Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንክ አገልግሎት በውክልና

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ በዘለለው የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥም ይዘግዩ እንጂ አዳዲስ አሠራሮች ብቅ እያሉ ነው፡፡

በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየታዩ ያሉ አገልግሎቶች፣ የባንክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ዕድል የሚሰጡና ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማጐልበት እንደሚረዱ ታምኖ እየተሠራባቸው ነው፡፡

ሞባይል ባንኪንግ፣ ኤጀንት ወይም ወኪል ባንኪንግ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ የባንክ አገልግሎቶችን ለመጀመር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለየአገልግሎቶቹ የሚሆን መመርያ በማዘጋጀት ባንኮች ወደ ሥራ እንዲገቡ ዕድል ሰጥቷል፡፡

ከእነዚህ የአገልግሎት ዓይነቶች ውስጥ ኤጀንት ወይም ወኪል ባንኪንግ አንዱ ነው፡፡ ኤጀንት ባንኪንግ ከሞባይል ባንኪንግ ጋር ተጣምሮ የሚሠራ ነው፡፡ እስካሁን ከሚታወቀው መደበኛ የባንክ ቅርንጫፎች ውጭ በተለያዩ አነስተኛ የንግድና አገልግሎት ተቋማት ውስጥ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የአሠራር ስልት ሲሆን፣ እስካሁን አምስት ባንኮችና አምስት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በጥምረት የፈጠሩት ኩባንያ አገልግሎቱን ለመስጠት ፍቃድ ወስደዋል፡፡ አገልግሎቱን እንደ ፋርማሲ፣ ምግብ ቤት፣ ነዳጅ ማደያ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች፣ ሱፐር ማርኬቶችና የመሳሰሉት ተቋማት ከባንኮች ውክልና ወስደው መሥራት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወኪሎች ንግድ ፍቃድ ያላቸውና በተሰማሩበት የንግድ ሥራ ሁለትና ከሁለት ዓመት በላይ የሠሩ መሆን አለባቸው፡፡ ያለምንም ቢዝነስ ሥራ ኤጀንት መሆን እንደማይቻልም የብሔራዊ ባንክ መመርያ ያስረዳል፡፡

የኤጀንት ባንኪንግ ፍቃድ ካገኙ ባንኮች ያሰባሰብነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከአራት ሺሕ በላይ ወኪል ባንኮች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ እስካሁን ባሉት መረጃዎች ከባንኮች ኅብረት ባንክ ወደ 300፣ አንበሳ ባንክ 1090 ወኪል ባንኮች በመያዝ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዳሸንና በኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንኮችም ቁጥሩ አይብዛ እንጂ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በወኪል ባንኮች እየሠሩ ናቸው፡፡ ከፍተኛውን ኤጀንቶች በማፍራት የሚጠቀሰው ግን በአምስት ማክሮ ፋይናንሶች ጥምረት የተቋቋመውና ‹‹ኤም ብር›› ከሚባለው የሞባይል ባንክ ጋር ተጣምሮ የሚሠራው የወኪል ባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ተቋማቱ በጥምረት ያላቸው ኤጀንቶች ከሁለት ሺሕ በላይ ደርሰዋል፡፡  

ዜጐች በቀላሉ የባንክ አገልግሎትን እንዲያገኙ ለማድረግ እንደ አንድ አማራጭ እየተሠራበት ያለውን አገልግሎት ለመጀመር ሌሎች ባንኮችም የብሔራዊ ባንክን ፍቃድ ጠይቀዋል፡፡ ፍቃዱን አግኝተው በዝግጅት ላይም ያሉ አሉ፡፡ አንድ ኤጀንት እንደ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብና ክፍያዎችን መፈጸም ይችላል፡፡

በኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት አንድ ደንበኛ በቀን ማንቀሳቀስ የሚችለው ስድስት ሺሕ ብር ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከባንኮች 1090 ኤጀንቶችን እንዳሉት የገለጸው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ከሔሎ ካሽ ጋር በማያያዝ አገልግሎቱን ከጀመረ ወዲህ 40 ሚሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡

የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎትን በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በጥምረት በመሆን ‹‹ኤም ብር›› በሚል መጠሪያ ካለው የሞባይል ባንክ አገልግሎት ጋር በማጣመር በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በማክሮ ፋይናንሶቹ ጥምረት በኩል እስካሁን ከሁለት ሺሕ በላይ በሚሆኑ ኤጀንቶች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከማክሮ ፋይናንስ ተቋሞቹ መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብቻ 420 በሚሆኑ ቅርንጫፎቹን በኤጀንትነት እየተጠቀመባቸው ሲሆን፣ 120 ተጨማሪ ኤጀንቶችንም ማፍራት ችሏል፡፡ ከ28,000 በላይ ደንበኞችም በዚህ አገልግሎት ለመጠቀም መመዝገባቸውን ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡  

እስካሁን በነበረው የባንክ አገልግሎት ብቻ የባንክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ስለማይቻል፣ የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት መጀመር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡ በተለይ መደበኛ ቅርንጫፎችን ለመክፈት እየጠየቀ ያለው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በባንኮች ዘንድ የኤጀንት ባንኪንግን ማስፋፋት ትኩረት የተደረገበት ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

መደበኛ ቅርንጫፍ ከፍቶ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ3.5 እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ይነገራል፡፡ ለቅርንጫፍ የሚሆን ቤት ለመከራየት በካሬ ሜትር የሚጠየቀው የኪራይ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ኤጀንት ባንኪንግን ማስፋቱ አንድ አማራጭ ሆኖ እየተሠራበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አገልግሎቱ ግን የተጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡

ከአንዳንድ የባንክ የሥራ ኃላፊዎችም የተገኘው መረጃ የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት የተጠበቀውን ያህል ያለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ያሉት ተገልጋዮች ቁጥርም ቢሆን አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡

የወኪል ባንኪንግ አገልግሎት አንድ ብሎ የጀመረው በዚህ ዓመት በመሆኑ፣ አሁን ባለው ደረጃ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እየተገኘ አይደለም ይላሉ፡፡ አሁን የማለማመድ ሥራ እየተሠራ መሆኑንና የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር ሊስፋፋ የሚገባው ነው ይላሉ፡፡

አገልግሎቱ የተጠበቀውን ያህል ያልሆነበት የተለያዩ ምክንያቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በተለይ አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ተጠቃሚዎችም ሆኑ ውክልናውን ወስደው የሚሠሩ ተቋማት በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ሊሠራ ይገባል ተብሏል፡፡ በኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩ ብቻ  ኤጀንት መሆን የሚችሉ ሲሆን፣ የኤጀንት ሥራን ብቻ ለመሥራት አይፈቀድም፡፡ እንደ ኬንያ ባሉ አገሮች ወኪል የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ለዚሁ ሥራ ብቻ ፍቃድ የሚሰጥ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ይህ መሆን አለበት የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡

አሁን በብሔራዊ ባንክ እየተጠና ያለውም ለኤጀንት ባንኪንግ የወጣውንና እየተሠራበት ያለውን መመርያ ሊያሻሽል የሚችል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በኤጀንት ባንኪንግ ሊንቀሳቀስ የሚገባው የገንዘብ መጠን አነስተኛ ሆኖ መገኘቱም አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት እንቅፋት ሆኗል የሚሉም አሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ በኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት የሚከፈት አካውንት ውስጥ ማስቀመጥ የሚቻለው 25 ሺሕ ብር ብቻ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ በዚህ አካውንት በቀን ስድስት ሺሕ ብር ብቻ መንቀሳቀስ እንዳለበት የብሔራዊ ባንክ መመርያ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ይህ የገንዘብ መጠን ከፍ ቢል የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት የበለጠ እንዲስፋፋ ያስችላል ተብሏል፡፡

ባንኮች አገልግሎቱን ከጀመሩ በኋላ ታየ የሚባለውን ክፍተት ለብሔራዊ ባንክ እንዳቀረቡም ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የኤጀንት ባንኪንግ ላይ ይታያሉ የተባሉትን ክፍተቶች ለመድፈንና የበለጠ እንዲሠራበት፣ በዓለም ባንክ ድጋፍ አንድ ኮሚቴ በማቋቋም አሠራሩን ሊያጠናክር የሚችል ሥራ እየሠራ ነው፡፡ መመርያውን የማሻሻል ዕቅድ እንዳለም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች