Saturday, March 2, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹ኮቱ› የሰሜን ሸዋው ግዙፍ ገበያና የፋሲካ ሰሞን ግብይት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአዲስ አበባ 107 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኮቱ ከተማ ውስጥ የሰሜን ሸዋ ትልቁ ገበያ ከተተከለ ብዙ መስቀል ተኩሷል፡፡ ኮቱ የሚለውን የኦሮምኛ ቃል በመዋስ የከተማዋ ስያሜ ኮቱ ሊባል እንደቻለ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡

አቶ ብርሃኑ ወልዴ በኮቱ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ከተማዋ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ከ1935 እስከ 1940 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ መመሥረቷ ይነገራል፡፡ አቶ ውቤ ነዋይ የተባሉ ሰው የከተማዋን ፕላን እንዳወጡ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ በስምንት ሰዎች አማካይነት ወፍጮ ቤት ለመትከል ታስቦ የተመሠረተው ኮቱ ገበያ ቀስ በቀስ እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው ምን እንደነበርም የአካባቢው ሰዎች ማብራሪያ አላቸው፡፡

በወቅቱ ጥቂት የጥራጥሬ ሽያጭ ይካሄድበት የነበረው ይህ ገበያ በግ፣ ፍየሉ፣ ፈረስና አህያው ሳይቀር እዚያው ኮቱ ገበያ ያልገበየ፣ ምንም ነገር እንዳይሸጥ እንዳይለውጥ በመባሉ ምክንያት ግብይቱ እየሰፋና እየደራ መጣ፡፡ ዛሬ ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ ገበያዎች ሁሉ በግዝፍናው ሁለተኛው ሆኖ ይገኛል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ጋር አዋሳኝ የሆነችው የኮቱ ከተማ፣ በውስጧ ኮቱ ገበያን ይዛለች፡፡ በሰሜን ሸዋ ከምንጃር ገበያ ቀጥሎ በግዙፍነቱ የሚጠቀሰው ኮቱ ገበያ፣ የሁሉም ሸቀጣ ሸቀጦችና የቁም እንስሳት ግብይት የሚካሄድበት ሥፍራ ነው፡፡ ለሁለት በተከፈለው የኮቱ ገበያ ሸቀጣ ሸቀጥና እንስሳት ለየብቻ በተመደበላቸው መገበያያ ቦታ ዘወትር ሰኞ ይገበያያሉ፡፡

ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ በርበሬ፣ ጥራጥሬ፣ አልበሳት ወዘተ. በኮቱ በገፍ የሚሸጡና የሚለወጡ ሸቀጦች ናቸው፡፡ አረቄ በውስኪ ጠርሙስም በጄሪካንም እየተሞላ ለቅምሻው ጎንጨት እየተደረገለት ከሚሸጥበት ገበያ ማዶ፣ የበግ፣ የፍየልና የበሬ ገበያው ትልቁና ዋነኛው ነው፡፡

ምንም እንኳ ከፋሲካ ዋዜማ በዓል አኳያ እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ በኮቱ የሰንጋ ገበያ በረት ውስጥ ሰኞ በሚውለው ገበያ መሐል ሲተራመስ ቢታይም፣ ትልልቅ የሚባለው ከብት ግን በገበያው እንዳልታየ አቶ ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ሪፖርተር በገበያው ተዘዋውሮ እንዳጠናቀረው መረጃ ከሆነ፣ አቅራቢያ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ከደብረ ብርሃን እስከ ሐገረ ማርያም ከዚያም ሲልቅ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ ድረስ ከብቶች ይጫናሉ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ብቻ በበርካታ አይሱዙዎች በአንድ የገበያ ቀን ብቻ በሺሕ የሚቆጠር ከብት እንደተጫነ መመልከት ይቻላል፡፡

ሰንጋ ገበያው ሰኞ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለበት ዕለት ትልቅ የተባለው ሰንጋ እስከ 18 ሺሕ ብር ቢሸጥም፣ መካከለኛው ከ11 እስከ 13 ሺሕ ብር አውጥቷል፡፡ ሆኖም ደህና የሚባለው ከብት እስከ 35 ሺሕ የሚሸጥበት ጊዜ እንዳለም ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡ በሰኞው ገበያ ላሞች ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሺሕ ብር አውጥተዋል፡፡ ሰንጋ በማደለብና በማርባት የሚታወቀው የኮቱ ከተማና የአጎራባች ቀበሌዎች ነዋሪዎች፣ ከሰኞ ገበያ ወይም ከበዓለ ፋሲካ ይልቅም ለግንቦት ሚካኤል የሚያወጡበት ከብት በብዛትና በዓይነት የተለየ መሆኑ ይነገርለታል፡፡

ቅቤ ከሰሞንኛው ገበያ ይልቅ መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ቀድሞ አንድ ኪሎ ቅቤ 200 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረው፣ አሁን ላይ እስከ 250 ብር አሻቅቧል፡፡ ሽንኩርት በኪሎ ከዘጠኝ ብር እስከ 11 ብር ሲሸጥ ታይቷል፡፡ ዶሮ አነስተኛው 90 ጀምሮ መካከለኛና ደህና ብልት ያለው እስከ 130 ብር ተሽጧል፡፡ አቶ ብርሃኑ በሰጡን ማብራሪያ በተለየ መንገድ ያለልክ የደለቡ ዶሮዎች 400 ብር ድረስ ሲሸጡ መታየቱንና ይህ የተለየ ክስተት በገበያው መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ምንም እንኳ በጤፍ አምራችነቷ ብዙም የማትታወቀው ኮቱ ከተማ ውስጥ ከከብት ቀጥሎ በስንዴ፣ በዘንጋዳ፣ በማሽላና በሌላውም ዓይነት አዝርዓት አምራችነቷ ትጠቀሳለች የሚለው ወጣቱ መለሰ ነጋሽ፣ ዘንድሮ የታየው የምርት መጠን ካምናውም የተሻለ እንደነበር ይናገራል፡፡ በአገሪቱ የታየው ድርቅ ያልነካካት ኮቱ፣ እንዲህ ያሉትን ጥራጥሬና አዝርዕት እስከ አዳማ ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች ታዳርሳለች፡፡

በኮቱ ገበያ የሚታየው ዋጋ ከመሃል ገበያ ብዙም ልዩነት የማይታይበት ይመስላል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ሲያብራሩ፣ በብዛት እንደ ሽንኩርትና መሰል በቶሎ የሚበላሹ ምርቶች ከሚመጡባቸው ከሸዋ ሮቢትና ከአንጾኪያ የሚመጡ ነጋዴዎች ለኮቱ ገበያ ነጋዴዎች ምርት ሲያስረክቡ ያልተጣራ ምርት ስለሚያስረክቡ ለበላተኛ የሚሸጡ ነጋዴዎች የተመረጠና ደህነኛውን ለይተው ስለሚሸጡ ዋጋውም በዚያው ልክ እንደሚጨምር አስረድተዋል፡፡

ከመላው የኦርቶዶስክስ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ለሁለት ወራት ያህል ሕዝበ ክርስቲያኑ ከጡልላተ ምግቦች (የፍስክ ምግቦች) ራሱን አቅቦ በመቆየቱ ለወትሮው ዓይን የሚያጥበረብር አምፑል ሰክተው፣ ሳልገኝ ከሽንጥ ወጥረው የሚቸበችቡ ልኳንዳ ቤቶች ተዘግተው ከርመዋል፡፡ አንዳንዶቹ ጊዜያዊ ንግድ ሲሸቅጡ ታይተዋል፡፡

ዳቦ ቤት፣ ምግብ ቤት ወዘተ. የመሳሰሉትን አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ሲያከናውኑ የቆዩት ሥጋ ቤቶች፣ የፋሲካ በዓል መቃረቡን ማብሰር ጀምረዋል፡፡ ቀለም እየተቀባቡ፣ የሥጋ መስቀያዎቻቸውን እያጠባበቁና እያደሱ ሲሰናዱ ይታያሉ፡፡ ከመሃል አገር እስከ ካራ ገበያ፣ ከዚያም አልፎ በአቅራቢያ ርቀት ላይ ወዳሉ ከተሞች የሚጓዝ ሁሉ ለፋሲካ ዋዜማ የሚደረገውን ሽርጉድ ይታዘባል፡፡ እግረ መንገዱን ሐሙስ ገበያና ሸኖ ገበያን ለመቃኘት የሚሻ ገበያተኛም ፀሎተ ሐሙስና ቅዳሜን መጠበቅ ግድ ይሆንበታል፡፡ በአሮሚያ ክልል የሚገኘው ሐሙስ ገበያ ዘወትር ሐሙስ የሚቆም ሌላው ትልቅ ገበያ ሲሆን፣ በቅቤ አምራችነቱ ተለይቶ የሚታየወቀው የሸኖ ገበያም በዕለተ ቅዳሜ ይቆማል፡፡ በኮቱ ገበያ ግብይት የዋለው ተገበያይ የሸጠውን ሸጦ፣ ለልጆቹና ለራሱ ልብስ ሲሸምት፣ ሌሎች ጌጣጌጦችንም ሲገበይ አምሽቶ ወደ ጎጆው አቅንቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች