የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል ጠርጥሯቸው ነሐሴ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ያስያዙት የግል የሞባይል ስልካቸው በኤግዚቢትነት የተያዘ ቢሆንም፣ ከታሰሩ በኋላ 18,420 ብር ቆጥሯል ተብሎ ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን አቶ ወንድሙ ቢራቱ ለፍርድ ቤት አመለከቱ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባልና የክልሉ ገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወንድሙ ማመልከቻውን ያቀረቡት በጠበቃቸው አቶ መሐመድ ኑር አብዱልከሪም አማካይነት ነው፡፡ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18 ወንጀል ችሎት ሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዳስረዱት፣ አቶ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ነሐሴ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስልካቸው በኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊሶች አማካይነት በኤግዚቢትነት ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት እንደቆጠረ ተገልጾ ከኢትዮ ቴሌኮም 18,420 ብር እንዲከፍሉ ቤተሰቦቻቸው ጥያቄ እንደቀረበላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲያጣራላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በዕለቱ የነበሩት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በሰጡት ምላሽ ሳይጣራ የተቋሙን ስም ማጥፋት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረው፣ በኤግዚቢት የተያዘ ስልክ ወጥቶ ለጥቅም መዋል አለመዋሉ በማስረጃ መረጋገጥ እንዳለበት አስታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በጽሑፍ እንዲቀርብ በማዘዝ፣ አጣርቶ ዕርምጃ እንደሚወስድ ተናግሯል፡፡
አቶ ወንድሙ በድጋሚ ባቀረቡት አቤቱታ የተያዘባቸው ላፕቶፕና ሌሎች ኤግዚቢቶች እንዲለቀቁላቸው ኮሚሽነሩና ምክትል ኮሚሽነሩ ፈርመው የፈቀዱ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ አመልክተዋል፡፡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁሉም አቤቱታ በጽሑፍ እንዲቀርብ በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የአቶ ወንድሙ ቢራቱ የክስ መዝገብ ተቀጥሮ የነበረው ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ የነበረ ቢሆንም፣ የምስክሮች መጥሪያ ከፍርድ ቤቱ ወጪ ሲደረግ በተሳሳተ ስምና አድራሻ ወጪ በመደረጉ ምስክሮቹ ሊገኙ አለመቻላቸው በችሎት ተነግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም ስህተቱ የፍርድ ቤቱ መሆኑን በመግለጽ ለግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ተለዋጭ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡