Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዲሱ ዓመት የንግድ ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት ጨረታ ያሸነፈው ኩባንያ ከሕግ ውጭ ውጤቱ እንደተሰረዘበት ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ኤግዚቢሽን ማዕከል የአሸናፊው ድርጅት ንግድ ፈቃድ ተገቢ ስላልሆነ ውጤቱ ተሰርዟል ይላል

– የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጨረታው ሦስተኛ ለወጣው ድርጅት የተሰጠበትን አግባብ ተችቶ ውጤቱ እንዲሰረዝ አድርጓል

ለ2009 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ የንግድ ትርዒትና ባዛር ለማዘጋጀት ከተጫረቱ አምስት ድርጅቶች መካከል በ20.1 ሚሊዮን ብር ያሸነፈው ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን የተባለ ኩባንያ፣ የኤግዚቢሸን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ያሸነፍኩትን ጨረታ ‹‹ከሕግና ከሥነ ሥርዓት ውጭ ሰርዞብኛል›› ሲል ቅሬታውን አሰማ፡፡ ከጨረታ አሸናፊነት የተሰረዘበት አግባብን ከመቃወም ባሻገር በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲታይለት ማመልከቱን ገልጿል፡፡ 

የዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን ድርጅት ባለቤት አቶ ኢዮብ አርጋው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ምንም እንኳ ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን በ20.1 ሚሊዮን ብር አሸናፊ ቢሆንም፣ አሸናፊነቱ ግን ውድቅ ተደርጐበታል፡፡ ድርጅቱ ጨረታውን ያሸነፈበት አግባብ ውድቅ የተደረገውም ከንግድ ፈቃድ ጋር በማያያዝ እንደሆነ ኤግዚቢሽን ማዕከል መግለጹን ከጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከል መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ማዕከሉ ምንም እንኳ ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን ከ20.1 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ በመስጠት አንደኛ መውጣቱን ቢገልጽም፣ በማዕከሉ አሠራር መሠረት ውድቅ የተደረገባቸውን ምክንያቶች ጠቅሷል፡፡

‹‹አግባብነት ካለው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ኦፊሻል መረጃ ጠይቀን አግኝተናል፤ ከሕግ አኳያም መታየት የሚገባቸውን አከናውነናል፤ በውጤቱም በተራ ቁጥር አንድና ሁለት የተጠቀሱት [ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽንና ሻዴም ሚዲያና ፕሮሞሽን] ተጫራቾች የንግድ ፈቃድ የተፈለገውን ንግድ ትርዒትና ባዛር ለማዘጋጀት እንደማያስችላቸው በመረጋገጡ ከጨረታው ተሰርዘዋል፤›› በማለት በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ታምራት አድማሱ የተፈረመው ደብዳቤ አስፍሯል፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ ከሪፖርተር ተጠይቀው ያብራሩት አቶ ታምራት ድርጅቶቹ የንግድ ፈቃዳቸው ለዓውደ ርዕይ አዘጋጅነት ብቁ የማያደርጋቸው መሆኑ ከመንግሥት ስለተገለጸልን፣ ውጤታቸው እንዲሰረዝ አድርገናል በማለት አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም በጨረታው ሦስተኛ የወጣው ሴንቼሪ ጄነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በ15.5 ሚሊዮን ብር የጨረታው አሸናፊ መባሉን ገልጸዋል፡፡ ለተጫራቾቹ በተለጠፈው ደብዳቤም ተገልጿል፡፡ ሁለተኛ የወጣው ሻዴም ሚዲያና ፕሮሞሽን ከ17.8 ሚሊዮን ብር በላይ አቅርቦ እንደነበር ኤግዚቢሽን ማዕከል የጻፈው ደብዳቤ ያረጋግጣል፡፡

ይህንን የኤግዚቢሽን ማዕከሉን ውሳኔ በመቃወም አቤት ያሉት ተጫራቾች፣ ጨረታው እንዲታገድና ሦስተኛ ለወጣው ተጫራች የተሰጠበት አግባብም በድጋሚ እንዲታይ ጠይቀው ነበር፡፡ ውጤት ባለማግኘታቸው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩን እንዲመለከተው አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ፣ የኤግዚቢሽን ማዕከልን ኮንኖ የጨረታው ውጤት እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ምክትል የቢሮ ኃላፊና የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ዋና የሥራ ሒደት መሪ በአቶ ግርማ ጊዲ ኦልጅራ ለኤግዚቢሽን ማዕከል የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያትተው፣ ሁለቱ ውጤት የተሰረዘባቸው ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለማዘጋጀት ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ አላቸው፡፡

‹‹… ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተሰጣቸው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ላይ እንደተገለጸው፣ ‹የማስታወቂያና ፕሮሞሽን ሥራዎች፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር የማዘጋጀት፣ የተለያዩ የባንድ አገልግሎትና ተያያዥ ዝግጅቶች እንዲሁም የኪነ ጥበብ ፕሮሞሽን ማዘጋጀት እንደሚችሉ የተገለጸና ጨረታ አውጪው አካል ይህንን ጉዳይ አይቶ ሥራው በእነዚህ ሙያዎች ሊሠራ ይችላል ወይስ አይችልም ማለት ሲገባው፣ ሦስተኛ ወገን ተጠይቆ የመጣ ማስረጃን መሠረት በማድረግ ድርጅቱን የሚጠቅም ዋጋ ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች እያሉ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበውን ተወዳዳሪ መምረጥ የመንግሥትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያሳጣ አካሄድ በመሆኑ፣ ጨረታው ተሰርዞ ሌላ ግልጽ ጨረታ መውጣት እንዳለበት የተወሰነ መሆኑን እናስታውቃለን፤›› በማለት ደብዳቤው አስፍሯል፡፡

የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮው በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ላይ ያቀረበው ሌላው ወቀሳ፣ ተጫራቾች በጨረታው ለመሳተፍ ሲቀርቡ፣ ለጨረታ ያስገቡት ዋጋ ከመታወቁ በፊት በቅድመ ጨረታ ግምገማ ወቅት መፍትሔ ሊሰጥበት ሲገባ፣ ዋጋ ከተከፈተና ከታወቀ በኋላ ፈቃድ የሰጠው አካል ማብራሪያ ተጠይቆ ተገኘ በተባለ መረጃ መሠረት የተወሰደው ዕርምጃ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡

ኤግዚቢሽን ማዕከል በበኩሉ የጨረታውን ውጤት ሲሰርዝ፣ የፕሮሞሽን ወይም የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ከፕሮሞሽንና ከማስታወቂያ ፈቃድ ጋር ተመሳሳይ ነው ብሎ ከሚመሰክርለት የንግድ ፈቃድ ውጭ ሌላ ፈቃድ ማቅረብ ክልክል ነው ሲል ለጨረታ ተሳታፊዎች ባወጣው ሰነድ ላይ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ይህ አሠራር ተግባራዊ መደረግ የነበረበት የጨረታ አሸናፊዎች ከመታወቃቸው ወይም ለጨረታ ያስገቡት ዋጋ ከመታወቁ በፊት እንደነበር በማብራራት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮው ጨረታው የተካሄደበትን አሠራር ተችቷል፡፡

ኤግዚቢሽን ማዕከል በበኩሉ የጨረታው አሸናፊዎች አላሟሉም ያላቸውን ነጥቦች በመዘርዘር ውጤቱን ለምን እንደሰረዘ አቤት ባዮች ባቀረቡት ማመልከቻ መሠረት ምላሽ ቢሰጥም፣ ውጤት የተሰረዘባቸው ሁለቱ ድርጅቶች ኤግዚቢሽን ማዕከሉ በሰጣቸው ምላሽ ባለመደሰታቸው ጉዳዩን ከከተማው አስተዳደር አድርሰውታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን በፀረ ሙስና እንዲታይለት አቤቱታ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች