቆርጦ ተፈናቃዮችን እዚያው በቋሚነት በማቋቋም ላይ ከፀና ድርጊቱ በጥላቻ የመሸነፍ ሌላ ገጽታ ነው፡፡ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ ኑሮና የቤተ እምነቶች አቅማችንን ሁሉ አስተባብረን ከአንጀት ከተነሳን ጥላቻንና ጥርጣሬን ማሸነፍ አያቅተንም፡፡ ከልብ ይቅር ከተባባልን ደግሞ ለየትኛውም ችግር መፍትሔ ማግኘት አያቅተንም፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንንም ሁሉ ወደ ነበሩበት መልሶና ተጋግዞ ማቋቋም ‹‹ለላም ቀንዷ…›› እንዲሉ አይከብደንም፡፡

እንዴት “እንደመር”? ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ የአመለካከቶች ‹‹መደመር››፣ የፖለቲካ ቡድኖች ‹‹መደመር››፣ የማኅበረሰቦች ‹‹መደመር›› እንደ ቁጥር ቀላል አደለም፣ የጋራ መያያዣ መቆናጠጥን ይጠይቃል፡፡ በ1960ዎች ጊዜ የነበረ ብሔረተኛነትንና አብዮተኝነትን በፊት እንደምናውቀው ደርቆ ዛሬ አናገኘውም፡፡ ያኔ የተዋጉ ዛሬ አንድ ላይ ሆነው ወይም ፍጥጫቸውን ጥለውና ዘፈናቸውን ቀይረው እናገኛቸዋለን፡፡ የኢሕአፓ ታጋይ የነበረው ብርሃኑ ነጋ ከኢሕአፓ አልፎ ተሰዶና ተምሮ በኢሕዴግ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የቀድሞ አመለካከቱን ተሸክሞ አልመጣም፡፡ የኢሕዴግ አገዛዝን በቅርብ ሆኖ ካየው በኋላ ስለኢሕአዴግ የነበረውም ግንዛቤ ገና ሲመጣ ከነበረው ግንዛቤ ጋር አንድ አልነበረም፡፡ በቅንጅት መፈጠርና ትግል ውስጥ አልፎ እስራትን ከቀመሰም በኋላ ወደ ትጥቅ ትግል የወሰደው የግንዛቤ ለውጥ ነው፡፡

በኦነግ ውስጥ ብሔርተኛ ሆኖ የታገለው ሌንጮ ለታም ሆነ ድርጅቱ ኦነግ በታሪክ አጋጣሚ በኢትዮጵያ መንግሥት መንበር ላይ በሆነ መልክ ከሌላ ቡድን ጋር አንድ ላይ እንቀመጣለን የሚል ዓላማም ግምትም አልነበራቸውም፡፡ ግን በ1983 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ አጋጣሚው ተከስቶ ሲሆንና ሲጨነግፍ ዓይተናል፡፡ ኦነግ ከሽግግር መንግሥት ወጥቶ በሒደት ብዙ ነገሮች ከመለዋወጣቸው ጋር የኦነግም አመለካከት ሴመኛ ሆኖ መቆየት አልቻለም፡፡ በልዩ ልዩ አንጃ መሰነጣጠቅ፣ እንደ ገና ደግሞ የመሰባሰብ ጥረት ዓይተናል፡፡ እነ ሌንጮ የፈጠሩት ስብስብ እንደ ዱሮ የትጥቅ ትግልን መንገዴ ያለ ሳይሆን ሰላማዊ ትግልን ያጠበቀ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ወደ ትጥቅ ትግል ከዞረው ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ኅብረት መፍጠር ችሎ ነበር፡፡

ዛሬ ደግሞ ሁኔታዎች ተቀይረው እነዚህ ቡድኖች አገር ውስጥ ወደ መግባትና ዴሞክራሲና ነፃነት የፈካበት አገር ወደ መገንባት ፊታቸውን መልሰዋል፡፡ በምሳሌነት የጠቀስናቸው ቡድኖችና ሰዎች ያለፉባቸው የፖለቲካ ጉዞዎች ሁሉ የአመለካከት ለውጦች የታዩባቸው እንደመሆናቸው ሁሉ፣ የተያያዥነትም መገለጫዎች ናቸው፡፡ ተያያዥነታቸው የሚገለጸው ተለያይቶ ከመታገል ወደ መጎዳኘት በመሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ያለፉባቸው የተቃረኑና የተፈናገጡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጊዜያት ውስጥ ለሁሉም ትምህርት እየሆኑ የአገሪቱን የፖለቲካ ልምድ በማብሰልና በማበልፀግ አስተዋፅኦ ስለሚሰጡም ነው፡፡ ከ1960ዎች እስካሁን 2010 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኑሮ ውስጥ ያለፍንበት እሳትና ጭድነት፣ መረሻሸን፣ ደብዛ ማጥፋት፣ ሴራ፣ ወዘተ የተገማሸረበት የፖለቲካ ልምድ፣ ገዳይም ተገዳይም፣ አልቃሽም፣ አቅራሪም፣ ግትርም ተገለባባጭም አድርጎ ለዋውሶን ሁላችንም አነሰም በዛ የየራሳችንንና ከትውልዳችን የተጋራነውን ጥፋትና ድክመት ከእነ ጥንካሬው እንድናይና እንድንሻሻል ዕድል ሰጠን እንጂ አልነፈገንም፡፡

ዛሬ ይቅር መባባላችንና ያለፈውን ትተን አብረን መሥራታችን የዚሁ መገለጫ ነው፡፡ ዘመኑን አርዝመን ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ ባለው የታሪክ ጎዳና ውስጥ የተካሄዱት የሕዝብ እንቅስቃሴዎች (ፍልስቶች፣ ዘግናኝ ጦርነቶች፣ የመገፋፋትና የመዋዋጥ ክንዋኔዎች) ሁሉ በባህል፣  በእምነት፣  በቋንቋዎችና በነገድ የተወራረሱ (ዝንጉርጉርና ተመሳሳይ ገጽታዎችን በአንድ ላይ ያዘለ) ሰፊ ኅብረተሰብና አገር እንዳስገኙልን ማየት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ ኩነናና ውዳሴያችንን ተሻግረን፣ የአተረጓጎም ልዩነትና ክርክር መኖሩም የማይቀር (ጤናማ የግንዛቤ ማበልፀጊያ) መሆኑን ተቀብለን በጋራ የሚያስማሙንን የታሪክ ፍሬ ነገሮች አንጥሮ የህሊናና የልቦና መያያዣችን የማድረግ ሥራን ገና አላሟላንም፡፡ ይህ ቀላል ጉድለት አይደለም፡፡

ይኸው ክፍተት የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይም ጥላውን ያጠላል፡፡ ኢሕአዴግ ከቁጥጥሩ ባልወጣ ውክልና አማካይነት ሕገ መንግሥት የማዘጋጀትና የማስወሰን ሒደት ውስጥ፣ የሰንደቅ ዓላማ አርማን መቀየሩና የቀለማት ትርጓሜን ማረቁ በመሠረቱ ሁሉንም የሚያስማማ ነገር የማበጀት በጎ ሙከራ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ነገር ሕዝብ በነፃነት እንዲወሰንበት ባለመተው ሙከራው የኢሕአዴግ (ቡድናዊ) ሥራ ተብሎ ከመፈረጅ አላመለጠም፡፡ እናም የኢሕዴግን አገዛዝ የመቃወም ትግል ሰንደቅ ዓላማ ላይ የታከለውን አርማ የሚምር አልሆነም፡፡ ይኸው ዛሬ ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ሀብት የሆነውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ (ያለ ዓርማ) ይዞ ሠልፍ መውጣት፣ የኢሕአዴግን አገዛዝ የመሰናበቻ ምልክት ሆኖ በአያሌ ሥፍራዎች ሲከሰት እያየን ነው፡፡

የአሁኑን አዝማሚያ ዓይተው ዓርማ የለሹ ባንዲራ ሳይነካካ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ሆኖ የፀደቀ ያህል የሚሰማቸውና ከወዲሁ ስለመፅደቁ ጥርጣሬ የሌላቸው ዝንባሌዎችም እየጎለበቱ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም (ይኼንኑ አዝማሚያ ዓይቶና አያሌ ድጋፍ የማፈስን አጋጣሚም አስቦም ይመስላል) የኢትዮጵያ ባንዲራ በሕዝብ ይሁንታ እንዲወሰን ከማለት ጋር ‹‹እንዲመለስ›› የሚል ጥያቄም አቅርቧል፡፡ አሁን እየደራ የመጣውን ልሙጥ ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብን በመቃረን ‹‹ሕገወጥነት እየተበራከተና ቅልበሳ እየመጣ ነው›› የማለትን ነገር፣ ያለፈውን ሕወሓታዊ የኢሕአዴግ አገዛዝ የመናፈቅ ነገር አድርጎ የማቅለልና የመናቅ ዝንባሌም አለ፡፡

ይህ ዝንባሌ በጊዜ ካልታረመ (አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ የሁላችን ሀብት የመሆኑን ያህል አዲስ ታሪክና ተስፋን የሚወክል ምልክት እንዲታከልላቸው የሚሹ ወገኖች እንዳሉንና ያለው የሰንደቅ ዓላማ ዓርማ መላ ሕዝቦችን በአግባቡ ማስተቃቀፍ ካቃተውም፣ ተረጋግቶ በሕግና በዴሞክራሲ ውስጥ እንደገና የማየትን ዕድል ማንም እንደማይነጥቀን ከወዲሁ ካልተጤነ)፣ አፈንጋጭ ፖለቲከኞች ውስጥ ውስጡን ቅስቀሳቸውን ለማድራት የደላ ሁኔታ ያገኛሉ፡፡ በዚያው ልክ የልሙጥ ሰንደቅ ዓላማ አፍቃሪነትም ለድርድር ቀዳዳ እስከ አለመስጠት ድረስ ደንድኖ መላተም እንዳያስከትል ያሰጋል፡፡  

በየብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች የፈለገውን ያህል የዓላማ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውምና በግንባር ቢሰባሰቡም፣ እያንዳንዳቸው ወደ ብሔራቸው ማድላታቸውና ከሌላው ይልቅ የብሔራቸውን ሰው የማመን ጉድጓድ ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም፡፡ ሕወሓት ዋነኛ በነበረበት የበፊቱ አገዛዝ ጊዜ ፌዴራላዊ አውታርን በሕወሓታዊ ቁጥጥር ውስጥ ማስገባቱም፣ በመሠረቱ የአመለካከቱና የአደራጃጀቱ ባህርይ ውጤት ነበር፡፡ ሌላውም በየአካባቢያዊ ገዥነቱ ውስጥ የዚያ ዓይነቱን ጥርነፋ ፈጽሞታል፡፡ በብሔር ተሰባስቦ መግዛት የእኔ ብሔር እየገዛ ነው የሚል ግንዛቤንና በብሔር መንገድ መጠቃቀምን እንደሚያመጣ፣ የብሔራችሁን ሌባ ሳታዩ የብሔሬን ሌባ አትዩብኝ እስከ ማለት ዕይታን እንደሚያጠናግር፣ በብሔር የበላይነት ሥር ወደቅን የሚል ቅሬታም እንደሚያስከትል ታይቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ብሔረተኛ ገዥ ቡድን የሚሠራቸው ጥፋቶችና ነውሮች ለብሔረሰቡም የሚተርፍ አሉታዊ ስሜት እንደሚውልዱ የእስካሁኑ ልምድ ሊዘነጋ የማይገባው ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ብሔረተኛ ቡድኖች ለብሔረሰቦች መጠመድ ጦስ ሊሆኑ የሚችሉበት ቀዳዳ ዛሬም እንዳለ ነው፡፡

የዴሞክራሲ ለውጥ ወዳዶች በኢሕአዴግም ውስጥ ከኢሕአዴግም ውጪ በልዩ ልዩ መልክ በርክተው ቢገኙም፣ ዴሞክራቶችን ከየአቅጣጫው እየሳበ በማሰባሰብ ላይ ያለና የመላ ሕዝቦችን አለኝታነት ለመቀዳጀት የሚሠራ ኅብረ ብሔራዊ አስኳል የለም፡፡ ያለ ማጋነን ዛሬ ከአገር ውስጥ እስከ ደጅ ድረስ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያ ተወላጆችን ያጥለቀለቀው ለዴሞክራሲ ለውጥ አንድ ላይ መቆም፣ ከድርጅቶች ይልቅ በሁለት ሦስት ግለሰቦች እንዲያውም በአንድ ዓብይ ዙሪያ የተጠመጠመ ነው፡፡

      በግለሰቡ ዓብይ አህመድ ዙሪያ የተሰባሰቡት የፖለቲካ ዝንባሌዎች ደግሞ ብዙ ዓይነት ናቸው፡፡ ብዙ ዓይነት ከመሆንም በላይ በሌላው ዓላማ ውስጥ ራስን አስገብቶ የሌላውን ሕመም ልረዳ የማለትና ስሜት ለስሜት የመቻቻል ነገር የሚቸግራቸው፣ እንዲያውም ብሽሽቅን ‹‹ትግል›› አድርገው የያዙም አሉባቸው፡፡ ለአብነት ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓብይና ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ሺሕ በላይ ታዳሚዎች ጋር በነበሩበት ሚሊኒየም አዳራሽ ውስጥ የተደረገውን ‹‹የምንሊክ … የኃይለ ሥላሴ አምላክ ለዕርቅ አበቃን!…›› የተባለበትን (ግን በጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተሞሻሪዎችን ፍቅር በነገር ከመውጋት የማይተናነሰውን) ንግግርና በዚያ ምክንያት የተወሰኑ ሰዎች አዳራሹን ለቀው የሄዱበትን ገጠመኝ ያስታውሷል፡፡ ነውረኛው ንግግር ጀግንነት የመሰላቸው፣ ዓብይ ልጆች ታቅፎ የሚታይበትን ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ለጥፈው ‹‹ይኸው ዓብይ ከእኛ ጋር ነውና ቅጥል በሉ›› ለማለት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ እናስ ዓብይ አህመድን ከመሀል አድርጎ የሚካሄድ ይህን መሰሉ መጓተትና መበሻሸቅ አድጎ ወይም ዓብይ ወደ አንዱ ወገን ሊያስፈርጅ የሚችል የምላስ ድጥ አምልጦት የለውጥ ሠፈራችን ሁለት የተካረረ ቦታ ቢፈነከትስ? አያድርገውና ሁላችንም ዋና መሰባሰቢያ ያደረግነው ዓብይ፣ ተካድን ባለ በሻቂ ወይም ሌላ ዓላማ ባነገበ ኃይል አንድ ነገር ቢሆንስ ወዴት አቅጣጫ ነው የምንሄደው?

ቀደም ብሎ የተጠቀሱት ጉድለቶችና እነዚህ ጥያቄዎች አስደንግጠው ሊያባንኑን ከቻሉ፣ እንዲሁም ግድያ የሚመስለው የኢንጅነር ስመኘው አማሟት የመሠረተ ልማት ግንባታዎቻችንም የጥቃት አደጋ ውስጥ መሆናቸውን ካስጠነቀቀን፣ ለዴሞክራሲ ለውጥ የቆሙ ቡድኖችና ምሁራን ሁሉ በቶሎ ከዓብይ መንግሥት ጋር አንድ ላይ ተባብረው ፀጥታንና ዴሞክራሲን ማደለደልን የጋራ ሥራቸው ማድረጋቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያከራክረንም፡፡ ይህ ከተደረገ መለስ ቀለስ እያሉ ያስቸገሩንን የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች በፖለቲካ መንገድም፣ ሕዝብን በሰላም ዘብነት በማነቃነቅና ባልተውሸለሸለ (የቀውስ አካባቢን ለይቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ማስገባትን በጨመረ) ሕጋዊ ዕርምጃም ለመቆጣጠር ይመቻል፡፡ እንጀራ ላይ የወጣ ወጥን ታህል ታሪክንና ፖለቲካን ያጠቀሱ ከአፍንጫ አይርቄዎች ብድግ እያሉ የፖለቲካ ፈትፋች የሚሆኑበትን ምስቅልቅል በመግራት ላይና እንጭጩን (ግን አደገኛውን) የፖለቲካ ብሽሽቅ በማምከን ላይ ብዙ አቅምን አስተባብሮ መሥራት ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...