ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ እስማኤል ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ አቶ አብዲ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነት ቢነሱም የፓርቲው ሊቀመንበር በመሆነው ያገለግላሉ፡፡
በምትካቸውም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውኃ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አህመድ አብዲ የክልሉ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል ሲሉም አቶ እድሪስ አስታውቀዋል፡፡
በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በተነሳ አመጽ በርካቶች የሞቱ ሲሆን፣ ንብረቶች መዘረፋቸውን፣ የመኖሪያና ቤቶች፣ የንግድና የእምነት ተቋማት መቃጠላቸውም ታውቋል፡፡
ማምሻውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በሰጡት መግለጫ፣ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ወደነበረበት ለመመለስ የመከላከያ ኃይል ጣልቃ መግባቱን ገልጸው፣ የክልሉም ፖሊስ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ተጣርተው ለሕግ እንደሚቀርቡም የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት የሚጣራ ኮሚቴ በፌዴራል ደረጃ መቋቋሙን ገልጸው፣ ኮሚቴው ውጤቱን አጣርቶ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡