Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበድሬዳዋ ከአሥር ዓመታት በኋላ በደረሰ የጎርፍ አደጋ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታወቀ

በድሬዳዋ ከአሥር ዓመታት በኋላ በደረሰ የጎርፍ አደጋ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታወቀ

ቀን:

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሚያዝያ 16 ቀን 2008 ዓ.ም እኩለ ሌሊት እስከ ሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት ድረስ የዘነበው ዝናብ ባስከተለው ከፍተኛ ጎርፍ፣ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ሦስት ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገለጸ፡፡

በቁልቢ፣ በደንገጎና በአካባቢው ሲጥል ያደረውና በከተማውም ያለማቋረጥ ለአምስት ሰዓታት የዘነበው ከባድ ዝናብ፣ በተለምዶ አሸዋ በር በሚባለው ሥፍራ የተገነባውን የጎርፍ መከላከያ ግንብ ደርምሶ በማለፍ መልካ ጀብዱ ድልድይ (መልካ ጀብዱንና ድሬዳዋን የሚያገናኝ መሸጋገሪያ ድልድይ) ሰብሮ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ማድረሱን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በ1998 ዓ.ም. በድንገት በሌሊት በዚሁ አካባቢ ወደ ከተማው የገባው ከባድ ጎርፍ በበርካታ ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል መጉደል፣ የመፈናቀልና የንብረት መውደም አደጋ ማድረሱን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይደርስ የጎርፍ መከላከያ በተለያዩ ሥፍራዎች እንደሚሠራ ሲገለጽ መክረሙን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአሸዋ በር አካባቢ ብቻ ወደ ክብነት የሚያደላ መጠነኛ ከፍታ ያለው የጎርፍ መከላከያ ግንብ ብቻ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡ ለጎርፍ መከላከያ የተሠራው ጠመዝማዛ በመሆኑ ውኃ ተጋጭቶ እንዲመለስ ሳይሆን አቅፎ የመያዝ ባህሪ ስለነበረው፣ ሚያዚያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የደረሰውን የጎርፍ ውኃ በመያዙና ሲሞላ በመደርመሱ አደጋው በድጋሚ ሊደርስ መቻሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በጎርፉ አደጋ ከጭቃ የተሠሩ ቁጥራቸው ያልታወቁ ቤቶችም መፍረሳቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎች፣ ጎርፉ የደረሰው ጠዋት በመሆኑ ሊድኑ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር የቀድሞውን የባቡር ሐዲድ በማደስ ላይ እንደነበር፣ በከፍተኛ ወጪ የሠራው በከተማው የ02 ቀበሌ (ችግኝ ጣቢያ) እና ሌሎቹን ቀበሌዎች የሚያገናኘው ድልድይ መደርመሱን ገልጸዋል፡፡

አሸዋ ሲጭኑ የነበሩ ሁለት ዩዲ የጭነት ተሽከርካሪዎች በጎርፉ መወሰዳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በጎርፉ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሳይወድም እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡

በሰዎች ላይ የደረሰው አደጋ የታወቁት ብቻ ተጠቀሰ እንጂ የአዕምሮ ሕሙማን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና አንዳንድ በተለያዩ ችግሮች ወደ ቤት የማይገቡ በርካታ ሰዎች ውጭ የሚያድሩ ስለሚኖሩ፣ ምናልባት የአደጋው ሰለባ ሳይሆኑ አይቀርም የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ከደረሰ በኋላ የከተማው አስተዳደርና ባለድርሻ አካላት በድጋሚ ሌላ የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስ እየተረባረቡ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በተለይ በተለምዶ ዜሮ አንድ ቀበሌ የመልካ ጀብዱ ነዋሪዎችን (አምስት ኪሎ ሜትር ከከተማው ይርቃል) እና ድሬዳዋን የሚያገናኘውን መልካ ጀብዱ ድልድይን ለመጠገን እየተረባረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድንገተኛው የጎርፍ አደጋ ስለደረሰው የሞትና ንብረት መውደም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ምን እየሠሩ እንደሆነ ማብራሪያ ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...