Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በፋሺዝም ላይ የተቀዳጀነውን አኩሪ ድል በአህጉር ደረጃ ከአፍሪካውያን ጋር የምናከብረው መሆን ነበረበት››

‹‹በፋሺዝም ላይ የተቀዳጀነውን አኩሪ ድል በአህጉር ደረጃ ከአፍሪካውያን ጋር የምናከብረው መሆን ነበረበት››

ቀን:

አቶ ጌታቸው በለጠ፣ የዮቤግ ኮሙዩኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት የተገኘው የዓድዋ ድል ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ በ1933 ዓ.ም. በፋሺዝም ላይ የተገኘው ድልም ለእነዚህም ሕዝቦች ጭምር በተለይም ለአፍሪካ አገሮች ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ትርጉሙም በቅኝ አገዛዝ ሥር ይማቅቁ የነበሩ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተነቃንቀው ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ትግል የጀመሩበትና በስተመጨረሻም ነፃነታቸውን የተቀዳጁበት አኩሪ የድል ክስተት ነው፤›› በማለት ያመለከቱት አቶ ጌታቸው በለጠ፣ የ75ኛው ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የድል በዓል አከባበር ኮሚቴ አባልና የዮቤግ ኮሙዩኒኬሽን ሚዲያና ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡

ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚከበረውን በፋሺስት ኢጣሊያ ላይ ድል የተገኘበትን 75ኛ የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ ሚያዝያ 14 ቀን በተከናወነው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ገለጻ  ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጌታቸው በለጠ የተናገሩት፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ላይ የተገኘው ድል ለአፍሪካ አገሮች ነፃነት እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጅ ለመሆኑ ማሳያው ሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ያለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ናቸው፡፡

ከድላቸው በኋላ እነዚህን ሦስት ቀለማት መምረጣቸውም የፀረ ፋሺስት ትግል ውጤት በልባቸው ምን ያህል እንዳደረ ወይም እንደሰረፀ የሚያሳይ መሆኑን ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቀው የነበሩት የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ገዢዎች የተገነቡ፣ በዓለም የታወቁ ፕሮፌሰሮችንና መሪዎችን ያበቀሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቢኖራቸውም በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት ነፃነታቸውን እንደተቀዳጁ ብዙዎቹ ወጣቶች ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ስኮላርሺፕ ጠይቀው ከተፈቀደላቸው በኋላ ተምረው ወደ አገራቸው በመመለስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የደረሱ እንደነበሩበት አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ቢሆንልን ኖሮ በፋሺዝም ላይ የተቀዳጀነውን አኩሪ ድል በአህጉር ደረጃ ከአፍሪካውያን  ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር የምናከብረው መሆን ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡

የአልማዝ ኢዮቤልዩው ከረቡዕ ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን አስታውቀዋል፡፡ ቀዳሚው መሰናዶ ከቀትር በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል በሚካሄደው የባህል ሲምፖዚም ከነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሥነ ቃል፣ ቀረርቶና ፉከራ ይቃኛሉ፡፡   የዐውደ ርዕይ ዝግጅት፣ ና የታሪክ ሲምፖዚየሞች በተለያዩ ቀናት አዳራሾች ይካሄዳሉ፡፡ የዐውደ ርዕዩ ዝግጅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሚያዝያ 19 ቀን ከቀትር በኋላ ሲከናወን አርበኞች ለማነቃቂያ ይላላኩዋቸው የነበሩና በአንፃሩ ደግሞ የፋሺስት ጦር ሕዝብን ለመከፋፈልና ለመደለል ይበትናቸው የነበሩ ጽሑፎች፣ እንዲሁም በጦርነቱ ላይ የዋሉ ልዩ ልዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች ይቀርባሉ፡፡

በቅድመ ፋሺስት፣ በፋሺስት ወረራ ዘመንና በድኅረ ፋሺስት የኢትዮጵያ ገጽታ ምን እንደሚመስል የሚያመላክቱ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት የታሪክ ሲምፖዚየም ሚያዝያ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ እንደሚካሄድ ማኅበሩ አመልክቷል፡፡

በሚቀርቡት ጽሑፎች ላይ ሲልቪያ ፓንክረስት የፋሺዝምን ወረራ በመቃወም በለንደን አደባባይ ያካሄዱት ሠልፍ፣ እንዲሁም አፍሪካ አሜሪካዊ  የጦር አውሮፕላን አብራሪ የሆነው ኰሎኔል ጆን ቻርልስ ሮቢንስን ይዘከራሉ፡፡ የታሪክ ሲምፖዚየሙ በአፍሪካ አዳራሽ እንዲካሄድ የተደረገበት ምክንያት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ከፋሺዝም ድል መሆን ጋር ተያያዥነት ስላለው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡  

ማኅበሩ እንዳስታወቀው፣ ዘመናዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመጻሕፍት፣ የእንግዳ ማረፊያ የሚኖረውና ለአርበኞች መታሰቢያ የሚሆን ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት በበዓሉ ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም.  ይካሄዳል፡፡ አንድ ጥቁር ደሃ አገር በግፍ መወረር የለባትም ብለው በሊግ ኦፍ ኔሽን (በመንግሥታቱ ማኅበር) ላይ ድምፃቸውን በማስተጋባት ለኢትዮጵያ የቆሙ አገሮች፣ እንዲሁም ሉአላዊነታችን በማስከበር ረገድ አስተዋፅኦ እያደረገ ላለው መከላከያ ኃይላችን አርበኞች ምስጋና የሚያቀርቡበትና ዕውቅና የሚሰጥበት ፕሮግራም፣ ከዚህም ሌላ በፖስታ አገልግሎት ድርጅት የታተሙ ስድስት የመታሰቢያ ቴምብሮች ምረቃና የአደራ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል፡፡

በመላ አገሪቱ እስከ 45,000 የሚጠጉ አርበኞች እንዳሉ መገመቱንና ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት የሚያስችል የማጣራት ሥራ በዞንና በወረዳ በቅርቡ እንደሚካሄድ በመግለጫው ወቅት ያስረዱት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ቀይአ ገብርኤል በተባለው ሥፍራ የፋሺስት ወራሪ ጦር በጋዝ ጭስ አፍኖ 5,500 ኢትዮጵያውያንን የፈጀበትና እስካሁንም የአንዳንዶቹ አጽም የሚገኝበት ‹‹አመፀኛ ዋሻ›› ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ፊልም ተቀርጾ በታሪክ ሰነድነት እንዲያዝ መደረጉንም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሳሲት ወረዳ ልዩ ስሙ አንቀላፌ በተባለው ቦታ ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም. ሲሆን ማኅበሩን ካቋቋሙት መካከል ባላምባራስ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች ከፍያለው (ራያ ከፍያለው) ወልደፃድቅ፣ ደጃዝማች ተሰማ ዕርገቴ፣ ደጃዝማዝ ፀሐይ እንቁሥላሴ፣ ደጃዝማች ተስፋዬ እንቁሥላሴና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ማኅበሩ የተቋቋመው ጠላት በሚዘዋወርበት፣ በሚገባበትና በሚሰባሰብበት ቦታዎች ላይ ሁሉ የስለላና የማጥቃት ሥራ ለማካሄድ የሚያስችል ስትራቴጂ ለመቅረጽ፣ የቆሰሉ አርበኞችን ማኅበረሰቡ እየደበቀ እንዲንከባከባቸው ለማድረግ፣ የጦር መሣሪያ ያለው ሰው መሣሪያ አልባ ለሆነው አርበኛ የሚያቀርብበትን ወይም የሚሰጥበትን አቅጣጫ ለመቀየስና አርበኞች እርስ በርሳቸው እንዳይዋጉ ለማድረግ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...