ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ የኦኮኖሚ ባለሙያና ተመራማሪ
ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ጎምቱ ከሚባሉት አንጋፋ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በኢኮኖሚው መስክ በልዩ ልዩ መስኮች ሙያዊ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከቀድሞው አለማያ እርሻ ኮሌጅ ጀምሮ ከሜሪካዎቹ ከኦክላሆማ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ከካንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በሌሎች የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ውስጥ በማስተማር በዲንነት፣ በምርምርና በማማከር ሥራዎች ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ አሁንም እየተሳተፉ ነው፡፡ በኬንያ ከስምንት ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ ደማር ኢትዮ አፍሪክ የተሰኘ የማማከር ተቋም በመክፈትም በግላቸው እየሠሩ የሚገኙት ደምስ (ዶ/ር)፣ የምርምር ሥራዎቻቸውን ያጠናቀሩባቸውን መጻሕፍትም አሳትመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በ2007 ዓ.ም. ያሳተሙትና በ900 ገጾች የተቀነበበው ‹‹ኢትዮጵያስ ኢንዲጂኒየስ ፖሊሲ ኤንድ ግሮውዝ፣ አግሪካልቸር፣ ፓስቶራል ኤንድ ሩራል ዴቨሎፕመንት›› የተሰኘው መጽሐፋቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት ሥራዎቻቸው መካከል ይመደባል፡፡ ከሰሞኑ ከሚታየው የኢኮኖሚ ሁኔታ በመነሳት በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገሪቱ ኢኮኖሚ አደጋ አንዣቦበታል ሲሉ እየተደመጡ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ ችግሮች ላይ፣ በግብርና ኢኮኖሚው ላይና በመሳሰሉት መስኮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅራቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በኢኮኖሚው ላይ የተወሰነ ጫና ማምጣቱ ይታያል፡፡ የአገሪቱ ሚኒስትሮችም ከሰሞኑ ተሰብስበው የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ገምግመዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ ከቀጠለ አደጋ ላይ ነው የሚሉ ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ?
ዶ/ር ደምስ ፡- በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ እያንዳንዱ ሚኒስትር የሚያይበት የራሱ ማዕዘን ይኖረዋል፡፡ ፖለቲከኞችና ጸሐፊዎች የሚያቀርቡትን ሐሳብ እንዳለ ወስደን ወደዚያ የምናዘም ከሆነና የሳቱት ነገር እንዳለ እያስቀመጥን ካልሄድን ለውድቀት መጋለጣችን አይቀርም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ እንደ የኢኮኖሚ ባለሙያ የማልስማማበት ምክንያት፣ ኢኮኖሚ ማለት የቁጥሮች ጋጋታ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ የነገሮችን ክንዋኔና ፍሰት ብሎም የምልከታ ጉዳዮችን ማስተዋል አለብን፡፡ የሚከናወኑ ሥራዎችን በማክሮ ወይም በማይክሮ ኢኮኖሚክስ ደረጃ ማየት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በማክሮ አቅጣጫ ሕዝቡ ካለው ሕይወትና ከፍጆታ ሥርዓቱ አኳያ ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሕዝቡ ከሰማይ ተወርውሮለት አይደለም እየኖረ ያለው፡፡ እርግጥ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር አለ፡፡ ባለውና በሌለው መካከል ክፍተቱ እየሰፋ መጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው የሚለው ቀርቶ ደሃና ሀብታም የሚለው መለያ ብቻ እየበዛ መጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢኮኖሚያችን ችግር ያለበት የሀብት ሥርጭትን በሚመለከት ያለው የፖሊሲ ዕርምጃ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው በጣም ደካማ ነው፡፡ ከኢንቨስትመት አኳያና ከመንግሥት ወጪዎች አኳያም ሲታይ ኢኮኖሚው ጥሩ መንገድ ላይ እንደሚገኝ መመልከት ይቻላል፡፡ በቅርቡ ለቢቢሲ በሰጠሁት መግለጫ ይህንኑ ገልጫለሁ፡፡ የአገሪቱ ዕዳ እየጨመረ ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ ግን ዕዳው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ እንጂ፣ አገሪቱ መክፈል አትችልም በማለት ሲገልጽ የሰማሁት ባለሥልጣን የለም፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ብናይ ሳይበደሩ ማደግ ከባድ ነው፡፡ በኢኮኖሚ በኩልም ብታይ ትልልቅ ፋብሪካም ለሚገነባ፣ እንደ አገርም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማልማት ብድር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ጥያቄው ግን የተበደርነውን በአግባቡ እንጠቀምበታለን ወይ? የሚለው ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በሙሉ ደማምሬ ሳስቀምጣቸው የኢኮኖሚው ሒደት አሁንም ጠንካራ እንደሆነና በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሚገኝ ያሳዩኛል፡፡
ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው ማለት ምን ማለት ነው? በነገራችን ላይ ከሦስት ዓመታት በፊት በኤልኒኖ ምክንያት የተዛባው የአየር ሁኔታ ድርቅ አስከትሎ ነበር፡፡ ሰዎች በቃ አገሪቱ ራሷን መመገብ የማትችልበት አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን የሚያረጋግጥ ጊዜ ነው ይሉ ነበር፡፡ በወቅቱ ከዶቸቨሌ ጋር በነበረኝ ውይይት እንዲህ ያለው ሐሳብ ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ማን ነገራችሁ? ነው ያልኳቸው፡፡ ኢኮኖሚውን በሦስት ጉዳዮች ላይ ተመርኩዘን ልናየው ይገባል፡፡ የፖለቲካ ግጭቱን እንየው፡፡ ይህ አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ በራሱና በኢኮኖሚው ደረጃ ሲታይ፣ እንዲሁም የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንት ቀጣይነት ሲታይ እንኳንና አሁን ለውጦች በሚታዩበት ወቅት፣ ያኔም በቀውሱ ወቅት አገሪቱ እንደምትወጣው ገልጬ ነበር፡፡ አገሪቱ ለራሷም ለዓለምም ቀውሶችን እንዴት መቋቋም እንደምትችል አረጋግጣለች፡፡ ቀውስ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊፈጥር የሚችለውን ከፍተኛ የመተማመን ሥጋት አሁን ቀንሷል፡፡ ዛሬ ሁሉም ሰው ከፍተኛ መነሳሳት እየታየበት ነው፡፡ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ጉብኝትና ሽኝት (ቃለ መጠይቁ በተካሄደበት ወቅት) ፖለቲካዊ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ ግን ትልቅ ተስፋ ያሳድርብኛል፡፡ አገሪቱ በምን አቅጣጫ መጓዝ እንደምትችል እያሳየች በመሆኗ፣ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው በሚለው አልስማማም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚው አደጋ ላይ ነው ስለሚያሰኘው ጉዳይ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት የአገሪቱ የወጪ ንግድ አቅም እየተዳከመ መምጣቱ ነው፡፡ ዶላር የማመንጨት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መጥቷል፡፡ ሁለተኛ የብድር ዕዳ ክምችት አገሪቱን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንደከተታት የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ መልሳ ወደ ከፍተኛ የብድር ዕዳ ጫና ያለባቸው አገሮች ተርታ መግባቷ እየታየ ነው፡፡ ለብድር ዕዳ ማቃለያ የሚከፈለው ገንዘብም ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ፣ በዚህ ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ ከ680 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለብድር ዕዳ ተከፍሏል፡፡ ግብርናው እንደሚጠበቀው እያመረተ አይደለም፡፡ 300 ሚሊዮን ኩንታል ሊመረት እንደሚችል ቢገመትም፣ የምርታማነት ጉዳይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ኢኮኖሚው በዚህ ከቀጠለ አደጋ ላይ ነው እየተባለ ስለሆነ ስለዚህስ ምን ይላሉ?
ዶ/ር ደምስ፡- በዚህ መቀጠል አደጋ ነው ከሚለው ልጀምር፡፡ ሚኒስትሮቹ አደጋ ነው ስላሉ ሳይሆን፣ ሕዝቡ በሚጠብቀው ደረጃ ሲታይ በእስካሁኑ አካሄድ መቀጠል ከባድ ነው፡፡ አደጋው ይህ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪና የውጭ ንግድ ሚዛንን እንይ፡፡ በነገራችን ላይ በዓለም ላይ ከፍተኛ የውጭ ንግድ ሚዛን ክፍተት ያለባት አገር አሜሪካ ነች፡፡ ከፍተኛ ሪከርዱ የአሜሪካ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን ይህ አይደለም፡፡ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነት ግን አሜሪካ ያላት የመገበያያ ገንዘብ በዓለም ላይ የሚነገድበት መሣሪያ ነው፡፡ እኛ የለንም፡፡ በእኛ አገር የውጭ ምንዛሪ ክፍተቱ የመጣበት ምክንያት ምንድን የሚለውን እንይ፡፡ ብዙ ምርት ወደ ውጭ ባለመላካችን በዕቅዱ መሠረት ስላልተላከ ነው የሚሉ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ በተወሰነ ደረጃ እውነትነት አለው፡፡ በሚፈለገው መጠንና ልክ ወደ ውጭ መላክ ያልቻልነው ግን የእኛ ሸቀጦች ዋጋ ውድ ሆኖ ነው? በዚህ ሳቢያስ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ መደረግ ነበረበት ወይ የሚለውን ስናይ፣ ስህተታችን እዚህ ላይ እንደሚጀምር እንገነዘባለን፡፡ ለዚህ ግፊት ያደረጉ አካላት ሁሉ ዛሬ መልሰው የብር የመግዛት አቅም ትክክል አልነበረም እያሉ ነው፡፡ የምንዛሪ ለውጡ ከመደረጉ በፊትም ሆነ አሁንም አቋሜ መደረግ አልነበረበትም የሚል ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው ቀውስ ከውጭ ምንዛሪ ለውጡ ጋርም የሚያያዝ ነው፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ስለጉዳዩ በጋዜጦች ሲጻፉ የነበሩት አግባብ አልነበሩም፡፡ በጠቅላላው የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ አልነበረም፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ የሚገኘው ከቡና ነው፡፡ ከቡና ይገኛል የተባለው ገቢ መጠን ቀንሷል፡፡ ቡናው የቀነሰው ግን በተቋማት ደካማነት፣ በዘርፉ ውስጥ ባሉ ላኪዎችና በመካከል ባሉ ደላሎች ችግር ነው፡፡ እነዚህ የተጫወቱት ጨዋታ ነው ዘርፉን ያዳከመው፡፡ ኢኮኖሚው በአገር ውስጥና በውጭ አካላት አሻጥር እየተፈጸመበት ስለመሆኑ ቀደም ብዬ ጽፌያለሁ፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህንኑ ያነሳሉ፡፡ ስለዚህ የወጪ ንግዱን አፈጻጸም ማስተካከል ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ችግሩም በአብዛኛው ሰው ሠራሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት የጠበበው በተወሰኑ የአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ነው፡፡ ቡና ላይ የውስጥ ችግሮች አሉበት፡፡ ጨዋታው ከኢኮኖሚክስ ሕግጋት ውጪ የሚከናወን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምርት አለ እያሉ ነው ማለት ነው?
ዶ/ር ደምስ፡- በቡና ላይ ችግራችን የምርት ብዛት ማነስ አይደለም፡፡ የእኛ ችግር ቡና አምራቾች ለሚያመርቱት ምርት ተገቢውን ክፍያ በማጣት ግማሹ ወደ ሌላ ምርት እየገባ መሆኑ ነው፡፡ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያ ለዚህ ምን ይደረግ? ብትለኝ ለገበያው ተውለት እልሃለሁ፡፡ አምራቹ እንደሚያመርተው ልክ ካልተከፈለው፣ የራሱን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ የምርት ችግር አይደለም ያለው፡፡ ቅድም ስለብድር ዕዳ ክምችት አንስተሃል፡፡ አዎ ወደ ከፍተኛ የብድር ዕዳ ጫና ያለባቸው አገሮች ተርታ ሊያስገቡን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሐሳባችንን ሁሉ እዚያ ላይ ካደረግን የትም አንድርስም፡፡ እኔ የዓለም የገንዘብ ድርጅትም፣ የዓለም ባንክም የሚያወጡት አኃዝ ሳይሆን እኛ ምን እየሠራን እንደሆነ ማወቁ ላይ የማተኩረው፡፡ በአንድ ወቅት የዋጋ ግሽበቱ በጣም በጨመረ ጊዜ እነዚህ ተቋማት ይህንን አድርጉ ያንን አታድርጉ በማለት ተረባርበው ነበር፡፡ መንግሥት ግን እንቢ ብሏቸው ነበር፡፡ ሆኖም የዋጋ ግሽበቱ በምን አግባብ ሊቀንስ እንደቻለ፣ መንግሥት በምን አግባብ ሊቆጣጠረው እንደቻለ ለማወቅ ስላልቻሉ ጥያቄ ማቅረብ ጀምረው ነበር፡፡ የአገር ውስጥ የፖሊሲና የስትራቴጂ አቅጣጫ ነው በአብዛኛው ሊያድነንም ሊያነሳንም የሚችለው፡፡ የመክፈል አቅም የለንም እስካላልን ድረስ የብድር ዕዳ ክምችት አያስፈራኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ለታዩት ችግሮች መንግሥት እንደሚገልጸው መነሻቸው የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ የሥራ ዕድል እንደ ልብ አለመፈጠር፣ ምርትና ምርትማነት እንደሚፈለገው አለመሆን፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አለመታየት ችግሮች ሲጠቀሱ ቆይተዋል፡፡ ኢኮኖሚስቶች ስለእነዚህ ጉዳዮች ምን ይላሉ?
ዶ/ር ደምስ፡- በዚህ ላይ እስማማለሁ፡፡ የምከራከረው ግን ፖለቲካው ሳይሆን ኢኮኖሚው ነው ወሳኝ ጉዳይ ብዬ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ላይ የሚገባውን ሥራ አልሠራንም፡፡ ምርትና ምርታማነት አልጨመረም ብለሃል፡፡ የግብርና ምርምር ብትሄድ ግን ለዚህች አገር የሚበቃ የሰብል ምርት ቴክኖሎጂ እንዳላቸው ይነግሩሃል፡፡ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ወዘተ ላይ ብዙ ቴክኖሎጂ አለን ይላሉ፡፡ የእንስሳት ሀብት ምርምር ዘንድ ስትሄድም ቴክሎጂው አለን ይሉሃል፡፡ ምርታማነት የቴክሎጂና የተሻሻሉ አሠራሮች ውጤት በመሆኑ፣ የተሻለ ምርት ለማስገኘት የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉ ቢባልም በምርምር ተቋማቱ ውስጥ የሚታየውን ዓይነት ውጤት በማሳያዎች እየታየ አይደለም፡፡ ሆኖም በፊት ከነበርንበት አሁን የተሻለ ምርት እየተገኘም ቢሆን ብዙ የሚያስኮፍስ አይደለም፡፡ በቆሎ በአማካይ 23 ኩንታል በሔክታር እየተገኘ ነው፡፡ በምርምር እንደተገኘው ከሆነ በሔክታር እስከ 120 ኩንታል መገኘት እንደሚችል እየታየ ነው፡፡ ይህ መምጣት መቻል አለበት፡፡ ሆኖም የአገሪቱ አማካይ የምርታማነት ደረጃ ከበፊቱ ጨምሯል፡፡ ነገር ግን ሌሎችም ችግሮች በመኖራቸው ውጤት እንደሚፈለገው አልተገኘም፡፡ ለግብርናው ኃላፊነት ሰጠነው እንጂ፣ ለዘርፉ ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጋችን አንደኛው የምርታማነት ችግር ነው፡፡ ለግብርናው ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ትራንስፎርሜሽን ፖለቲከኞች ሲያወሩ እንደሚሉት አይደለም የሚመጣው፡፡ በትክክል በማቀድ፣ በመተግበርና በሥራ ነው የሚመጣው፡፡
የመንግሥት ሰዎች ሁሌም ስለአቅም ግንባታ ያወራሉ፡፡ ይህ ለእኔ እርባና የሌለው ወሬ ነው፡፡ እስከ መቼ ነው ስለአቅም ግንባታ እያወራን የምንኖረው? ሀብት ማባከን ነው እየታየ ያለው፡፡ በየዓመቱ ስንትና ስንት ሥልጠና እየተሰጠ ሀብት እየባከነ፣ ነገር ግን ወደኋላ ነው እየተሄደ ያለው፡፡ ያለህን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም መጣጣር ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትም ለጋሾችም በግብርናው ላይ ገንዘብ ሲያፈሱ ቆይተዋል፡፡ እኔ ግን ከ20 ዓመታት በፊት ከውጭ ስመጣ ያገኙሁት የግብርና ሚኒስቴር አሁን ካለው የበለጠ አቅም እንዳለው ተገንዝቤያለሁ፡፡ ይህንኑ በመጽሐፌ ጠቅሻለሁ፡፡ ብዙዎቹን ነገሮች እንዲያ ለማለት ያህል እንጂ አስፈላጊውን ሥራ ለማከናወን ያለው የተቀናጀ አሠራር ደካማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሲነሱ ከነበሩ ክርክሮች በመነሳት ለግብርና የተሰጠውን እንይ፡፡ ግብርና በመሬትና በሰው ጉልበት ብቻ ነበር ለውጥ እንደሚያመጣ የሚታሰበው፡፡ ካፒታል ለግብርና አልተመደበም ነበር፡፡ ነገር ግን ካፒታል ያስፈልገው ነበር፡፡ 600 ሺሕ ቶን ስንዴ በየዓመቱ ከውጭ የምናስገባበት ሁኔታ መፈጠር አልነበረበትም፡፡ በአፍሪካ የስንዴ የልቀት ማዕከል ለመሆን በተነሳች አገር ውስጥ ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ሀብቱ አለ፡፡ መሬቱም፣ የሰው ጉልበቱም አለ፡፡ ትንሽ ካፒታል ጨመር አድርጎ ለአገር ፍጆታ ብቻም ሳይሆን ለሌላውም የሚተርፍ ውጤት ማግኘት በተቻለ ነበር፡፡ ከሥራ ይልቅ ግን በንድፈ ሐሳብ ላይ ነው ጊዜ እየጠፋ ያለው፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ መመለስ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡
የኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬዎች መካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው አምራቾች እንዲሆኑ ይፈለጋል ወይ? አነስተኛ ገበሬ እየተባለ ማዳበሪያና ዘር መንግሥት እያቀበለው፣ ገበያውን እየፈጠረለት ይዞት ሊዞር አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ነው ችግር ያለው፡፡ የኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬዎች ሁሉም በአንድ ዓይነት መለኪያ መታየት የለባቸውም፡፡ የተወሰኑት ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የምርት ሒደት ውስጥ ለመቆየት ይገደዱ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉት አነስተኛ ገበሬዎች ወደ መካከለኛና ከፍተኛ አምራችነት እንዲቀየሩ የሚያግዛቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ ይፈልጋሉ፡፡ ይህም የፖሊሲና የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ገበሬዎች ትልልቅ የእርሻ መሬት ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ በመሬት ጉዳይ ለውጥ መደረግ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አገሪቱ ካላት 112 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ከ60 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መታረስ ይችላል ይባላል፡፡ ከዚህ ውስጥ እየታረሰ ያለው ግን 15 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ይህ ምን ይናገራል?
ዶ/ር ደምስ፡- አሁን ያልኩህን ነዋ፡፡ ግብርናው አሁንም ድረስ ኋላቀር በሆነ ሥሪት ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ አብዛኛው የግብርና ሥራ በደጋማ አካባቢዎች ነው በሰፊው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡ አብዛኛው ምርት እየተገኘ ያለውም በደጋማው ክፍል በተበጣጠሰ እርሻ ከሚታረሰው መሬት ነው፡፡ ነገር ግን በቂ እርጥበት በሚገኝበት አካባቢም መግባት ያስፈልጋል፡፡ ወደ መካከለኛ ደጋውና ቆላማው አካባቢ መግባት ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው የደጋው ክፍል ከፍተኛው የእርሻ ሥራ የሚካሄድበት ቢሆንም ስንቱ ነው የተሻሻለ ዝርያ የሚጠቀመው? ስንቱስ ነው የቴክኖሎጂ ውጤት እንደልቡ የሚያገኘው? የሚለውን ስታየው ብዙ ይቀረዋል፡፡ ታንቡር እንመታለን እንጂ በብዙ ጉዳይ ገና ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ሩሲያ ‹‹ቨርጂን ላንድ›› (ድንግል መሬት) የሚለውንና ያልታረሱ መሬቶችን በማረስ ሰፊ የግብርና ሥራ የመሥራት ዘመቻ የጀመረችበት እ.ኤ.አ. የ1950ዎቹ ዘመን፣ ኢትዮጵያም ሰፋፊና ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎችን ማለትም እንደ አርሲ የተቀናጀ የግብርና ልማት ቡድን፣ የወላይታ የተቀናጀ የግብርና ልማት ቡድን፣ ወዘተ ያሉትን ፕሮጀክቶች ያስዋወቀችበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሩሲያውያን ብዙ ሄደዋል፡፡ በፍጆታቸውና በምርታቸው መካከል የነበረውን ክፍተት የሞሉት በመጀመርያው አንድ ዓመት የቨርጂን ላንድ ዘመቻ ነበር፡፡ የእኛ ሁሉን አቀፍ የሜካናይዜሽን ዘመቻው ግን ጠብ የሚል ለውጥ አላመጣም፡፡ ግብርናው አሁንም ከመንፏቀቅ አልወጣም፡፡ ምንድን ነው ችግሩ?
ዶ/ር ደምስ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ከፈለግን ኢኮኖሚውን ከመንግሥት ጋር ማያያዛችንን መቀነስ ይኖርብናል፡፡ አሁን የመንግሥት ወጪ ከጠቅላላ የአገሪቱ ምርት አኳያ ሲታይ ከአሥር በመቶ አይበልጥም፡፡ ኢኮኖሚህን በዘመቻ ለመለወጥ መነሳት ዘላቂነት የለውም፡፡ የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ሚና እንዳለው ከሚያቀነቅኑ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ አነስተኛ ገበሬዎችን እንደ ግል ዘርፍ ተዋናይ በማየት ጭምር ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ለምሳሌ የአርሲ የሜካናይዜሽን ግብርና የተቀናጀ የልማት ቡድንን ጠቅሰሃል፡፡ በአካባቢው የነበሩት አነስተኛ ገበሬዎች ለቴክኖሎጂ የነበራቸው ቅርበት ባመጣው ለውጥ አሁን በዚያ አካባቢ ስለትራክተር ወይም ኮምባይነር፣ ስለምርጥ ዘር አጠቃቀም ማስተዋወቅ አይጠበቅብህም፡፡ እነሱ አልፈው ሄደዋል፡፡ በዚያው ልክ ግን በወቅቱ ከፍ ከፍ ያሉ እንደ ተድላ አበበ እርሻ የሚባሉ ትልልቅ አምራቾችም መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር፡፡ በግል ደረጃ በዚህ ልክ የሚንቀሳቀሱትን እንደ ልብ እንዲሠሩ አድርገናል ወይ? ብንል አላደረግንም፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበራቱና በሌላውም ትክክለኛ አምራቾቹን ገበሬዎች የግል ኢንቨስተር እንዲሆኑ ምን አድርገናል የሚለውን በምን አግባብ እያየነው ነው? ምን ማምረት እንዳለበት፣ መቼ፣ ለምንና ለማን ማምረት እንዳለበት መወሰን ያለበት ገበሬው ነበር፡፡ ይህ በግብርና ትምህርት የሚሰጥ መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡ ውሳኔ የመወሰን ድርሻው የራሳቸው የአስተኛ ገበሬዎች መሆኑን ይገባው ነበር፡፡ ይህ ግን እየሆነ አይደለም፡፡ አነስተኛ ገበሬዎቻችን ምርጥ ዘርም ማዳበሪያም ለማግኘት በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ውሳኔ ለመወሰን እንኳ የእነዚህ ባለሙያዎች ጥገኛ እየሆኑ ነው፡፡ ገበያ ለማግኘትም እንዲሁ፡፡
ነገር ግን እንደ አሜሪካ ባለው አገር ሁለት በመቶ የማይሞላው ገበሬ ከአገሩ አልፎ ዓለምን ይመግባል፡፡ ምክንያቱም በቴክኖሎጂ ታግዘውና በራሳቸው ወስነው ስንትና ስንት ሺሕ ሔክታር መሬት ስለሚያርሱ ነው፡፡ ገበሬዎቻችን የግል ዘርፍ አካላት መሆናቸውን በመቀበል በዚሁ አግባብ እንዲሠሩ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ሞዴል አርሶ አደሮች እየተባሉ ሲሸለሙ አየን፣ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ገበሬዎች ካፒታላቸው ባደገ መጠን ግብርናው ላይ አይደለም ኢንቨስት ሲያደርጉ የሚታዩት፡፡ ከተማ ወጣ ብለው ዲስኮ ቤቶች መክፈት፣ አይሱዙ መግዛትና ሌላውም ቢዝነስ ውስጥ መግባት ነው የሚመርጡት፡፡ ምክንያቱም ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ ግብርናው ላይ መልሰው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ስለማይጋብዟቸው ነው፡፡ ግብርናው የሚሞተውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሌላውን ከማምጣት በፊት እኮ እነዚህን ገበሬዎች በመደገፍ እዚያው ግብርናቸው ውስጥ እንዲያድጉና ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ መደገፍ ይገባ ነበር፡፡ እንደ ሩሲያ በዘመቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ መንግሥት በክላስተርና በኤክስቴንሽን የሚሠራውን ነገር ብዙም አልቀበለውም፡፡ ሌሎች አዋጪ መንገዶች አሉ፡፡ ግብርናው ውስጥ ላሉት ትክክለኛ አምራቾች ትክክለኛውን ድጋፍ በማድረግ፣ ተገቢውን ፋይናንስ በማቅረብ ካልቀየርከው በቀር በቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ የትም አታደርሰውም፡፡ አነስተኛ ገበሬዎች ግን ሁሌም አነስተኛ ሆነው እንዲኖሩ የሚፈልግ አሠራር ነው ያለው፡፡ ብድር እንኳ ሲሰጣቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ነው የሚቀርብላቸው፡፡ ከስንት ሙግት በኋላ ነው የሊዝ ፋይናንስ የመጣው፡፡ እንደ አርሲና ባሌ ገበሬዎች ለምንድነው ሌሎችም ገበሬዎች ትራክተርና ኮምባይነር የማይጠቀሙት ብትል፣ መልሱ ተገቢውን ፋይናንስ ስለማያገኙ ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ብድር ጠይቀው እኮ የሚሰጣቸው አላገኙም፡፡ ለዚህ ነው ግብርናው ባለበት የሚረግጠው፡፡ መንግሥት ከዘመቻ ሥራ መውጣት አለበት፡፡ የግሉ ዘርፍ ሊገባ እስካልቻለ ድረስ በተወሰነ ደረጃ መንግሥት ኢኮኖሚውን መምራት አለበት በሚለው ብስማማም፣ አሁን ግን በተወሰነ ደረጃ እያሻሻልን የተወሰነውን ለግሉ ዘርፍ እየተውን መምጣት አለብን፡፡ ባሌ አርሲ ላይ ሰፋፊ የስንዴ እርሻዎች ተጀምረው ነበር፡፡ ገበሬው አምርቶ ማስረከብ የሚችልባቸው አሠራሮችም ተጀምረው ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም (ኤጂፒ) የሚባሉ ፕሮጀክቶች ግብርናውን ለመለወጥ ሚናቸው እንዴት ይታያል?
ዶ/ር ደምስ፡- ሌላው ትልቁ ችግራችን ከእነዚህ ነው የሚመነጨው፡፡ የውጭ ፕሮጀክቶች እየገቡ ትክክኛውን መስመር ሲያዛቡት እየታየ ነው፡፡ ኤጂፒ ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ያላቸውን አነስተኛ አቅም ካላቸው አካባቢዎችና ወረዳዎች ሲመድብ የእንስሳት ሀብቱን፣ ቡናንና የመሳሰሉትን ረስቷቸው ነበር፡፡ የዕቅድህንና የልማት አቅጣጫህችን በትክክል አስቀምጠህ ፕሮግራሞችን የምትተገብርባቸውን ተቋማት አጠናክረህ ካስመጥክ በኋላ፣ ከውጭ የሚመጡ ፕሮጀክቶች ባስመጥከው መስመር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወደ መዳረሻ ግብህ እንዲወስዱህ ነው መደረግ ያለበት፡፡ ይኼ ግን እየሆነ አይደለም፡፡ ትልቅ ፕሮግራም ትቀርፃለህ፡፡ ከጎን ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው ይመጡና መንገድ ያስቀሩሃል፡፡ የሆነች ሳንቲም ጣል ያደርጉልህና መሀል ላይ ትተውህ ይሄዳሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሚመደበው በጀትና ዋናውን ሥራ የሚሠሩት ሰዎች አይጣጣሙም፡፡ ወረዳና ቀበሌ ላይ ነው ዋናዎቹ ሠራተኞች የሚገኙት፡፡ ስንት መወለጥ የሚችል ገንዘብ ግን ለውድ የቢሮ ዕቃዎች ግዥ እየዋለ ብክነት እየታየ ነው፡፡ ሀብት ምደባ ከታች ነው መጀመር ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ተስፋ ያላቸው ነገሮች የሚባሉትን እንይ፡፡ ነዳጅ ተገኝቷል፡፡ የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ላይ ተስፋ የሚያጭሩ ነገሮች እየታዩ ናቸው፡፡ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሚባል አካሄድ እየመጣ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ኢኮኖሚውን ምን ያህል ሊደጉሙት ይችላሉ?
ዶ/ር ደምስ፡- የነዳጅ ጉዳይ ላይ እንነጋገር፡፡ በቅርቡ በናይጄሪያ ለአንድ ስብሰባ ተጋብዤ ሄጄ ነበር፡፡ ስለኢትዮጵያ ተሞክሮ ገለጻ ለመስጠት ተዘጋጅቼ ነው የሄድኩት፡፡ የእነሱ ኢኮኖሚ ከእኛ አኳያ ትልቅ መሆኑን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከእኛ በብዙ እንደሚበልጥ፣ በሕዝብ ብዛትና በመሳሰሉት ከእኛ በእጥፍ እንደሚበልጡ አኃዞችን አጣቅሼ ሳቀርብ፣ አንድ ናይጄሪያዊ ባለሙያ የአገራቸው ኢኮኖሚ በነዳጅ ምክንያት ሳይገባው ትልቅ እንደሆነ እንደሚወራለት በመግለጽ ተከራከሩኝ፡፡ አገሪቱ ሀብታም የምትመስለው በነዳጅ የተነሳ እንደሆነ፣ እውነታው ግን የተለየ መሆኑን ገለጹልኝ፡፡ ምንም እንኳ ናይጄሪያ ከ2,000 ዶላር በላይ የነፍስ ወከፍ ገቢ አላት ቢባልም፣ በትክክለኛው ከታየ ከ500 ዶላር እንደሚያንስ ባለሙያው በግልጽ ተከራክረዋል፡፡ በናይጄሪያ ያለው ድህነት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እንዲገኝ እንዳደረገውም ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ኢኮኖሚው ነዳጅ ሳይኖርም ምን ያህል ማደግ እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ ነዳጅ ሲመጣ አብሮ ይዟቸው የሚመጣቸው ውስጣዊና ውጫዊ ውስብስብ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ እስከ ዛሬም ነዳጅ ሳይኖር ቀርቶ አልነበረም ያልወጣው፡፡ በዘርፉ ጠለቅ ያለ ንባብ አካሂጃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ ውስጥ በአሜሪካ ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የማነብበት ዕድል ነበረኝ፡፡ ሰነዶች ሰርስረህ ስታይ ኢትዮጵያ ነዳጅ እንዳላት ከታወቀ መቆየቱን ትገነዘባለህ፡፡ ሆኖም በነዳጁ እንዳንጠቀም የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ቀድመው ያወጡ አገሮች የሚሠሩት አሻጥር አለ፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ይቆማል ማለት አይቻልም፡፡ ካፒታሊዝም ይተኛል ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፡፡ ካፒታሊዝም አፍሪካን በመቀራመት ወቅት ብቻም ሳይሆን አሁንም ድረስ ለአፍሪካ ሥጋት እንደሆናት ነው፡፡ የነዳጅ መገኘት ተስፋ የሚሰጠው በአገር ውስጥና በውጭ እንዴት እንደምንጠቀምበትና እንደምናስተዳድረው በቅጡ ስናውቅ ነው፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልገናል፡፡
የመንግሥት አስተዳደር ለውጡ የሰውን ተስፋ አለምልሟል፡፡ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ዳያስፖራውን አልተጠቀምንበትም፡፡ አንድ ዶላር በቀን የሚለውን ጥሪ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራውያን ምላሽ ቢሰጡበት በዓመት 365 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ ማለት ነው፡፡ በትረስት ፈንዱ አማካይነት ዳያስፖራዎቹ የሚሳተፉበት ኮርፖሬሽን ቢቋቋም፣ በዚሁ ትረስት ፈንድ አማካይነት በአገሪቱ እንደ አየር መንገድ ባሉ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ፣ የአክሲዮን ድርሻ እንዲገዙ ቢደረግ ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ የተጠቀሰው ገንዘብ በሁለት ወይም በሦስት ዓመታት ውስጥ የህዳሴውን ግንብ ለመገንባት ያስችላል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አስተዳደር የምጠብቀው ለውጥ አለ፡፡ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ወሳኙ በአገር ውስጥ አቅም ያለው ሸማች መፈጠሩ ነው፡፡ ለማናቸውም ኢኮኖሚ መሠረቱ በአገር ውስጥ አቅም ያለው ሸማች መኖሩ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉት በውጭ ሰዎች እንዲጎበኙ ሲደረግ እያየን ነው፡፡ ለሠራተኛው ተገቢውን የደመወዝ አከፋፈል የሚፈቅድ ፖሊሲ ከሌለ በፍጆታ አቅም ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ የኢንቨስተሮቹን ፍላጎት ለመጠበቅ ግን ሠራተኞች ላይ ጫና እየተደረገ ነው፡፡
ኢንቨስተሮች ተንቀሳቃሽ ስለሆኑ እነሱን ወደዚህ ለማምጣት መሥራት ያለብን ሁሉ እንሠራለን የሚሉ የመንግሥት ኃላፊዎችን እንሰማለን፡፡ ይህ እርባና ቢስ አነጋገር ነው፡፡ ኢንቨስተሮች ኢንቨስት የሚያደርጉት የዘላንነት አመል ስላለባቸው ወይም እኛን ለመደገፍ ስለሚያስደስታቸው አይደለም፡፡ ትርፍ ለማካበት ነው የሚመጡት፡፡ ብዙዎቹ ኢንቨስተሮች ለምን ትንሽ ደመወዝ እንደሚከፍሉ ሲጠየቁ መንግሥት ከለከለን እንጂ፣ ከምንከፍላችሁ በላይ መክፈል እንችላለን ይላሉ፡፡ ኢንዲስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ዜጎች ትንሽ እንዲከፈላቸው የሚሟገተው የመንግሥት አካል፣ ኢትዮጵያውያን ወደ ዓረብ አገሮች ሄደው እንዲሠሩና ሦስት እጥፍ እንዲከፈላቸው ሲደራደር ግን እያየን ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? እዚህ አትሥሩ፣ ፓርኮቹ ውስጥ የምትሠሩት ለአጭር ጊዜ ነው፣ ወደ ውጭ ሂዱ እየተባሉ እኮ ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ኢንቨስተሩ አላተርፍኩም፣ አልከፍልም አላለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በገቢና በደመወዝ ፖሊሲው ላይ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ መጠንን ሊወስን ይገባዋል፡፡ ችግሩ በዚህ ነው የሚፈታው፡፡ ኬንያውያን በዚህ ረገድ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው ሕዝብ ቁጥሩ ትልቅ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ግን ባላቸውና በሌላቸው መካከል ያለው የገቢ ልዩነት ክፍተት እየሰፋ መጥቷል፡፡ ስለዚህ የገቢና የሀብት ክፍፍል ሥርጭት ችግሩን ልትፈታ የምትችለው በፖሊሲ ድጋፍ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡