Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሚሊዮኖች አባት

የሚሊዮኖች አባት

ቀን:

‹‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች፤ ደህና ናችሁ ልጆች፤ . . .›› በማለት አባባ ተስፋዬ እጆቻቸውን በፍቅር ሲያወዛውዙ በቴሌቪዥን የተመለከቱ ሕፃናት ይኼን ያህል ይሆናሉ ከማለት ይልቅ ቤት ሠፈር ይቁጠራቸው ማለት ይቀላል፡፡ የአባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሳህሉ) ተረቶች፣ ምክሮችና ጨዋታዎች የብዙዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ናቸው፡፡ ዕውቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ተስፋዬ ሳህሉ፣ በተለይ በታዳጊዎችና ወጣቶች ዘንድ በይበልጥ የሚታወቁት በልጆች ክፍለ ጊዜ ሲሆን፣ የብዙ ሙያዎች ባለቤትም ናቸው፡፡

አባባ ተስፋዬ ተዋናይ፣ ዘፋኝ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ የዳንስ አሠልጣኝ፣ መድረክ መሪና ምትሀተኛ ናቸው፡፡ አንጋፋው ባለሙያ ለኪነ ጥበብ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለመዘከርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው ዝግጅት የአባባ ተስፋዬ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ጥናት ቀርቦ በባለሙያው አበርክቶ ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡

በቴአትር ምሩቁ የባህል ማዕከሉ ኤክስፐርት አቶ ቆንሲል ተፈራ የቀረበው ጽሑፍ  የባለሙያውን ሙያዊና ግላዊ ሕይወት ዳሷል፡፡ በልጅነታቸው ወደ ኪነ ጥበብ የገቡበት ሁኔታ፣ ሙያዊ አበርክቷቸውና አሁን ያሉበት ሁኔታ በጥናቱ የተካተተ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የአባባ ተስፋዬ ቤተሰቦችና አድናቂዎች ተካፍለዋል፡፡

ጥናቱ የተሠራው ለአባባ ተስፋዬና የሙያ አጋሮቻቸው ቃለ መጠይቅ በማድረግና ሌሎች ጽሑፎችን በማጣቀስ ነው፡፡ ጥናቱ መነሻውን ያደረገው የልጅነት ጊዜያቸውን ነው፡፡ በ1916 ዓ.ም. ባሌ የተወለዱት ባለሙያው በልጅነታቸው የቄስ ትምህርት ተምረዋል፡፡ አባታቸው በሥራ ምክንያት ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ አብረው ተጉዘዋል፡፡ ሐረር ፈረንሣይ ትምህርት ቤት፣ አዲስ አበባ ደግሞ ኮከበ ጽባሕ የተማሩ ሲሆን፣ ከአራተኛ ክፍል በላይ አልዘለቁም፡፡

የወጣትነት ዘመናቸው በብዙ ትዝታዎች የተሞላ ነው፡፡ በፋሽስት ኢጣልያ ወረራ ወቅት እንደሌሎቹ ጓደኞቻቸው መዝመት ቢፈልጉም ጉልበታቸውን ስለታመሙ ሳይዘምቱ ቀሩ፡፡ በሕመማቸውም ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ ከመታከም በተጨማሪ ቀስ በቀስ የዶክተሮቹን እንቅስቃሴ ጣልያንኛና ቀለል ያሉ የሕክምና ፕሮሲጀሮች ይከታተሉ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ ዶክተሮች ስለተወደዱም እዛው መሥራት ጀመሩ፡፡ መርፌ በመውጋት፣ በቀዶ ሕክምና ወቅት መብራት በመያዝና በሌላም ያግዛሉ፡፡ ጣሊያኖችም አንድ ጥቁር እንዴት ነገሮችን በፍጥነት ተምሮ ያለ ስህተት ይፈጽማል ብለው በመገረም ‹‹ቪልጎራ›› (ማነህ) የሚል ቅጽል ስም ሰጧቸው፡፡

ወቅቱ ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍጨፋ ያጡበት ነበር፡፡  በ1929 ዓ.ም. የተካሄደው ጭፍጨፋ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎችም የአገሪቱ ዜጎች በግፍ ያለቁበት ነው፡፡ አባባ ተስፋዬ አቡነ ጴጥሮስ በጣልያኖች በተገደሉበት ወቅት በቦታው ተገኝተዋል፡፡ በሚሠሩበት ሆስፒታል እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች የሚፈጸመው ይህ ግፍ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ የሆስፒታሉን ሥራ ለቀው ወደ አስተናጋጅነት የገቡትም ለዚሁ ነበር፡፡ መጀመርያ በእቴጌ ሆቴል (ጣይቱ ሆቴል) ከዛም ወደ ሐረር ተጉዘው በራስ ሆቴል ሠርተዋል፡፡ ራስ ሆቴል ውስጥ የሙዚቃ ችሎታቸውን ያስተዋሉት ልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ጽፈው ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው፡፡ በ1937 ዓ.ም. የሙዚቃ ሥልጠና በመውሰድም ሙያውን ተቀላቀሉ፡፡

ከልጅነታቸው  ጀምሮ የኪነ ጥበብ ዝንባሌ የነበራቸው አባባ ተስፋዬ፣ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተቀጠሩ፡፡ በልጅነታቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲፎክሩና እንዲሸልሉ ያበረታቷቸው ነበር፡፡ የተለያዩ አጋጣሚዎች መነሻ የሆኗቸው ተስፋዬ፣ በማዘጋጃ ቤት በትወና፣ በመድረክ መሪነትና በሙዚቀኛነት ሠርተዋል፡፡ ክራር፣ መሰንቆ፣ ዋሽንት፣ በገና፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮንና ትሮምቦን ከሚጫወቷቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ግጥምና ዜማ ይጽፋሉም፤ ያቀነቅናሉም፡፡ ‹‹አንቺ ዓለም››፣ ‹‹አንድ ጊዜ ሳሚኝ›› እና ‹‹ሰው ሆይ  ስማ››  ካዜሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በትወና ረገድ፣ ሴት ተዋንያን ባልነበሩበት ወቅት እንደ ሴት ሆነው መጫወታቸው ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ጎንደሬው››፣ ‹‹መቀነቷን ትፍታ›› እና ‹‹ጠላ ሻጭ›› የሴት ገጸ ባህሪ ተላብሰው ከተጫወቱባቸው ተውኔቶች መካከል ናቸው፡፡ በ1948 ዓ.ም. ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተዘዋውረው መሥራት ጀመሩ፡፡ አስቂኝ ሥራዎቻቸውን ለመመልከት የጓጉ ተመልካቾች ሲጋፉ የቴአትር ቤቱን በር እስከመስበር ደርሰው ነበር፡፡ በወቅቱ በቴአትር ቤቱ የዘመናዊ ዳንስ ሥልጠናም ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ነደድኩልሽ››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ››፣ ‹‹ኦቴሎ›› እና ሌሎችም በርካታ ቴአትሮች ላይ ተውነዋል አባባ ተስፋዬ፡፡

በኮሪያ ጦርነት ወቅት ወደ ኮሪያ ተጉዘው ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ያቀርቡ ነበር፡፡ የአሥር አለቃነት ማዕረግም አግኝተዋል፡፡ ኮሪያ የተማሩትን ምትሀት ኢትዮጵያ ያገኙት አይሁዳዊ አሠልጣኝ አጠናክሮላቸው፣ አስደናቂ ትርዒቶች ማሳየት ችለው ነበር፡፡ የዓለም አቀፍ ምትሀተኞች ማኅበር አባልም ሲሆኑ፣ በምትሀት ቤት ማቃጠልና በመጽሐፍ ላይ የሚሠሩ ምትሀቶች የታወቁባቸው ትርዒቶች ናቸው፡፡ ከብዙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ህሊና የማይጠፉ ተረቶችን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ ማቅረብ የጀመሩት ጣቢያው በተመሠረተበት በ1957 ዓ.ም. ነበር፡፡ በማኅበረሰቡ የሚወደዱ ታዋቂ ተረቶችን በአዲስ መልክ ያቀርቡ ነበር፡፡ ልጆችን የሚያስተምሩና የሚያዝናኑ ተረቶቻቸውና ተረትና ምሳሌዎቻቸው የብዙዎች የማይረሱ ትዝታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተረቶቻቸው በመጽሐፍም ቀርበዋል፡፡ አምስት የተረት መጽሐፎቻቸውን በአዲስ መልክ የማሳተም ዕቅድም አላቸው፡፡

‹‹ኪነ ጥበብ አባቴ፣ ንጉሤና አሳዳሪዬ ነው፡፡ እፈራዋለሁ፡፡ አከብረዋለሁ፡፡ የኪነ ጥበብ ባሪያ ነኝ፤ ከኪነ ጥበብ የምለየው ስሞት ነው፤›› የሚሉት አባባ ተስፋዬ፣ በ1993 ዓ.ም. ከ36 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጡረታ ወጥተል፡፡ አጥኚው ከሙያ አጋሮቻቸው ጠይቆ በተረዳው መሠረት ባለሙያው፣ ኪነ ጥበብን ያከብራሉ፡፡ ይወዳሉ፡፡ ሁለገብ ባለሙያ ከመሆናቸውም ባሻገር በሥነ ምግባር የታነፁ እንደሆኑም ይናገራል፡፡

አሁን አባባ ተስፋዬ 93 ዓመታቸው ነው፡፡ ከሚወዱት ሙያ በጡረታ በመገለላቸው ደስተኛ አይደሉም፡፡ ተፈራ የተባለው ልጃቸው ስፒሪቺዋል አርት የተማረ ሲሆን፣ ከአምስቱ የልጅ ልጆቻቸው ሁለቱ በኪነ ጥበቡ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አባባ ተስፋዬ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሦስት የወርቅ ሜዳልያ አግኝተዋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶችም ልዩ ልዩ ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ሌሎች ባለሙያዎችንም በተመሳሳይ መልክ ዘክሯል፡፡ በዝክረ ተስፋዬ ሳህሉ ዕለት የተገኙ ሰዎች ይህን ተግባር አበረታትተዋል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹አባባ ተስፋዬ ሊረሳ የማይገባ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ አበርክቷቸው ግን በስፋት አይታወቅም፤›› ብለው ጥናቱ ለተማሪዎች መማርያም እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የሙያ አጋራቸው መርዓዊ ስጦት በበኩላቸው፣ ‹‹ተስፋዬ የሌለበት ቴአትርና ሙዚቃ አይሞቅም ነበር፡፡ ለሙዚቃና ለቴአትር ዕድገት የከፈለው ውለታ ዕዳው አልተከፈለውም፡፡ በሚኖርበት ቤት ለመገንባት የታሰበው የኪነ ጥበብ ማዕከል ዕውን መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ይህን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሕይወት እያሉ ስለ አስተዋጽዎአቸው መዘከርና መሸለም አለባቸው የሚል አስተያየትም በተደጋጋሚ ተሰንዝሯል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...