Sunday, April 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የሪፎርም ሥራዎችን የሚያጠና ኮሚቴ አዋቀረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዳያስፖራ አካውንት ስለመክፈት የሚደነግገው መመርያ ሊሻሻል ነው

የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማራመድ የሚያስችሉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመንግሥት ሥር ያሉ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ አመራሮች እንደተሰየሙላቸው ይታወሳል፡፡ የፋናንስ ተቋማቱን በቦርድ የሚያስተዳድሩ አዳዲስ አባላትም ቦታውን እንዲረከቡ ተደርጓል፡፡

የአመራር ለውጡን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አሠራር ብሎም  በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላሉ የተባሉ አዳዲስ አሠራሮችን ለመተግበር ብሔራዊ ባንክ ኮሚቴ አዋቅሮ መሥራት ጀምሯል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (አይኤምኤፍ) እና የብሔራዊ ባንክ ባለሙያዎችን አካቶ የተዋቀረው አዲሱ የሪፎርም ኮሚቴ፣ ከየአቅጣጫው ያሰባሰባቸውን መረጃዎች መሠረት በማድረግ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ውስጥ እልባት እንዲያገኙ የሚፈለጉ ጉዳዮችን በመለየት እየሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኮሚቴው በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የሚታየውን ክፍተት በማጤን ማሻሻያዎችን ለማድረግ ያስችላል የተባለ ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ኮሚቴው አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮች ላይ የደረሰበትን ድምዳሜ ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ዙሪያ ይደረጋል የተባለው ሪፎርም በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በባንኩ መመርያዎች ዙሪያ የቀረቡ የማሻሻያ ሐሳቦችንም እንደ መነሻ ይጠቀማል ተብሏል፡፡ በቅርቡ የንግዱ ኅብረተሰብ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ባደረገው ውይይት ወቅት፣ ያቀረባቸው ሐሳቦችና ጥያቄዎች እንደ ግብዓት መካተታቸውን እነዚሁ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የባንኩ ገዥ ከአገሪቱ ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅትም ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የተባሉ ጉዳዮችንም የሪፎርም ኮሚቴው ተመልክቶ አስተያየቱን እንደሚሰጥባቸው ተጠቁሟል፡፡

ለፋይናንስ ኢንዱስትሪውም ሆነ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቃሚነት ያላቸው ሌሎች ጉዳዮችም በዚሁ ኮሚቴ በኩል እየታዩ እንደሚገኙ ሲገለጽ፣ መስተካከል የሚገባቸው ሕጎችን ለማሻሻል ውጥን ተይዟል፡፡ ከብሔራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሪፎርም ኮሚቴው በሁለት ሳምንታት ውስጥ የደረሰበትን ድምዳሜ ካቀረበ በኋላ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጥባቸዋል የተባሉት የመፍትሔ ሐሳቦች ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ላይ አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎ በአፋጣኝ ሥራ ላይ  እንዲውሉ ይደረጋል ተብሏል፡፡  

በሪፎርሙ ሒደት ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ ዳያስፖራውን የተመለከቱና ከዳያስፖራው ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን እንደገና የማየት ሒደት እንደሚኖር ታውቋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ከዳያስፖራው ጋር በተገናኘ ከሚስተካከሉት ውስጥ ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ ባንኮች በኩል በውጭ መገበያያ ገንዘቦች ማስቀመጥ የሚፈቀድላቸው የገንዘብ መጠን ላይ የተቀመጠውን መመርያ ይጠቀሳል፡፡ 

እስካሁን እየተሠራበት በሚገኘው መመርያ መሠረት ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ ባንኮች እንዲያስቀምጡ የሚፈቀድላቸው የውጭ ገንዘብ መጠን ጣሪያው በ50 ሺሕ ዶላር የተገደበ ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ እስካሁን ድረስ ባለው አሠራር የማጠራቀሚያ የባንክ ሒሳብ ከፍተው በውጭ ገንዘብ አማካይነት የሚያስቀምጡ ዳያስፖራዎች ገንዘቡን እንዴት እንደሚጠቀሙት በዝርዝር የተቀመጡ አንቀጾች የተካተቱበት ሲሆን፣  መመርያው ግን በርካታ ክፍተቶች እንደሚታዩበት ይጠቀሳል፡፡

በመመርያው መሠረት የዳያስፖራ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት ተቀባይነት ያላቸው ከዶላር በተጨማሪ ፓውንድ ስተርሊንግና ዩሮ ናቸው፡፡ ይሁንና አስቀማጮች በካናዳ ዶላር፣ በሳዑዲ ሪያል፣ በጃፓን የን፣ በአውስትራሊያ ዶላር፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ድርሃም ሒሳብ መክፈት የሚፈልጉ ከሆነም በመጀመርያ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት የውጭ ገንዘቦች (ዶላር፣ ፓውንድ ወይም ዩሮ) በአንዱ በመመንዘር ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡   

መመርያው ዳያስፖራዎች ብቻም ሳይሆኑ፣ ትልውደ ኢትዮጵያውያን ሆነው ነገር ግን በልዩ ልዩ የዲፕሎማቲክ ሥራዎች ውስጥ የሚሳተፉና በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የሌሎች አገሮች ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውንንም ያካትታል፡፡ ሆኖም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚከፈቱት የውጭ ገንዘብ ማጠራቀሚያ የባንክ ሒሳብ ውስጥ የሚያስቀምጡት ገንዘብ በትክክልም ከውጭ ስለመላኩ የሚያረጋግጥ ዲክሌሪሲዮን እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ አሠራር አለው፡፡ በሕጋዊ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ስለመሆኑ ማረጋገጡ ተገቢ ቢሆንም፣ በአሠራሮቹ ሒደት ሲታይ ግን ዳያስፖራው ገንዘቡን በተፈለጉት የውጭ ገንዘቦች አማካይነት እንዲያስቀምጥ የማያነሳሱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የሚያስቀምጡትንም ገንዘብ ለማንቀሳቀስ በሚፈልጉበት ወቅትም በአብዛኛው የውጭ ገንዘቦች በብር ተመንዝረው የሚሰጣቸው በመሆኑም ጭምር የዳያስፖራዎችን ተሳትፎ እንዳቀጨጨው ይነገራል፡፡ ሆኖም በውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉትን ክፍያ ግን ሊፈጽሙበት እንደሚችሉ መመርያው ይፈቅዳል፡፡

መመርያው እስከ 50 ሺሕ ዶላር ብቻ ማስቀመጥ ቢፈቅድም፣ በርካቶች ግን በዚህ አሠራር እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ ሪፎርሙ ይህንን በመቀየር የ50 ሺሕ ዶላር ገደቡን በማንሳት ዳያስፖራው በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጠው ገንዘብ መጠን ያለ ገደብ እንዲሆን የሚያስችል መመርያ እንደሚወጣ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ለዚህ አሠራር ተጨማሪ ዝርዝር ሕግ ተዘጋጅቶለት በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዳያስፖራው በአገር ውስጥ ባንኮች አካውንት ከፍቶ የሚያስቀምጠው ገንዘብ ጣሪያው ቢነሳና ሕግን ተከትሎ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ማስቀመጥ ቢችል ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም በሚል መነሻ ተሻሽሎ እንደሚተገበር ተጠቅሷል፡፡ ነባሩ መመርያ መሻሻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሌሎች ዳያስፖራውን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ሊፈተሹ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ኢንቨስት ከማድረግ የሚገድበው ሕግ መሻሻል ይኖርበታል የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ መሠረት ከግል ባንኮች የአክሲዮን ባለድርሻነት እንዲወጡ መደረጋቸው ትልቅ ተቃውሞ ማስነሳቱም ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች