Wednesday, October 4, 2023

ሥጋት ያጠላበት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ምሥረታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአራት ዓመታት በፊት ደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አዲሷ አባል አገር ሆና ስትቀላቀል፣ የአንድ አገር ዋና ምሰሶ የሆነው ሥርዓተ መንግሥት የማቋቋም ፈተና ገጥሟታል፡፡ ከደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ ሚያዚያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በኋላ የተገናኙት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው ዶ/ር ማቻር የጋራ መንግሥት የመመሥረት ጉዞ ‹‹ሀ›› ብለው ጀምረዋል፡፡ ቀጣይነቱ ግን በሥጋት የተሞላ ይመስላል፡፡

ቀስ በቀስ የብሔር ጎራ እየያዘ የመጣውን ግጭት አንዳንዶች በዋናው የሰሜን ሱዳን መንግሥትና በአዲሷ ነፃይቱ ደቡብ ሱዳን መካከል ለአንድ ዓመት የተካሄደው ጦርነት ቅጥያ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ይኼው ግጭት ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎችን ለሕልፈት ሲዳርግ ከአንድ ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ለመፈናቀል ተገዷል፡፡

ያጋጠመው ችግር በተለያዩ ታዛቢዎች ከግጭትም በዘለለ አካባቢያዊ ቀውስ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ ቀድሞ ችግሩን ለመፍታት ኃላፊነት የተሰጠው ኢጋድም ድካሙን ከንቱ የቀረ አስመስሎት ነበር፡፡

ረዥሙ ሽምግልና ላይ ያጠላው ተስፋ መቁረጥ

ከመነሻው ደቡብ ሱዳን ከእናት አገሯ ከሰሜን ሱዳን ነፃነቷን ለመቀዳጀት የኢትዮጵያ ተከታታይ መንግሥታት ሚና ከፍተኛ ሲሆን፣ አዲሷ ደቡብ ሱዳን እንደ አገር በሁለት እግሯ ትቆም ዘንድ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢጋድ አማካይነት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ሁለቱንም ጎራ ለማቀራረብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕውቅና የተሰጠው የኢጋድን የልዑካን ቡድን የመሩት ኢትዮጵያን ለ20 ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ አምባሳደር ሥዩም መስፍን ናቸው፡፡ የሶማሊያን ቀውስ በመፍታትም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ቀጥለው ከፍተኛ ሚና የነበራቸው መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡

ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራር ሌላ መልክ እየያዘ መምጣቱ በስፋት ቢነገርም፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ባስገኘችው ሰላም የተቸራት ዓለም አቀፍ ዕውቅና በደቡብ ሱዳን የምትደግመው አይመስልም ተብሎም ተሰግቶ ነበር፡፡ ከመነሻው አደራዳሪው ቡድን በኢትዮጵያ መመራቱን የሚቃወሙ አባል አገሮች (ኬንያን ጨምሮ) መኖራቸውን ቀድሞ የተገለጸ ሲሆን፣ የዕርቅ ሒደቱ ላለመሳካት ተፅዕኖ እንደነበረው የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ከረዥም የሽምግልና ሒደት በኋላ ባለፈው ነሐሴ ወር አዲስ አበባ ውስጥ የተፈረመው የጋራ መንግሥት የመመሥረት ስምምነት ቀነ ገደቡ በቅርቡ ተጠናቋል፡፡ አደራዳሪው ኢጋድና የጎንዮሽ ዕርዳታ የሚሰጠው ‹‹ትሮይካ›› በሚል ይበልጥ የሚታወቀው ኖርዌይ፣ እንግሊዝና አሜሪካንን ያካተተው ቡድን በሒደቱ ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸው ነበር፡፡

የተፈረመው ስምምነት በዋናነት የጋራ መንግሥት ማቋቋም ላይ ያለመ ነው፡፡ የሥልጣን መጋራት፣ የመከላከያ ኃይል አወቃቀርና ወደፊት የሚመሠረተው መንግሥት ቅርፅ ዋነኛ ትኩረቱ ናቸው፡፡

ከኢጋድ አደራዳሪነት ጎን ለጎን አብዛኞቹ በራሱ በድርጅቱ አነሳሽነት፣ ሌሎችም ያለ ድርጅቱ ዕውቅና ውስጥ ለውስጥ የተለያዩ የዕርቅ ሒደቶች ሲያከናወኑ መቆየታቸው በቅርቡ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

በዋናነት የተፈረመው የመጨረሻው ስምምነትና በአገሪቱ ለተከሰተው ቀውስ እልባት ያስገኛል ተብሎ የታመነበትን የአዲስ አበባውን የስምምነት ሒደት በመከታተል እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የዓለም አቀፍ የቁጥጥርና ክትትል ኮሚሽን ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት፣ በያዝነው ሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንታት የጋራ መንግሥት ምሥረታ ተግባራዊ እንዲሆን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ሒደቱ ውድቅ ሊሆን ተቃርቦ ነበር፡፡ በተፈረመው ስምምነት መሠረት ግጭቱን ተከትሎ ከደቡብ ሱዳን ውጪ ሆነው ሲሸመገሉ የቆዩት ዶ/ር ማቻር ሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ተመልሰው በአዲሱ መንግሥት የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሾሙ ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁንና ወደ ጁባ ለመብረር ያደረጉዋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች በፕሬዚዳንት ኪር መንግሥት ውድቅ መደረጋቸው በጎ ያልሆነ መንፈስ አጥልቆበት ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የኖርዌይና የቻይና መንግሥታት ቅሬታቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ትሮይካ በመባል የሚታወቁት ሦስቱ አገሮች ለደቡብ ሱዳን መንግሥት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኪርቢ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አገራቸው የዕርቅ ሒደቱን ለማሳካት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ስትሠራ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ በአስቸኳይ ዕልባት ካላገኘ አገራቸው የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድም አሳስበው ነበር፡፡ እንዲሁም የእንግሊዝ መንግሥት ጁባ በሚገኘው ኤምባሲው አማካይነት ባወጣው መግለጫ ክልከላው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር፡፡

ሁለቱም አገሮች በሁኔታው እጅግ ማዘናቸውን በገለጹበት መግለጫቸው፣ ሁለቱም ወገኖች ለተጀመረው የጋራ መንግሥት ምሥረታ የመተባበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበው ነበር፡፡

የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥት በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በሚመራው መንግሥት ላይ ቅሬታቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ የክልከላው መነሻ ግን ዶ/ር ማቻር በሚበሩበት አውሮፕላን ቀድሞ ከተደረሰው ስምምነት ውጪ ወታደሮችና የጦር መሣሪያ ይዘው ለመግባት በመሞከራቸው መሆኑን ምንጮች ያመለክታሉ፡፡

በእርግጥ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አደራዳሪ ወገኖች ተስፋ ለመቁረጥ ምክንያት የሆናቸው የሰሞኑ የማቻር በረራ ክልከላ ብቻ አልነበረም፡፡ እንዲመሠረት የታሰበው መንግሥት ቅርፅና መልክ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት፣ ጁባ ያለው በሳልቫ ኪር የሚመራው መንግሥት ከስምምነቱ ያልመነጩ አንዳንድ ዕርምጃዎችን ቀድሞ መውሰድ መጀመሩም ተነግሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተለይ በአገሪቱ የፌዴራል መንግሥት ሥር 29 ክልሎች እንዲዋቀሩ አድርገዋል፡፡ ማቻርና ሌሎች ተቃዋሚዎች ዕርምጃውን በመቃወም ድምፃቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ የታሰበው የጋራ መንግሥት ዕውን ስለመሆኑ ከፍተኛ ጥርጣሬ ፈጥሮ ነበር፡፡

መገንጠል እንደ ምክንያት

ዶ/ር መሐሪ ታደለ ማሩ በአፍሪካ ኅብረትና በዓለም አቀፍ የሕግና የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪና አማካሪ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የደቡብ ሱዳን ግጭት በተከሰተ ማግስት፣ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ድርጅት ኤስፒኤልኤ (SPLA) በውስጡ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ እንደሌለው፣ አንድ አድርጎት የቆየውም የካርቱም መንግሥት ጠላትነትና እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የግዛት ነፃነት ብቻ እንደነበር በአልጄዚራ ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸው ነበር፡፡ በመሆኑም ኤርትራን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ማብቃት በኋላ እንደሆነው ሁሉ ራሱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ካላደረገ፣ መሰነጣጠቁ የማይቀር የጊዜ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ አምባገነን ኃይል በመሆን እንደ የኤርትራ መንግሥት እንደ ሽፍታ የሚታይበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል የሚል ግምት አስቀምጠው ነበር፡፡ የዕርቅ ሒደቱ ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆንም አሳስበው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን፣ ደቡብ ሱዳን ደግሞ የኤርትራን ገጽታ እየያዘች መምጣቷ የማይቀር መሆኑን በማስፈር፣ መገንጠል በራሱ ለሕዝቦች ጥያቄ ምላሽ እንደማይሆን አመልክተዋል፡፡ በቅርቡ ተመሳሳይ ዕርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያለችውን ሶማሊላንድን ከዚህ ትምህርት እንድትወስድም አሳስበዋል፡፡

በቅርቡ ከደቡብ ሱዳን መምጣታቸውና የሙርሌ ጎሳ አባላት መሆናቸው የተነገረላቸው የታጣቂ ቡድን አባላት፣ በጋምቤላ ክልል ውስጥ በመግባት አሰቃቂ ግድያ መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ ዶ/ር መሐሪ የደቡብ ሱዳን ቀውስ ዕልባት ካላገኘ በአካባቢው በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ አሳስበው ነበር፡፡ በተለይ ሁለቱም ጎረቤት አገሮች የሚጋሩት ሀብትና ኅብረተሰብ መኖሩ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የደቡብ ሱዳን ስደተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ መጠለሉ በጥንቃቄ እንዲያዝ አሳስበው ነበር፡፡

ይህ ታጣቂ ቡድን የኢትዮጵያ ድንበርን ጥሶ በመግባት የወሰደው የጥፋት ዕርምጃ፣ ተንታኞች የደቡብ ሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በመከታተል ኢትዮጵያ ልትወስደው ይገባል ያሉትን የጥንቃቄ ማሳሰቢያ ችላ በማለት የተከሰተ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ደቡብ ሱዳን ውስጥ በየዕለቱ በሚከሰተው ጉዳይ ላይ ክትትል እንዲደረግና በድንበር አካባቢዎች በቂ ክትትል እንዲደረግ ያሳስባሉ፡፡

ዶ/ር ጆን ያንግ በቅርቡ “A Fractious Rebellion፡ Inside the SPLM-IO” በሚል ርዕስ ያሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ደግሞ፣ የኢጋድ የመሸምገል ሒደት በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች አመራሮች መካከል የሥልጣን መጋራት ለመፍጠር ብቻ ያለመ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ምንም እንኳ የጋራ መንግሥት ቢፈጠርም መፈረካከሱ አይቀርም በማለት ይደመድማል፡፡

እንደ ምሁሩ እምነት የዕርቅ ሒደቱ ሌላው ቀርቶ በዶ/ር ማቻር የሚወከለው ተቃዋሚ ቡድን ውስጥ ያሉትን የኑዌር ብሔረሰብ ጄኔራሎች ፍላጎትና ቅሬታ እንኳን ግምት ያስገባ አይመስልም፡፡ በደቡብ ሱዳን ጦር አመራርና የዶ/ር ማቻር የፖለቲካ አመራር የሚንፀባረቁ ተቃራኒ ፍላጎቶችን ወደ ጎን ያለ አካሄድ መጨረሻው ውድቀት ነው ይላሉ፡፡ 

በዚህ ሁሉ ጥርጣሬና ሥጋት መካከል ቀደም ሲል በኢጋድ ሸምጋይነት የተፈረመው የጋራ መንግሥት የማቋቋም ጉዞ ግን ሚያዚያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -