Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት ሪል ስቴቶች የተወዛገቡበት የግንባታ ቦታ ታገደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቡራዩ ከተማ ለሪል ስቴት ልማት እንዲውሉ በሊዝ ከተሸጡ ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነውና የባለቤትነቱ ጉዳይ አወዛጋቢ እየሆነ የመጣው 300 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ታግዶ እንዲቆይ ተወሰነ፡፡

ከኦሮሚያ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በተጻፈ ደብዳቤ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዲያካሂድበት የታገደው ይህ መሬት፣ ኒው ላይን ሪል ስቴት ጀኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባለውን ጨምሮ ተመሳሳይ ስያሜ ያላቸው የይገባኛል ጥያቄ ያነሱበት ሲሆን፣ ኒውላይን ሪል ስቴት ጄነራል ትሬዲንግ ድርጅቶች ከቤት አስገንቢዎች ቅድሚያ ክፍያ በመቀበል በቦታው ላይ ግንባታ ማካሄድ ጀምሮም ነበር፡፡

ነገር ግን ከዚህ ቦታ ጋር በተያያዘ እየተነሱ ያሉ ውዝግቦች እንዲሁም ከቦታው አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ተከሰቱ የተባሉ ማጭበርበሮችና ጥርጣሬዎች እስኪጣሩ ድረስ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይካሄድበት ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ግንባታውን አግዶታል፡፡ ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዚህ ቦታ አሰጣጥና ባለቤትነት ላይ የተፈጠሩ መጭበርበሮች ስለመኖራቸው ፍንጭ በመታየቱና በቦታ አሰጣጡ ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ በመሆኑ፣ ሁኔታው እስኪጣራ ለሪል ስቴት ግንባታ የተሰጠው መሬት ታግዶ እንዲቆይ ተወስኗል፡፡ ኒውላይን ሪል ስቴትና ጄኔራል ትሬዲንግ የተባለው ኩባንያ ግን 300 ሺሕ ካሬ ሜትሩ ቦታ ለእሱ የተፈቀደ መሆኑን በማሳየት 600 የሚደርሱ ቪላዎችን ለመገንባት ወደ ሥራ ገብቶ ነበር፡፡ ኒውላይን ሪል ስቴት ጄኔራል ትሬዲንግ በተባለው ድርጅት ውጥን መሠረት ከ600ዎቹ ቤቶች በመጀመሪያ ዙር 400 ቤቶችን መገንባት እንደሚጀምር ለቤት አስገንቢዎች በመግለጽ ቁጥራቸው 200 ከሚደርሱ ደንበኞች ጋር በጽሑፍ ውለታ በመግባት ግንባታ መጀመሩን እንዳሳወቃቸው የቤት አሠሪዎቹ ተወካዮች ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በውለታው መሠረት ግንባታውን ማካሄድ ባለመቻሉ የቤት አስገንቢ ደንበኞች ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና ለተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ባለፈው ወር አቤቱታ አቅርበው መፍትሔና ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ኒውላይን ሪል ስቴት ጄኔራል ትሬዲንግ የተባለው ድርጅት በ300 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ቤት ለማስገንባት መዋዋላቸውን በመረጃ ጭምር የሚያቀርቡት የቤት አሠሪዎች፣ እንዲገነባላቸው በፈለጉት የቤት ዲዛይን መሠረት እንዲከፍሉ ከተጠየቁት ገንዘብ ውስጥ የመጀመሪያውን ዙር ክፍያ ፈጽመዋል፡፡ ለዚህም መረጃዎቻቸውን ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት አያይዘው አቅርበዋል፡፡ ቤት ገዥዎቹ ለቤቶቹ ማስገንቢያ ከከፈሉት የቅድሚያ ክፍያ ባሻገር ለቦታው የተጠየቀውን የመሬት ሊዝ ክፍያ አሰባስበው በኒውላይን ጄኔራል ትሬዲንግ ስም ለመንግሥት እንደከፈሉም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም መረጃዎቻቸውን በአባሪነት አያይዘዋል፡፡

የኮሚቴ አባላቱ እንደሚገልጹት፣ ድርጅቱ መክፈል ያልቻለውን የሊዝ ዋጋ
ወደ መክፈሉ ደረጃ የደረሱት፣ ድርጅቱ ያሳያቸውን የቦታ ባለቤትነት የሚያረጋግጥ መረጃ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ በድርጅቱ ስም የተመዘገበ የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር በመመልከት ጭምር ነበር፡፡ መሬቱ ለድርጅቱ ከመንግሥት ስለመሰጠቱ የሚያሳይ ካርታና የግንባታ ፈቃድም የተያያዘ በመሆኑ በዚሁ መሠረት ያለጥርጣሬ ገንዘባቸውን መክፈላቸውን ይናገራሉ፡፡  

ድርጅቱ መክፈል የነበረበትን የመሬት የሊዝ ዋጋ በማዋጣት ለመክፈል የወሰንነውም ቤት ለመገንባት ባለን ጉጉት ነበር ይላሉ፡፡ ለዚህ የሪል ስቴት ልማት ወደ ሥራ መግባት የዚህን ያህል ጥረት ካደረጉ በኋላ ግን በውለታቸው መሠረት ድርጅቱ ይገነባሉ ከተባሉት ቤቶች ውስጥ ያስጀመረው ከ30 የማይበልጡ ቤቶች ብቻ እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ‹‹በውለታው መሠረት ድርጅቱ የቤት ግንባታውን እንዳላካሄደ እያሳወቅን ባለንበት ወቅት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው መታሰርና የግንባታ ቦታው ላይ የይገባኛል ጥያቄ መነሳቱ ተደማምሮ ነገሩ ስለተወሳሰበ መንግሥት መፍትሔ ይሰጠኝ፤›› በማለት አቤት ለማለት መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ቢሆንም ከከሳሽና ተከሳሽ ሆነው ከቀረቡት ሌላ ቀደም ብሎ ኒውላይን ሪል ስቴት አሜሪካን ኦሮሞ ቪሌጅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል ስያሜ ያለው ሌላ ኩባንያም ሲንቀሳቀስ እንደነበር መረጃ መገኘቱ ደግሞ ነገሩን አወሳስቦታል ተብሏል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ሦስቱም ኩባንያዎች ባለአክሲዮን ሆነው ከተመዘገቡት ውስጥ የተወሰኑት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት እንዳላቸው የሦስቱም ኩባንያዎች መመሥረቻ ጽሑፍ ያሳያል፡፡

እንዲህ ያሉ የተያያዙ ነገር መፈጠራቸው ደግሞ ቤት አስገንቢዎቹን አሳስቧል፡፡ ለሪል ስቴት ልማቱ የተሰጠው ቦታ የማነው? የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ከመሆን አልፎ ተመሳሳይ በሆኑ ስሞች እንዴት የንግድ ፍቃድ ተሰጠ የሚለውም ጉዳይ በመፈተሽ ላይ ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን ሕጋዊ መረጃዎችን በማየት ቤት ለመግባት ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመናል ያሉት ቤት አሠሪዎች ጉዳይ ተንጠልጥሎ ቀርቷል፡፡ አቤቱታቸውን ለክልሉ መንግሥት አቅርበው መልስ ከመጠባበቅ ውጭ አማራጭ ማጣታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች