‹‹ጥልቅ ክብርና ኩራት ተሰምቶኛል!››
ታዋቂው አይሪሻዊ አቀንቃኝ ሰር ቦብ ጊልዶፍ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሚያዝያ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በፊትና አሁንም ላከናወነውና እያከናወነ ላለው በጎ ተግባር በሂዩማኒቲስ ዘርፍ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሲሰጠው የተናገረው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኘው ቦብ ጊልዶፍ፣ ከሦስት አሠርታት በፊት ትግራይ የደረሰበት አጋጣሚ የአገሪቱ ሕዝብ በጦርነትና በረሀብ በሚሞትበት ጊዜ እንደነበረ አስታውሶ፣ ‹‹እንዲህ ዛሬ የተቀመጥኩበትና የቆምንበት ዩኒቨርሲቲ ግን ማሰብ አይቻለኝም ነበር፤›› ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በ1977 ዓ.ም. በአስከፊ ድርቅና ረሀብ በተመታችበትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት በቀጠፈበት ወቅት፣ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ድጋፍ ካደረጉት በጎ አድራጊዎች መካከል ሰር ቦብ ጊልዶፍ አንዱ ነበረ፡፡ በተለይ በዓለም ዙርያ ታዋቂ ሙዚቀኞችን በማስተባበር በ “We Are the World” (ዊ አር ዘ ወርልድ) የሙዚቃ ኮንሰርት የተፈጸመው አለኝታነት ይወሳል፡፡