Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተስፋ ባይኖር ልፋት ከንቱ ይሆን ነበር!

እነሆ መንገድ። ከሜክሲኮ ወደ መርካቶ ልንጓዝ ነው። የወትሮው የጎዳና ትዕይንት በዓውደ ዓመት ሽርጉድ መደማመቅ ጀምሯል፡፡ እዚያ አንዱ መንታ አውራ ዶሮዎች ዘቅዝቆ ይዞ የሸክም ዋጋ ያጫርታል። ‹‹አሁን ለዶሮ የሚሆን ክንድ አጥቶ ነው እነኚህን ምስኪኖች የሚያናክሳቸው? በዚህ ዓይነት በሬ ቢሸምቶ ኖሮ ምን ሊያደርግ ነው?” ትላለች የወያላው የድጋፍ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ። “ሔሊኮፕተር’ ይጠራላ፤” ይላታል ከጎኗ የተሰየመ መልከ መልከም ወጣት። “ወይ ጊዜ! ሰው በቃ ኢንተርኔት ላይ ያሻውን ፎቶ ‘ዳውን ሎድ’ ማድረግ ለምዶ ‘ሔሊኮፕተርን’ ከዶሮ እኩል ይተምነው ጀመረ? የማንሰማው የለም እኮ እናንተ፤” መሀል መቀመጫ የተሰየመ ጎልማሳ ነው ይኼን የሚለው። “በነገራችን ላይ ‘ሔሊኮፕተር’ ሊፈጠር የቻለው ዶሮ በመብረርና ባለመብረር መሀል መቅረቷን በመታዘብ ነው ይባላል፤” ብላ ጋቢና የተሰየመች ሳቂታ ዘወር ስትል፣ “ምነው ታዲያ የእኛ በመብረርና ባለመብረር መሀል መዋለል ታይቶ መፍትሔ ቢበጅልን?” አላት ጎልማሳው።

“ምነው ጋሼ? እኛ እኮ ከዶሮ ጩኸት ቀድመን የመከዳዳት እንጂ የመብረር አልያም ያለመብረር ችግር ላይ ገና አልደረስንም፤” አለችው ወይዘሮዋ። “እንዴት?” ሲላት ምንም ጊዜ ሳትፈጅ አሰላስላ በአዕምሮዋ የሰደረቻቸውን ሐሳቦች መተንተን ቀጠለች። “ለምሳሌ እይ እዚያ ማዶ ሊስትሮዎቹ መደዳ። ያ ጉብል ተቀምጦ ሊስትሮውን እያመናጨቀ ጫማውን እንዴት እንደሚያስወለውል ታያለህ አይደል? አጠገቡስ? አንድ እግር የሌለው አካል ጉዳተኛ ወድቋል። ነገር ግን ያ ባለጫማ ለአፍታ ዘወር ብሎም ያየው አይመስልም። በእርግጥ ማየቱን እናያለን። ግን አናስተውልም። ታዲያ ይኼ የማስተዋል ጉድለት እንጂ የክንፍ ችግር ነው እንዴ የእኛ ችግር?” ስትለው በአዎንታ አንገቱን ነቅንቆ ዝም አላት። ዶሮና ሔሊኮፕተር ያስነሱትን አቧራ አንዱ ሲያስጠርገው አንዱ ፍራሽ አድርጎት ይኼው ፈስከን የሸኘነው ትንሳዔ በኩዳዴ አድርጎ መጥቶ ሊጠቃለል ህማማትን በማጋመስ ላይ ነው፡፡

“ሾፌር እንሂድ እንጂ። ሰዓቴን እኮ እዚሁ በላኸው?” ትላለች ጋቢና የተሰየመች የተመረረች። “የፍስክ ነው የፆም?” ሾፌሩ ያሾፍባታል። “ምኑ?” ስትለው ግራ ተጋብታ፣ “የበላሁብሽ ሰዓት የፍስክ ነው የፆም?” ደገመላት። “አቦ አያስቅም። ጥቁር አንበሳ እወርድልሃለሁ ያኔ ለምን ያሻህን ያህል ቆመህ አትጭንም?” አለችው እየተንቆራጠጠች። “ኧረ ተይ በፈጠረሽ? ይኼ ሁሉ ሰው ዘመዴ መሰለሽ? እንዳንቺ ይቸኩላል እኮ? አንቺን እስካወርድ ምን አስከሰረኝ? ነው በብር ከሃምሳ ላዳ አለ ብለውሽ ነው አዲስ አበባ የገባሽው?” ሲላት የምር ተናደደች። “ሥነ ሥርዓት እሺ? እርድ ያልኩ ያራዳ ልጅ ነኝ። እዚሁ ተወልጄ ያደግኩ የሸገር ልጅ፤” የጦፈ የማንነት ክርክር ውስጥ ገባች።

“ይቅርታ ካስቀየምኩሽ። ግን ምነው ታዲያ እዚሁ ተወልደሽ ካደግሾ መኪና የሌለሽ? እኩዮችሽ እኮ ዛሬ ከአውቶሞቢል አውቶሞቢል እያማረጡ ነው። ዕድሜ ለልማታዊ መንግሥታችን  . . . ማለቴ ለልማታዊ ባለሀብቶቻችን፤” ሲላት የደም ሥሮቿ ተገታተሩ። ነገር ግን በኃይለ ቃል ለመመለስ አልፈለገችም። ከገመታት በላይ የተማረች የተመራመረች ትመስላለች። “ይመስልሃል የአራዳ ልጆች የሥነ ምግባር ኮድ አቋራጭ? ይመስልሃል የአዋቂ የከተማ ልጆች ሥርዓትና ወግ ሁለት እግር አለኝ እያሉ ሁለት ሦስት ዛፍ ላይ መንጠልጠል? ለነገሩ አንተ ምን ታደርግ? ዛሬ ጨዋና አራዳ የሚባለው አውቀን እንዳላወቀ በሆንበት የሥነ ምግባር ደንብ እየተጫወተ ባለቤት፣ ባለመኪናና ባለፎቅ የሆነው ነው፤” ብላ በትካዜ እልም አለች፡፡ ሾፌሩ የስሜቷን መጎዳት አይቶ ያባብላት ጀመር። “ቀልድና ምንትስ ቤት ያበላሻል ይሏችኋል ይኼ ነው፤” ሲል ዘግየት ብሎ የገባ ተሳፋሪ፣ “ቀልዱስ ቀልድ ነው። ዘንድሮ እኮ ቤቱን እያበላሸ ያስቸገረን ቀልድ የሚመስለው ቁምነገራችን ነው፤” አለው ጎልማሳው። ወያላው በሩን ዘጋ።

ጉዟችን ተጀምሯል። ገና ሒሳብ ሳይከፍል መጨረሻ ከተቀመጡት አንዱ፣ “መልሴን አትሰጠኝም እንዴ?” ብሎ ወያላው ላይ ጮኸበት። ግራ ገብቶን ተያየን። “መቼ ከፈልክ?” ወያላው በትህትና ጠየቀው። “ወይኔ ሃምሳ ብሬ ተበላሁ፤” እያለ  ታክሲያችንን በአንድ ጎማዋ አቆማት። ለካስ ለመጣበት ታክሲ ሃምሳ ብር እንደሰጠ መልስ ሳይቀበል ወርዶ ኖሯል። “አውርደኝ! አውርደኝ!” ብሎ ሲጮህ ታክሲያችን ጥጓን ያዘች። በምትኩ ሦስት ወጣት ታዳጊ ሴቶች ተተክተው ጉዟችን እንደቀጠለ፣ “ምስኪን አሁን በምኑ ሊፈስክ ነው?” ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት ጠየቀ። “በሃምሳ ብር ይፈሰካል እንዴ? ያውስ ስንት እንደተቆረጠለት አላወቅንም፤” ብላ ወይዘሮዋ ጠየቀችው። “እሱማ የምር እንፈስክ ካልን መቶ ሺሕም አይበቃንም፤’’ አላት ወጣቱ እየሳቀ።

“የብር የመግዛት አቅም ቢወድቅ ቢወድቅ እንዲያው ለአንድ ፋሲካ መቶ ሺሕ እንዴት ብሎ ያንሳል እባክህ? ስም አጥፊ፤”  ወይዘሮዋ ለነገሩ የነገር፣ ለሳቁ የሳቅ አፀፋ ስትመልስ፣ “የሦስት ሺሕ ዘመን ፆም መቶ ሺሕ አይደለም ቢሊዮን አይበቃውም ብዬ ነዋ፤” አላት።  “ታዲያ እሱንማ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች መሳካት እንጂ በቤት እንስሳት ተዋጽኦዎች ብቻ ይፈሰካል እንዴ?” አለችው ከኋላ አንዷ ጭምት። “አፈር ልብላልሽ እንዳልልሽ ዘመኔን ሙሉ ጭቃ እያቦካሁ ስለኖርኩ ካሳ አይሆንልሽም። ትልቅ ቁም ነገር ተናገርሽ። ሰው የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ሲባል ፖለቲካ ይመስለዋል። ዶሮና በግ ስለተወደደበት ብቻ ኑሮው ያሽቆለቆለ ይመስለዋል። ይኼው በእኔ ሕይወት ያየሁት ለውጥ ግን ታላቅ ምስክር ነው። ዕድሜ ለልማታዊው መንግሥታችን ጊዜ ጠብቆ ከሚረግፍ ጭቃ አቡኪነት ሲሚንቶ ለሳኝ ሆኛለሁ። ማንም አይወቀኝ። የሲሚንቶ ልስኖቼ ግን ከጭቃዎቹ ተሽለው ገና ከትውልድ ትውልድ ይሻገራሉ። ታዲያ ከዚህ በላይ ፆም መፈሰክ የት አለ?” ብለው ከጎኗ የተቀመጡ የጎበጡ አዛውንት በዝምታ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ስናይ ሐዘንና ደስታችን ተምታታ። አይዘከርም እንጂ ይኼም ህማማት ነበር!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ መልስ ይመልሳል። መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ቀልበ ቢስ ልጅ እግር መሀል መቀመጫ ተዳብለው ከተሰየሙት ጓደኞቿ ጋር ጮክ ብላ ታወራለች። “ኧረ ጋይስ ምንድነው? የካርድ ወጪ እኮ አናቴ ላይ ወጣ፤” ከማለቷ ወዲያው አንዷ ተቀብላ፣ “ካርዱን እርሺው። ዘንድሮ ቴሌን ካልጠበስን ዋጋም የለን፤” አለቻት። የተሳፋሪውን ቀልብ የሳቡት እንዲህ ነበር። “ስሚማ?” ሦስተኛዋ በከፊል ዞራ ተቀመጠች። “የት ነው የምትቀነደቢው እባክሽ? አያምርም አቀነዳደቧ?” ለምስክር መልሳ አጠገቧ ወደ ተቀመጠችው ወዳጇ ዞረች። “እሷ ምን አለባት? ጥፍር ቀለሟ ሳይለቅ ጥፍሯን የምታሠራ ጀግና ናት እኮ። ይልቅ ያ ፀጉር ሠሪሽ ‘ቴስትራ’ የሚሠራው 80 ብር ነው አይደል?” ብላ ሦስተኛዋ በተራዋ ወደኋላ ተጠማዘዘች። “ቲፕ ሃያ ብር ስትጨምሪበት ድፍን ‘አመድ፤” አለች እየሳቀች ተደናቂዋ የውበት እመቤት።

“ኧረ በፈጠራችሁ ስለሌላ ነገር አውሩ። ቢያንስ በህማማቱ ሥጋችሁን አትረሱም?” ጎልማሳው ሳይኮሳተርና ሳይስቅ ጣልቃ ገባ። “ለእርድ እየተዘጋጀን እንዴት ብለን ሥጋን እንርሳ?” ስትለው አንደኛይቱ ሌላኛይቱ ተቀብላ፣ “ክርስቶስ በነፃነት እንድንኖር ከሕግ ቀንበር ነፃ አወጣን እንጂ ለባርነት አሳልፎ አልሰጠንም፤” አለችው። ይኼኔ ሾፈሩ ጨንቆት ይመስላል የከፈተውን የውዳሴ መዝሙር ዘግቶ፣ “ኧረ አስታራቂ የለም ወይ?” የሚል ዘፈን ከፈተ። ‹‹ኃላፊነቱን ሳያስተምሩን ንግግሩንና የመናገር ነፃነቱን አውጀው እኮ ተተራመስን፤” ያለኝ ተሳፋሪ ባቡር ይሆን ታክሲ ይኼኔ የተሳፈረው? ቅርፁን እያየን ተልኳችንን የሳትነው በዛን እኮ እናንተ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ጋቢና የተሰየመችው ችኩል ወርዳ በምትኳ ረጋ ያሉ ሴት ተሳፍረዋል። ስልክ እያወሩ ነው። “ደርሶኛል ልጄ . . . ምን ዶላርና ብር አንድ ሆኗል እኮ ዘንድሮ . . . እንዴት? ምን እንዴት አለው ዶሮዎቹና በጎቹ በዜግነት እንጂ ኢትዮጵያዊ ዋጋ ላይ እኮ ዜግነታቸው አውሮፓና አሜሪካ ነው . .. ያ ባይሆን አስቸግርሽ ነበር ልጄ?” ይላሉ። “ኑሪልኝ ያኑርሽ የተባረከ የተደላደለ ትዳር ይስጥሽ፤” ብለው ሳይጨርሱ ስልኩ ተቋረጠ። “ኔትወርኩ ነው እስኪ እይልኝ ልጄ ዓይኔ አያይም፤” ብለው አጠገባቸው ለተቀመጠ ተሳፈሪ አይፎናቸውን ሰጡት። “ካርድዎ አልቆ ነው፤›› አላቸው፡፡ “ምን ልዩነት አለው? ኔትወርኩና ካርዱ አንድ ሆኗል። ኑሮአችን አላልቅ ብሎ እኮ እኛ አለቅን፤” ሲሉት ሲያሳስቃቸው፣ ሲያመቻቻቸው ቆይቶ ወደ ሲኒማ ራስ ታጥፈን ቆም ስንል በሩን ከፍቶ ወርዶ ሮጠ። “እ-ህ?! ምን ሆኖ ነው?” ብለው ጎንበስ ቢሉ ቀና ቢሉ ስልካቸው እጃቸው ላይ የለም። ጩኸታቸው መርካቶን ሰንጥቆ አልፎ አርያምን አስበረረገገ። ተሳፋሪዎች የሚያደርጉት የሚሠሩት ጠፋው። ወያላው ወርዶ ሌባው ወደ ሮጠበት አቅጣጫ ትንሽ ሮጦ ተመለሰ። ማፅናኛ ጠፋ።

አውሮፓ ያለች ልጃቸው ጉልበቷን፣ ማንነቷንና ክብሯን ሸጣ ገዝታ ከላከችላቸው ገና ሳምንቱ እንደነበር ሃያ ሺሕ ብር የገመቱትን ስልክ ታሪክ ሳግ እያነቃቸው ተረኩ። ይኼኔ ከጭቃ አቡኪነት ወደ ሲሚንቶ ለሳኝነት በመሸጋገራቸው ሕይወት ፍትሕ ታውቃለች ብለው የደመደሙት አዛውንት ወደፊት ጠጋ ብለው፣ “ሁሉ ለበጎ ነው፡፡ አይዞዎት። እሱ እኮ የጠፋውን ሊፈልግ መጥቶ ነው የተሰቀለው። ታዲያ እኛ ከእሱ አንበልጥ፤” ካሉ በኋላ ወደተቀሩት ተሳፋሪዎች ዞረው፣ “ምን ኑሮ ቢከብድ፣ ምን ፈተናው ቢበዛ እባካችሁ የቅርቡን አይታችሁ የአጭር ጊዜ ደስታ አያሸንፋችሁ ልጆቼ። ባይመችም ቅሉ ፈጣሪ የሰጠን ተስፋ ከሞዝቮልድ አልጋ ህልም ያማረ ነው፤” ብለው አንገታቸውን ደፉ። ወዲያው ወያላው “መጨረሻ” ሲለን መርካቶ ገብተን ተጠፋፋን። ወይ ሰውና ተስፋ? ግን ስንቱን ተስፋ እናድርግ? ለነገሩ ተስፋ በሌለበት ልፋት ከንቱ ነው፡፡ መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት