Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባንኮች ብዙም ጥቂትም አትራፊዎች ሆነዋል

የአገራችን ባንኮች በአትራፊ ዓመታትን ስለመዝለቃቸው በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ አንብበናል፡፡ የሒሳብ ሪፖርታቸውም ይህን ያሳያሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በኪሳራ የተዘጋ ባንክ የሌላት አገር በመሆኗም ዘርፉን ለየት ያደርገዋል ሲባል እንሰማለን፡፡ የባንኮቹ የትርፍ ምጣኔ ግን አስገራሚ ነው፡፡ እንደውም የኢትዮጵያ ባንኮች የሚያገኙት የትርፍ መጠን፣ በሌላው ዓለም የማይታይ ከፍተኛ ትርፍ እንደሆነም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ስለአገሪቱ ባንኮች የትርፍ ምጣኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ የምንሰማው፣ የኢትዮጵያ ባንኮች የሚያገኙት ትርፍ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ፣ የተጋነነና ከፍተኛ ስለመሆኑ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት አብዛኛዎቹ ባንኮች ለአንድ አክሲዮን ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚደርስ የትርፍ ድርሻ ያስገኙባቸው ጊዜያት እንደነበሩም እናስታውሳለን፡፡ ይህም ማለት፣ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን እስከ 60 ብር ያስገኛል ማለት ነው፡፡ 100 ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን በአንድ ዓመት 60 ሺሕ ብር ያገኛል ማለት ነው፡፡ እሰየው ይሁን፡፡

ከዚህ ውስጥ ግን 30 በመቶው የመንግሥት ድርሻ ስለመሆኑ አንዘንጋ፡፡ አሥር በመቶ ደግሞ ለትርፍ ድርሻ ክፍፍል የሚከፈል ግብር ነው፡፡ ይህም የመንግሥትን ድርሻ ወደ 40 በመቶ ያደርሰዋል፡፡ መንግሥት በእጅ አዙር ትልቁ ባለአክሲዮን ሆነ ማለት አይደል? ለማንኛውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ የተለጠጠ የግል ባንኮች የትርፍ ምጣኔ እየጠበበ መጥቷል፡፡ በአብዛኛው አንድ አክሲዮን የሚያስገኘው የትርፍ ድርሻ ወደ 30 ወይም 40 በመቶ መውረዱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከሌሎች የውጭ ባንኮች የትርፍ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር፣ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ የአገሪቱ ባንኮች የትርፍ መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ለማሳየትም በሌሎች አገሮች ባንኮች ውስጥ የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ ከአሥር በመቶ በታች እንደሆነና፣ በበርካታ አገሮች የሚታየው ግን ከሦስት እስከ ሰባት በመቶ ትርፍ እንደሆነ፣ የአገሪቱ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉም ይኼንኑ የሚያረጋግጥ ገለጻ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መናገራቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

የአገሪቱ ባንኮች የትርፍ መጠን ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ፣ ከፍተኛ ነው የሚያሰኘው ሌላ ምን ምክንያት አለ ሲባል የሚሰጠው ምላሽ ተገቢነት ያለው ቢሆንም እርግጥ ግን የሚገኘው የትርፍ መጠን ከፍተኛ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ የባንኮቹ ትርፍ ከዶላር ዋጋ አንፃር ሲመዘን፣ ምን ያህል ነው? ብለን ካሰላን ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚነገርለት ትርፍ የሚባልለትን ያህል ትልቅ እንዳልሆነ ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ ከአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም አንፃር ሲመዘን፣ የባንኮች የትርፍ መጠን እንደሚወራለት ከፍተኛ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደውም አነስተኛ እየሆነ ነው፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የብር የመግዛት አቅም ምን ያህል እየተዳከመ እንደመጣ ብናሰላ ተገኘ የተባለው ትርፍ ምን ያህል እያነሰ መምጣቱን ሊያስረዳን ይችላል፡፡ ይህንን ጉዳይ በቀላሉ ለማሳየት፣ በየዓመቱ የተገኘውን ትርፍ በየወቅቱ ካለው  የምንዛሪ ዋጋ ጋር መንዝረን ማየቱ ይረዳል፡፡ የውጭ ባንኮች ጋር እናመዛዝነው ከተባለም፣ የባንኮቻችን ትርፍ ዝቅተኛ መሆኑ ግልጽ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለማንኛውም  የተገኘውን ትርፍ በዶላር ሒሳብ አስልተን የትርፍ ምጣኔው ከፍተኛ ሊባል አይችልም በማለት ልንሟገትበትም እንችላለን፡፡ የባንኮቹ ትርፍ እያደረገ ቢመጣም የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ የትርፍ ድርሻ መጠን ግን እየቀነሰ መምጣቱን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኮች የሚያገኙት ትርፍ ከዶላር አንፃር ሲታይ፣ አነስተኛ ነው ቢባልም ባንኮች ብድር ሲሰጡ የሚጠይቁት የወለድ መጠን ከትርፋቸውም በላይ ሊያነጋግረን የሚገባው ጉዳይ ሆኗል፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሁሉም የግል ባንኮች ሊባል በሚችል ደረጃ፣ የብድር ወለድ ዋጋ  እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአንፃሩ የወለድ መጠኑ ጨመር ተብሎ ብድር ከመጠየቅ የሚቆጠብ ስለሌለ፣ ለብድር ጠያቂው ሁሉ ብድር ማዳረስም አልተቻለም፡፡ ወለዱ የቱንም ያህል ቢጨምር የብድር አቅርቦቱ ከፍላጎቱ አኳያ ሲታይ አነስተኛ ነውና፡፡

የግል ባንኮች ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች የሚያውሉት ብድርና ለዚህም ማስከፈያ የሚጠይቁት ወለድ እንደ ብድር ዓይነቱ እስከ 20 በመቶ እየነካ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የወለድ መጠን የሚጠየቁ እንዳሉ እንሰማለን፡፡ በዚህን ያህል ወለድ ገንዘብ ተበድሮ  የሚሠራ ሥራ አዋጭነቱ ቢያጠያይቅም፣ ነጋዴዎች ያዋጣናል በማለት ብድር እየወሰዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የወለድ መጠን የቱንም ያህል ቢያዋጣ፣ ሸክሙ ግን ጤነኛው ሊሆን አይችልም፡፡ ከነፃ ገበያ መርህ አንፃርም ቢሆን ሁኔታው ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የወለዱ ጡጫ አሳሳቢነቱ የሚጎላው ደግሞ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሲታይ ነው፡፡ ይህን ያህል ወለድ ተከፍሎት የሚሠራ የንግድ ሥራ የሚያስገኘው ትርፍ ታክሎበት ለሸማቹና ለተገልጋዩ ሲቀርብ፣ የሚያደርሰው የዋጋ ጭማሪና ተያያዥ ጉዳት ግልጽ ነው፡፡ ለኑሮ ውድነት ምክንያት በመሆን የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመሆኑም አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ አካሄዱ አንድ ቦታ ላይ መታየትና መታረም እንዳለበት ይጠቁማል፡፡

ነገር ግን ባንኮች ለሚሰጡት ብድር 20 በመቶና ከዚያም በላይ ወለድ የሚያስቡት ለምንድነው? ብንል በምላሹ ባንኮቹም አሳማኝ ምክንያት እንዳላቸው እንገነዘባለን፡፡ አንዱ ምክንያት ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት ወለድ ጥቂትም ቢሆን መጨመሩ ነው፡፡ እንደፈለጉ ማበደር እንዳይችሉ የሚገድቧቸው መመርያዎች የተጣሉባቸው መሆኑም ሌላው ችግር ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ብድራቸው ለቦንድ ግዥ የሚያውሉት የ27 በመቶ አስገዳጅ መመርያም ከዚህ ጋር ይያያዛል፡፡ በልዩ ልዩ መንገዶች ያገኙት የነበረው ገበያ፣ በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትም በብሔራዊ ባንክ በመገደቡ ሥራው አሽቆልቁሏል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድና በእኩል ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ መደረጋቸው፣ በልዩ ሁኔታ ለተቀማጭ ገንዘብ ከአሥር በመቶ በላይ የሚከፈልበት ሁኔታ መከሰቱ ሁሉ እነሱም በሚያበድሩት ገንዘብ ላይ የወለድ ጭማሪ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡

ስለዚህ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ ለማርገብ በተመጣጣኝ የወለድ መጠን ለማበደር እንዲችሉና ባንኮቹን ወደዚህ የገፏቸውን ገዳቢ መመርያዎች ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ችግሩ እየሰፋ ሄዶ ለኑሮ ውድነት ምክንያት እየሆነ በመሄድ ኢኮኖሚውን አዘቅት ውስጥ እንዳይጥለው ይታሰብበት፡፡ መመርያዎቻችንም አንዱን ለማስተካከል ተብሎ ሌላውን የመደርመስ ዕርምጃ እንዳይፈጥሩ በአግባቡ ይቃኙ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት