የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ውስጥ ባለፈው እሑድ የተካሄደው ለንደን ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ በውድድሩ በዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) ስማቸው በከፍተኛ ደረጀ ሲነሳ የቆዩት ኬንያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ በበላይነት አጠናቀዋል፡፡ የረዥም ርቀት የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎች ንጉሡ ቀነኒሳ በቀለ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
በኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የለንደን ማራቶን ከፍተኛ ቀድሞ ግምት ተሰጥቶት ወደ ስፍራው ያመራው ቀነኒሳ በቀለ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት 06 ደቂቃ 36 ሰከንድ የወሰደበት ጊዜ ሲሆን፣ ያስመዘገበው ሰዓትም ለሪዮ ኦሊምፒክ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል እንዲጠቀስ ያስቻለው ሆኗል፡፡ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው የገቡት ኬንያውያኑ ኪፕቾጌና ስታንሌይ በዊቴ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2፡03፡05 እና 2፡03፡51 መሆኑም ታውቋል፡፡
የለንደንን ጨምሮ በማራቶን ውድሮሮች ሲሳተፍ የዘንድሮው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ የሚነገርለት ቀነኒሳ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበበት የፓሪስ ማራቶን 2 ሰዓት 05፡03 አጠናቆ የገባበት ሰዓት የቦታው ክብረወሰን እንደነበርም ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የቺካጎና ከሳምንታት በኋላ በተሳተፈበት የአምናው ለንደን ማራቶን ተጠብቆ ሳይሳካለት መቅረቱም ተመልክቷል፡፡
በሴቶች መካከል በተከናወነው ተመሳሳይ ውድድር ኬንያዊቷ ጀሚማ ሳምጎን እንደወንዶቹ ሁሉ አይበገሬነቷን አረጋግጣለች፡፡ አትሌቷ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2፡22፡58 ወስዶባታል፡፡ በውድድሩ ትልቅ ቅደመ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የአምናው አሸናፊ ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት ቱፋ 2፡23፡05 በሆነ ጊዜ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች፡፡ ሌላዋ ኬንያዊት ፍሎረንስ ኪፕላጋት 2፡23፡41 አጠናቃ ሦስተኛ ወጥታለች፡፡